የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ‘አምላክን በሚገባ ደስ አሰኝቷል’
    መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017 | ቁጥር 1
    • ‘ሞትን እንዳያይ ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ’

      የሄኖክ ሕይወት ያበቃው እንዴት ነበር? የሄኖክ አሟሟት፣ ከሕይወቱ የበለጠ አስገራሚና ትኩረት የሚስብ ነው። በዘፍጥረት ላይ የሚገኘው ዘገባ የሚናገረው የሚከተለውን ብቻ ነው፦ “ሄኖክ ከእውነተኛው አምላክ ጋር መሄዱን ቀጠለ። አምላክ ስለወሰደውም ከዚያ በኋላ አልተገኘም።” (ዘፍጥረት 5:24) አምላክ ሄኖክን የወሰደው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል፦ “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ፤ አምላክ ወደ ሌላ ቦታ ስለወሰደውም የትም ቦታ ሊገኝ አልቻለም፤ ከመወሰዱ በፊት አምላክን በሚገባ ደስ እንዳሰኘ ተመሥክሮለት ነበርና።” (ዕብራውያን 11:5) ጳውሎስ “ሞትን እንዳያይ . . . ተወሰደ” ሲል ምን ማለቱ ነው? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አምላክ ሄኖክን ወደ ሰማይ እንደወሰደው ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ሊሆን አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ በመሄድ ረገድ የመጀመሪያ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናገራል።—ዮሐንስ 3:13

      ታዲያ ሄኖክ “ሞትን እንዳያይ . . . ተወሰደ” የተባለው ከምን አንጻር ነው? ሄኖክ በጠላቶቹ እጅ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዳይገደል ይሖዋ ታድጎት መሆን አለበት፤ በዚህ መንገድ ሳይሠቃይ በሞት እንዲያንቀላፋ በማድረግ ወስዶታል ሊባል ይችላል። ከመወሰዱ በፊት ግን “አምላክን በሚገባ ደስ እንዳሰኘ ተመሥክሮለት ነበር።” እንዴት? ልክ ከመሞቱ በፊት፣ አምላክ ገነት የሆነችውን ምድር በራእይ አሳይቶት ሊሆን ይችላል። ሄኖክ በይሖዋ ፊት ሞገስ እንዳገኘ የሚያሳየውን ይህን ግልጽ ምልክት ካየ በኋላ በሞት አንቀላፋ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሄኖክን ጨምሮ ስለ ሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ሲናገር “እምነታቸውን እንደጠበቁ ሞቱ” ብሏል። (ዕብራውያን 11:13) ከዚያ በኋላ ጠላቶቹ አስከሬኑን ለመፈለግ ሞክረው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም የሄኖክ አስከሬን “የትም ቦታ ሊገኝ አልቻለም”፤ ይህ የሆነው ይሖዋ እነዚህ ሰዎች አስከሬኑን እንዳያረክሱት ወይም የሐሰት አምልኮን ለማራመድ እንዳይጠቀሙበት ለማገድ ሲል ስለሰወረው ሊሆን ይችላል።b

      መጽሐፍ ቅዱስ ሄኖክ “ተወሰደ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ተመልክተናል፤ አሁን ደግሞ ሕይወቱ ያበቃው እንዴት እንደሆነ በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል እንሞክር። እስቲ የሚከተለው ሁኔታ እንደተፈጠረ አድርገን እናስብ። ሄኖክ ከጠላቶቹ ሲሸሽ ቆይቶ አሁን በጣም ደክሞታል። ጠላቶቹ በተናገረው የፍርድ መልእክት ደማቸው ፈልቶ እያሳደዱት ነው። ሄኖክ መደበቂያ ቦታ አግኝቶ አረፍ አለ፤ ይሁንና ጠላቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈልገው እንደሚያገኙት ገብቶታል። በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገደልበት ጊዜ በጣም እንደተቃረበ ተሰምቶታል። አረፍ እንዳለ ወደ አምላኩ መጸለይ ጀመረ። ከዚያም አስገራሚ የሆነ የመረጋጋት ስሜት ተሰማው። ልክ በእውን እንደሚያየው ያለ ራእይ እየተመለከተ ጭልጥ ብሎ ሄደ።

      ሄኖክ እያሳደዱት ያሉት ሰዎች ሲያልፉ ዋሻ ውስጥ ተደብቆ ሲያይ

      ይሖዋ ሄኖክን የወሰደው በአሰቃቂ ሁኔታ ሊገደል ተቃርቦ በነበረበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም

      ሄኖክ፣ እሱ ከሚያውቀው በጣም የተለየ ዓለም በፊቱ ወለል ብሎ ሲታየው በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ቦታው ልክ እንደ ኤደን ገነት ያለ ውብ ስፍራ ነው፤ ሆኖም ሰዎች እንዳይገቡ የሚከለክሉ ኪሩቤል በዚያ የሉም። ጤናማና ወጣት የሆኑ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ይታያሉ። የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርስ ምንም ነገር የለም። ሄኖክን ያስመረረው ጥላቻና ስደትም ሙሉ በሙሉ ተወግዷል። ከዚያም ይሖዋ እንደተደሰተበትና እንደሚወደው እንዲሁም በፊቱ ሞገስ እንዳገኘ ተሰማው። ወደፊት በዚህ ቦታ መኖሩ እንደማይቀር እርግጠኛ ሆነ። ሄኖክ ከምንጊዜውም ይበልጥ ውስጣዊ ሰላምና የመረጋጋት ስሜት ተሰማው፤ ከዚያም ዓይኖቹን ሲከድን ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደው።

      ሄኖክ እስካሁን በሞት እንዳንቀላፋ ይገኛል፤ ሆኖም ገደብ የሌለው የማስታወስ ችሎታ ያለው ይሖዋ አምላክ፣ ሄኖክን ፈጽሞ አይረሳውም! ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት፣ አምላክ የሚያስታውሳቸው ሰዎች በሙሉ የክርስቶስን ድምፅ ሰምተው ከመቃብር ይወጣሉ፤ ከዚያም ውብ በሆነና ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ይኖራሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29

  • ‘አምላክን በሚገባ ደስ አሰኝቷል’
    መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017 | ቁጥር 1
    • b አምላክ የሙሴና የኢየሱስ አስከሬንም ቢሆን እንዳይገኝ ያደረገው ሰዎች አስከሬናቸውን እንዳያረክሱት ወይም የሐሰት አምልኮን ለማራመድ እንዳይጠቀሙበት ለማገድ ሲል ሊሆን ይችላል።—ዘዳግም 34:5, 6፤ ሉቃስ 24:3-6፤ ይሁዳ 9

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ