-
‘አምላክ ስጦታቸውን ተቀብሏል’የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
-
-
ንጹሕ አምልኮን በተመለከተ አቤል የተወው ምሳሌ
10. አቤል ንጹሕ አምልኮን በተመለከተ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
10 አቤል አምልኮ ሊቀርብ የሚገባው ለይሖዋ ብቻ እንደሆነ ስላወቀ መሥዋዕት ያቀረበው ለይሖዋ ነው። የስጦታው ጥራትም ቢሆን እንከን የሚወጣለት አልነበረም፤ ያቀረበው “ከመንጋው በኩራት መካከል የተወሰኑትን” መርጦ ነበር። ዘገባው አቤል መሥዋዕቱን ያቀረበው በመሠዊያ ላይ ይሁን አይሁን ባይናገርም መሥዋዕቱን ያቀረበበት መንገድ ተቀባይነት እንደነበረው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አቤል ካቀረበው መሥዋዕት ጋር በተያያዘ ጎልቶ የሚታየውና ከስድስት ሺህ ዓመታት በኋላ ለምንኖረው ለእኛ ትልቅ ትምህርት የያዘልን ስጦታውን ለማቅረብ ያነሳሳው የልብ ዝንባሌ ነው። አቤልን መሥዋዕት እንዲያቀርብ ያነሳሳው በአምላክ ላይ ያለው እምነትና ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች የነበረው ፍቅር ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን?
አቤል ንጹሕ አምልኮ የሚጠይቃቸውን አራት መሠረታዊ መሥፈርቶች አሟልቷል (አንቀጽ 10ን ተመልከት)
11. ኢየሱስ አቤል ጻድቅ ሰው እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው?
11 በመጀመሪያ ኢየሱስ ስለ አቤል ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ አቤልን በደንብ ያውቀው ነበር፤ አቤል በሕይወት በነበረበት ወቅት ኢየሱስ በሰማይ ይኖር ነበር። ኢየሱስ የአቤልን ሁኔታ በቅርበት ይከታተል እንደነበር ጥያቄ የለውም። (ምሳሌ 8:22, 30, 31፤ ዮሐ. 8:58፤ ቆላ. 1:15, 16) ስለዚህ ኢየሱስ፣ አቤል ጻድቅ ሰው እንደሆነ ሲናገር በዓይኑ ስላየው ነገር መናገሩ ነበር። (ማቴ. 23:35) ጻድቅ የሆነ ሰው ትክክልና ስህተት ስለሆኑት ነገሮች መሥፈርት የሚያወጣው ይሖዋ መሆኑን አምኖ ይቀበላል። ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አይወሰንም፤ እነዚህን መሥፈርቶች እንደሚቀበል በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ያሳያል። (ከሉቃስ 1:5, 6 ጋር አወዳድር።) ጻድቅ ሰው የሚል ስም ለማትረፍ ጊዜ ይጠይቃል። ስለዚህ አቤል ለአምላክ መሥዋዕት ከማቅረቡ በፊትም ቢሆን የይሖዋን መሥፈርቶች ጠብቆ በመኖር ረገድ ጥሩ ታሪክ አስመዝግቦ መሆን አለበት። እንዲህ ያለውን አካሄድ መከተል ቀላል አልነበረም። ታላቅ ወንድሙ ቃየን ልቡ ክፉ ሆኖ ስለነበር ለእሱ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነው እንደማይችል የታወቀ ነው። (1 ዮሐ. 3:12) እናቱ ደግሞ አምላክ የሰጠውን ቀጥተኛ ትእዛዝ የጣሰች ሲሆን አባቱም ቢሆን መልካምና ክፉ የሆነውን በራሱ ለመወሰን ስለፈለገ በይሖዋ ላይ ዓምፆአል። (ዘፍ. 2:16, 17፤ 3:6) አቤል ከቤተሰቡ ፈጽሞ የተለየ አካሄድ ለመምረጥ ከፍተኛ ድፍረት ጠይቆበት መሆን አለበት!
12. በቃየንና በአቤል መካከል የነበረው መሠረታዊ ልዩነት ምንድን ነው?
12 ቀጥሎ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ እምነትና ጽድቅ ያላቸውን ዝምድና እንዴት እንደገለጸ እንመልከት። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አቤል፣ ቃየን ካቀረበው የበለጠ ዋጋ ያለው መሥዋዕት ለአምላክ በእምነት አቀረበ፤ አምላክ ስጦታውን ስለተቀበለ በዚህ እምነቱ የተነሳ ጻድቅ እንደሆነ ተመሥክሮለታል።” (ዕብ. 11:4) ጳውሎስ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ ከቃየን በተለየ መልኩ አቤል ዕድሜውን በሙሉ በይሖዋና እሱ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ ልባዊ እምነት እንደነበረውና ይህም ለአምላክ መሥዋዕት ለማቅረብ እንዳነሳሳው ያሳያል።
13. አቤል ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
13 አቤል የተወው ምሳሌ ንጹሕ አምልኮ ሊመነጭ የሚችለው ከንጹሕ የልብ ዝንባሌ ብቻ እንደሆነ ያስተምረናል፤ አንድ ሰው ንጹሕ አምልኮ ማቅረብ የሚችለው በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ካለውና ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ ከሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም ንጹሕ አምልኮ አንድ ጊዜ ብቻ ከሚቀርብ የአምልኮ ሥርዓት ያለፈ ነገርን እንደሚጠይቅ እንማራለን። ንጹሕ አምልኮ መላ ሕይወታችንን ማለትም አኗኗራችንንና ምግባራችንን በሙሉ የሚመለከት ነገር ነው።
-