የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 10/15 ገጽ 8-13
  • ኢየሩሳሌም “የታላቁ ንጉሥ ከተማ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኢየሩሳሌም “የታላቁ ንጉሥ ከተማ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘የይሖዋ ዙፋን’ የሚገኝበት ቦታ
  • ከሰላም ወደ ባድማነት
  • የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ከነበሩ ጎረቤቶች የገጠማቸው ተቃውሞ
  • መሲሑ ታየ!
  • የዘላቂ ሰላም ናሙና
  • ምድራዊቱ ኢየሩሳሌም ከሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ጋር ስትነጻጸር
    “የሰላሙ መስፍን“ ሲገዛ በምድር ዙሪያ የሚገኝ ዋስትና ያለው ሕይወት
  • ከስሟ ትርጉም ጋር የምትስማማዋ ኢየሩሳሌም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ምን ታመለክታለች?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • አንጸባራቂዋ ከተማ
    ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 10/15 ገጽ 8-13

ኢየሩሳሌም “የታላቁ ንጉሥ ከተማ”

“ከቶ አትማሉ፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና።”​—⁠ማቴዎስ 5:​34, 35

1, 2. ኢየሩሳሌምን በተመለከተ አንዳንዶችን ምን ነገር ግራ ያጋባቸው ይሆናል?

ኢየሩሳሌም​—⁠ስሟ ራሱ በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ጠንካራ ስሜት ያሳድራል። እንዲያውም ይህች ጥንታዊት ከተማ በዜና ማሰራጫዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ስለምትጠቀስ ማናችንም ብንሆን ስለዚህች ከተማ ማሰባችን አይቀርም። የሚያሳዝነው ግን ኢየሩሳሌም ሁልጊዜ የሰላም ቦታ አለመሆኗን ብዙ ዘገባዎች ያሳያሉ።

2 ይህ ሁኔታ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎችን ግራ ያጋባ ይሆናል። በድሮ ጊዜ የኢየሩሳሌም አጭር አጠራር ሳሌም ሲሆን ትርጉሙም “ሰላም” ማለት ነው። (ዘፍጥረት 14:​18፤ መዝሙር 76:​2፤ ዕብራውያን 7:​1, 2) ታዲያ ‘ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህን የመሰለ ስም ያላት ከተማ ሰላም ያጣችው ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

3. ስለ ኢየሩሳሌም አስተማማኝ መረጃ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?

3 ይህን ጥያቄ ለመመለስ ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪክን በመመርመር ስለ ጥንቷ ኢየሩሳሌም ማወቅ ያስፈልገናል። ሆኖም አንዳንዶች ‘የጥንት ታሪክ ለማጥናት ጊዜ የለንም’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ስለ ኢየሩሳሌም የቀድሞ ታሪክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ለሁላችንም ይጠቅማል። መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን አስፈላጊነት በሚከተሉት ቃላት ይገልጻል:- “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” (ሮሜ 15:​4) ኢየሩሳሌምን በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው እውቀት ሊያጽናናን እንዲሁም በዚያች ከተማ ብቻ ሳይሆን በመላው ምድር ላይ ስለሚሰፍነው የሰላም ተስፋ ሊሰጠን ይችላል።

‘የይሖዋ ዙፋን’ የሚገኝበት ቦታ

4, 5. ኢየሩሳሌም በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ላይ ቁልፍ ሚና እንድትጫወት በመርዳት ረገድ ዳዊት ተካፋይ የነበረው እንዴት ነው?

4 በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ኢየሩሳሌም ሰላምና ደኅንነት የሰፈነበት መንግሥት ዋና ከተማ በመሆን ዓለም አቀፍ እውቅናን አግኝታ ነበር። ይሖዋ አምላክ ወጣቱ ዳዊትን በዚያ ጥንታዊ ብሔር ማለትም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ቀብቶት ነበር። ዳዊትና ዘሮቹ የመስተዳድሩ መቀመጫ በኢየሩሳሌም በሆነው “በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን” ወይም ‘በእግዚአብሔር ዙፋን’ ላይ ተቀምጠው ነበር።​—⁠1 ዜና መዋዕል 28:​5፤ 29:​23 የ1980 እትም

5 ከይሁዳ ነገድ የሆነው እስራኤላዊው ዳዊት ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሲሆን ጣዖት አምላኪዎች የሆኑትን ኢያቡሳውያንን ወግቶ ኢየሩሳሌምን ያዘ። በዚያን ወቅት ከተማዋ የምታካልለው ጽዮን የሚባለውን ኮረብታ ብቻ ነበር፤ ሆኖም ይህ ስም ሌላ የኢየሩሳሌም መጠሪያ ሆኖ አገልግሏል። ከጊዜ በኋላ ዳዊት የአምላክን የቃል ኪዳን ታቦት ከእስራኤላውያን ጋር በመሆን ወደ ኢየሩሳሌም ከወሰደው በኋላ በድንኳን ውስጥ እንዲቀመጥ አደረገ። ከዓመታት በፊት አምላክ በዚህ ቅዱስ ታቦት ላይ በነበረ ደመና ውስጥ ሆኖ ከነቢዩ ሙሴ ጋር ተነጋግሯል። (ዘጸአት 25:​1, 21, 22፤ ዘሌዋውያን 16:​2፤ 1 ዜና መዋዕል 15:​1–3) ትክክለኛው የእስራኤል ንጉሥ ይሖዋ ስለነበር ታቦቱ የአምላክን በዚያ መኖር የሚያመለክት ነበር። ስለዚህ በሁለት መንገድ ይሖዋ አምላክ በኢየሩሳሌም ከተማ ሆኖ ይገዛ ነበር ሊባል ይቻላል።

6. ይሖዋ ዳዊትንና ኢየሩሳሌምን በተመለከተ ምን ተስፋ ሰጥቶ ነበር?

6 በጽዮን ወይም በኢየሩሳሌም የተሰየመው የንግሥና መስመሩ እንደማይቋረጥ ይሖዋ ለዳዊት ቃል ገብቶለት ነበር። ይህ ማለት የዳዊት ዝርያ የሆነ ሰው በአምላክ የተቀባ ማለትም መሲሕ ወይም ክርስቶስ ሆኖ ለዘላለም የመግዛት መብት ያገኛል ማለት ነው።a (መዝሙር 132:​11–14፤ ሉቃስ 1:​31–33) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ‘የይሖዋ ዙፋን’ ዘላለማዊ ወራሽ በኢየሩሳሌም ብቻ ሳይሆን በሁሉም ብሔራት ላይ እንደሚገዛ ይገልጻል።​—⁠መዝሙር 2:​6–8፤ ዳንኤል 7:​13, 14

7. ንጉሥ ዳዊት ንጹሕ አምልኮ እንዲስፋፋ ያደረገው እንዴት ነበር?

7 በአምላክ የተቀባውን ንጉሥ ዳዊትን ከሥልጣን ለማውረድ የተደረጉ ሙከራዎች ከሽፈዋል። ከዚህ ይልቅ ጠላት የነበሩ ብሔራት ተሸንፈው የተስፋይቱ ምድር ድንበሮች አምላክ እስከ ወሰነው መጠን ድረስ ተስፋፍተዋል። ዳዊት ይህን አጋጣሚ ንጹሑን አምልኮ ለማስፋፋት ተጠቅሞበታል። እንዲሁም አብዛኞቹ የዳዊት መዝሙሮች ይሖዋ እውነተኛው የጽዮን ንጉሥ መሆኑን የሚያወድሱ ናቸው።​—⁠2 ሳሙኤል 8:​1–15፤ መዝሙር 9:​1, 11፤ 24:​1, 3, 7–10፤ 65:​1, 2፤ 68:​1, 24, 29፤ 110:​1, 2፤ 122:​1–4

8, 9. በንጉሥ ሰሎሞን የንግሥና ዘመን እውነተኛው አምልኮ የተስፋፋው እንዴት ነበር?

8 በዳዊት ልጅ በሰሎሞን የንግሥና ዘመን የይሖዋ አምልኮ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ሰሎሞን የሞርያን ኮረብታ (በአሁኑ ጊዜ ዶም ኦቭ ዘ ሮክ የተባለው የእስላም መቅደስ ይገኝበታል) ለማካተት ሲል ኢየሩሳሌምን በስተ ሰሜን አስፍቷት ነበር። ሰሎሞን በዚህ ከፍተኛ ቦታ ላይ ለይሖዋ ክብር ዕጹብ ድንቅ የሆነ ቤተ መቅደስ የመገንባት መብት አግኝቷል። የቃል ኪዳኑ ታቦት በዚህ ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ተቀመጠ።​—⁠1 ነገሥት 6:​1–38

9 የእስራኤል ብሔር ኢየሩሳሌምን ማዕከል ላደረገው የይሖዋ አምልኮ ሙሉ ድጋፉን በሰጠ ጊዜ ሰላምን አግኝቶ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች ሁኔታውን ውብ በሆነ መንገድ ሲገልጹት እንዲህ ይላሉ:- “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር። . . . በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን [ለሰሎሞን] ሰላም ሆኖለት ነበር። . . . ይሁዳና እስራኤል . . . እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልሎ ይቀመጥ ነበር።”​—⁠1 ነገሥት 4:​20, 24, 25

10, 11. ሰሎሞን ንጉሥ በነበረበት ጊዜ ኢየሩሳሌም ስለነበራት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው እውነት መሆኑን አርኪኦሎጂ ያረጋገጠው እንዴት ነው?

10 የበለጸገ ስለነበረው የሰሎሞን ግዛት የሚገልጸው ይህ ታሪክ የአርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ድጋፍ አለው። ፕሮፌሰር ዮሃናን አሃሮኒ ዚ አርኪኦሎጂ ኦቭ ዘ ላንድ ኦቭ ኢዝሬል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ከየአቅጣጫው ወደ ቤተ መንግሥቱ ይጎርፍ የነበረው ሀብትና የንግዱ መስፋፋት . . . በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ፈጣንና ጉልህ የሆነ ለውጥ አምጥቷል። . . . ጉልህ ለውጥ የታየው በቅንጦት ዕቃዎች ረገድ ብቻ ሳይሆን በተለይ በሴራሚክ ውጤቶች ረገድም ትልቅ እመርታ ታይቷል። . . . የሸክላ ሥራ ጥራትና ዕቃዎቹን በእሳት የመተኮሱ ሂደት ከሚገመተው በላይ መሻሻል አሳይቶ ነበር።”

11 በተመሳሳይም ጄሪ ኤም ላንዴይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የእስራኤል የመገልገያ ቁሳቁሶች በሰሎሞን አገዛዝ ሥር በነበሩት ሦስት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ያሳየው እድገት ቀደም ሲል በነበሩት ሁለት መቶ ዓመታት ውስጥ ካሳየው እድገት እጅግ የላቀ ነበር። በሰሎሞን ዘመን ታላላቅ የግንባታ ሥራዎች፣ ግዙፍ ግንቦች ያሏቸው ታላላቅ ከተሞች፣ ሃብታሞች የሚኖሩባቸው በግሩም ሁኔታ የተሠሩ የመኖሪያ ቤቶች መስፋፋትና የሸክላ ሠሪው ቴክኒካዊ ብቃትና የማምረት ሂደቱ ከፍተኛ እመርታ አሳይተው እንደነበር በመሬት ቁፋሮ ከተገኙ ንብብሮች (strata) ለመመልከት እንችላለን። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የሆነ የንግድ ልውውጥ መኖሩን የሚያመለክቱ ከሩቅ አገር የመጡ የዕደ ጥበባት ውጤቶች ቅሪት እናገኛለን።”​—⁠ዘ ሃውስ ኦቭ ዴቪድ

ከሰላም ወደ ባድማነት

12, 13. በኢየሩሳሌም እውነተኛው አምልኮ መስፋፋቱን ያልቀጠለው እንዴት ነበር?

12 የይሖዋ መቅደስ የሚገኝባት ከተማ ስለሆነችው ስለ ኢየሩሳሌም ሰላምና ብልጽግና መጸለይ ተገቢ ነበር። ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በኢየሩሳሌም ከተማ ሰላም እንዲሆን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፣ ‘የሚወዱሽ ሁሉ ይበልጽጉ፤ በቅጥሮችሽ ውስጥ ሰላም ይሁን፤ በቤተ መንግሥትሽም ውስጥ ጸጥታ ይኑር።’ በዘመዶቼና በወዳጆቼ ምክንያት ኢየሩሳሌምን ‘ሰላም ከአንቺ ጋር ይሁን’ እላታለሁ።” (መዝሙር 122:​6–8 የ1980 ትርጉም) ሰሎሞን ሰላም በሰፈነባት በዚያች ከተማ ውስጥ ያንን ታላቅ ቤተ መቅደስ የመገንባት መብት ቢያገኝም ከጊዜ በኋላ ብዙ አረማዊ ሚስቶችን አገባ። እነሱም፣ ሰሎሞን በስተርጅናው በዘመኑ የነበሩትን የሐሰት አማልክት አምልኮ እንዲያስፋፋ ልቡን አዘነበሉት። ይህ ክህደት ጠቅላላውን ብሔር የሚበክል፣ የከተማዋንም ሆነ የነዋሪዎቿን እውነተኛ ሰላም የሚገፍፍ ነበር።​—⁠1 ነገሥት 11:​1–8፤ 14:​21–24

13 በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ግዛት የመጀመሪያ ዓመታት ላይ አሥር ነገዶች ዓምፀው ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት አቋቋሙ። ጣዖት አምላኪዎች በመሆናቸው ምክንያት አምላክ ይህ መንግሥት በአሦር እንዲወድቅ ፈቀደ። (1 ነገሥት 12:​16–30) ሁለት ነገዶችን ያቀፈው ደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ኢየሩሳሌምን ማዕከሉ አድርጎ ቀጠለ። ሆኖም ከጊዜ በኋላ እነሱም ከንጹሕ አምልኮ ዘወር በማለታቸው አምላክ ይቺን ዓመፀኛ ከተማ በ607 ከዘአበ በባቢሎናውያን እንድትጠፋ ፈቀደ። የአይሁድ ግዞተኞች በባቢሎን ምርኮኞች ሆነው ለ70 ዓመታት ማቀቁ። ከዚያም አምላክ ምሕረት ስላደረገላቸው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና ንጹሑን አምልኮ መልሰው እንዲያቋቁሙ ተፈቀደላቸው።​—⁠2 ዜና መዋዕል 36:​15–21

14, 15. ኢየሩሳሌም ከባቢሎን ግዞት በኋላ የነበራትን ቁልፍ ቦታ መልሳ ያገኘችው እንዴት ነበር? ሆኖም ምን ለውጥ ነበር?

14 ከ70 ዓመታት ባድማነት በኋላ እነዚያ የወደሙ ሕንፃዎች በአረም ተሸፍነው መሆን አለበት። በአንድ ወቅት ትላልቅ በሮችና ቅጥሩን ደግፈው የሚያቆሙ ግንቦች የነበሩት የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈራርሶ ክፍት ሆኗል። ሆኖም ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዶች ድፍረት ነበራቸው። የቀድሞው ቤተ መቅደስ በነበረበት ቦታ ላይ መሠዊያ በመሥራት በየቀኑ ለይሖዋ መሥዋዕቶችን ማቅረብ ጀመሩ።

15 ይህ ተስፋ የሚሰጥ ጅምር ቢሆንም ተመልሳ የተቋቋመችው ኢየሩሳሌም የንጉሥ ዳዊት ዝርያ የሆነ ሰው በዙፋን ላይ ተቀምጦ የሚገዛበት መንግሥት ዋና ከተማ አትሆንም ነበር። ከዚያ ይልቅ አይሁዶች ባቢሎንን ድል ያደረገው ኃይል በሾሙላቸው ገዥ የሚተዳደሩ ሲሆን ለፋርሳውያን ጌቶቻቸውም ቀረጥ መክፈል ነበረባቸው። (ነህምያ 9:​34–37) ኢየሩሳሌም “የተረገጠች” ብትሆንም በመላው ምድር ከሚገኙ ከተሞች ይልቅ በይሖዋ ፊት ሞገስን ያገኘች ከተማ ነበረች። (ሉቃስ 21:​24) የንጹሕ አምልኮ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን አምላክ በዳዊት ዘር አማካኝነት በምድር ላይ ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት እንዳለው የምታመለክትም ነበረች።

የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ከነበሩ ጎረቤቶች የገጠማቸው ተቃውሞ

16. ከባቢሎን የተመለሱት አይሁዶች ኢየሩሳሌምን መልሰው መገንባታቸውን ያቆሙት ለምን ነበር?

16 ከግዞት ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት አይሁዳውያን ወዲያውኑ አዲስ ቤተ መቅደስ ለመሥራት መሠረት ጣሉ። ሆኖም የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የነበሩት ጎረቤቶቻቸው ለፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ አይሁዳውያን ሊያምፁ መሆኑን የሚገልጽ የሐሰት ደብዳቤ ላኩ። በመሆኑም አርጤክስስ የኢየሩሳሌም ግንባታ እንዲቆም አደረገ። የምትኖረው በዚያች ከተማ ቢሆን ኖሮ ይህች ከተማ የወደፊት ዕጣዋ ምን ይሆን ብለህ መጠየቅህ አይቀርም ነበር። በኋላ እንደታየውም አይሁዳውያን የቤተ መቅደሱን ግንባታ አቁመው የራሳቸውን ሥጋዊ ፍላጎቶች ለማሟላት መሯሯጣቸውን ተያያዙት።​—⁠ዕዝራ 4:​11–24፤ ሐጌ 1:​2–6

17, 18. ኢየሩሳሌም ተመልሳ እንድትገነባ ለማድረግ ይሖዋ በምን ዘዴ ተጠቅሟል?

17 አምላክ ሕዝቦቹ ወደ አገራቸው ከተመለሱ ወደ 17 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ አስተሳሰባቸውን ለማስተካከል ሲል ሐጌና ዘካርያስ የተባሉ ነቢያትን አስነሳ። አይሁዳውያን ንስሐ በመግባት ቤተ መቅደሱን እንደገና መገንባት ጀመሩ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ዳርዮስ የፋርስ ንጉሥ ሆነ። ኢየሩሳሌም ተመልሳ እንድትገነባ የሚያዘውን የንጉሥ ቂሮስ ትእዛዝ ትክክል መሆኑን አረጋገጠ። ዳርዮስ ለአይሁዳውያን ጎረቤቶች ‘ከኢየሩሳሌም እንዲርቁ’ የሚያስጠነቅቅና የግንባታ ሥራው እንዲጠናቀቅ ለንጉሡ ከሚገባው ቀረጥ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ደብዳቤ ላከላቸው።​—⁠ዕዝራ 6:​1–13

18 አይሁዳውያን በተመለሱ በ22ኛው ዓመት ቤተ መቅደሱን ሠርተው ጨረሱ። ይህ የሥራ ውጤት ለደስታ ምክንያት እንደሚሆን ልትገነዘብ ትችላለህ። ሆኖም ኢየሩሳሌምና ቅጥሮቿ አሁንም ቢሆን በአብዛኛው እንደፈራረሱ ነበር። ከተማዋ “በአለቃውም በነህምያ በጸሐፊውም በካህኑ በዕዝራ ዘመን” አስፈላጊውን ትኩረት አግኝታለች። (ነህምያ 12:​26, 27) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ማብቂያ ላይ ኢየሩሳሌም የጥንቱ ዓለም የታወቀች ከተማ በመሆን ሙሉ በሙሉ እንደገና ተገንብታ ነበር።

መሲሑ ታየ!

19. መሲሑ ኢየሩሳሌም የነበራትን ልዩ ቦታ አምኖ መቀበሉን ያሳየው እንዴት ነበር?

19 ሆኖም እስቲ የተወሰኑ መቶ ዘመናት ወደፊት መለስ እንበልና በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከፍተኛ ግምት የተሰጠውን ጉዳይ ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ እንመልከት። የይሖዋ አምላክ መልአክ ድንግል ለሆነችው የኢየሱስ እናት እንዲህ አላት:- “ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ . . . ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” (ሉቃስ 1:​32, 33) ከዓመታት በኋላ ኢየሱስ በጣም የታወቀውን የተራራ ስብከቱን አከናወነ። በዚያም ላይ በብዙ ጉዳዮች ላይ ማበረታቻና ምክር ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል አድማጮቹ ለአምላክ የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ አሳስቧል፤ ሆኖም በከንቱ ከመማል እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ደግሞ ለቀደሙት:- በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ:- ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና።” (ማቴዎስ 5:​33-35) ኢየሱስ፣ ኢየሩሳሌም ለዘመናት ይዛ የቆየችውን ልዩ ቦታ አምኖ መቀበሉ ትኩረት የሚስብ ነው። አዎን፣ “የታላቁ ንጉሥ [የይሖዋ አምላክ] ከተማ” ነበረች።

20, 21. በኢየሩሳሌም በሚኖሩ በብዙዎች ዘንድ ምን አስገራሚ የሆነ የአመለካከት ለውጥ ተከስቶ ነበር?

20 ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ማብቂያ አካባቢ ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ራሱን የተቀባ ንጉሥ አድርጎ አቅርቧል። በዚያ የሚያስፈነድቅ ጊዜ ብዙዎች “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት” እያሉ በደስታ ተናግረዋል።​—⁠ማርቆስ 11:​1-10፤ ዮሐንስ 12:​12–15

21 ይሁን እንጂ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሕዝቡ የኢየሩሳሌም ሃይማኖታዊ መሪዎች በኢየሱስ ላይ እንዲነሱ ፈቀደ። ኢየሱስ የኢየሩሳሌም ከተማም ሆነች መላው ብሔር በአምላክ ፊት የነበራቸውን ሞገስ እንደሚያጡ አስጠንቅቆ ነበር። (ማቴዎስ 21:​23, 33–45፤ 22:​1–7) ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፣ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።” (ማቴዎስ 23:​37, 38) በ33 እዘአ በዋለው የማለፍ በዓል ላይ የኢየሱስ ተቃዋሚዎች ከኢየሩሳሌም ውጪ ፍትሕ በጎደለው መንገድ እንዲገደል አደረጉ። ያም ሆኖ ግን ይሖዋ የቀባውን ልጁን በማስነሳትና በሰማያዊቱ ጽዮን የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት በመስጠት ክብር አጎናጽፎታል፤ ከዚህ ታላቅ ክንውን ሁላችንም ልንጠቀም እንችላለን።​—⁠ሥራ 2:​32–36

22. ከኢየሱስ ሞት በኋላ ኢየሩሳሌምን በተመለከተ የተሰጡ በርካታ መግለጫዎች ምን ትርጉም አላቸው?

22 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለ ጽዮን ወይም ስለ ኢየሩሳሌም የተነገሩ ፍጻሜያቸውን ያላገኙ አብዛኞቹ ትንቢቶች ተግባራዊ የሚሆኑት በሰማያዊው ዝግጅት ወይም በኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ላይ እንደሚሆን ማስተዋል ይቻላል። (መዝሙር 2:​6–8፤ 110:​1–4፤ ኢሳይያስ 2:​2–4፤ 65:​17, 18፤ ዘካርያስ 12:​3፤ 14:​12, 16, 17) ከኢየሱስ ሞት በኋላ የተጻፉ “ኢየሩሳሌምን” ወይም “ጽዮንን” የሚያመለክቱ በርካታ መግለጫዎች ምሳሌያዊ ትርጉም ያላቸው ሲሆን ቃል በቃል ከተማዋን ወይም ቦታውን የሚያመለክት አይደለም። (ገላትያ 4:​26፤ ዕብራውያን 12:​22፤ 1 ጴጥሮስ 2:​6፤ ራእይ 3:​12፤ 14:​1፤ 21:​2, 10) ኢየሩሳሌም በዳንኤልና በኢየሱስ ክርስቶስ በተተነበየው መሠረት የሮማ ሠራዊት በ70 እዘአ ባድማ ባደረጋት ጊዜ “የታላቁ ንጉሥ ከተማ” መሆኗ ማብቃቱን የሚያሳየው የመጨረሻው ማረጋገጫ እውን ሆኗል። (ዳንኤል 9:​26፤ ሉቃስ 19:​41–44) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም ሆኑ ኢየሱስ ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም በአንድ ወቅት በይሖዋ ዘንድ የነበራትን ልዩ ሞገስ መልሳ እንደምታገኝ አልተነበዩም።​—⁠ገላትያ 4:​25፤ ዕብራውያን 13:​14

የዘላቂ ሰላም ናሙና

23. አሁንም ቢሆን ስለ ኢየሩሳሌም ለማወቅ የምንፈልገው ለምንድን ነው?

23 የምድራዊቷን ኢየሩሳሌም የቀድሞ ታሪክ በመመርመር ከተማዋ በንጉሥ ሰሎሞን ሰላማዊ የንግሥና ዘመን “የዕጥፍ ሰላም ባለቤት [ወይም፣ መሠረት]” ከሚለው የስሟ ትርጉም ጋር የሚስማማ ሁኔታ እንደነበራት ማንም ሰው ሊክድ አይችልም። ሆኖም ይህ ሁኔታ ገነት በሆነች ምድር ላይ የሚኖሩ አምላክን የሚወዱ ሰዎች በቅርቡ ለሚያገኙት ሰላምና ብልጽግና እንደ ናሙና ነበር።​—⁠ሉቃስ 23:​43

24. ሰሎሞን በነገሠበት ጊዜ ሰፍነው ከነበሩ ሁኔታዎች ምን ለመማር እንችላለን?

24 መዝሙር 72 በንጉሥ ሰሎሞን የንግሥና ዘመን ሰፍኖ የነበረውን ሁኔታ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ይህ ውብ መዝሙር በመሲሑ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ ግዛት ወቅት የሰው ልጅ ስለሚያገኛቸው በረከቶች የሚናገር ትንቢት ነው። መዝሙራዊው ስለ እሱ እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፣ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው። . . . ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል፤ ስማቸው [“ደማቸው፣” NW] በፊቱ ክቡር ነው። [“በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር፤ ተራራዎች በሰብል ይሸፈኑ፣” የ1980 ትርጉም]።”​—⁠መዝሙር 72:​7, 8, 12–14, 16

25. ስለ ኢየሩሳሌም ይበልጥ ለመማር መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?

25 በኢየሩሳሌምም ሆነ በምድር ላይ በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ አምላክን የሚወዱ ሰዎች እነዚህ ቃላት እንዴት ያለ ማጽናኛና ተስፋ ይሰጣሉ! አንተም በመሲሐዊቷ የአምላክ መንግሥት ሥር ከሚኖረው ምድር አቀፍ ሰላም ተቋዳሽ መሆን ትችላለህ። ስለ ኢየሩሳሌም ያለፈ ታሪክ እውቀት ማግኘታችን አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ለማስተዋል ይረዳናል። የሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ በሰባተኛውና በስምንተኛው አሥርተ ዓመታት በተከናወኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ይሆናሉ። ይህ ለታላቁ ንጉሥ ለይሖዋ አምላክ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለማቅረብ ለሚፈልጉ ሰዎች ማጽናኛ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “መሲሕ” (ከዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ) እና “ክርስቶስ” (ከግሪክኛ የተወሰደ) የሚሉት የማዕረግ ስሞች “የተቀባ” የሚል ትርጉም አላቸው።

[ታስታውሳለህን?]

◻ ኢየሩሳሌም “የይሖዋ ዙፋን” የሚገኝባት ቦታ ልትሆን የቻለችው እንዴት ነበር?

◻ ሰሎሞን እውነተኛ አምልኮን በማስፋፋት ረገድ ምን ጉልህ ሚና ነበረው?

◻ ኢየሩሳሌም የይሖዋ አምልኮ ማዕከል መሆኗ ማብቃቱን እንዴት እናውቃለን?

◻ ስለ ኢየሩሳሌም ይበልጥ ለመማር የምንፈልገው ለምንድን ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዳዊት ከተማ በአንድ ደቡባዊ ኮረብታ ላይ ትገኝ ነበር፤ ሆኖም ሰሎሞን ከተማዋን በስተ ሰሜን በማስፋት ቤተ መቅደሱን ገንብቷል

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ