የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የኖኅ መርከብ ተገኝቷል?
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሐምሌ 1
    • መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኖኅ መርከብ “በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 8:4) የአራራት ክልል፣ በቱርክ ምሥራቃዊ ክፍል ያለውንና በአሁኑ ጊዜ አራራት ተብሎ የሚጠራውን ረጅም ተራራ ይጨምራል፤ ይህ ተራራ የሚገኘው በአርሜኒያና በኢራን ድንበር አቅራቢያ ነው።

      በርካታ ሰዎች በዚህ አካባቢ የኖኅን መርከብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ በኋላ አስገራሚ ሐሳቦችን የሰነዘሩ ቢሆንም ተጨባጭ ማስረጃ ያቀረበ አንድም ሰው የለም። ከአውሮፕላን ላይ የተነሱ አስገራሚ ፎቶግራፎችና መርከቡ እንደታየ የሚናገሩ ሪፖርቶች መኖራቸው እንዲሁም በቅጥራን የተሸፈኑ የእንጨት ቁርጥራጮች መገኘታቸው ሰዎች ይበልጥ ተጨባጭ የሆነ ማስረጃ ለማግኘት እንዲነሳሱ አድርገዋቸዋል። ይሁንና ፍለጋው ቀላል አልሆነም። በመጀመሪያ ደረጃ መርከቡ አርፎበታል ተብሎ በአብዛኛው የሚጠቀሰው የአራራት ተራራ ክፍል ወደ 4,600 ሜትር ከፍታ አለው። በሁለተኛ ደረጃ በአካባቢው ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የውጭ አገር አሳሾች ወደ ተራራው ለመውጣት ፈቃድ የሚያገኙት ሁልጊዜ አይደለም።

      ያም ሆኖ መርከቡ እንዲገኝ በጣም የሚጓጉ በርካታ ሰዎች፣ በተራራው ላይ ተጨማሪ አሰሳ እንዲደረግ ይፈልጋሉ። እነዚህ ሰዎች የመርከቡ የተወሰነ ክፍል በበረዶ በተሸፈነው የአራራት ተራራ ላይ አሁን ድረስ ሳይፈራርስ እንደሚገኝና አብዛኛውን የዓመቱን ክፍል በበረዶ ተሸፍኖ እንደሚቆይ ይናገራሉ። ከዚህም በተጨማሪ መርከቡን የማየትም ሆነ ወደ መርከቡ የመቅረብ አጋጣሚ የሚኖረው ሞቃታማ የሆኑ የበጋ ወራት ባሏቸው ዓመታት ውስጥ ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ።

      በርካታ ሪፖርቶች ይህ ተስፋ እንዲለመልም አድርገዋል። በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ፣ በአራራት ክልል ባሉ ተራሮች ላይ መርከቡ እንደሚታይ ስለተናገሩ የተለያዩ የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች ጠቅሷል። እንዲያውም ሰዎች በቅጥራን የተሸፈኑ የእንጨት ቁርጥራጮችን ለማስታወሻነት ይወስዱ እንደነበር የሚገልጹ ሪፖርቶችም አሉ። ጆሴፈስ ከጠቀሳቸው ሰዎች መካከል በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ባቢሎናዊው ታሪክ ጸሐፊ በራሰስ ይገኝበታል።

      የብዙዎችን ትኩረት ከሳቡት ሪፖርቶች መካከል አንዱ፣ ባለፈው መቶ ዘመን ጆርጅ ሃጎፕያን የተባሉ አርመናዊ የተናገሩት ነገር ነው። እኚህ ሰው፣ ልጅ ሳሉ ማለትም በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከአጎታቸው ጋር ሆነው መርከቡ ያለበት ቦታ እንደሄዱ አልፎ ተርፎም መርከቡ ላይ እንደወጡ ተናግረዋል። ሃጎፕያን በ1972 የሞቱ ቢሆንም እሳቸው የተናገሩት ነገር አሁንም ድረስ ብዙዎች የኖኅን መርከብ ለማግኘት እንዲጓጉና ስለ መርከቡ እንዲጠይቁ አነሳስቷቸዋል።

      ለእምነት ጠንካራ መሠረት ሊሆን ይችላል?

      አሳሾች መርከቡን እንዳገኙት ለማመን አሊያም ደግሞ ወደፊት እንደሚያገኙት ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል መሠረት አለ? ይኖር ይሆናል፤ ይሁንና ስለ ኖኅ መርከብ መገኘት የሚቀርቡት ማስረጃዎች በአብዛኛው ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ይመስላሉ። መጀመሪያ ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውኃው ሲጎድል መርከቡ የት እንዳረፈ ለይቶ በግልጽ አይናገርም። ከዚህ ይልቅ የሚሰጠው መረጃ መርከቡ “በአራራት ተራሮች” ላይ እንዳረፈ ብቻ ነው።

      ስለ ኖኅ መርከብ ግምታዊ ሐሳብ የሚሰነዝሩ ሰዎችና አሳሾች በአካባቢው ካሉት ተራሮች ሁሉ ከፍተኛ በሆነው ተራራ ላይ እንደሚያነጣጥሩ ግልጽ ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአሁኑ ጊዜ ከባሕር ወለል በላይ ወደ አምስት ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ከፍታ ባለውና በጣም ቀዝቃዛ በሆነው የአራራት ተራራ አናት ላይ መርከቡ እንዲያርፍ አምላክ እንዳደረገ አይናገርም።a ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡ ተራራው ላይ ካረፈ በኋላ ለብዙ ወራት እዚያው መርከቡ ውስጥ እንደቆዩ አስታውስ። (ዘፍጥረት 8:4, 5) ከመርከቡ ከወጡ በኋላም ቢሆን ልክ ተራራ እንደሚወጡ ስፖርተኞች እንስሳቱን ይዘው ከረጅሙ ተራራ አናት ላይ ቁልቁል መውረድ ነበረባቸው ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። እንግዲያው መርከቡ ያረፈበት ቦታ አንዳንድ ዘመናዊ አሳሾች ከሚገምቱት የበለጠ ለመሬት ቅርብ ሳይሆን አይቀርም። እንደዚያም ሆኖ በዘፍጥረት 8:4, 5 ላይ ከሚገኘው መግለጫ አንጻር መርከቡ ያረፈበት ቦታ ከመሬት የተወሰነ ከፍታ ያለው መሆንም አለበት። መርከቡ ያረፈው በአራራት አካባቢ የትም ይሁን የት ሰዎች ቀስ በቀስ ከመርከቡ ላይ ሊጠቀሙበት የሚችሉትን ነገር ሲወስዱ ወይም በመበስበሱ ምክንያት ከዘመናት በፊት ጠፍቶ ሊሆን አይችልም?

  • የኖኅ መርከብ ተገኝቷል?
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | ሐምሌ 1
    • a በአሁኑ ጊዜ አራራት ተብሎ የሚጠራው ተራራ ከ1840 ወዲህ ምንም እንቅስቃሴ የማይታይበት እሳተ ገሞራ ነው። ከፍታው 5,165 ሜትር የሚደርስ ሲሆን ዓመቱን ሙሉ በበረዶ የተሸፈነ ነው።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ