አብርሃም እዚህ ተቀብሯል፤ ግን ሕያው ነውን?
ለብዙ መቶ ዘመናት አይሁዶች፣ እስላሞችና ክርስቲያኖች ወደዚህ ሥፍራ ተጉዘዋል።
ቦታውን ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ በምትገኘው በጥንቷ የኬብሮን ከተማ ሊያገኙት ይችላሉ። ይህ ቦታ ሃራም ኤል ካሊልና የዕብራውያን አባቶች መቃብር ተብሎ ይጠራል። አዎን፣ ይህ ቦታ ዕብራውያን አባቶች የሆኑት የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ እንዲሁም በቅደም ተከተላቸው መሠረት የሚስቶቻቸው የሣራ፣ የርብቃና የልያ የመቃብር ቦታ መሆኑ በስፋት ተቀባይነት አግኝቷል።
አብርሃም ውድ ሚስቱ ሣራ ስትሞት በኬብሮን አቅራቢያ በምትገኘው በማክጴላ መቃብር የሚሆን ዋሻና አንድ መሬት መግዛቱን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር ያስታውሱ። (ዘፍጥረት 23:2–20 የ1980 ትርጉም) ከጊዜ በኋላ አብርሃምም በዚህ ቦታ ተቀበረ፤ ሌሎች የቤተሰብ አባሎችም እንደዚሁ በዚህ ቦታ ተቀበሩ። ብዙ መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላ ታላቁ ሄሮድስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር በቆየው በዚህ መቃብር ዙሪያ ማራኪ የሆነ ግንብ ገነባ። ከጊዜ በኋላ ድል አድርገው አካባቢውን የተቆጣጠሩት ሰዎች የራሳቸውን ሃይማኖታዊ እምነቶች በሚያንጸባርቅ መንገድ መልኩን ለወጡት፤ እንዲሁም አስፍተው ሠሩት።
መግቢያው ላይ ስድስት ባዶ መቃብሮችን ይመለከታሉ። በስዕሉ ላይ ለብቻው የሚታየው የአብርሃምን ልጅ የይስሐቅን መቃብር ያሳያል። በአጠገቡ ወለሉ ላይ ከሥር ያለውን ነገር ማየት የሚቻልባቸው ቀዳዳዎች አሉ። ተመራማሪዎች በርካታ ጥንታውያን አፅሞችን ይዘው እንደነበር የሚገመቱ ደርቦችን አግኝተዋል።
አብርሃምስ? የተቀበረው ከዚህ በታች ባለው ዋሻ ውስጥ ከነበረ ከሞተ ብዙ ጊዜ ሆኖታል ማለት ነው። አይደለም እንዴ? ይህን ሥፍራ የጎበኙ አብዛኛዎቹ ሰዎች በዚህ ይስማማሉ። ሆኖም ከአብርሃም የሚበልጥ አንድ ነቢይ አብርሃም አሁንም ሕያው ነው ሊባል የሚቻልበት መንገድ እንዳለ ተናግሯል። እንዴት? ይህ ነገር በእምነትዎ ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችል ይሆን?
“የምታፈቅሯቸው በሞት የተለዩአችሁ ሰዎች የት ናቸው?” የሚለውን ርዕስ (ገጽ 3) እባክዎን ያንቡት። ያ ታላቅ ነቢይ ስለ አብርሃም ሕያውነት ምን እንዳለ ርዕሱ ይገልጻል። የሚያቀርበው መረጃ ለእርስዎም ሆነ ለቤተሰብዎ ትልቅ ዋጋ ሊኖረው ይችላል።