የምትገነባው በምን ዓይነት መሠረት ላይ ነው?
የአንድ ሕንጻ ጥንካሬ በአመዛኙ የተመካው መሠረቱ ጠንካራ በመሆኑ ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መሠረታዊ እውነታ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል።
ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋ አምላክ ‘ምድርን እንደመሠረተ’ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 51:13) ይህ መሠረት የምድርን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩትንና ቦታዋን ጠብቃ እንድትሽከረከር የሚያደርጓትን የአምላክን የማይለዋወጡ ሕግጋት የሚያመለክት ነው። (መዝሙር 104:5) የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ደግፎ ስለያዘው ‘መሠረትም’ ይናገራል። ይህ መሠረት ፍትሕን፣ ሕግንና ሥርዓትን ያካትታል። እነዚህ ነገሮች በፍትሕ መጓደል፣ በሥነ ምግባር ብልሹነትና በዓመጽ ምክንያት ‘ከተናዱ’ ወይም ከተዳከሙ ማኅበራዊው ሥርዓት ለውድቀት ይዳረጋል።—መዝሙር 11:2-6፤ ምሳሌ 29:4
ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለሰዎችም በግለሰብ ደረጃ ይሠራል። ኢየሱስ ክርስቶስ ዝነኛውን የተራራ ስብከቱን ሲደመድም እንዲህ ብሎ ነበር:- “ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን ብልኅ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ በዐለት መሠረትም ላይ ስለተመሠረተ አልወደቀም። ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውለው ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያንን ቤት መታው፤ ቤቱም ወደቀ፤ አወዳደቁም የከፋ ነበር።”—ማቴዎስ 7:24-27
አንተስ ሕይወትህን የምትገነባው በምን ዓይነት መሠረት ላይ ነው? መጨረሻው ውድቀት በሆነው፣ እንደ አሸዋ በተመሰለውና አምላካዊ አክብሮት የሌለው ዓለም በሚያራምደው ሰብዓዊ ፍልስፍና ላይ ነው? ወይስ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ማዕበል መሰል ችግሮችን ለመቋቋም በሚያስችለውና የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በመታዘዝ በተመሰለው ጠንካራ ዐለት ላይ?