-
ከይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መጠቀምመጠበቂያ ግንብ—2002 | ግንቦት 15
-
-
የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ነፃነትና ጥበቃ ያስገኛል
11, 12. (ሀ) ዮሴፍ የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት የቀመሰው በምን ዓይነት መከራ ሥር እያለ ነው? (ለ) ከዮሴፍ ጋር በተያያዘ የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት የታየው እንዴት ነበር?
11 አሁን ደግሞ ዘፍጥረት ምዕራፍ 39ን እንመልከት። ታሪኩ የአብርሃም የልጅ ልጅ፣ ልጅ በሆነው ለባርነት ተሸጦ ወደ ግብፅ በተወሰደው በዮሴፍ ላይ ያተኩራል። ይሁንና “እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ።” (ቁጥር 1, 2) እንዲያውም ግብፃዊው የዮሴፍ ጌታ ጲጥፋራ እንኳ እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንዳለ ማወቅ ችሏል። (ቁጥር 3) ይሁን እንጂ ዮሴፍ በጣም ከባድ ፈተና ደረሰበት። የጲጥፋራን ሚስት በፆታ ሊደፍር ሞክሯል በሚል በሐሰት ተወንጅሎ ታሰረ። (ቁጥር 7-20) “በግዞት” እያለ “እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፣ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ።”—ዘፍጥረት 40:15፤ መዝሙር 105:18
12 በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ምን ተፈጸመ? “እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም [“ፍቅራዊ ደግነትንም፣” NW ] አበዛለት።” (ቁጥር 21ሀ) ይሖዋ ያሳየው ፍቅራዊ ደግነት ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ከመከራ ነፃ እንዲወጣ ያስቻሉ በርካታ ክስተቶች ደረጃ በደረጃ እንዲፈጸሙ አድርጓል። ይሖዋ ‘በግዞት ቤቱ አለቃ ፊት [ዮሴፍ] ሞገስ እንዲያገኝ አደረገ።’ (ቁጥር 21ለ) ከዚህም የተነሳ የግዞት ቤቱ አለቃ ለዮሴፍ ኃላፊነት ሰጠው። (ቁጥር 22) ከዚያ በኋላ ዮሴፍ ከአንድ ሰው ጋር የተገናኘ ሲሆን ይህም ሰው ውሎ አድሮ ዮሴፍ ያለበትን ሁኔታ ለግብፁ ገዢ ለፈርዖን አሳወቀለት። (ዘፍጥረት 40:1-4, 9-15፤ 41:9-14) በኋላም ንጉሡ ዮሴፍን በግብፅ ላይ ሁለተኛ ገዢ አድርጎ የሾመው ሲሆን ይህም በረሃብ በተመታችው በግብፅ ምድር ሕይወት አድን ሥራ እንዲያከናውን አጋጣሚ ከፈተለት። (ዘፍጥረት 41:37-55) ዮሴፍ የገጠመው መከራ የጀመረው የ17 ዓመት ልጅ እያለ ሲሆን ከ12 ዓመት በላይ በመከራ ሥር ኖሯል! (ዘፍጥረት 37:2, 4፤ 41:46) ሆኖም ችግርና መከራ ይደርስበት በነበረበት በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ይሖዋ አምላክ ዮሴፍን ከከፋ አደጋ በመጠበቅና በመለኮታዊ ዓላማ ውስጥ ልዩ ሚና እንዲጫወት ሕይወቱን በመታደግ ፍቅራዊ ደግነቱን ገልጦለታል።
-
-
ከይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት መጠቀምመጠበቂያ ግንብ—2002 | ግንቦት 15
-
-
16. መጽሐፍ ቅዱስ አብርሃምንና ዮሴፍን በጥሩ ሁኔታ የሚገልጻቸው እንዴት ነው?
16 ዘፍጥረት ምዕራፍ 24 ላይ የሚገኘው ዘገባ አብርሃም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንደነበረው በግልጽ ያሳያል። የመጀመሪያው ቁጥር “እግዚአብሔርም አብርሃምን በሥራው ሁሉ ባረከው” ሲል ይገልጻል። የአብርሃም ሎሌ ይሖዋን “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ” ሲል ጠርቶታል። (ቁጥር 12, 27) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ደግሞ አብርሃም ‘ጻድቅ’ እንደሆነና ‘የእግዚአብሔር ወዳጅ እንደተባለ’ ተናግሯል። (ያዕቆብ 2:21-23) የዮሴፍ ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። በይሖዋና በዮሴፍ መካከል ያለው የጠበቀ ዝምድና በዘፍጥረት ምዕራፍ 39 ውስጥ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። (ቁጥር 2, 3, 21, 23) በተጨማሪም ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ዮሴፍን በማስመልከት “እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ” ሲል ተናግሯል።—ሥራ 7:9
-