-
በአምላካችን በይሖዋ ስም እንሄዳለንመጠበቂያ ግንብ—2005 | መስከረም 1
-
-
በአምላካችን በይሖዋ ስም እንሄዳለን
“አሕዛብ ሁሉ፣ በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” Nw] ስም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።”—ሚክያስ 4:5
1. በኖኅ ዘመን ሰዎች በሥነ ምግባር ረገድ እንዴት ነበሩ? ኖኅ የተለየ የነበረው እንዴት ነው?
አካሄዱን ከአምላክ ጋር እንዳደረገ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ሰው ሄኖክ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኖኅ ነው። ዘገባው “ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:9) በጥቅሉ ሲታይ በኖኅ ዘመን ሰዎች ከንጹሕ አምልኮ ርቀው ነበር። መጥፎ የነበረው የጊዜው ሁኔታ የባሰ እንዲከፋ ያደረገው ደግሞ ከሃዲ መላእክት ከተፈጥሯቸው ውጪ ሴቶችን በማግባት “በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ” ኔፊሊም የሚባሉ ልጆችን መውለዳቸው ነው። ስለዚህ ምድር በዓመጽ መሞላቷ ምንም አያስገርምም! (ዘፍጥረት 6:2, 4, 11) የሆነ ሆኖ ኖኅ ጻድቅ መሆኑን ከማረጋገጡም በተጨማሪ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) አምላክ፣ ኖኅ ሕይወቱን የሚያተርፍበት መርከብ እንዲያዘጋጅ በነገረው ጊዜ “ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።” (ዘፍጥረት 6:22) በእርግጥም ኖኅ ከአምላክ ጋር ሄዷል።
2, 3. ኖኅ በዛሬው ጊዜ ላለነው ምን ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል?
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ታማኝ ምሥክሮችን በዘረዘረ ጊዜ ስለ ኖኅም እንዲህ ብሏል:- “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።” (ዕብራውያን 11:7) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ኖኅ የይሖዋ ቃል መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኛ ስለነበረ የአምላክን ትእዛዝ ለመፈጸም ጊዜውን፣ ጉልበቱንና ሀብቱን ሰውቷል። ዛሬም በተመሳሳይ ይህ ዓለም ለሚከፍትላቸው አጋጣሚዎች ጀርባቸውን ሰጥተው ይሖዋን ለመታዘዝ ሲሉ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን የሚሰዉ ብዙ ሰዎች አሉ። የእነዚህ ሰዎች እምነት የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት የሚያድን በመሆኑ ላቅ ያለ ዋጋ አለው።—ሉቃስ 16:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16
3 ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው እንደ ኖኅ ቅድመ አያት እንደ ሄኖክ ሁሉ ኖኅና ቤተሰቦቹ በእምነት ለመመላለስ ከብዷቸው መሆን አለበት። ልክ እንደ ሄኖክ ዘመን በኖኅ ዘመንም እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ቁጥር በጣም ትንሽ ነበር፤ ታማኝነታቸው የተረጋገጠውና ከጥፋት ውኃ የተረፉት ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ኖኅ ዓመጸኛ በነበረውና ሥነ ምግባር በጎደለው ዓለም ውስጥ ጽድቅን ይሰብክ ነበር። ከዚህም በላይ እርሱና ቤተሰቦቹ የእንጨት መርከብ በመሥራት ዓለም አቀፍ ለሆነው የጥፋት ውኃ ተዘጋጅተው ነበር፤ ይሁንና ከዚያ በፊት ዝናብ ሲዘንብ ያየ ማንም ሰው አልነበረም። በመሆኑም ይመለከቷቸው የነበሩት ሰዎች ነገሩ እንግዳ ሳይሆንባቸው አልቀረም።
4. ኢየሱስ ጎላ አድርጎ የጠቀሰው በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች የፈጸሙትን የትኛውን ስህተት ነው?
4 የሚገርመው ነገር ዓመጽ፣ የሐሰት ሃይማኖትና መጥፎ ሥነ ምግባር አሳፋሪ ድርጊቶች ቢሆኑም ኢየሱስ ስለ ኖኅ ዘመን በተናገረበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች አልጠቀሰም። ኢየሱስ ስህተት እንደሆነ ጎላ አድርጎ የጠቀሰው ሕዝቡ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተቀብሎ እርምጃ አለመውሰዱን ነበር። “ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ” ኢየሱስ ተናግሯል። መብላትና መጠጣት፣ ማግባትና መጋባት ስህተት ነው? ሰዎቹ ማስጠንቀቂያውን ችላ ብለው የተለመደውን ኑሮ ይመሩ ነበር! ነገር ግን የጥፋት ውኃ መምጫው ተቃርቦ ነበር፤ ኖኅም ጽድቅን ይሰብክ ነበር። የሚነግራቸው ነገርና አኗኗሩ ማስጠንቀቂያ ሊሆናቸው ይገባ የነበረ ቢሆንም ‘እስከዚያ ጊዜ ድረስ ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ ድንገት የጥፋት ውሃ አጥለቅልቋቸዋል።’—ማቴዎስ 24:38, 39
5. ኖኅና ቤተሰቡ ምን ዓይነት ባሕርያትን ማዳበር አስፈልጓቸው ነበር?
5 ያንን ዘመን መለስ ብለን ስናስብ ኖኅ ጥበብ ያለበት ኑሮ ይመራ እንደነበር ማየት እንችላለን። ይሁን እንጂ ከጥፋት ውኃ በፊት በነበሩት ጊዜያት ከሌሎች የተለዩ ሆኖ መኖር ድፍረት ይጠይቅ ነበር። ኖኅና ቤተሰቡ ትልቅ መርከብ ለመገንባትና የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎችን ወደ መርከቡ ለማስገባት ጠንካራ እምነት አስፈልጓቸዋል። ከእነዚህ ጥቂት ታማኞች መካከል አንዳንዶቹ የሰዎችን ትኩረት ሳይስቡ እንደሌሎቹ ሰዎች የተለመደውን ኑሮ ለመኖር የተመኙበት ጊዜ ይኖር ይሆን? እንዲህ ያለ ሐሳብ መጥቶባቸው ሊሆን ቢችልም ጽኑ አቋማቸውን አላላሉም። ኖኅ የነበረው እምነት፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ማናችንም ከሚኖረን ዕድሜ በላይ ቆይቶ ከመጣው የጥፋት ውኃ ለመትረፍ አስችሎታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የተለመደውን ዓይነት ኑሮ ሲመሩ የነበሩትንና በምን ዓይነት ጊዜ ውስጥ እየኖሩ እንዳሉ ያላስተዋሉትን ሰዎች ሁሉ የቅጣት ፍርድ ፈጽሞባቸዋል።
-
-
በአምላካችን በይሖዋ ስም እንሄዳለንመጠበቂያ ግንብ—2005 | መስከረም 1
-
-
ለይሖዋ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት እንሰጣለን
9. ያለንበት ዘመን ከጥፋት ውኃ በፊት ከነበረው ጊዜ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
9 ይሖዋ በኖኅ ዘመን የሰው ልጆችን ያጠፋው ክፉ ሰዎች በኔፊሊሞች ገፋፊነት ከባድ ዓመጽ በመፈጸማቸው ምክንያት ነበር። ዛሬስ በምድር ላይ የሚፈጸመው ነገር በዚያ ዘመን ከነበረው ያንሳል? በፍጹም አያንስም! በተጨማሪም በኖኅ ዘመን እንደነበረው በዛሬው ጊዜ ሰዎች የዕለት ተዕለት ጉዳዮቻቸውን በማከናወን የተለመደውን ኑሮ ለመምራት ይሯሯጣሉ፤ እየተሰጡ ያሉትንም ማስጠንቀቂያዎች ሰምተው እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኞች አይደሉም። (ሉቃስ 17:26, 27) ይሖዋ በድጋሚ የሰው ልጆችን አያጠፋም ብለን የምንጠራጠርበት ምክንያት ይኖራል? በጭራሽ።
10. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ በተደጋጋሚ ምን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ብቸኛው የጥበብ አካሄድ ምንድን ነው?
10 ሄኖክ የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በዘመናችን ስለሚደርሰው ጥፋት ተንብዮአል። (ይሁዳ 14, 15) ኢየሱስም ስለመጪው “ታላቅ መከራ” ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:21) ሌሎች ነቢያትም እንዲሁ ስለዚያ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። (ሕዝቅኤል 38:18-23፤ ዳንኤል 12:1፤ ኢዩኤል 2:31, 32) እንዲሁም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የመጨረሻውን ጥፋት በሚመለከት ሕያው መግለጫ ተሰጥቷል። (ራእይ 19:11-21) እኛም በግለሰብ ደረጃ የኖኅን ምሳሌ በመኮረጅ በትጋት ጽድቅን እንሰብካለን። ለይሖዋ ማስጠንቀቂያዎች ትኩረት እንሰጣለን፣ ጎረቤቶቻችንም እንዲሁ እንዲያደርጉ በፍቅር ተነሳስተን እንረዳቸዋለን። በመሆኑም ልክ እንደ ኖኅ ከአምላክ ጋር እንሄዳለን። ሕይወትን የሚፈልግ ማንም ሰው ከአምላክ ጋር መሄዱን መቀጠል እንዳለበት የተረጋገጠ ነው። የሚያስጨንቅ ነገር በየዕለቱ እያጋጠመንም እንኳን እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ዓላማ እንደሚፈጸም ጠንካራ እምነት በማዳበር ነው።—ዕብራውያን 11:6
-