የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • mwbr22 መስከረም ገጽ 1-12
  • “የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ” የማመሣከሪያ ጽሑፎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ” የማመሣከሪያ ጽሑፎች
  • የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ከመስከረም 5-11
  • ከመስከረም 12-18
  • ከመስከረም 19-25
  • ከመስከረም 26–ጥቅምት 2
  • ከጥቅምት 3-9
  • ከጥቅምት 10-16
  • ከጥቅምት 17-23
  • ከጥቅምት 24-30
  • ከጥቅምት 31–ኅዳር 6
የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—2022
mwbr22 መስከረም ገጽ 1-12

የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች

ከመስከረም 5-11

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ነገሥት 9-10

“ይሖዋን ለጥበቡ አወድሱት”

w99 7/1 30 አን. 6

ከፍተኛ ወሮታ ያስገኘ ጉብኝት

ንግሥቲቱ ከሰሎሞን ጋር በተገናኘች ጊዜ “አመራማሪ በሆኑ ጥያቄዎች” ትፈትነው ጀመር። (1 ነገሥት 10:​1 NW) እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “እንቆቅልሽ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ሆኖም እንዲህ ሲባል ንግሥቲቱ ሰሎሞንን በአልባሌ ቀልዶች አጥምዳዋለች ማለት አይደለም። በመዝሙር 49:​4 NW ላይ ኃጢአትን፣ ሞትንና ቤዛን የሚመለከቱ አሳሳቢ ጥያቄዎችን ለመግለጽ ይኸው የዕብራይስጥ ቃል የተሠራበት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ስለዚህ የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን የማስተዋል ጥልቀት የሚፈትኑ ከበድ ያሉ ጉዳዮችን ሳታወያየው አትቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ “በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው” ሲል ይገልጻል። በአጸፋው ደግሞ ሰሎሞን “የጠየቀችውን ሁሉ ፈታላት፤ ሊፈታላት ያልቻለውና ከንጉሡ የተሰወረ ነገር አልነበረም።”​—​1 ነገሥት 10:​2, 3

w99 11/1 20 አን. 6

የተትረፈረፈ ልግስና

ንግሥቲቱ በሰማችውና ባየችው ነገር እጅግ ተደንቃ በትህትና እንዲህ ስትል መለሰች፦ “በፊትህ ሁል ጊዜ የሚቆሙ ጥበብህንም የሚሰሙ ሰዎችና እነዚህ ባሪያዎችህ ምስጉኖች [“ደስተኛ፣” NW] ናቸው።” (1 ነገሥት 10:​4-8) የሰሎሞን አገልጋዮች በሃብት የታጠሩ ቢሆኑም እንኳ ደስተኛ ያለቻቸው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ በመገኘታቸው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የሰሎሞን አገልጋዮች አምላክ ለንጉሡ የሰጠውን ጥበብ ዘወትር የመስማት አጋጣሚ ስለነበራቸው የተባረኩ ነበሩ። የሳባ ንግሥት ዛሬ በፈጣሪና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ጥበብ ለሚደሰቱት የይሖዋ ሕዝቦች እንዴት ግሩም ምሳሌ ናት!

w99 7/1 30-31

ከፍተኛ ወሮታ ያስገኘ ጉብኝት

የሳባ ንግሥት በሰሎሞን ጥበብና በመንግሥቱ ብልጽግና ከመደነቋ የተነሳ “ነፍስ አልቀረላትም” ነበር። (1 ነገሥት 10:​4, 5) አንዳንዶች ይህን ሐረግ ንግሥቲቱ “እስትንፋሷ ቀጥ አለ” ማለት እንደሆነ አድርገው ይረዱታል። እንዲያውም አንድ ሃይማኖታዊ ምሁር ሕሊናዋን እንደሳተች ተናግረዋል! ያም ሆነ ይህ ንግሥቲቱ ባየችውና በሰማችው ነገር ተደንቃ ነበር። የሰሎሞን አገልጋዮች የዚህን ንጉሥ ጥበብ መስማት በመቻላቸው ደስተኞች መሆናቸውን ከመግለጿም በላይ ሰሎሞንን በማንገሡ ይሖዋን ባርካለች። ከዚያም ለንጉሡ በጣም ውድ ስጦታዎች የሰጠችው ሲሆን ወርቁ ብቻ እንኳ አሁን ባለው የዋጋ ተመን 40,000,000 የአሜሪካ ዶላር ያወጣል። ሰሎሞንም ስጦታዎች በማምጣት “የወደደችውን ሁሉ ከእርሱም የለመነችውን ሁሉ” ለንግሥቲቱ ሰጣት።​—​1 ነገሥት 10:​6-13

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

w08 11/1 22 አን. 4-6

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ንጉሥ ሰለሞን ምን ያህል ወርቅ ነበረው?

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለሰለሞን 4,000 ኪሎ ግራም ወርቅ እንደላከለትና የሳባ ንግሥትም ተመሳሳይ መጠን ያለው ወርቅ በስጦታ እንዳበረከተችለት ከመግለጻቸውም ሌላ የራሱ የሰለሞን የንግድ መርከቦች ከኦፊር ከ15,000 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ እንዳመጡለት ይናገራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት መክሊት [ወይም ከ25,000 ኪሎ ግራም በላይ] ወርቅ ነበር” ይላል። (1 ነገሥት 9:14, 28፤ 10:10, 14) ይህ ሊታመን የሚችል ነገር ነው? በዚያን ዘመን በነገሥታት እጅ ይገኝ የነበረው የወርቅ ክምችት ምን ያህል ነበር?

ምሁራን ተአማኒነቱን ያረጋገጡለት ተቀርጾ የተገኘ አንድ ጽሑፍ፣ የግብጹ ፈርኦን ሣልሳዊ ቱትሞሰ (በ16ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት) በካርናክ ለሚገኘው የአሙንራ ቤተ መቅደስ 13,500 ኪሎ ግራም ገደማ የሚመዝን ወርቅ በስጦታ እንደሰጠ ይናገራል። በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የአሦር ንጉሥ ሣልሳዊ ቴልጌልቴልፌልሶር ከ4,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ወርቅ ከጢሮስ ግብር ተቀብሏል። ዳግማዊ ሳርጎን ይህንኑ የሚያህል መጠን ያለው ወርቅ ለባቢሎን አማልክት በስጦታ አበርክቷል። የመቄዶንያው ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ (359-336 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ትሬስ ውስጥ የማዕድን ክምችት ካለበት ከፓንጌየም አካባቢ በየዓመቱ ከ28,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ወርቅ ያወጣ እንደነበር ተዘግቧል።

የፊሊፕ ልጅ ታላቁ እስክንድር (336-323 ከክርስቶስ ልደት በፊት) የፋርሳውያን ከተማ የሆነችውን ሱሳን በተቆጣጠረበት ወቅት ከሱሳ ከአንድ ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ወርቅ፣ ከመላው የፋርስ ግዛት ደግሞ ወደ ሰባት ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሚጠጋ ወርቅ እንደወሰደ ይነገራል። ስለዚህ ከእነዚህ ዘገባዎች አንጻር ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ ንጉሥ ሰለሞን የነበረውን ወርቅ አስመልክቶ ያሰፈረው ዘገባ የተጋነነ አይደለም።

ከመስከረም 12-18

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ነገሥት 11-12

“የትዳር ጓደኛችሁን በጥበብ ምረጡ”

w18.07 18 አን. 7

“ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው?”

7 ከንጉሥ ሰለሞን ምሳሌ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። ሰለሞን ወጣት ሳለ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት ያደርግ ነበር። አምላክ ከፍተኛ ጥበብ የሰጠው ከመሆኑም ሌላ በኢየሩሳሌም ያለውን ዕፁብ ድንቅ ቤተ መቅደስ የመገንባት ኃላፊነት ሰጥቶታል። ከጊዜ በኋላ ግን ሰለሞን ከይሖዋ ጋር የነበረውን ወዳጅነት አጥቷል። (1 ነገ. 3:12፤ 11:1, 2) የአምላክ ሕግ አንድ ዕብራዊ ንጉሥ “ልቡ ከትክክለኛው መንገድ ዞር እንዳይል ለራሱ ሚስቶች አያብዛ” የሚል ቀጥተኛ መመሪያ ይሰጥ ነበር። (ዘዳ. 17:17) ሰለሞን ግን ይህን መመሪያ በመጣስ 700 ሴቶችን አገባ፤ በተጨማሪም 300 ቁባቶችን ለራሱ ወሰደ። (1 ነገ. 11:3) ከሚስቶቹ መካከል አብዛኞቹ እስራኤላውያን ያልሆኑና የሐሰት አማልክትን የሚያመልኩ ነበሩ። በመሆኑም ሰለሞን እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሴቶችን እንዳያገቡ የሚከለክለውን የአምላክ ሕግም ጥሷል።—ዘዳ. 7:3, 4

w19.01 15 አን. 6

ልብህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

6 ሰይጣን ልክ እንደ እሱ የይሖዋን መሥፈርቶች የምናቃልልና በራስ ወዳድነት ምኞት የምንመራ ዓመፀኞች እንድንሆን ይፈልጋል። እርግጥ ነው፣ ሰይጣን የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረንና ከእሱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት እንድንፈጽም ሊያስገድደን አይችልም። በመሆኑም ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሌሎች መንገዶችን ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ በእሱ አስተሳሰብ በተበከሉ ሰዎች እንድንከበብ ያደርጋል። (1 ዮሐ. 5:19) ይህን የሚያደርገው እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ጊዜ እንድናሳልፍ ስለሚፈልግ ነው፤ ሰይጣን መጥፎ ጓደኝነት አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን ‘እንደሚያበላሸው’ ወይም እንደሚበክለው እያወቅንም የተሳሳተ ውሳኔ እንድናደርግ ይፈልጋል። (1 ቆሮ. 15:33) ይህ ዘዴ ከንጉሥ ሰለሞን ጋር በተያያዘ ሠርቶለታል። ሰለሞን በርካታ የባዕድ አገር ሴቶችን አግብቶ ነበር፤ እነዚህ ሴቶች በሰለሞን ላይ ‘ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩበት’ ሲሆን “ቀስ በቀስ ልቡ” ከይሖዋ እንዲርቅ አድርገውታል።—1 ነገ. 11:3 ግርጌ

w18.07 19 አን. 9

“ከይሖዋ ጎን የሚቆም ማን ነው?”

9 ይሁንና ይሖዋ መጥፎ ድርጊትን ፈጽሞ በቸልታ አያልፍም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ሰለሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት . . . ከይሖዋ ልቡ ስለሸፈተ ይሖዋ በሰለሞን ላይ ተቆጣ፤ ደግሞም ሌሎች አማልክትን እንዳይከተል በማዘዝ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ አስጠንቅቆት ነበር። እሱ ግን ይሖዋ ያዘዘውን ነገር አልጠበቀም።” በዚህም የተነሳ ሰለሞን የአምላክን ሞገስና ድጋፍ አጥቷል። የሰለሞን ዘሮች አንድ በሆነው የእስራኤል መንግሥት ላይ መግዛት ያልቻሉ ከመሆኑም ሌላ ለበርካታ ትውልዶች የሚዘልቅ መከራ ደርሶባቸዋል።—1 ነገ. 11:9-13

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

w18.06 13 አን. 5 እስከ 14 አን. 3

የአምላክን ሞገስ ማግኘት ይችል ነበር

ሮብዓም ለሕዝቡ ዓመፅ ምላሽ ለመስጠት ሠራዊቱን አሰባሰበ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ነቢዩን ሸማያህን በመላክ ለሮብዓምና ለሠራዊቱ እንዲህ አላቸው፦ “ከወንድሞቻችሁ ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት አትውጡ። ይህ እንዲሆን ያደረግኩት እኔ ስለሆንኩ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።”—1 ነገ. 12:21-24

ሮብዓም ጭራሽ መዋጋት የለበትም ማለት ነው? ይህ ሮብዓምን ምን ያህል አሳስቦት እንደሚሆን መገመት ትችላለህ! ተገዢዎቹን “በእሾህ አለንጋ” እንደሚገርፋቸው ሲዝት የነበረው ንጉሥ፣ የተነሳበትን ዓመፅ ሳያስቆም እጁን አጣጥፎ እንደተቀመጠ ሲያይ ሕዝቡስ ምን ይላል? (ከ2 ዜና መዋዕል 13:7 ጋር አወዳድር።) ያም ቢሆን ንጉሡና ሠራዊቱ “የይሖዋን ቃል ሰሙ፤ ይሖዋ እንደነገራቸውም ወደየቤታቸው ተመለሱ።”

ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? አምላክን መታዘዝ ለፌዝ ሊዳርገን ቢችልም እንኳ እሱን መታዘዛችን የጥበብ እርምጃ ነው። አምላክን መታዘዝ የእሱን ሞገስና በረከት ለማግኘት ያስችላል።—ዘዳ. 28:2

ታዲያ ሮብዓም መታዘዙ ምን ውጤት አስገኘ? ሮብዓም አምላክን በመታዘዝ፣ አዲስ የተቋቋመውን ሰሜናዊ መንግሥት ለመውጋት የነበረውን ዕቅድ ተወ፤ ከዚያም በግዛቱ ሥር ባሉት የይሁዳና የቢንያም ነገድ ክልሎች ውስጥ ከተሞች መገንባት ጀመረ። በርካታ ከተሞችንም “እጅግ አጠናከራቸው።” (2 ዜና 11:5-12) ከዚህም በላይ ለተወሰነ ጊዜ የይሖዋን ሕግ ተከትሏል። በኢዮርብዓም ግዛት ሥር የነበረውና አሥሩን ነገዶች ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ጣዖት አምልኮ ውስጥ ሲዘፈቅ፣ በእስራኤል መንግሥት ውስጥ የነበሩ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን መቆም የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ “ለሮብዓም ድጋፍ” ሰጥተዋል። (2 ዜና 11:16, 17) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ሮብዓም ታዛዥ መሆኑ ንግሥናውን አጠናክሮለታል።

ከመስከረም 19-25

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ነገሥት 13-14

“ባለን መርካትና ልካችንን ማወቅ—ለምን?”

w08 8/15 8 አን. 4

ባልተከፋፈለ ልብ በታማኝነት መጽናት

4 ከዚያም ኢዮርብዓም የእውነተኛውን አምላክ ሰው “አብረኸኝ ወደ ቤት እንሂድ፤ አንድ ነገር ቅመስ፤ ስጦታም አደርግልሃለሁ” አለው። (1 ነገ. 13:7) ታዲያ ነቢዩ በዚህ ጊዜ ምን ያደርግ ይሆን? ንጉሡን የሚያወግዝ መልእክት ተናግሮ ሲያበቃ የንጉሡን ግብዣ መቀበል ይገባዋል? (መዝ. 119:113) ወይስ ንጉሡ የተጸጸተ ቢመስልም እንኳ ነቢዩ የንጉሡን ግብዣ ለመቀበል እንቢ ይበል? ኢዮርብዓም፣ ባለጠጋ በመሆኑ ለወዳጆቹ ውድ ስጦታዎች ሊሰጥ ይችል እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። የአምላክ ነቢይ በልቡ ቁሳዊ ነገሮችን ይመኝ ከነበረ የንጉሡ ግብዣ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንበት አይካድም። ሆኖም ይሖዋ፣ ነቢዩን “እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ” በማለት አዞታል። በመሆኑም ነቢዩ “ግማሽ ሀብትህን ብትሰጠኝ እንኳ፣ አብሬህ አልሄድም፤ እዚህ፣ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም” በማለት ቁርጥ ያለ መልስ ሰጠው። ከዚያም በሌላ አቅጣጫ ከቤቴል ወጥቶ ሄደ። (1 ነገ. 13:8-10) ይህ ነቢይ ያደረገው ውሳኔ ከልብ የመነጨ ታማኝነት በማሳየት ረገድ ምን ትምህርት ይሰጠናል?—ሮሜ 15:4

w08 8/15 11 አን. 15

ባልተከፋፈለ ልብ በታማኝነት መጽናት

15 ከይሁዳ የመጣው ነቢይ ከሠራው ስህተት ምን ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን? ምሳሌ 3:5 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” ይላል። ከይሁዳ የመጣው ነቢይ፣ ከዚያ ቀደም ያደርገው እንደነበረው በይሖዋ ከመታመን ይልቅ በዚህ ወቅት በራሱ ማስተዋል ታምኗል። የሠራው ስህተት ሕይወቱን እንዲሁም በአምላክ ዘንድ የነበረውን መልካም ስም እንዲያጣ አድርጎታል። በዚህ ነቢይ ላይ የደረሰው ነገር ይሖዋን በትሕትና እንዲሁም በታማኝነት የማገልገልን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው!

w08 8/15 9 አን. 10

ባልተከፋፈለ ልብ በታማኝነት መጽናት

10 ከይሁዳ የመጣው ነቢይ፣ በአረጋዊው ነቢይ ዘዴ ሊታለል አይገባም ነበር። ይህ ነቢይ፣ ‘ይሖዋ ለእኔ አዲስ መመሪያ ለመስጠት መልአኩን ወደ ሌላ ሰው መላክ ለምን አስፈለገው?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይችል ነበር። በተጨማሪም ነቢዩ፣ መመሪያውን ግልጽ እንዲያደርግለት ይሖዋን መጠየቅ ይችል ነበር፤ ሆኖም ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ማድረጉን አይገልጹም። ከዚህ በተቃራኒ ይህ ነቢይ ከሽማግሌው ጋር ‘አብሮት ተመልሶ በቤቱ እንደበላና እንደጠጣ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሖዋ በዚህ ሁኔታ አልተደሰተም። የተታለለው ነቢይ ወደ ቤቱ ሲመለስ መንገድ ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው። የነቢይነት ተልእኮው በዚህ መንገድ መደምደሙ ምንኛ አሳዛኝ ነው!—1 ነገ. 13:19-25

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

w10 7/1 29 አን. 5

በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የሚያይ አምላክ

ከሁሉ በላይ ግን በ1 ነገሥት 14:13 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ይሖዋንና በልባችን ውስጥ የሚመለከተውን ነገር በተመለከተ አንድ ትልቅ ቁም ነገር ያስተምረናል። በአብያ ልብ ውስጥ መልካም ነገር ‘እንደተገኘበት’ አስታውስ። ይሖዋ አንድ መልካም ነገር እስኪያገኝበት ድረስ የአብያን ልብ የመረመረ ይመስላል። ከቤተሰቡ አንጻር ሲታይ አብያ “በተከመረ ጠጠር መካከል” ብቻዋን እንደተቀመጠች ዕንቁ ሊታይ እንደሚችል አንድ ምሑር ተናግረዋል። ይሖዋ የአብያን መልካምነት ከፍ አድርጎ የተመለከተው ከመሆኑም ሌላ ክፉ ከሆነ ቤተሰብ ለወጣው ለዚህ ሰው በተወሰነ መጠንም ቢሆን ምሕረት በማሳየት አክብሮታል።

ከመስከረም 26–ጥቅምት 2

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ነገሥት 15-16

“አሳ በድፍረት እርምጃ ወስዷል—አንተስ?”

w12 8/15 8 አን. 4

‘የድካማችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ’

እስራኤል ለሁለት ከተከፈለች በኋላ ባሉት 20 ዓመታት ይሁዳ በጣዖት አምልኮ ተዘፍቃ ነበር። አሳ በ977 ዓ.ዓ. ሥልጣን ላይ ሲወጣ በቤተ መንግሥቱ የነበሩ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ የከነዓናውያንን የመራባት አማልክት ያመልኩ ነበር። ይሁን እንጂ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአሳ የግዛት ታሪክ እንዲህ ይላል፦ “አሳ በአምላኩ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር አደረገ፤ ባዕዳን መሠዊያዎችንና ማምለኪያ ኰረብታዎችን አስወገደ፤ ማምለኪያ ዐምዶችን አፈረሰ፤ አሼራ ለተባለች ጣዖት አምላክ የቆሙ የዕንጨት ቅርጽ ምስሎችንም ቈራረጠ።” (2 ዜና 14:2, 3) በተጨማሪም አሳ በቤተ መቅደስ ውስጥ በሃይማኖት ስም ግብረ ሰዶም ይፈጽሙ የነበሩትን “ወንደቃዎች” ከይሁዳ ግዛት አስወጣ። አሳ በዚህ ብቻ አላበቃም። ሕዝቡ “የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] እንዲፈልጉ፣ ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲፈጽሙ የይሁዳን ሕዝብ” አሳሰባቸው።​—1 ነገ. 15:12, 13፤ 2 ዜና 14:4

w17.03 19 አን. 7

ይሖዋን በሙሉ ልብ አገልግሉ!

7 እያንዳንዳችን ሙሉ ለሙሉ ለአምላክ ያደርን መሆናችንን ለማወቅ ልባችንን መመርመር ይኖርብናል። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይሖዋን ለማስደሰት፣ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ለመቆም እንዲሁም የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ?’ አሳ፣ አያቱን ማአካን እንደ ንጉሡ እናት ተቆጥራ ከተሰጣት ቦታ ለመሻር ምን ያህል ድፍረት ጠይቆበት እንደሚሆን መገመት እንችላለን። እርግጥ ነው፣ አንተ የምታውቃቸው ሰዎች እንደ ማአካ ዓይነት ድርጊት አይፈጽሙ ይሆናል፤ ይሁንና አሳ ያሳየውን ዓይነት ቅንዓት ማሳየት አስፈላጊ የሚሆንበት ሁኔታ ሊያጋጥምህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የቤተሰብህ አባል ወይም የቅርብ ጓደኛህ ኃጢአት ቢፈጽምና ንስሐ ሳይገባ ቀርቶ ቢወገድ ምን ታደርጋለህ? ከዚህ ግለሰብ ጋር ያለህን ግንኙነት በማቋረጥ ቁርጥ ያለ እርምጃ ትወስዳለህ? በዚህ ጊዜ ልብህ ምን እንድታደርግ ይገፋፋሃል?

it-1 184-185

አሳ

አሳ ጥበብና መንፈሳዊ ማስተዋል እንደጎደለው ያሳየባቸው ጊዜያት አሉ፤ ሆኖም መልካም ባሕርያቱና የሐሰት አምልኮን ለማስወገድ ያደረገው ጥረት ስህተቶቹን ሸፍነውለታል፤ በዚህም የተነሳ በይሁዳ መስመር ከተነሱት ታማኝ ነገሥታት እንደ አንዱ ሊቆጠር ችሏል። (2ዜና 15:17) አሳ በንግሥና በቆየባቸው 41 ዓመታት ስምንት የእስራኤል ነገሥታት ተፈራርቀዋል፤ እነሱም ኢዮርብዓም፣ ናዳብ፣ ባኦስ፣ ኤላህ፣ ዚምሪ፣ ኦምሪ፣ ቲብኒ (የኦምሪ ተቀናቃኝ ሆኖ አንደኛውን የእስራኤል አንጃ ገዝቷል) እና አክዓብ ናቸው። (1ነገ 15:9, 25, 33፤ 16:8, 15, 16, 21, 23, 29) አሳ ሲሞት ልጁ ኢዮሳፍጥ በምትኩ ንጉሥ ሆኗል።—1ነገ 15:24

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

w98 9/15 21-22

አምላክ ለአንተ እውን ነውን?

ለምሳሌ ያህል ኢያሪኮን ማደስ ስለሚያስከትለው ቅጣት የሚናገረውን ትንቢት አንብብና ከዚያም የትንቢቱን ፍጻሜ መርምር። ኢያሱ 6:​26 እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜም ኢያሱ፦ ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኩር ልጁ ይጥፋ፣ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ ብሎ ማለ።” ይህ ትንቢት ከተነገረ ከ500 ዓመት በኋላ ፍጻሜውን ያገኘ ሲሆን በ1 ነገሥት 16:​34 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “በእርሱም [በንጉሥ አክዓብ] ዘመን የቤቴል ሰው አኪኤል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ እጅ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፣ በበኩር ልጁ በአቢሮን መሠረትዋን አደረገ፣ በታናሹ ልጁም በሠጉብ በሮችዋን አቆመ።” እንዲህ ያለውን ትንቢት ሊናገርና ፍጻሜውንም ሊከታተል የሚችለው እውን የሆነ አምላክ ብቻ ነው።

ከጥቅምት 3-9

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ነገሥት 17-18

“በሁለት ሐሳብ የምታነክሱት እስከ መቼ ነው?”

w17.03 14 አን. 6

እምነት በማዳበር ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጉ!

6 የጥንቶቹ እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር መኖር ከጀመሩ በኋላ፣ መሠረታዊና አስፈላጊ የሆነ አንድ ውሳኔ ማድረግ ነበረባቸው፤ ይሖዋን ከማምለክና ሌሎች አማልክትን ከመከተል አንዱን መምረጥ ነበረባቸው። (ኢያሱ 24:15​ን አንብብ።) ይህ ቀላል ውሳኔ ይመስል ይሆናል። ሆኖም የሚያደርጉት ውሳኔ ሕይወት ሊያስገኝ አሊያም ሞት ሊያስከትል ይችላል። እስራኤላውያን በመሳፍንት ይተዳደሩ በነበሩበት ዘመን በተደጋጋሚ ጊዜ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ያደርጉ ነበር። ይሖዋን በመተው የሐሰት አማልክትን አምልከዋል። (መሳ. 2:3, 11-23) ከተወሰነ ጊዜ በኋላም የአምላክ ሕዝቦች ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ነቢዩ ኤልያስ የነበራቸውን ምርጫ በግልጽ አስቀምጦላቸዋል፦ ይሖዋን አሊያም ደግሞ ባአል የተባለውን የሐሰት አምላክ ከማገልገል አንዱን መምረጥ ነበረባቸው። (1 ነገ. 18:21) እስራኤላውያን ይወላውሉ ስለነበር ኤልያስ ወቅሷቸዋል። ሕዝቡ የተደቀነባቸው ውሳኔ ቀላል እንደነበር ታስብ ይሆናል፤ ምክንያቱም ይሖዋን ማገልገል ምንጊዜም ቢሆን ጠቃሚና ጥበብ የሚንጸባረቅበት አካሄድ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። በእርግጥም አስተዋይ የሆነ ማንኛውም ሰው ባአልን ለማምለክ ሊመርጥ አይችልም። እስራኤላውያን ግን “በሁለት ሐሳብ [እያነከሱ]” ነበር። ኤልያስ ከሁሉ የላቀውን አምልኮ ይኸውም የይሖዋን አምልኮ እንዲመርጡ አጥብቆ አሳስቧቸዋል።

ia 88 አን. 15

ለንጹሕ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል

15 የበኣል ካህናትም ከቁጥጥር ውጭ ሆነው “እየጮኹ እንደ ልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስ ድረስ ሰውነታቸውን በሰይፍና በጩቤ ያቈስሉ ነበር።” ይህን ሁሉ ያደረጉት እንዲያው በከንቱ ነበር! “አሁንም ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም።” (1 ነገ. 18:28, 29) በእርግጥም በኣል የሚባል አምላክ የለም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ሰዎችን ከይሖዋ ለማራቅ የፈጠረው የሐሰት አምላክ ነው። ከይሖዋ ይልቅ ሌላ አምላክ ለማገልገል መምረጥ ለሐዘን ብሎም ለውርደት መዳረጉ አይቀሬ ነው።—መዝሙር 25:3​ን እና መዝሙር 115:4-8​ን አንብብ።

ia 90 አን. 18

ለንጹሕ አምልኮ ጥብቅና ቆሟል

18 ኤልያስ ጸሎት ከማቅረቡ በፊት ሕዝቡ ‘ይሖዋም ልክ እንደ በኣል ሐሰተኛ አምላክ ይሆን እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮበት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ከጸሎቱ በኋላ እንዲህ ስላለው ነገር ለማሰብ የሚያስችል ጊዜ እንኳ አልነበራቸውም። ዘገባው ስለ ሁኔታው ሲገልጽ “ከዚያም የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጕድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች” ይላል። (1 ነገ. 18:38) እንዴት ያለ አስደናቂ ምላሽ ነው! ታዲያ ሕዝቡ ምን ተሰማው?

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

w08 4/1 19 ሣጥን

በንቃትና በትዕግሥት ተጠባብቋል

በኤልያስ ዘመን ተከስቶ የነበረው ድርቅ የቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው?

የይሖዋ ነቢይ የነበረው ኤልያስ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ድርቅ በቅርቡ እንደሚያበቃ ለንጉሥ አክዓብ አሳውቆት ነበር። ድርቁ ያቆመው “በሦስተኛው ዓመት” ላይ ሲሆን ዓመቱ መቆጠር የጀመረው ኤልያስ ስለ ድርቁ ከተናገረበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ እንደሚሆን ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (1 ነገሥት 18:1) ኤልያስ፣ ዝናብ እንደሚጥል ከተናገረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ይሖዋ እንዲዘንብ አደረገ። ከዚህ በመነሳት አንዳንዶች ድርቁ ያቆመው በሦስተኛው ዓመት ላይ ስለሆነ የቆየው ከሦስት ዓመት ላነሰ ጊዜ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሱ ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስና ያዕቆብ ድርቁ እስከ “ሦስት ዓመት ተኩል” እንደቆየ ይነግሩናል። (ሉቃስ 4:25፤ ያዕቆብ 5:17) ታዲያ በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫል?

በፍጹም አይጋጭም። የጥንቷ እስራኤል የበጋ ወራት በጣም ረጅም ሲሆን እስከ ስድስት ወር ድረስ ይዘልቃል። ኤልያስ ለአክዓብ ስለ ድርቁ ሊነግረው የመጣው የበጋው ወራት ከመጠን በላይ እንደረዘመና ከባድ እየሆነ እንደመጣ በግልጽ መታየት ከጀመረ በኋላ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። እንግዲያው የድርቁ ዘመን በትክክል የጀመረው ኤልያስ ለአክዓብ ስለ ድርቁ ሊነግረው ከመምጣቱ ከስድስት ወር ገደማ ቀደም ብሎ ነው ለማለት ይቻላል። በመሆኑም ኤልያስ ድርቁ ማብቃቱን ያሳወቀው ቀደም ሲል ስለ ድርቁ በተናገረ “በሦስተኛው ዓመት” ላይ ቢሆንም ድርቁ በአጠቃላይ የቆየው ወደ ሦስት ዓመት ተኩል ለሚጠጋ ጊዜ ነበር። ሕዝቡ ሁሉ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የቀረበውን ታላቅ ፈተና ለማየት በተሰበሰቡ ጊዜ ‘የሦስት ዓመት ተኩሉ’ ጊዜ አልፎ ነበር።

ኤልያስ ለመጀመሪያ ጊዜ አክዓብን ለማነጋገር ሲሄድ ሕዝቡ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደነበር ተመልከት። ሕዝቡ፣ በኣል የበጋውን ወራት በማሳለፍ ዝናብ የሚያመጣ “ደመና ጋላቢ” አምላክ እንደሆነ ያምኑ ነበር። የበጋው ወራት ከተለመደው በላይ ሲረዝም ‘በኣል የት አለ? ዝናቡ እንዲጥል የሚያደርገው መቼ ነው?’ በማለት ሳይጠይቁ አልቀሩም። ኤልያስ፣ እሱ ይሆናል እስከሚልበት ጊዜ ድረስ ዝናብም ሆነ ጠል እንደማይኖር መናገሩ የበኣል አምላኪዎችን ሳያበሳጫቸው አልቀረም።—1 ነገሥት 17:1

ከጥቅምት 10-16

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ነገሥት 19-20

“ማጽናኛ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር በሉ”

w19.06 15 አን. 5

የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ በይሖዋ ታመኑ

5 አንደኛ ነገሥት 19:1-4​ን አንብብ። ኤልያስ፣ ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው ስትዝትበት ግን በፍርሃት ተዋጠ። በመሆኑም ወደ ቤርሳቤህ ሸሸ። በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ‘እንዲሞት መለመን ጀመረ።’ ኤልያስ ይህን ያህል ተስፋ የቆረጠው ለምንድን ነው? ይህ ነቢይ “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው” ፍጹም ያልሆነ ሰው ነበር። (ያዕ. 5:17) በጣም ከመጨነቁና ከመዛሉ የተነሳ ሁኔታዎች ከአቅሙ በላይ እንደሆኑ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ኤልያስ፣ ሕዝቡ ይሖዋን እንዲያመልክ የሚያደርገው ጥረት መና እንደቀረ፣ በእስራኤል ያለው ሁኔታ ምንም እንዳልተሻሻለና ይሖዋን እያገለገለ ያለው እሱ ብቻ እንደሆነ አስቦ ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 18:3, 4, 13፤ 19:10, 14) ይህ ታማኝ ነቢይ እንዲህ የተሰማው መሆኑ ያስገርመን ይሆናል። ይሖዋ ግን የኤልያስን ስሜት ተረድቶለታል።

ia 103 አን. 13

አምላኩ አጽናንቶታል

13 ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ በጣም የሚወደውንና ሞቱን እየተመኘ የነበረውን ይህን ነቢይ ምድረ በዳ ውስጥ ባለች አንዲት ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሲመለከተው ምን የተሰማው ይመስልሃል? መልሱን መገመት አያስፈልገንም። ኤልያስ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶት ሳለ ይሖዋ አንድ መልአክ ላከ። መልአኩም ኤልያስን ቀስ ብሎ ነካ በማድረግ ከቀሰቀሰው በኋላ “ተነሥና ብላ” አለው። መልአኩ በደግነት ትኩስ ዳቦና ውኃ ስላቀረበለት ኤልያስ ተነስቶ በላ እንዲሁም ጠጣ። ኤልያስ ከበላ በኋላ መልአኩን አመስግኖታል ብለህ ታስባለህ? ዘገባው የሚናገረው ነቢዩ ከበላና ከጠጣ በኋላ ተመልሶ እንደተኛ ብቻ ነው። ምናልባት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ከመዋጡ የተነሳ መናገር እንኳ ተስኖት ይሆን? ያም ሆነ ይህ መልአኩ ኤልያስን በድጋሚ ቀሰቀሰው፤ በዚህ ወቅት ጎህ ሳይቀድ አይቀርም። አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ “ተነሥና ብላ” በማለት እንዲበላ ገፋፋው፤ በተጨማሪም መልአኩ “ሩቅ መንገድ ስለምትሄድ” የሚል ሐሳብ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው።—1 ነገ. 19:5-7

ia 106 አን. 21

አምላኩ አጽናንቶታል

21 ሦስቱም ሁኔታዎች በተከሰቱበት ወቅት ይሖዋ በእነዚያ አስደናቂ የተፈጥሮ ኃይሎች ውስጥ እንዳልነበር ዘገባው ይነግረናል። ኤልያስ፣ ይሖዋ አምላኪዎቹ “ደመና ጋላቢ” ወይም ዝናብ አምጪ እንደሆነ በማሰብ ክብር እንደሚሰጡት እንደ በኣል ያለ በተፈጥሮ ኃይሎች ውስጥ የሚገኝ ምናብ የወለደው አምላክ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ይሖዋ በጣም አስደናቂ የሆኑት የተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ ምንጭ ከመሆኑም በላይ እሱ ከሠራው ከማንኛውም ነገር እጅግ የላቀ ነው። ግዑዝ የሆኑት ሰማያትም እንኳ ሊይዙት አይችሉም! (1 ነገ. 8:27) ታዲያ ኤልያስ ይህን ሁሉ መመልከቱ የጠቀመው እንዴት ነው? ኤልያስ ምን ያህል ፈርቶ እንደነበር አስታውስ። ታዲያ ኤልያስ፣ በፈለገው ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችል ይህ ነው የማይባል ኃይል ያለው ይሖዋ ከጎኑ እያለለት አክዓብንም ሆነ ኤልዛቤልን የሚፈራበት ምን ምክንያት አለ?—መዝሙር 118:6​ን አንብብ።

ia 106 አን. 22

አምላኩ አጽናንቶታል

22 እሳቱ እንዳለፈ ጸጥታ ሰፈነ፤ ከዚያም ኤልያስ “ለስለስ ያለ ድምፅ” ሰማ። ድምፁም ኤልያስ ስሜቱን በድጋሚ እንዲገልጽ የሚያበረታታ ነበር፤ ስለሆነም ኤልያስ ያስጨነቀውን ነገር ለሁለተኛ ጊዜ ግልጥልጥ አድርጎ ተናገረ። ምናልባትም እንዲህ ማድረጉ ይበልጥ ቀለል እንዲለው ሳያደርገው አልቀረም። ያም ሆኖ ‘ለስለስ ያለው ድምፅ’ ቀጥሎ የተናገረው ሐሳብ ኤልያስን ይበልጥ አጽናንቶት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሖዋ፣ ኤልያስ እሱ እንዳሰበው ዋጋ ቢስ አለመሆኑን እንዲገነዘብ ረዳው። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? አምላክ የበኣል አምልኮን ከእስራኤል ምድር ለማስወገድ ከሚደረገው ጦርነት ጋር በተያያዘ ወደፊት ምን ለማድረግ እንዳሰበ ገለጸለት። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የአምላክ ዓላማ አንዳች የሚገታው ነገር ሳይኖር ወደፊት በመገስገስ ላይ ስለሆነ የኤልያስ ልፋት ከንቱ ሆኖ አልቀረም። ከዚህም በላይ ይሖዋ ለኤልያስ አንዳንድ ዝርዝር መመሪያዎችን በመስጠት እንደገና ወደ ሥራው እንዲመለስ ስላደረገው ይህ ነቢይ አሁንም ቢሆን በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተው ሚና አለ።—1 ነገ. 19:12-17

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

w97 11/1 31 አን. 1

የራስን ጥቅም የመሰዋትና በታማኝነት የመጣበቅ ምሳሌ

በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች ተመሳሳይ የሆነ የራስን ጥቅም የመሰዋት መንፈስ ያሳያሉ። አንዳንዶች ራቅ ባሉ ክልሎች ምሥራቹን ለመስበክ ወይም የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነው ለማገልገል ሲሉ “እርሻቸውን” ማለትም የሚተዳደሩበትን ሥራ ትተዋል። ሌሎች ደግሞ በማኅበሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለመሥራት ወደ ባዕድ አገሮች ሄደዋል። ብዙዎች ዝቅተኛ ሥራዎች ሊባሉ የሚችሉትን በፈቃደኝነት ተቀብለዋል። ሆኖም ይሖዋን የሚያገለግል ማንኛውም ሰው የሚያከናውነው አገልግሎት ፈጽሞ አይናቅም። ይሖዋ በፈቃደኝነት እርሱን የሚያገለግሉትን ያደንቃል፤ የራስን ጥቅም የመሰዋት መንፈሳቸውንም ይባርካል።—ማርቆስ 10:29, 30

ከጥቅምት 17-23

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 1 ነገሥት 21-22

“ይሖዋ ሥልጣኑን የሚጠቀምበትን መንገድ ኮርጁ”

it-2 21

የሠራዊት ጌታ ይሖዋ

ኢያሱ በኢያሪኮ አቅራቢያ ሳለ አንድ መልአክ አየና “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ብሎ ጠየቀው፤ መልአኩም “አይደለሁም፤ እኔ አሁን የመጣሁት የይሖዋ ሠራዊት አለቃ ሆኜ ነው” ሲል መለሰለት። (ኢያሱ 5:13-15) ነቢዩ ሚካያህ ለንጉሥ አክዓብና ለንጉሥ ኢዮሳፍጥ “ይሖዋ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የሰማያት ሠራዊትም ሁሉ በቀኙና በግራው አጠገቡ ቆመው አየሁ” ብሏቸዋል፤ ይህን ሲል የይሖዋን መንፈሳዊ ልጆች ማመልከቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። (1ነገ 22:19-21) እዚህ ላይ “ሠራዊት” የሚለው ቃል የብዙ ቁጥር አመልካች ያለው መሆኑ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም የመላእክት ሠራዊት ኪሩቤል፣ ሱራፌልና መላእክት በሚሉት ምድቦች ብቻ ሳይሆን (ኢሳ 6:2, 3፤ ዘፍ 3:24፤ ራእይ 5:11) በተደራጀ መንገድ በቡድን በቡድን የተከፋፈሉ እንደሆኑም እንረዳለን። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “ከ12 ሌጌዎን የሚበልጡ መላእክት” እንዲላኩለት መጠየቅ እንደሚችል ተናግሯል። (ማቴ 26:53) ሕዝቅያስ ባቀረበው የእርዳታ ልመና ላይ ይሖዋን “ከኪሩቤል በላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ” ሲል ጠርቶታል። ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል የቃል ኪዳኑን ታቦትና መክደኛው ላይ ያሉትን የኪሩብ ምስሎች አስቦ መሆን አለበት፤ ይህም ለይሖዋ ሰማያዊ ዙፋን ተምሳሌት ነው። (ኢሳ 37:16፤ ከ1ሳሙ 4:4 እና 2ሳሙ 6:2 ጋር አወዳድር።) በፍርሃት የተዋጠው የኤልሳዕ አገልጋይ፣ በጠላት በተከበበችው የኤልሳዕ ከተማ ዙሪያ “የእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች . . . ተራራማውን አካባቢ ሞልተውት” አይቷል፤ በዚህ ተአምራዊ ራእይ አማካኝነት ከይሖዋ የመላእክት ሠራዊት የተወሰነውን ክፍል ማየቱ እንዲረጋጋ ረድቶታል።—2ነገ 6:15-17

w21.02 4 አን. 9

“የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ” ነው

9 ትሕትና። ይሖዋ ከማንም በላይ ጥበበኛ ነው፤ ያም ቢሆን የአገልጋዮቹን ሐሳብ ያዳምጣል። (ዘፍ. 18:23, 24, 32) በእሱ ሥልጣን ሥር ያሉ አገልጋዮቹ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ፈቅዶላቸዋል። (1 ነገ. 22:19-22) ይሖዋ ፍጹም ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከእኛ ፍጽምናን አይጠብቅም። ከዚህ ይልቅ ፍጹማን ያልሆንን የሰው ልጆች እንዲሳካልን ይረዳናል። (መዝ. 113:6, 7) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሖዋ ‘ረዳት’ ተብሎ ተገልጿል። (መዝ. 27:9፤ ዕብ. 13:6) ንጉሥ ዳዊት፣ ታላቅ ነገር ማከናወን የቻለው በይሖዋ ትሕትና እንደሆነ ተናግሯል።—2 ሳሙ. 22:36

it-2 245

ውሸት

ይሖዋ አምላክ፣ ሐሰትን የሚመርጡ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሚገልጸው ወንጌል ይልቅ “ሐሰት የሆነውን ያምኑ ዘንድ አታላይ በሆነ ተጽዕኖ ተሸንፈው እንዲስቱ ይፈቅዳል።” (2ተሰ 2:9-12) ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት በእስራኤላዊው ንጉሥ በአክዓብ ላይ የደረሰው ነገር ይህን ያጎላል። የሐሰት ነቢያት፣ ከራሞትጊልያድ ጋር በሚያደርገው ውጊያ ድል እንደሚቀናው ለአክዓብ ነግረውት ነበር፤ የይሖዋ ነቢይ የሆነው ሚካያህ ግን ጥፋት እንደሚደርስበት ተነበየ። ሚካያህ፣ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር በአክዓብ ነቢያት አፍ ላይ “አሳሳች መንፈስ” ለመሆን ያቀረበው ጥያቄ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ሲያገኝ በራእይ ተመልክቷል። ታዲያ ይህ መንፈሳዊ ፍጡር ያደረገው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ ነቢያት እውነቱን ከመናገር ይልቅ እነሱ ራሳቸው መናገር የሚፈልጉትንና አክዓብ መስማት የሚፈልገውን ነገር እንዲናገሩ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል። አክዓብ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም የነቢያቱን ውሸት ለማመን መረጠ፤ ይህም ሕይወቱን አሳጥቶታል።—1ነገ 22:1-38፤ 2ዜና 18

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

w21.10 3 አን. 4-6

እውነተኛ ንስሐ ምንድን ነው?

4 በመጨረሻም የይሖዋ ትዕግሥት ተሟጠጠ። ኤልያስን በመላክ በአክዓብና በኤልዛቤል ላይ ፍርድ አስተላለፈ። ፍርዱ መላው ቤተሰባቸው እንደሚደመሰስ የሚገልጽ ነበር። አክዓብ፣ ኤልያስ የተናገረውን ነገር ሲሰማ በጣም ደነገጠ! የሚገርመው ያ ትዕቢተኛ ሰው ‘ራሱን አዋረደ።’—1 ነገ. 21:19-29

5 አክዓብ በዚያ ወቅት ራሱን ያዋረደ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ያደረገው ነገር ንስሐው እውነተኛ እንዳልነበር ያሳያል። የበዓል አምልኮን ከግዛቱ ለማስወገድ ጥረት አላደረገም። የይሖዋን አምልኮ ለማስፋፋትም አልሞከረም። አክዓብ እውነተኛ ንስሐ አለመግባቱ በሌሎች መንገዶችም ታይቷል።

6 ከጊዜ በኋላ አክዓብ የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን ኢዮሳፍጥን ከሶርያውያን ጋር በሚያደርገው ውጊያ አብሮት እንዲሄድ ጠይቆት ነበር። ጥሩ ንጉሥ የነበረው ኢዮሳፍጥም በመጀመሪያ የይሖዋን ነቢይ እንዲጠይቁ ሐሳብ አቀረበ። መጀመሪያ ላይ አክዓብ ሐሳቡን በመቃወም እንዲህ አለ፦ “በእሱ አማካኝነት ይሖዋን ልንጠይቅ የምንችልበት አንድ ሰው ይቀራል፤ ሆኖም ስለ እኔ መጥፎ ነገር ብቻ እንጂ መልካም ነገር ፈጽሞ ስለማይተነብይ በጣም እጠላዋለሁ።” በኋላ ላይ ግን ነቢዩ ሚካያህን ጠየቁ። እንደተጠበቀው የአምላክ ነቢይ በአክዓብ ላይ መጥፎ ነገር እንደሚደርስበት ተነበየ! በዚህ ጊዜ ክፉው ንጉሥ አክዓብ የይሖዋን ምሕረት ከመለመን ይልቅ ነቢዩን እስር ቤት አስገባው። (1 ነገ. 22:7-9, 23, 27) ንጉሡ የይሖዋን ነቢይ ቢያሳስረውም ትንቢቱ እንዳይፈጸም ማድረግ አልቻለም። በጦርነቱ አክዓብ ተገደለ።—1 ነገ. 22:34-38

ከጥቅምት 24-30

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 1-2

“ግሩም የሥልጠና ምሳሌ”

w15 4/15 13 አን. 15

ሽማግሌዎች ሌሎች ብቃቱን እንዲያሟሉ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?

15 የኤልያስ ተተኪ ስለሆነው ስለ ኤልሳዕ የሚናገረው ዘገባ ወንድሞች ተሞክሮ ላካበቱ ሽማግሌዎች ተገቢውን አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነም ይጠቁማል። ኤልያስና ኤልሳዕ በኢያሪኮ የሚገኙ ነቢያትን ከጎበኙ በኋላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዱ። በዚያም “ኤልያስ የነቢይ ልብሱን አውልቆ በመጠቅለል ውኃውን መታው፤ ውኃውም ግራና ቀኝ ተከፈለ።” የደረቀውን ወንዝ ከተሻገሩ በኋላ ‘እየተጨዋወቱ መሄዳቸውን’ ቀጠሉ። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኤልሳዕ ሁሉንም ነገር ተምሮ እንደጨረሰ አልተሰማውም። ኤልያስ ከእሱ እስከተለየበት ጊዜ ድረስ አስተማሪው የሚናገረውን ሁሉ በጥሞና ይከታተል ነበር። ከዚያም ኤልያስ አውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ወደ ሰማይ ወጣ። በኋላም ኤልሳዕ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ተመልሶ ውኃውን በኤልያስ ልብስ በመምታት “የኤልያስ አምላክ ይሖዋ የት አለ?” አለ። ውኃውም በድጋሚ ለሁለት ተከፈለ።—2 ነገ. 2:8-14

w15 4/15 13 አን. 16

ሽማግሌዎች ሌሎች ብቃቱን እንዲያሟሉ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?

16 ኤልሳዕ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጸመው ተአምር ኤልያስ ለመጨረሻ ጊዜ ከፈጸመው ተአምር ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ልብ አልክ? ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? ኤልሳዕ አሁን በኃላፊነት ላይ ያለው እሱ ስለሆነ ኤልያስ ይጠቀምበት የነበረውን መንገድ ወዲያውኑ መቀየር እንዳለበት አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎቱን ኤልያስ ያከናውን በነበረበት መንገድ ማከናወኑን ቀጥሏል፤ ይህም ለአስተማሪው አክብሮት እንዳለው የሚያሳይ ሲሆን ሌሎች ነቢያትም በእሱ ላይ እንዲተማመኑ ረድቷቸዋል። (2 ነገ. 2:15) ከጊዜ በኋላ ግን ኤልሳዕ ለ60 ዓመታት በነቢይነት ባገለገለበት ወቅት በይሖዋ እርዳታ ከኤልያስ የበለጠ ብዙ ተአምራት ፈጽሟል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ ተማሪዎች ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

w05 8/1 9 አን. 1

የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

2:11—‘ኤልያስ በዐውሎ ነፋስ ያረገው’ ወደየትኛው “ሰማይ” ነው? ይህ ሰማይ በግዑዙ አጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኝን ሩቅ ቦታ ወይም አምላክና መላእክቱ የሚኖሩበትን መንፈሳዊ ሥፍራ አያመለክትም። (ዘዳግም 4:19፤ መዝሙር 11:4፤ ማቴዎስ 6:9፤ 18:10) ኤልያስ ያረገበት “ሰማይ” የሚያመለክተው በዓይናችን የምናየውን ሰማይ ነው። (መዝሙር 78:26፤ ማቴዎስ 6:26) ኤልያስ በእሳት ሰረገላ አማካኝነት በአየር ላይ ወደ ሌላ የምድር ክፍል ከተጓዘ በኋላ በተወሰደበት ሥፍራ ለተወሰኑ ጊዜያት ኖሯል። ዓመታት ካለፉ በኋላ ኤልያስ የይሁዳ ንጉሥ ለነበረው ለኢዮራም ደብዳቤ ልኮለታል።—2 ዜና መዋዕል 21:1, 12-15

ከጥቅምት 31–ኅዳር 6

ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | 2 ነገሥት 3-4

“ልጅሽን አንሺው”

w17.12 4 አን. 7

“በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ”

7 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የምናገኘውን ሁለተኛውን ትንሣኤ ያከናወነው ደግሞ የኤልያስ ተተኪ የሆነው ነቢዩ ኤልሳዕ ነው። በሹነም የምትኖር አንዲት ታዋቂ እስራኤላዊት ለኤልሳዕ ታላቅ ደግነት አሳየችው። አምላክ በነቢዩ አማካኝነት በገባው ቃል መሠረት፣ ልጅ የሌላትን ይህችን ሴትና በዕድሜ የገፋውን ባለቤቷን ስለባረካቸው ልጅ መውለድ ቻሉ። የሚያሳዝነው ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ልጃቸው ሞተ። እናትየው ምን ያህል በሐዘን እንደምትደቆስ መገመት አያዳግትም። ሴትየዋ፣ ወደ ኤልሳዕ እንደምትሄድ ለባሏ ከነገረችው በኋላ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የነበረውን ይህን ነቢይ ለማግኘት 30 ኪሎ ሜትር ያህል ተጓዘች። ነቢዩም አገልጋዩን ግያዝን ወደ ሹነም ቀድሟቸው እንዲሄድ ላከው። ሆኖም ግያዝ የሞተውን ልጅ ሊያስነሳው አልቻለም። ብዙም ሳይቆይ፣ ልጇን ያጣችው እናትና ኤልሳዕ ሹነም ደረሱ።—2 ነገ. 4:8-31

w17.12 5 አን. 8

“በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ”

8 በዚያም ኤልሳዕ የልጁ አስከሬን ወዳለበት ክፍል ገብቶ መጸለይ ጀመረ። የሞተውም ልጅ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሕያው ሆነ! እናትየው ልጇን ስታገኝ በደስታ ፈነደቀች። (2 ነገሥት 4:32-37​ን አንብብ።) ይህች እናት፣ ቀደም ሲል መሃን የነበረችው ሐና በማደሪያው ድንኳን ውስጥ እንዲያገለግል ሳሙኤልን ስታመጣው ያቀረበችውን ጸሎት አስታውሳ ሊሆን ይችላል፤ ሐና በጸሎቷ ላይ “ይሖዋ . . . ወደ መቃብር ያወርዳል፤ ከዚያም ያወጣል” ብላ ነበር። (1 ሳሙ. 2:6) አምላክ፣ በሹነም የነበረው ልጅ ዳግመኛ ሕያው እንዲሆን ማድረጉ ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው።

መንፈሳዊ ዕንቁዎች

it-2 697 አን. 2

ነቢይ

“የነቢያት ልጆች።” አንድ ጽሑፍ እንዳብራራው ቤን (የ. . . ልጅ) ወይም ቤኔ (የ. . . ልጆች) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “የአንድ ማኅበር (የአንድ ጎሳ ወይም የአንድ መደብ) አባል” መሆንን ሊያመለክት ይችላል። (ጀሴኒየስ ሂብሩ ግራመር) (ከነህ 3:8 ጋር ማወዳደር ይቻላል፤ ጥቅሱ ላይ “ከቅባት ቀማሚዎች አንዱ” የሚለው ሐረግ ቃል በቃል ሲተረጎም “የቅባት ቀማሚዎች ልጅ” ማለት ነው።) ከዚህ አንጻር “የነቢያት ልጆች” የሚለው አገላለጽ ለነቢይነት ተልእኮ የተጠሩ ሰዎች የሚሠለጥኑበትን ትምህርት ቤት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል፤ ወይም እንዲሁ የነቢያት መረዳጃ ማኅበር ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ የነቢያት ማኅበራት በቤቴል፣ በኢያሪኮና በጊልጋል እንደነበሩ ተጠቅሷል። (2ነገ 2:3, 5፤ 4:38፤ ከ1ሳሙ 10:5, 10 ጋር አወዳድር።) ሳሙኤል በራማ የሚገኘው ማኅበር መሪ ነበር፤ (1ሳሙ 19:19, 20) ኤልሳዕም በዘመኑ ተመሳሳይ ኃላፊነት የነበረው ይመስላል። (2ነገ 4:38፤ 6:1-3፤ ከ1ነገ 18:13 ጋር አወዳድር።) ዘገባው እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን መኖሪያ ቤት እንደገነቡና የግንባታ መሣሪያ ከሰው እንደተዋሱ ይገልጻል፤ ይህም አኗኗራቸው ቀላል እንደነበር የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ የሚኖሩትም ሆነ የሚመገቡት አንድ ላይ ነው፤ ሆኖም አንድ ዓይነት የነቢይነት ተልእኮ እንዲወጡ ለብቻቸው ኃላፊነት የሚሰጣቸው ጊዜ አለ።—1ነገ 20:35-42፤ 2ነገ 4:1, 2, 39፤ 6:1-7፤ 9:1, 2

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ