በሌሎች ዘንድ ምን ዓይነት ስም እያተረፍክ ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ስም” የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው በሌሎች ዘንድ ያለውን ዝና ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፣ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል።” (መክብብ 7:1፤ ከምሳሌ 22:1 ጋር አወዳድር።) እንደ ሰሎሞን አባባል አንድ ሰው ጥሩ ስም ይዞ አይወለድም። ከዚህ ይልቅ ትክክለኛ ትርጉም ያለው ስም የሚያገኘው በሚያሳልፈው የሕይወቱ ዘመን ወቅት ነው። ሰውዬው በሕይወት ዘመኑ የሚያተርፈው ስም ለጋስ ወይም ራስ ወዳድ፣ ርኅሩኅ ወይም ጨካኝ፣ ትሑት ወይም ትዕቢተኛ ሌላው ቀርቶ ጻድቅ ወይም ክፉ መሆኑን በመግለጽ የግል ባሕርያቱን ለይቶ ያመለክታል።
የዳዊትን ምሳሌ ውሰድ። በንግሥናው ዘመን ጠንካራና ጽኑ መሆኑን አስመስክሯል። ከዚህም በተጨማሪ ዳዊት ስህተቶቹን በትሕትና አምኖ ከመቀበሉም በላይ ለፈጸማቸው ከባድ ኃጢአቶችም ንስሐ ገብቷል። የይሖዋ ነቢይ፣ ዳዊት ‘[ለአምላክ] ልብ የሚስማማ ሰው’ መሆኑን መግለጹ አለ ምክንያት አይደለም። (1 ሳሙኤል 13:14) ወጣቱ ዳዊት ቀድሞም በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም አትርፎ ነበር።
በአንፃሩ ደግሞ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮራም መጥፎ ስም አትርፏል። በእሱ ሥር ያሉት ሕዝቦች ይሖዋን ከማምለክ እንዲርቁ ከማድረጉም በላይ ስድስት ወንድሞቹን ጨምሮ አንዳንድ የይሁዳ መሳፍንት እንዲገደሉ አድርጓል። መጨረሻ ላይ ይሖዋ ኢዮራምን ለሞት በዳረገው አሰቃቂ በሽታ ቀሰፈው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢዮራም “ማንም ሳያዝንለት ሄደ” በማለት ይገልጻል፤ ወይም ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ባሰፈረው መሠረት “እሱ ሲሞት ማንም አላዘነለትም ነበር።”—2 ዜና መዋዕል 21:20
ዳዊትና ኢዮራም የተከተሉት የሕይወት መንገድ ቀጥሎ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እውነት መሆኑን ያሳያል:- “የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል።” (ምሳሌ 10:7) ይህም በመሆኑ ሁላችንም ‘በአምላክና በሰዎች ዘንድ ምን ዓይነት ስም እያተረፍኩ ነው?’ የሚለውን ጥያቄ በጥሞና ልናስብበት ይገባል።