-
“በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
-
-
ምዕራፍ 11
“በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ”
ጳውሎስ ተቃዋሚዎችንና መልእክቱን የማይቀበሉ ሰዎችን ከያዘበት መንገድ የምናገኘው ትምህርት
በሐዋርያት ሥራ 13:1-52 ላይ የተመሠረተ
1, 2. በርናባስና ሳኦል ሊያደርጉት ያሰቡትን ጉዞ ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚያከናውኑት ሥራስ የሐዋርያት ሥራ 1:8 ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
በአንጾኪያ ያለው ጉባኤ እጅግ የተደሰተበት ዕለት ነው። በዚያ ከነበሩት ነቢያትና አስተማሪዎች መካከል በርናባስና ሳኦል በመንፈስ ቅዱስ ተመረጡ፤ ተልእኳቸው ምሥራቹን ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ማድረስ ነው።a (ሥራ 13:1, 2) እውነት ነው፣ ከዚያ በፊትም ቢሆን ብቃት ያላቸው ወንዶች ይላኩ ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ሚስዮናውያን የተላኩት የክርስትናን እምነት የተቀበሉ ሰዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች ነው። (ሥራ 8:14፤ 11:22) በዚህ ጊዜ ግን በርናባስና ሳኦል አብዛኞቹ ሰዎች ምሥራቹን ወዳልሰሙባቸው ቦታዎች ሊላኩ ነው፤ ዮሐንስ ማርቆስም አብሯቸው ይጓዛል፤ በጉዟቸው ላይ እንደ አገልጋይ ሆኖ ይረዳቸዋል።
2 ከ14 ዓመት ገደማ በፊት ኢየሱስ ተከታዮቹን “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር። (ሥራ 1:8) በርናባስና ሳኦል ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ መሾማቸው ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል!b
‘ለሥራው የተለዩ’ (የሐዋርያት ሥራ 13:1-12)
3. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ረጅም ርቀት መጓዝ አስቸጋሪ የነበረው ለምንድን ነው?
3 እንደ መኪና እና አውሮፕላን ለመሳሰሉት ዘመናዊ መጓጓዣዎች ምስጋና ይግባቸውና በዛሬው ጊዜ በአንድ ወይም በሁለት ሰዓት ውስጥ ረጅም ርቀት መጓዝ ይቻላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነበር። ሰዎች በየብስ ላይ ከቦታ ወደ ቦታ ለመሄድ ብዙውን ጊዜ በእግራቸው መጓዝ ነበረባቸው፤ አብዛኞቹ መንገዶች ደግሞ ለጉዞ ምቹ አልነበሩም። የአንድ ቀን የእግር ጉዞ ከ30 ኪሎ ሜትር እምብዛም አይበልጥም፤ ጉዞውም ሰውነትን የሚያዝል ነው!c በመሆኑም በርናባስና ሳኦል፣ ተልእኳቸው አድካሚና ምቾትን መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ እንደሚሆን አይጠፋቸውም፤ ያም ሆኖ ወጥተው ለማገልገል እንደሚጓጉ ጥርጥር የለውም።—ማቴ. 16:24
4. (ሀ) በርናባስና ሳኦል የተመረጡት እንዴት ነው? የእምነት ባልንጀሮቻቸውስ በእነሱ መመረጥ ምን ተሰማቸው? (ለ) ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን ለሚቀበሉ ወንድሞች ድጋፍ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
4 ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ‘ለአንድ ሥራ እንዲለዩ’ ከሌሎቹ ሁሉ በርናባስንና ሳኦልን የመረጠው ለምንድን ነው? (ሥራ 13:2) መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱን አይገልጽም። የምናውቀው ነገር ቢኖር እነዚህ ሰዎች የተመረጡት መንፈስ ቅዱስ በሰጠው መመሪያ መሠረት መሆኑን ነው። በአንጾኪያ የነበሩት ነቢያትና አስተማሪዎች ውሳኔውን ለመቀበል አንገራግረው እንደነበር የሚጠቁም ምንም ነገር አናገኝም። ከዚህ ይልቅ የእነሱን መመረጥ ሙሉ በሙሉ ደግፈዋል። ዘገባው “ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው፤ ከዚያም አሰናበቷቸው” ይላል፤ በርናባስና ሳኦል መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ምንም የቅናት ስሜት ሳያድርባቸው ሲያሰናብቷቸው ምን ያህል ተበረታተው እንደሚሆን አስብ። (ሥራ 13:3) እኛም ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች የሚሰጣቸውን ሁሉ ልንደግፋቸው ይገባል፤ ይህም የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆነው የሚሾሙትን ወንድሞች ይጨምራል። እንዲህ ዓይነት መብቶች ባገኙ ወንድሞች ከመቅናት ይልቅ “በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት” ልናሳያቸው ይገባል።—1 ተሰ. 5:13
5. በርናባስና ሳኦል በቆጵሮስ ደሴት የሰበኩት እንዴት ነው?
5 በርናባስና ሳኦል በአንጾኪያ አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ሴሌውቅያ ወደብ በእግራቸው ተጓዙ፤ ከዚያም መርከብ ተሳፍረው 200 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው የቆጵሮስ ደሴት አቀኑ።d በርናባስ የቆጵሮስ ተወላጅ እንደመሆኑ መጠን ለአገሩ ሰዎች ምሥራቹን ለመንገር ጓጉቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በመጨረሻም በደሴቲቱ ምሥራቃዊ ጠረፍ ወደምትገኘው ስልማና ከተማ ደረሱ፤ ጊዜ ሳያጠፉም “የአምላክን ቃል በአይሁዳውያን ምኩራቦች ማወጅ ጀመሩ።”e (ሥራ 13:5) ከዚህኛው የቆጵሮስ ጫፍ ተነስተው ደግሞ እስከ ሌላኛው ጫፍ ድረስ ተጓዙ፤ እግረ መንገዳቸውን ደሴቲቱ ላይ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ምሥራቹን ሰብከው መሆን አለበት። እነዚህ ሚስዮናውያን የትኛውን መንገድ ይዘው እንደተጓዙ ባናውቅም በጥቅሉ 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ሳይጓዙ አልቀሩም!
6, 7. (ሀ) ሰርግዮስ ጳውሎስ ማን ነው? በርያሱስ ይህ ሰው ምሥራቹን እንዳይሰማ ሊያከላክል የሞከረውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሳኦል፣ በርያሱስ ላስነሳው ተቃውሞ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?
6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ቆጵሮስ የሐሰት አምልኮ መናኸሪያ ነበረች። በርናባስና ሳኦል በደሴቲቱ ምዕራባዊ ዳርቻ ወደምትገኘው ወደ ጳፎስ በደረሱ ጊዜ ያጋጠማቸው ሁኔታ ይህን በግልጽ የሚያሳይ ነው። በዚያ “በርያሱስ የተባለ . . . ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ” አገኙ። እሱም “ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ የሮም አገረ ገዢ ጋር ነበር።”f በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሠለጠኑ ናቸው የሚባሉ በርካታ ሮማውያን ትላልቅ ውሳኔዎች ሲያደርጉ ጠንቋዮችን ወይም ኮከብ ቆጣሪዎችን የማማከር ልማድ ነበራቸው፤ እንደ ሰርግዮስ ጳውሎስ ያሉ “አስተዋይ” ሰዎችም እንኳ ይህን ያደርጉ ነበር። ይሁንና ሰርግዮስ ጳውሎስ የመንግሥቱን ምሥራች ሲሰማ ደስ አለው፤ “የአምላክን ቃል ለመስማት [ጓጓ]።” ይህ ግን በርያሱስን አላስደሰተውም፤ በርያሱስ ‘ኤልማስ’ በመባልም ይታወቅ የነበረ ሲሆን ትርጉሙ “ጠንቋይ” ማለት ነው።—ሥራ 13:6-8
7 በርያሱስ የመንግሥቱን መልእክት ይቃወም ጀመር። ደግሞም የሰርግዮስ ጳውሎስ አማካሪ በመሆን ያገኘውን ከፍተኛ ሥልጣን ጠብቆ ማቆየት የሚችለው “አገረ ገዢው ይህን እምነት እንዳይቀበል” ማደናቀፍ ከቻለ ብቻ ነው። (ሥራ 13:8) ሆኖም ሳኦል፣ ይህ ጠንቋይ ለሰርግዮስ ጳውሎስ እንቅፋት እንዲሆን አልፈለገም። ታዲያ ምን አደረገ? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ ተብሎ የሚጠራው ሳኦል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ተመለከተው፤ ከዚያም እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ተንኮልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፣ የዲያብሎስ ልጅ፣ የጽድቅም ሁሉ ጠላት! ቀና የሆነውን የይሖዋን መንገድ ማጣመምህን አትተውም? እነሆ፣ የይሖዋ እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዓይነ ስውር ትሆናለህ፤ ለተወሰነ ጊዜም የፀሐይ ብርሃን አታይም።’ ወዲያውኑም ጭጋግና ጨለማ ዓይኑን ጋረደው፤ እጁን ይዞ የሚመራው ሰው ለማግኘትም ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ።”g ታዲያ ይህ ተአምራዊ ክንውን ምን ውጤት አስገኘ? አገረ ገዢው “ስለ ይሖዋ በተማረው ነገር ተደንቆ ስለነበር ይህን ባየ ጊዜ አማኝ ሆነ።”—ሥራ 13:9-12
ልክ እንደ ጳውሎስ፣ ተቃውሞ በሚኖርበት ጊዜም እንኳ በድፍረት ለእውነት ጥብቅና እንቆማለን
8. ጳውሎስ ድፍረት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
8 ጳውሎስ በርያሱስን አልፈራውም። እኛም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን እምነት ለማዳከም የሚሞክሩ ተቃዋሚዎችን መፍራት የለብንም። እርግጥ ነው፣ ንግግራችን “ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው” መሆን ይኖርበታል። (ቆላ. 4:6) ይሁን እንጂ ከሌሎች ጋር ላለመጋጨት ስንል ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ከመርዳት መቆጠብ የለብንም። ወይም የሐሰት ሃይማኖቶች የሚፈጽሙትን መጥፎ ድርጊት ከማጋለጥ ወደኋላ አንልም፤ ምክንያቱም እነሱም እንደ በርያሱስ “ቀና የሆነውን የይሖዋን መንገድ” ያጣምማሉ። (ሥራ 13:10) ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም እውነትን በድፍረት እናውጅ፤ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ከመርዳትም ወደኋላ አንበል። እርግጥ ነው፣ በጳውሎስ ጊዜ እንደሆነው፣ አምላክ የሚሰጠን ድጋፍ በግልጽ አይታይ ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚገባቸውን ሰዎች ወደ እውነት ለመሳብ ቅዱስ መንፈሱን እንደሚጠቀም እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዮሐ. 6:44
‘የሚያበረታታ ቃል’ (የሐዋርያት ሥራ 13:13-43)
9. ጳውሎስና በርናባስ በዛሬው ጊዜ ጉባኤውን ግንባር ቀደም ሆነው ለሚመሩ ወንድሞች ግሩም ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?
9 እነዚህ ሰዎች ከጳፎስ ተነስተው ባሕር ላይ በመጓዝ ጴርጌ ደረሱ፤ በትንሿ እስያ የባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው ጴርጌ ከጳፎስ 250 ኪሎ ሜትር ትርቃለች። በዚህ ጊዜ አንድ ለውጥ የተደረገ ይመስላል። ምክንያቱም በሐዋርያት ሥራ 13:13 ላይ ዘገባው “ጳውሎስና ባልደረቦቹ” ይላል። ይህ አባባል ጳውሎስ ቡድኑን በግንባር ቀደምትነት መምራት እንደጀመረ ይጠቁማል። ሆኖም በርናባስ በጳውሎስ እንደቀና የሚጠቁም ምንም ነገር አናገኝም። ከዚህ በተቃራኒ እነዚህ ሁለት ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ተባብረው መሥራታቸውን ቀጥለዋል። ጳውሎስና በርናባስ በዛሬው ጊዜ ጉባኤውን ግንባር ቀደም ሆነው ለሚመሩ ወንድሞች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ክርስቲያኖች፣ አንዳቸው ከሌላው ልቀው ለመታየት ከመሞከር ይልቅ ኢየሱስ “እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ አክሎም “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል” ብሏል።—ማቴ. 23:8, 12
10. ጳውሎስና በርናባስ ከጴርጌ ወደ ጵስድያዋ አንጾኪያ ያደረጉትን ጉዞ ግለጽ።
10 ጴርጌ ሲደርሱ ዮሐንስ ማርቆስ ትቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ዮሐንስ ማርቆስ ድንገት የተመለሰበት ምክንያት አልተገለጸም። ጳውሎስና በርናባስ ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ ከጴርጌ ተነስተው ወደ ጵስድያዋ አንጾኪያ ሄዱ፤ አንጾኪያ በገላትያ አውራጃ የምትገኝ ከተማ ነች። ጉዞው ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም የጵስድያዋ አንጾኪያ የምትገኘው ከባሕር ጠለል በላይ 1,100 ሜትር ከፍታ ላይ ነው። ተራሮችን አቋርጠው የሚያልፉት አሳቻ መንገዶች ሽፍቶች የበዙባቸው ነበሩ። ይህ ሁሉ እንዳይበቃ ደግሞ በዚህ ወቅት ጳውሎስ የጤና እክል ሳያጋጥመው አልቀረም።h
11, 12. ጳውሎስ በጵስድያዋ አንጾኪያ በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ንግግር ባቀረበበት ጊዜ የአድማጮቹን ፍላጎት መቀስቀስ የቻለው እንዴት ነው?
11 ጳውሎስና በርናባስ በጵስድያዋ አንጾኪያ በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገቡ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “የሕጉና የነቢያት መጻሕፍት በሕዝቡ ፊት ከተነበበ በኋላ የምኩራቡ አለቆች ‘ወንድሞች ሆይ፣ ሕዝቡን የሚያበረታታ የምትናገሩት ቃል ካላችሁ ተናገሩ’ የሚል መልእክት ላኩባቸው።” (ሥራ 13:15) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ሊናገር ተነሳ።
12 ጳውሎስ ንግግሩን የጀመረው “የእስራኤል ሰዎችም ሆናችሁ አምላክን የምትፈሩ ሌሎች ሰዎች ሁሉ” ብሎ ነው። (ሥራ 13:16) ጳውሎስን ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አሕዛብ ነበሩ። አድማጮቹ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና አያውቁም፤ ታዲያ ጳውሎስ ትኩረታቸውን ለመሳብ ምን አደረገ? በመጀመሪያ የአይሁድ ብሔርን ታሪክ በአጭሩ ተረከላቸው። ይሖዋ “በግብፅ ምድር ባዕዳን ሆነው ይኖሩ በነበረበት ጊዜ . . . ሕዝቡን ከፍ ከፍ [እንዳደረጋቸው]” ገለጸ፤ ነፃ ከወጡ በኋላ ደግሞ ‘ለ40 ዓመት ያህል በምድረ በዳ እንዴት እንደታገሣቸው’ አብራራላቸው። በተጨማሪም ጳውሎስ እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር መውረስ የቻሉት እንዲሁም ይሖዋ “ምድራቸውን ርስት አድርጎ [የሰጣቸው]” እንዴት እንደሆነ ገለጸ። (ሥራ 13:17-19) አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ፣ ጳውሎስ የጠቀሳቸው ነጥቦች የተወሰዱት አድማጮቹ በዚያ የሰንበት ዕለት ጥቂት ቀደም ብሎ ከሰሙት የቅዱሳን መጻሕፍት ንባብ ሳይሆን አይቀርም። እውነታው እንዲህ ከሆነ፣ ጳውሎስ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።—1 ቆሮ. 9:22
13. የአድማጮቻችንን ልብ መማረክ የምንችለው እንዴት ነው?
13 እኛም ምሥራቹን ማራኪ በሆነ መንገድ ለማቅረብ መጣር ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ሃይማኖቱ ምን እንደሆነ ማወቃችን ትኩረቱን የሚስቡ ርዕሰ ጉዳዮችን ለመምረጥ ያግዘናል። በተጨማሪም ግለሰቡ ከሚያውቃቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ልንጠቅስለት እንችላለን። ሰውየው ጥቅሱን ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ እንዲያነብ ማድረግም ይበልጥ ውጤታማ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንግዲያው የአድማጮችህን ልብ መማረክ የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ።
14. (ሀ) ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች ለአድማጮቹ ያስተዋወቀው እንዴት ነው? ምን ማስጠንቀቂያስ ሰጠ? (ለ) አድማጮቹ ለጳውሎስ ንግግር ምን ምላሽ ሰጡ?
14 ጳውሎስ በመቀጠል ‘አዳኝ የሆነው ኢየሱስ’ በእስራኤል የነገሥታት መስመር እንደመጣ አብራራ፤ መጥምቁ ዮሐንስ ለኢየሱስ መንገድ ጠራጊ እንደነበረም ተናገረ። ከዚያም ኢየሱስ እንዴት እንደተገደለና ከሞት እንደተነሳ ገለጸ። (ሥራ 13:20-37) አክሎም እንዲህ አለ፦ “በእሱ በኩል የሚገኘው የኃጢአት ይቅርታ አሁን እየታወጀላችሁ እንዳለ እወቁ፤ በኢየሱስ የሚያምን ማንኛውም ሰው፣ በእሱ አማካኝነት ‘ከበደል ነፃ ነህ’ ሊባል ይችላል።” ከዚያም ለአድማጮቹ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፦ “በነቢያት መጻሕፍት እንዲህ ተብሎ የተነገረው ነገር በእናንተ ላይ እንዳይደርስ ተጠንቀቁ፦ ‘እናንተ ፌዘኞች፣ ተመልከቱ፣ ተደነቁ፣ ጥፉም፤ ማንም በዝርዝር ቢነግራችሁ እንኳ ፈጽሞ የማታምኑትን ሥራ በእናንተ ዘመን እያከናወንኩ ነውና።’” አድማጮቹ ለጳውሎስ ንግግር የሰጡት ምላሽ አስደናቂ ነበር። ዘገባው እንደሚናገረው “ሰዎቹ ስለዚሁ ጉዳይ በሚቀጥለው ሰንበትም እንዲነግሯቸው ለመኗቸው።” በተጨማሪም በምኩራቡ የተደረገው ስብሰባ ከተበተነ በኋላ “ከአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ተለውጠው አምላክን ከሚያመልኩት መካከል ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው።”—ሥራ 13:38-43
“ለአሕዛብ እንሰብካለን” (የሐዋርያት ሥራ 13:44-52)
15. ጳውሎስ ንግግር ባቀረበ በቀጣዩ ሰንበት ምን ነገር ተከሰተ?
15 በቀጣዩ ሰንበት “የከተማዋ ሕዝብ ሁሉ ማለት ይቻላል” ጳውሎስን ለመስማት አንድ ላይ ተሰበሰበ። ይህ ሁኔታ ያላስደሰታቸው አንዳንድ አይሁዳውያን “ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በመቃወም ይሳደቡ ጀመር።” በዚህ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ በድፍረት እንዲህ አሏቸው፦ “የአምላክ ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገሩ አስፈላጊ ነበር። እናንተ ግን ወደ ጎን ገሸሽ እያደረጋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ እየፈረዳችሁ ስለሆነ እኛም ለአሕዛብ እንሰብካለን። ይሖዋ ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ መዳንን እንድታመጣ ለብሔራት ብርሃን አድርጌ ሾሜሃለሁ’ በማለት ትእዛዝ ሰጥቶናልና።”—ሥራ 13:44-47፤ ኢሳ. 49:6
“በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት አስነሱ፤ . . . ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።”—የሐዋርያት ሥራ 13:50-52
16. አይሁዳውያኑ የጳውሎስንና የበርናባስን ጠንከር ያለ ንግግር ሲሰሙ ምን ምላሽ ሰጡ? ጳውሎስና በርናባስስ ተቃውሞ ሲነሳባቸው ምን አደረጉ?
16 ንግግሩን ያዳመጡት ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች እጅግ ተደሰቱ፤ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ።” (ሥራ 13:48) ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ቃል በመላ አገሪቱ እየተስፋፋ ሄደ። የአይሁዳውያኑ ምላሽ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ጳውሎስና በርናባስ እንዳሉት የአምላክ ቃል በመጀመሪያ የተነገረው ለአይሁዳውያኑ ቢሆንም መሲሑን አንቀበልም ብለዋል፤ በዚህም የተነሳ የአምላክ ፍርድ እንደማይቀርላቸው ጳውሎስና በርናባስ በግልጽ ነግረዋቸዋል። አይሁዳውያኑ፣ በከተማዋ የሚኖሩትን የተከበሩ ሴቶችና ታላላቅ ወንዶች በመቀስቀስ “በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት አስነሱ፤ ከክልላቸውም አስወጧቸው።” በዚህ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ ምን አደረጉ? “የእግራቸውን አቧራ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ።” ታዲያ የክርስትና እምነት በጵስድያዋ አንጾኪያ አከተመለት ማለት ነው? በፍጹም! ዘገባው በዚያ ስለቀሩት ደቀ መዛሙርት ሲናገር “በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ” ይላል።—ሥራ 13:50-52
17-19. ጳውሎስና በርናባስ የተዉትን ግሩም ምሳሌ መከተል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ለደስታችን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?
17 እነዚህ ታማኝ ሰዎች ተቃውሞ በተነሳባቸው ጊዜ ካደረጉት ነገር ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። በዓለም ላይ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰዎች መልእክቱን እንዳናውጅ ቢከለክሉን እንኳ መስበካችንን አናቆምም። ጳውሎስና በርናባስ፣ የአንጾኪያ ሰዎች መልእክቱን አንቀበልም ባሉ ጊዜ “የእግራቸውን አቧራ አራግፈው [እንደሄዱ]” ልብ በል፤ ይህ በሁኔታው እንደተቆጡ የሚያሳይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ኃላፊነታቸውን እንደተወጡና በሕዝቡ ላይ ለሚደርሰው ነገር ተጠያቂ አለመሆናቸውን የሚጠቁም ምልክት ነው። እነዚህ ሚስዮናውያን፣ ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ ማስገደድ እንደማይችሉ ተገንዝበው ነበር። ማድረግ የሚችሉት ነገር ቢኖር መስበካቸውን መቀጠል ነው። ደግሞም ያደረጉት ይህንኑ ነው፤ ወደ ኢቆንዮን ሄደው መስበካቸውን ቀጠሉ!
18 በአንጾኪያ የቀሩት ደቀ መዛሙርትስ ምን አደረጉ? የሚሰብኩበት ክልል ተቃዋሚዎች የበዙበት እንደሆነ አይካድም። ሆኖም ደስታቸው የተመካው ሰዎች በሚሰጡት በጎ ምላሽ ላይ አልነበረም። ኢየሱስ “የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት [ደስተኞች] ናቸው!” ብሏል። (ሉቃስ 11:28) በጵስድያዋ አንጾኪያ ያሉት ደቀ መዛሙርትም ይህንኑ ለማድረግ ቆርጠው ነበር።
19 ልክ እንደ ጳውሎስና እንደ በርናባስ ሁሉ እኛም ኃላፊነታችን ምሥራቹን መስበክ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። መልእክቱን መቀበል ወይም አለመቀበል የምንሰብክላቸው ሰዎች ውሳኔ ነው። ሰዎች መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ በማይሆኑበት ጊዜ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ደቀ መዛሙርት ምሳሌ እንከተል። እውነትን የምናደንቅና የመንፈስ ቅዱስን አመራር የምንቀበል ከሆነ ተቃውሞ ደስታችንን ሊያጠፋው አይችልም።—ገላ. 5:18, 22
a “በርናባስ—‘የመጽናናት ልጅ’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
b በዚህ ወቅት በሶርያዋ አንጾኪያ ሳይቀር ጉባኤዎች ተቋቁመው ነበር፤ ይህች ከተማ የምትገኘው ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን 550 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ነው።
d በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ አንድ መርከብ የነፋሱ ሁኔታ ጥሩ ከሆነ በቀን 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ይጓዝ ነበር። የአየሩ ሁኔታ አመቺ በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ ጉዞው ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል።
e “በአይሁዳውያን ምኩራቦች ውስጥ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
f ቆጵሮስ በሮም አገዛዝ ሥር ነበረች። ደሴቲቱን የሚያስተዳድረው አገረ ገዢው ሲሆን በሮም የተሾመ የአካባቢው ባለሥልጣን ነበር።
g ሳኦል ከዚህ ጊዜ አንስቶ ጳውሎስ ተብሎ መጠራት ጀመረ። አንዳንዶች ሳኦል በሮማዊ ስሙ መጠራት የጀመረው ለሰርግዮስ ጳውሎስ ክብር ሲል እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ቆጵሮስን ለቅቆ ከሄደ በኋላም በዚህ ስም መጠራቱን መቀጠሉ ከዚህ የተለየ ምክንያት እንዳለ የሚጠቁም ነው፤ አዎ፣ ጳውሎስ “ለአሕዛብ [የተላከ] ሐዋርያ” ስለሆነ በሮማዊ ስሙ ለመጠራት መርጧል። ምናልባት ሌላው ምክንያት ደግሞ ሳኦል ከሚለው የዕብራይስጥ ስሙ ጋር የተያያዘ ይሆናል፤ የዚህ ስም ግሪክኛ አጠራር መጥፎ መልእክት ከሚያስተላልፍ አንድ የግሪክኛ ቃል ጋር በጣም ይመሳሰላል።—ሮም 11:13
-
-
“ከይሖዋ ባገኙት ሥልጣን በድፍረት” ተናገሩ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
-
-
ምዕራፍ 12
“ከይሖዋ ባገኙት ሥልጣን በድፍረት” ተናገሩ
ጳውሎስና በርናባስ ትሕትና፣ ጽናትና ድፍረት አሳይተዋል
በሐዋርያት ሥራ 14:1-28 ላይ የተመሠረተ
1, 2. ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራ በነበሩበት ጊዜ ምን ነገሮች ተከሰቱ?
በልስጥራ ከፍተኛ ሁካታ ተፈጥሯል። ሁለት ፀጉረ ልውጥ ሰዎች፣ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረን አንድ ሰው ፈውሰዋል፤ ሰውየው ከደስታው የተነሳ እየዘለለ ነው። ሕዝቡ በጣም ተገርሟል፤ አንድ የዙስ ካህን፣ ሕዝቡ እንደ አማልክት ለቆጠራቸው ለእነዚህ ሁለት ሰዎች የአበባ ጉንጉን ይዞ መጣ። ካህኑ በሬዎች አምጥቶ ለመሥዋዕት ማዘገጃጀት ጀመረ። ጳውሎስና በርናባስ ይህን ሲያዩ እየጮኹ ድርጊቱን አጥብቀው ተቃወሙ። ልብሳቸውን ቀድደው እየሮጡ ሕዝቡ መሃል ገቡ፤ እንዳያመልኳቸው ይማጸኗቸውም ጀመር፤ ያም ሆኖ ሕዝቡ ይህን እንዳያደርግ ያስጣሉት በብዙ ችግር ነበር።
2 ከዚያም ተቃዋሚ የሆኑ አይሁዳውያን ከጵስድያዋ አንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ። የሐሰት ወሬ በማስወራትም የልስጥራን ሕዝብ አእምሮ መረዙ። ጳውሎስንና በርናባስን ካላመለክናቸው ብለው ግብ ግብ የገጠሙት ሰዎች አሁን ጳውሎስን ከበቡት፤ ራሱን እስኪስት ድረስም በድንጋይ ወገሩት። ንዴታቸውን ከተወጡበት በኋላ የቆሳሰለውን ጳውሎስን ከከተማዋ አውጥተው ጣሉት፤ ይህንም ያደረጉት የሞተ መስሏቸው ነበር።
3. በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 ለመሆኑ ሁኔታው ወደዚህ ያመራው እንዴት ነው? በዘመናችን ያሉ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች ስለ በርናባስ፣ ስለ ጳውሎስና እንደ እስስት ተለዋዋጭ ስለነበረው የልስጥራ ሕዝብ ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? በርናባስና ጳውሎስ “ከይሖዋ ባገኙት ሥልጣን በድፍረት እየተናገሩ” አገልግሎታቸውን በጽናት አከናውነዋል፤ ታዲያ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእነሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?—ሥራ 14:3
“ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው” ሰዎች “አማኞች ሆኑ” (የሐዋርያት ሥራ 14:1-7)
4, 5. ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢቆንዮን የሄዱት ለምን ነበር? እዚያስ ምን አጋጠማቸው?
4 ከጥቂት ቀናት በፊት ጳውሎስና በርናባስ የሮማውያን ከተማ በሆነችው በጵስድያዋ አንጾኪያ ስደት ተነስቶባቸው ነበር፤ ተቃዋሚ የሆኑ አይሁዳውያን ከከተማዋ አባረሯቸው። ይሁንና የከተማዋ ነዋሪዎች መልእክቱን ስላልተቀበሏቸው ተስፋ አልቆረጡም፤ ከዚህ ይልቅ “የእግራቸውን አቧራ አራግፈው . . . ሄዱ።” (ሥራ 13:50-52፤ ማቴ. 10:14) አዎ፣ ጳውሎስና በርናባስ በሰላም አካባቢውን ለቅቀው ወጡ፤ ለሚደርስባቸው ነገር ተጠያቂዎቹ ራሳቸው መሆናቸውን ለተቃዋሚዎቻቸው በመግለጽ ፍርዱን ለአምላክ ትተው ተሰናበቱ። (ሥራ 18:5, 6፤ 20:26) ሁለቱ ሚስዮናውያን ደስ እያላቸው የስብከት ጉዟቸውን ቀጠሉ። በስተ ደቡብ ምሥራቅ 150 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጓዙ፤ ከዚያም በቶረስና በሱልጣን የተራራ ሰንሰለቶች መካከል ወደሚገኝ ለም የሆነ አምባ ደረሱ።
5 ጳውሎስና በርናባስ መጀመሪያ የሄዱት ወደ ኢቆንዮን ነው፤ ኢቆንዮን የግሪክ ባሕል ማዕከል ነች፤ የሮም አውራጃ በሆነችው በገላትያ ካሉት ዋና ዋና ከተሞችም አንዷ ናት።a በዚህች ከተማ ውስጥ፣ ተሰሚነት ያላቸው ብዙ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ጳውሎስና በርናባስም እንደ ልማዳቸው ወደ ምኩራብ ገብተው መስበክ ጀመሩ። (ሥራ 13:5, 14) “በዚያም ጥሩ ንግግር ስለሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና ግሪካውያን አማኞች ሆኑ።”—ሥራ 14:1
6. ጳውሎስና በርናባስ ውጤታማ አስተማሪዎች ሊሆኑ የቻሉት ለምንድን ነው? እኛስ የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
6 ጳውሎስና በርናባስ የሰጡት ንግግር ውጤታማ የነበረው ለምንድን ነው? ጳውሎስ የካበተ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት ነበረው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች፣ ከትንቢቶችና ከሙሴ ሕግ ላይ በዘዴ እያጣቀሰ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን ያሳምን ነበር። (ሥራ 13:15-31፤ 26:22, 23) የበርናባስ አነጋገር ደግሞ ለሰዎች ያለውን ልባዊ አሳቢነት በግልጽ የሚያሳይ ነበር። (ሥራ 4:36, 37፤ 9:27፤ 11:23, 24) ሁለቱም በራሳቸው ማስተዋል ከመታመን ይልቅ “ከይሖዋ ባገኙት ሥልጣን” ይናገሩ ነበር። አንተስ በምትሰብክበት ጊዜ እነዚህ ሚስዮናውያን የተዉትን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነገሮች በማድረግ ነው፦ የአምላክን ቃል ጠንቅቀህ እወቅ፤ አድማጮችህን ይበልጥ ሊማርኩ የሚችሉ ጥቅሶችን ምረጥ፤ የምትሰብክላቸውን ሰዎች ልታጽናና የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ፤ እንዲሁም የምታስተምረው ትምህርት በራስህ ጥበብ ሳይሆን ምንጊዜም በይሖዋ ቃል ላይ የተመሠረተ ይሁን።
7. (ሀ) የምሥራቹ መልእክት ምን ውጤት ያስከትላል? (ለ) በምሥራቹ ምክንያት በቤተሰብህ መካከል መከፋፈል ተፈጥሮ ከሆነ ምን ማስታወስ ይኖርብሃል?
7 ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ በተናገሩት ነገር የተደሰቱት ሁሉም የኢቆንዮን ነዋሪዎች አይደሉም። ሉቃስ “ያላመኑት አይሁዳውያን ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ሰዎች በማነሳሳት በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው አደረጉ” በማለት ዘግቧል። ሆኖም ጳውሎስና በርናባስ በዚያ መቆየትና ለምሥራቹ ጥብቅና መቆም እንዳለባቸው ስለተገነዘቡ “በድፍረት እየተናገሩ በኢቆንዮን ረዘም ላለ ጊዜ ቆዩ።” ከዚህም የተነሳ “የከተማዋ ሕዝብ ተከፋፈለ፤ አንዳንዶቹ ከአይሁዳውያን ጎን ሲቆሙ ሌሎቹ ደግሞ ከሐዋርያት ጎን ቆሙ።” (ሥራ 14:2-4) በዛሬው ጊዜም የምሥራቹ መልእክት ተመሳሳይ ውጤት ያስከትላል። ለአንዳንዶች የአንድነት ኃይል ይሆናል፤ ለሌሎች ደግሞ የክፍፍል ምክንያት ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 10:34-36) ለምሥራቹ መልእክት ታዛዥ በመሆንህ ምክንያት በቤተሰብህ መካከል መከፋፈል ተፈጥሮ ይሆን? ከሆነ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ተቃውሞ የሚነሳው ባልተጨበጠ መረጃ ወይም አንዳንዶች ስም ለማጥፋት ብለው በሚያናፍሱት ወሬ የተነሳ መሆኑን አስታውስ። የምታሳየው መልካም ምግባር ለእንዲህ ዓይነቱ ተቃውሞ ማርከሻ ነው፤ ውሎ አድሮ የሚቃወሙህን ሰዎች ልብ ሊያለሰልስ ይችላል።—1 ጴጥ. 2:12፤ 3:1, 2
8. ጳውሎስና በርናባስ ኢቆንዮንን ለቅቀው የሄዱት ለምንድን ነው? እነሱ ከተዉት ምሳሌስ ምን እንማራለን?
8 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በኢቆንዮን ያሉት ተቃዋሚዎች ጳውሎስንና በርናባስን ለመውገር ሴራ ጠነሰሱ። እነዚህ ሁለት ሚስዮናውያን ይህን ሲሰሙ ወደ ሌላ የአገልግሎት ክልል ለመሄድ ወሰኑ። (ሥራ 14:5-7) በዛሬው ጊዜ ያሉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም ተመሳሳይ የሆነ የጥበብ እርምጃ ይወስዳሉ። ሰዎች የቃላት ጥቃት ሲሰነዝሩብን በድፍረት ምላሽ እንሰጣለን። (ፊልጵ. 1:7፤ 1 ጴጥ. 3:13-15) የኃይል ጥቃት የመሰንዘር አዝማሚያ እንዳለ ካስተዋልን ግን የራሳችንንም ሆነ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር አናደርግም።—ምሳሌ 22:3
‘ሕያው የሆነውን አምላክ አምልኩ’ (የሐዋርያት ሥራ 14:8-19)
9, 10. ልስጥራ የምትገኘው የት ነበር? ስለ ከተማዋ ነዋሪዎችስ ምን የምናውቀው ነገር አለ?
9 ጳውሎስና በርናባስ ከኢቆንዮን በስተ ደቡብ ምዕራብ 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘው ልስጥራ ደረሱ፤ ልስጥራ የሮማውያን ቅኝ ግዛት የሆነች ከተማ ነች። ከጵስድያዋ አንጾኪያ ጋር ብዙ የሚያመሳስላት ነገር ቢኖርም በዚህች ከተማ ውስጥ ብዙ አይሁዳውያን አልነበሩም። የከተማዋ ነዋሪዎች ግሪክኛ መናገር ሳይችሉ አይቀሩም፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ግን የሊቃኦንያ ቋንቋ ነበር። በከተማዋ ውስጥ ምኩራብ ስለሌለ ሳይሆን አይቀርም ጳውሎስና በርናባስ በአደባባይ መስበክ ጀመሩ። ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም፣ ሲወለድ ጀምሮ የአካል ጉዳተኛ የነበረ አንድ ሰው ፈውሷል። በዚህ ተአምር የተነሳም እጅግ ብዙ ሰዎች አማኝ ሆነው ነበር። (ሥራ 3:1-10) ጳውሎስ ደግሞ በልስጥራ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ፈውሷል። (ሥራ 14:8-10) ይሁን እንጂ ይህ ተአምር ያስገኘው ውጤት በኢየሩሳሌም ከተፈጸመው ተአምር ፈጽሞ የተለየ ነው።
10 የልስጥራ ነዋሪዎች አረማውያን አማልክትን የሚከተሉ ነበሩ፤ በመሆኑም በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ሽባ የነበረው ሰው ዘሎ ሲራመድ ባዩ ጊዜ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደረሱ። በርናባስን የአማልክት አለቃ በሆነው በዙስ ስም ጠሩት፤ ጳውሎስን ደግሞ ሄርሜስ አሉት፤ ሄርሜስ የዙስ ልጅና የአማልክት ቃል አቀባይ ነው። (“ልስጥራ እንዲሁም የዙስና የሄርሜስ አምልኮ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይሁን እንጂ በርናባስና ጳውሎስ ሕዝቡ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ አልፈለጉም፤ የተናገሩትም ሆነ ተአምር የፈጸሙት ብቸኛው እውነተኛ አምላክ በሆነው በይሖዋ ሥልጣን እንጂ አማልክት ስለሆኑ እንዳልሆነ ለማሳመን ቆርጠው ነበር።—ሥራ 14:11-14
‘እነዚህን ከንቱ ነገሮች ትታችሁ ሰማይንና ምድርን የፈጠረውን ሕያው አምላክ አምልኩ።’—የሐዋርያት ሥራ 14:15
11-13. (ሀ) ጳውሎስና በርናባስ ለልስጥራ ነዋሪዎች ምን ብለው ተናገሩ? (ለ) ጳውሎስና በርናባስ ከተናገሩት ነገር የምናገኘው አንዱ ትምህርት ምንድን ነው?
11 የሕዝቡ ያልተጠበቀ ምላሽ ከፍተኛ ትርምስ ፈጥሯል፤ ጳውሎስና በርናባስ ግን በዚህ ወቅትም እንኳ የአድማጮቻቸውን ልብ ለመንካት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል። ሉቃስ ያሰፈረው ይህ ዘገባ ምሥራቹን ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች መስበክ የሚቻልበትን ውጤታማ ዘዴ ያስተምረናል። ጳውሎስና በርናባስ የአድማጮቻቸውን ልብ ለመንካት ምን እንዳሉ ልብ በል፦ “እናንተ ሰዎች፣ እንዲህ የምታደርጉት ለምንድን ነው? እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን። ምሥራቹን እያወጅንላችሁ ያለነውም እነዚህን ከንቱ ነገሮች ትታችሁ ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረውን ሕያው አምላክ እንድታመልኩ ነው። ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ፈቀደላቸው፤ ይሁንና ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችሁን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል።”—ሥራ 14:15-17
12 እኛስ ከዚህ ልብ የሚነካ አነጋገር ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስና በርናባስ፣ ራሳቸውን ከአድማጮቻቸው የተሻሉ አድርገው እንዳልቆጠሩ እናያለን። ያልሆኑትን ሆነው ለመታየት አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ እነሱም አረማዊ እንደሆኑት አድማጮቻቸው ሁሉ ድክመቶች እንዳሉባቸው በትሕትና ገለጹ። እውነት ነው፣ ጳውሎስና በርናባስ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፤ ደግሞም ከሐሰት ትምህርቶች ነፃ ወጥተዋል። ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋም ተሰጥቷቸዋል። ይሁንና የልስጥራ ነዋሪዎችም ክርስቶስን ከታዘዙ እነዚህኑ ስጦታዎች ማግኘት እንደሚችሉ ተገንዝበው ነበር።
13 እኛስ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት አለን? ከእኛ ጋር እኩል እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን? በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት እንዲማሩ ሌሎችን በምንረዳበት ጊዜ የተለየ ውዳሴ እንዲቸረን ባለመፈለግ የጳውሎስንና የበርናባስን ምሳሌ እንከተላለን? የተዋጣለት አስተማሪ የሆነው ቻርልስ ቴዝ ራስል በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል፤ ራስል በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይመራ ነበር። ሆኖም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለእኛም ሆነ ለምናዘጋጃቸው ጽሑፎች ሙገሳና ውዳሴ መቀበል አንፈልግም፤ ‘አባ’ ወይም ‘ረቢ’ ተብለን መጠራትም አንፈልግም።” አዎ፣ ወንድም ራስል ልክ እንደ ጳውሎስና በርናባስ ትሑት ነበር። እኛም የምንሰብከው ለራሳችን ክብር ለማምጣት ሳይሆን ሰዎች ‘ሕያው የሆነውን አምላክ እንዲያመልኩ’ ለመርዳት ነው።
14-16. ጳውሎስና በርናባስ ለልስጥራ ነዋሪዎች ከተናገሩት ነገር የምናገኘው ሁለተኛና ሦስተኛ ትምህርት ምንድን ነው?
14 ከዚህ ንግግር የምናገኘውን ሁለተኛ ትምህርት ደግሞ እስቲ እንመልከት። ጳውሎስና በርናባስ አቀራረባቸውን እንደ ሁኔታው ያስተካክሉ ነበር። የልስጥራ ነዋሪዎች፣ በኢቆንዮን እንዳሉት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች አይደሉም፤ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍትም ሆነ አምላክ ከእስራኤል ብሔር ጋር ስለነበረው ግንኙነት ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ይሁንና ጳውሎስንና በርናባስን ያዳምጧቸው የነበሩት እነዚህ ሰዎች በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ ነበሩ። ልስጥራ ምቹ የሆነ የአየር ጠባይና ለም መሬት የታደለች ነበረች። በመሆኑም ነዋሪዎቿ የፈጣሪን ግሩም ባሕርይ ለማየት የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ ነበራቸው፤ ለምሳሌ ፍሬያማ የሆኑ ወቅቶችና በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ነገሮች ስለ ፈጣሪ የሚያስተምሯቸው ነገሮች አሉ፤ ሚስዮናውያኑም አድማጮቻቸው እንዲያመዛዝኑ ለመርዳት ይህን በጋራ የሚያስማማ ነጥብ ጠቅሰዋል።—ሮም 1:19, 20
15 እኛስ አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው ለመለወጥ ጥረት እናደርጋለን? አንድ ገበሬ አንድ ዓይነት ዘር በተለያዩ ማሳዎች ላይ ሊዘራ ይችላል፤ መሬቱን ለማለስለስ የሚጠቀምበትን ዘዴ ግን እንደየሁኔታው መቀያየር ይኖርበታል። አንዳንዱ መሬት ቀድሞውንም ቢሆን የለሰለሰና ሊዘራበት የሚችል ይሆናል። ሌላው ደግሞ ለማለስለስ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ እኛም የምንዘራው ዘር አንድ ዓይነት ነው፤ እሱም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው የመንግሥቱ መልእክት ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ እንዳደረጉት ሁሉ የምንሰብክላቸውን ሰዎች ሁኔታና ሃይማኖት ለማስተዋል ጥረት እናደርጋለን። ከዚያም የመንግሥቱን መልእክት በምንናገርበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ እናስገባለን።—ሉቃስ 8:11, 15
16 ስለ ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም ስለ ልስጥራ ነዋሪዎች ከሚናገረው ዘገባ የምናገኘው ሦስተኛ ትምህርትም አለ። የቱንም ያህል ጥረት ብናደርግ የዘራነው ዘር ተነጥቆ ሊወሰድ ወይም ድንጋያማ መሬት ላይ ሊወድቅ ይችላል። (ማቴ. 13:18-21) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ተስፋ መቁረጥ የለብንም። በኋላ ላይ ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት ደቀ መዛሙርት የሰጠውን ማሳሰቢያ እናስታውስ፤ የአምላክን ቃል የምናወያየውን ግለሰብ ጨምሮ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።”—ሮም 14:12
“ለይሖዋ አደራ ሰጧቸው” (የሐዋርያት ሥራ 14:20-28)
17. ጳውሎስና በርናባስ ከደርቤ ተነስተው ወዴት ሄዱ? ለምንስ?
17 ሕዝቡ ጳውሎስን ከልስጥራ እየጎተቱ ካወጡትና የሞተ መስሏቸው ትተውት ከሄዱ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው ከበቡት፤ በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ተነስቶ ወደ ከተማዋ በመግባት በዚያ አደረ። በማግስቱ ጳውሎስና በርናባስ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ደርቤ አቀኑ። ይህ አድካሚ ጉዞ ጳውሎስን ምን ያህል እንዳሠቃየው መገመት አያዳግትም፤ በድንጋይ የተወገረው ከተወሰኑ ሰዓታት በፊት ስለሆነ ገና ቁስለኛ ነው። ያም ሆኖ እሱም ሆነ በርናባስ ምንም ነገር ጉዟቸውን እንዲያስተጓጉልባቸው አልፈቀዱም፤ ደርቤ በደረሱም ጊዜ “በርካታ ደቀ መዛሙርት [አፈሩ]።” ከዚያም መኖሪያቸው ወደሆነችው ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ በአቋራጭ ከመመለስ ይልቅ “ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ [ጵስድያዋ] አንጾኪያ ተመለሱ።” ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? “በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት ደቀ መዛሙርቱን [ለማጠናከር]” ነበር። (ሥራ 14:20-22) በእርግጥም እነዚህ ሁለት ወንድሞች ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል! ከራሳቸው ምቾት ይልቅ የጉባኤውን ጥቅም አስቀድመዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስዮናውያን እነሱ የተዉትን ምሳሌ ይከተላሉ።
18. ሽማግሌዎች የሚሾሙት እንዴት ነው?
18 ጳውሎስና በርናባስ በቃልና ምሳሌ በመሆን ደቀ መዛሙርቱን ከማበረታታት ባሻገር “በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው።” ይህን የሚስዮናዊነት ጉዞ የጀመሩት “በመንፈስ ቅዱስ ተልከው” ቢሆንም ሽማግሌዎቹን ‘ለይሖዋ አደራ የሰጧቸው’ ጾመውና ጸልየው ነው። (ሥራ 13:1-4፤ 14:23) ዛሬም ያለው አሠራር ተመሳሳይ ነው። የሽማግሌዎች አካል አንድ ወንድም እንዲሾም ሐሳብ ከማቅረቡ በፊት፣ ሽማግሌዎቹ ወንድም ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ በጸሎት ይገመግማሉ። (1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9፤ ያዕ. 3:17, 18፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) ዋነኛው መመዘኛ ግለሰቡ በእውነት ቤት የቆየበት ጊዜ አይደለም። ግለሰቡ የመንፈስ ቅዱስን አመራር ምን ያህል ይከተላል የሚለውን የሚያሳየው አነጋገሩ፣ ምግባሩና በሌሎች ዘንድ ያተረፈው ስም ነው። የበላይ ተመልካቾች ሊያሟሏቸው የሚገቡ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሰፈሩ ብቃቶችን ካሟላ የመንጋው እረኛ ሆኖ ለማገልገል ብቁ ይሆናል። (ገላ. 5:22, 23) ከዚያም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሽማግሌ አድርጎ ይሾመዋል።—ከ1 ጢሞቴዎስ 5:22 ጋር አወዳድር።
19. ሽማግሌዎች ስለ ምን ነገር ተጠያቂዎች እንደሆኑ ያውቃሉ? የጳውሎስንና የበርናባስን ምሳሌ መከተል የሚችሉትስ እንዴት ነው?
19 የተሾሙ ሽማግሌዎች ጉባኤውን የሚይዙበትን መንገድ በተመለከተ በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ያውቃሉ። (ዕብ. 13:17) ሽማግሌዎች እንደ ጳውሎስና በርናባስ ሁሉ በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይካፈላሉ። የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በቃል ያበረታታሉ። ደግሞም ምንጊዜም ከራሳቸው ምቾት ይልቅ የጉባኤውን ጥቅም ለማስቀደም ፈቃደኞች ናቸው።—ፊልጵ. 2:3, 4
20. ወንድሞቻችን በታማኝነት ስላከናወኗቸው ሥራዎች የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ማንበባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
20 በመጨረሻም ጳውሎስና በርናባስ ወደ መኖሪያቸው ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ ተመለሱ፤ እዚያ ላሉት ወንድሞች “አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች እንዲሁም ለአሕዛብ የእምነትን በር እንደከፈተላቸው ተረኩ።” (ሥራ 14:27) እኛም ክርስቲያን ወንድሞቻችን በታማኝነት ስላከናወኑት ሥራ ማንበባችንና ይሖዋ ጥረታቸውን እንዴት እንደባረከ ማየታችን ‘ከይሖዋ ባገኘነው ሥልጣን በድፍረት መናገራችንን’ እንድንቀጥል ያበረታታናል።
a “ኢቆንዮን—የፍርግያውያን ከተማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
-