የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ልጆቻችን ውድ ስጦታ ናቸው
    መጠበቂያ ግንብ—2005 | ሚያዝያ 1
    • ልጆቻችን ውድ ስጦታ ናቸው

      “እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው።”—መዝሙር 127:3

      1. የመጀመሪያው ሕፃን የተወለደው እንዴት ነው?

      ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ሲፈጥር ታላቅ ተአምር ሊከናወን የሚችልበትን ሁኔታ እንዴት እንዳዘጋጀ ተመልከት። አባትየው አዳምና እናቲቱ ሔዋን የየራሳቸውን ክፋይ አዋጥተው የተፈጠረው ሕዋስ በሔዋን ማሕጸን ውስጥ አድጎ ሙሉ አዲስ ሰው ሆነና የመጀመሪያው ልጅ ተወለደ። (ዘፍጥረት 4:1) እስከዚህ ዘመን ድረስ የአንድ ልጅ መፀነስና መወለድ በጣም ሲያስገርም የኖረ ጉዳይ ሲሆን ብዙዎች ይህ ክስተት ተአምር እንደሆነ ይናገራሉ።

      2. በአንዲት ነፍሰ ጡር ማሕጸን ውስጥ የሚፈጸመው ክንውን ተዓምር ነው እንድትል የሚያደርግህ ምንድን ነው?

      2 እናቲቱ ከአባትየው ጋር ባደረገችው ግንኙነት ምክንያት የተፈጠረው የመጀመሪያው ሕዋስ በ270 ቀናት ውስጥ አድጎ በብዙ ትሪሊዮኖች በሚቆጠሩ ሕዋሳት የተገነባ ሕፃን ይሆናል። በመጀመሪያው ሕዋስ ውስጥ ከ200 የሚበልጡ የተለያዩ ዓይነት ሕዋሳትን ለመሥራት የሚያስችል መመሪያ አለ። በአስገራሚ ሁኔታ የተወሳሰቡት እነዚህ ሕዋሳት ከሰው ልጆች የመረዳት ችሎታ በላይ በሆነው በዚህ እጹብ ድንቅ መመሪያ መሠረት በተወሰነላቸው ቅደም ተከተልና ሥርዓት ተቀናጅተው አዲስ ሕያው አካል ያስገኛሉ!

      3. ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው በርካታ ሰዎች ልጅ እንዲወለድ የሚያደርገው አምላክ መሆን እንዳለበት የሚስማሙት ለምንድን ነው?

      3 ታዲያ የዚህ ሕፃን ፈጣሪ ማን ነው ትላለህ? የሕይወት ምንጭ የሆነው አምላክ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 100:3 የ1954 ትርጉም) ወላጆች፣ እንዲህ ያለ ውድ ሕፃን የወለዳችሁት የተለየ ችሎታ ስላላችሁ እንዳልሆነ አሳምራችሁ ታውቁታላችሁ። አንድ ሕፃን ልጅ ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችለው ለጥበቡ ዳርቻ የሌለው አምላክ ብቻ ነው። ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ሰዎች አንድ ሕፃን በእናቱ ማሕጸን ውስጥ እንዲፈጠር የሚያደርገው ታላቁ ፈጣሪ መሆኑን በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲያምኑበት ቆይተዋል። አንተስ?—መዝሙር 139:13-16

      4. ይሖዋ የትኛው መጥፎ የሰዎች ባሕርይ ፈጽሞ አይታይበትም?

      4 ይሁን እንጂ ይሖዋ ሰዎች ዘር መተካት የሚችሉበትን ባዮሎጂያዊ ሂደት ፈጥሮ ብቻ አሳቢነት በጎደለው ሁኔታ እርግፍ አድርጎ ትቷቸዋል? አንዳንድ ሰዎች አሳቢነት የጎደላቸው ናቸው፤ ይሖዋ ግን ፈጽሞ እንደዚያ አይደለም። (መዝሙር 78:38-40) መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 127:3 ላይ “እነሆ፤ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው” በማለት ይናገራል። እስቲ በመጀመሪያ ስጦታ ምን እንደሆነና ምን እንደሚያረጋግጥልን እንመልከት።

      ውርስ እና ችሮታ

      5. ልጆች ውርስ ወይም ስጦታ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

      5 ውርስ እንደ ስጦታ ነው። ብዙውን ጊዜ ወላጆች ለልጆቻቸው በስጦታ መልክ ውርስ ለማውረስ ብዙ ይደክማሉ። ይህ ውርስ ወይም ስጦታ ገንዘብ፣ ንብረት አሊያም አንድ ዓይነት ውድ ሀብት ሊሆን ይችላል። ስጦታው ምንም ይሁን ምን ወላጆች ልጆቻቸውን እንደሚወዷቸው የሚያረጋግጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በፍቅር ተገፋፍቶ ልጆችን ለወላጆች ስጦታ አድርጎ እንደሰጣቸው ይናገራል። ወላጅ ከሆንክ፣ ተግባርህ ልጆችህን ከጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ በአደራ እንዳገኘሃቸው ስጦታዎች አድርገህ እንደምትመለከታቸው የሚያሳይ ይመስልሃል?

      6. ይሖዋ ለሰዎች ልጅ የመውለድ ችሎታ የሰጣቸው ለምንድን ነው?

      6 ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ልጅ የመውለድ ስጦታ የሰጠበት ዋነኛው ዓላማ ምድር በዘሮቻቸው እንድትሞላ ነበር። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ኢሳይያስ 45:18) ይሖዋ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክት በቀጥታ ወደ ሕልውና እንዲመጡ እንዳደረገው እያንዳንዱን ሰው በግለሰብ ደረጃ አልፈጠረም። (መዝሙር 104:4፤ ራእይ 4:11) ከዚህ ይልቅ አምላክ ሰዎች መሰላቸውን የመውለድ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጎ ፈጥሯቸዋል። አንድ አባትና አንዲት እናት እንዲህ ያለ ልጅ ወልደው የማሳደግ አጋጣሚ ማግኘታቸው እንዴት ያለ አስደናቂ መብት ነው! ወላጅ ከሆንክ እንዲህ ያለውን ውድ ስጦታ ማግኘት የምትችልበትን ችሎታ ስለሰጠህ ይሖዋን ታመሰግነዋለህ?

      ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ተማር

      7. ከአንዳንድ ወላጆች በተቃራኒ ኢየሱስ ‘ለሰው ልጆች’ አሳቢነትና ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው?

      7 የሚያሳዝነው ግን ልጆቻቸውን ከይሖዋ እንደተገኙ በረከቶች አድርገው የሚመለከቱት ሁሉም ወላጆች አይደሉም። በርካታ ወላጆች ለልጆቻቸው ርኅራኄ የላቸውም። እንዲህ ያሉ ወላጆች የይሖዋን ወይም የልጁን ዓይነት ባሕርይ አያንጸባርቁም። (መዝሙር 27:10፤ ኢሳይያስ 49:15) በተቃራኒው ግን ኢየሱስ ምን ያህል ለልጆች አሳቢ እንደነበረ ተመልከት። ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ማለትም ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር በነበረበት ወቅት እንኳ ‘በሰው ልጆች ደስ ይሰኝ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 8:31) ለእኛ ለሰው ልጆች ታላቅ ፍቅር ስለነበረው የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንድንችል ሕይወቱን በፈቃደኝነት ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 10:18

      8. ኢየሱስ ለወላጆች ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?

      8 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ወላጆች ሊከተሉት የሚችሉት ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል። እስቲ ምን አድርጎ እንደነበር እንመልከት። በጣም ሥራ በበዛበትና ውጥረት ውስጥ በነበረበት ጊዜም እንኳ ከልጆች ጋር ጊዜ አሳልፏል። ልጆች ገበያ ውስጥ ሲጫወቱ ተመልክቶ ሲያደርጉት የነበረውን ነገር ሌሎችን ለማስተማር ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 11:16, 17) ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዘበት ወቅት መከራ እንደሚደርስበትና እንደሚገደል አውቆ ነበር። በዚህ ጊዜ ሰዎች ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ኢየሱስ ሲመጡ ደቀ መዛሙርቱ ተጨማሪ ውጥረት እንዳይፈጥርበት በማሰብ ሳይሆን አይቀርም ልጆቹን ሊያባርሯቸው ሞከሩ። ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱን የገሠጻቸው ከመሆኑም በላይ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው” በማለት በልጆች ‘ደስ እንደሚሰኝ’ አሳይቷል።—ማርቆስ 10:13, 14

      9. ከቃል ይልቅ ድርጊት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ለምን ሊሆን ይችላል?

      9 ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ሥራ ቢበዛብን እንኳ ልጆች ወደ እኛ ሲመጡ የምንቀበላቸው እንዴት ነው? ልክ እንደ ኢየሱስ ነው? ኢየሱስ በፈቃደኝነት ካደረገው ነገር እንደምንገነዘበው ልጆች በተለይ የወላጆቻቸውን ጊዜና ትኩረት ይሻሉ። “እወድሃለሁ ወይም እወድሻለሁ” እንደሚሉት ያሉ ቃላትን መናገር አስፈላጊ እንደሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ ከቃላት ይልቅ ተግባር የጎላ ድምፅ አለው። ፍቅራችሁ የሚገለጸው በቃል ብቻ ሳይሆን ይበልጡኑ በድርጊታችሁ ነው። ለልጆቻችሁ ያላችሁ ፍቅር በምትሰጧቸው ጊዜና ትኩረት እንዲሁም በምታደርጉላቸው እንክብካቤ መጠን ይለካል። ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ አድርጋችሁም እንኳ እናንተ እንደምታስቡት ወዲያውኑ ተጨባጭ ውጤት አታገኙ ይሆናል። ትዕግሥት አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበትን መንገድ የምንኮርጅ ከሆነ ትዕግሥት መማር እንችላለን።

      ኢየሱስ ያሳየው ትዕግሥትና ፍቅር

      10. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ትሕትና ያስተማራቸው እንዴት ነበር? መጀመሪያ ላይ ተሳክቶለት ነበር?

      10 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ትልቅ ቦታ ለማግኘት እርስ በርሳቸው በተደጋጋሚ እንደሚፎካከሩ ያውቅ ነበር። አንድ ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቅፍርናሆም ከደረሱ በኋላ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። “እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ።” ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እያመናጨቀ ከመገሠጽ ይልቅ ህያው የሆነ ምሳሌ በመጠቀም በትዕግሥት ትሕትናን አስተማራቸው። (ማርቆስ 9:33-37) ምሳሌው የሚፈልገውን ውጤት አስገኝቶለት ይሆን? ወዲያውኑ አላስገኘም። ከስድስት ወራት ገደማ በኋላ ያዕቆብና ዮሐንስ በአምላክ መንግሥት የላቀ ቦታ እንዲሰጣቸው ኢየሱስን በእናታቸው በኩል ጠየቁት። በዚህ ጊዜም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ በትዕግሥት ረድቷቸዋል።—ማቴዎስ 20:20-28

      11. (ሀ) የኢየሱስ ሐዋርያት የማለፍን በዓል ወደሚያከብሩበት ቤት ከደረሱ በኋላ ሳያከናውኑ የቀሩት የአካባቢው ልማድ ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ምን አደረገ? ጥረቱስ ወዲያው ተሳክቶለት ነበር?

      11 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሚከበረው የማለፍ በዓል ሲደርስ ኢየሱስና ሐዋርያቱ በዓሉን ለብቻቸው ለማክበር ተሰባሰቡ። አንድ ፎቅ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ በደረሱበት ወቅት ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዳቸውም እንኳ በአካባቢው ልማድ መሠረት የጓደኞቻቸውን አቧራ የለበሰ እግር ለማጠብ በፈቃደኝነት አልተነሱም። እግር ማጠብ በአገልጋዮች ወይም በሴቶች መከናወን ያለበት ዝቅተኛ ሥራ ተደርጎ ይታይ ነበር። (1 ሳሙኤል 25:41፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:10) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ትልቅ ሥልጣን ወይም ቦታ ለማግኘት የሚያደርጉትን ፉክክር እንዳልተዉ የሚያሳይ ሁኔታ ሲመለከት በጣም አዝኖ መሆን አለበት! በመሆኑም ኢየሱስ የእያንዳንዳቸውን እግር በማጠብ እነርሱም ሌሎችን በማገልገል ምሳሌውን እንዲኮርጁ አጥብቆ አሳሰባቸው። (ዮሐንስ 13:4-17) ታዲያ ምሳሌውን ተከትለው ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ደግሞም ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ” በማለት በዚያው ምሽት ትንሽ ቆየት ብሎ ስለተከሰተው ሁኔታ ይናገራል።—ሉቃስ 22:24

      12. ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሠልጠን በሚያደርጉት ጥረት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

      12 እናንተ ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የሰጣችኋቸውን ምክር ተግባራዊ ሳያደርጉ ሲቀሩ ኢየሱስ እንዲህ ያለ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ትሞክራላችሁ? ኢየሱስ ሐዋርያቱ ስህተታቸውን ለማረም ጊዜ ቢወስድባቸውም እንኳ ተስፋ እንዳልቆረጠ አስታውሱ። ያሳየው ትዕግሥት ውሎ አድሮ ፍሬ አፍርቷል። (1 ዮሐንስ 3:14, 18) ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ለማሠልጠን በምታደርጉት ጥረት ረገድ ፈጽሞ ተስፋ ባለመቁረጥ ኢየሱስ ያሳየውን ፍቅርና ትዕግሥት መኮረጅ ይኖርባችኋል።

      13. አንድ ወላጅ ልጁ ጥያቄ ሲጠይቀው ተቆጥቶ ማባረር የማይገባው ለምንድን ነው?

      13 ልጆች ወላጆቻቸው እንደሚወዷቸውና እንደሚያስቡላቸው ሊሰማቸው ይገባል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደሚያስቡ የማወቅ ፍላጎት ስለነበረው ጥያቄ ሲጠይቁት ያዳምጣቸው ነበር። እንዲሁም ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ምን እንደሚሰማቸው ይጠይቃቸው ነበር። (ማቴዎስ 17:25-27) አዎን፣ ውጤታማ ከሆኑት የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል በትኩረት ማዳመጥና ልባዊ አሳቢነት ማሳየት ይገኙበታል። አንድ ወላጅ ልጁ ጥያቄ ሲጠይቀው “ሂድ ከዚህ! ሥራ ላይ መሆኔ አይታይህም?” በማለት ተቆጥቶ ማባረር የሚቀናው ከሆነ ማስተካከል ይኖርበታል። በእርግጥ ሥራ በዝቶበት ቢሆን እንኳ ጉዳዩን በኋላ እንደሚነጋገሩበት ለልጁ ሊነግረው ይገባል። ከዚያም ወላጆች ቃላቸውን አክብረው ልጁን ማነጋገር አለባቸው። እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ልጁ ወላጆቹ በእርግጥ እንደሚያስቡለት ስለሚሰማው ይበልጥ ይተማመንባቸዋል።

      14. ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅር ማሳየትን በሚመለከት ከኢየሱስ ምን መማር ይችላሉ?

      14 ወላጆች እጃቸውን በልጆቻቸው ትከሻ ላይ ጣል በማድረግና በማቀፍ ፍቅራቸውን መግለጻቸው አስፈላጊ ነው? ወላጆች በዚህም ረገድ ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ትምህርት መቅሰም ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው” በማለት ስለ ኢየሱስ ይናገራል። (ማርቆስ 10:16) ሕፃናቱ ምን የተሰማቸው ይመስልሃል? ከልብ ደስ እንዳላቸውና ኢየሱስንም በጣም እንደወደዱት ምንም ጥርጥር የለውም! በእናንተ በወላጆችና በትንንሽ ልጆቻችሁ መካከል ልባዊ ፍቅርና መዋደድ ካለ ልጆቻችሁ የምትሰጧቸውን ተግሣጽና ትምህርት መቀበል አይከብዳቸውም።

      ከልጆችህ ጋር ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ ይኖርብሃል?

      15, 16. የልጆችን አስተዳደግ በሚመለከት ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ጽንሰ ሐሳብ የትኛው ነው? የመነጨውስ ከምን ሊሆን ይችላል?

      15 ይሁን እንጂ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፋቸውና ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየታቸው ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። የልጆችን አስተዳደግ በሚመለከት ‘ከልጆች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ በቂ ነው’ የሚል በረቀቀ ዘዴ የተሰራጨ አንድ ጽንሰ ሐሳብ አለ። የዚህ ጽንሰ ሐሳብ አቀንቃኞች ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ትርጉም ያለው፣ በሚገባ የታሰበበትና ጥሩ እቅድ የወጣለት እስከሆነ ድረስ ሰፊ መሆን እንደማያስፈልገው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ ትክክል ነው? እውነት የልጆችን ደኅንነት ግምት ውስጥ ያስገባ ጽንሰ ሐሳብ ነው?

      16 በርካታ ልጆችን ያነጋገሩ አንድ ጸሐፊ ልጆች “ከወላጆቻቸው በጣም የሚፈልጉት ሰፊ ጊዜ” እና “ያልተከፋፈለ ትኩረት” እንደሆነ ተናግረዋል። አንድ የኮሌጅ ፕሮፌሰር ይህ ጽንሰ ሐሳብ “ወላጆች ከሚሰማቸው የሕሊና ወቀሳ የመነጨ ነው። ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ላለማሳለፍ የፈለጉ ሰዎች የፈጠሩት ሰበብ ነው” በማለት የሰነዘሩት አስተያየት ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ታዲያ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል?

      17. ልጆች ከወላጆቻቸው የሚፈልጉት ምንድን ነው?

      17 መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ጊዜ አይልም። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ወላጆች በቤት ሲቀመጡ፣ በመንገድ ላይ ሲሄዱ፣ ሲተኙና ሲነሱ ከልጆቻቸው ጋር እንዲነጋገሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 6:7) ይህ ሲባል ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መቀራረብና በየዕለቱ የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅመው እነርሱን ማስተማር ይኖርባቸዋል ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው።

      18. ኢየሱስ ያገኘውን አጋጣሚ ደቀ መዛሙርቱን ለማሠልጠን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ወላጆች ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

      18 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የሚበላበትንና የሚጓዝበትን፣ አልፎ ተርፎም አረፍ የሚልበትን ጊዜ ተጠቅሞ በሚገባ አሠልጥኗቸዋል። በዚህ መልኩ፣ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ እነርሱን ለማስተማር ጥሩ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ማርቆስ 6:31, 32፤ ሉቃስ 8:1፤ 22:14) በተመሳሳይ ክርስቲያን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት፣ ግንኙነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እንዲሁም እነርሱን በይሖዋ መንገድ ለማሠልጠን የሚያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ጥሩ አድርገው ሊጠቀሙበት ይገባል።

      ልጆች መማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው? እንዴትስ?

      19. (ሀ) ከልጆች ጋር ጊዜ ከማሳለፍ በተጨማሪ የሚያስፈልገው ምንድን ነው? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸውን በዋነኝነት ማስተማር የሚኖርባቸው ምንድን ነው?

      19 ይሁን እንጂ ልጆችን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ የሚያስፈልገው ነገር የተወሰነ ጊዜ ከእነርሱ ጋር ማሳለፍና ማስተማር ብቻ አይደለም። ልጆች ‘የሚማሩት ምንድን ነው’ የሚለውም ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ምን መማር እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸውን ልብ በል። “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት . . . ለልጆችህም አስጠናቸው [“በልጆችህ ልብ ውስጥ ቅረጻቸው፣” NW]” ይላል። ልጆች መማር የሚያስፈልጓቸው ‘እነዚህ ትእዛዛት’ ምንድን ናቸው? በቁጥር 5 ላይ “አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ” ተብሎ የተገለጸው ትእዛዝ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ዘዳግም 6:5-7) ኢየሱስ ይህ ትእዛዝ አምላክ ከሰጣቸው ትእዛዛት ሁሉ እንደሚበልጥ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:28-30) ስለዚህ ወላጆች በፍጹም ነፍስ ሊወደድና ሊመለክ የሚገባው እርሱ ብቻ የሆነው ለምን እንደሆነ ለልጆቻቸው በማስረዳት በዋነኝነት ስለ ይሖዋ ማስተማር ይኖርባቸዋል።

      20. አምላክ በጥንት ዘመን የነበሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ምን እንዲያስተምሩ አዟቸው ነበር?

      20 ይሁን እንጂ ወላጆች ለልጆቻቸው ማስተማር የሚጠበቅባቸው ‘እነዚህ ትእዛዛት’ አምላክን በፍጹም ልብ መውደድን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነገሮችንም ይጨምራሉ። ሙሴ በዘዳግም ምዕራፍ 5 ውስጥ አምላክ በጽላት ላይ ጽፎ የሰጠውን አሥርቱን ትእዛዛት በድጋሚ እንደጠቀሳቸው ሳትገነዘብ አትቀርም። ከእነዚህ ሕግጋት ውስጥ አትዋሽ፣ አትስረቅ፣ አትግደል፣ አታመንዝር የሚሉት ትእዛዛት ይገኙበታል። (ዘዳግም 5:11-22) በመሆኑም በዚያ ዘመን የነበሩት ወላጆች የሥነ ምግባር እሴቶችን ለልጆቻቸው ማስተማሩ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጾላቸዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወላጆችም ልጆቻቸው ወደፊት አስተማማኝና ደስታ የሰፈነበት ሕይወት እንዲመሩ ለመርዳት የሚፈልጉ ከሆነ ተመሳሳይ ትምህርት መስጠት ይኖርባቸዋል።

      21. የአምላክን ቃል በልጆች ልብ ውስጥ ‘መቅረጽ’ ሲባል ምን ማለት ነው?

      21 ወላጆች “እነዚህን ትእዛዛት” ለልጆቻቸው እንዴት እንደሚያስተምሩም እንደተነገራቸው ልብ በል። ‘በልጅህ ልብ ውስጥ ቅረጸው’ ተብለው ታዝዘዋል። ‘መቅረጽ’ ተብሎ የተተረጎመው ኢንከልኬት የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “ደግሞ ደጋግሞ በመናገር ወይም በማሳሰብ ማስተማርና ማስገንዘብ፤ ማበረታታት ወይም በአእምሮ ውስጥ እንዲተከል ማድረግ” የሚል ፍቺ አለው። ስለዚህ አምላክ፣ ወላጆች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ መንፈሳዊ ጉዳዮችን የመትከል ግብ ይዘው በሚገባ የታሰበበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም ማዘጋጀት እንደሚኖርባቸው ማሳሰቡ ነበር።

      22. እስራኤላውያን ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ምን እንዲያደርጉ ተነግሯቸው ነበር? ይህስ ምን ትርጉም አለው?

      22 እንዲህ ያለው የታሰበበት ፕሮግራም የወላጆችን ተነሳሽነት ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “[እነዚህን ትእዛዛት] በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ። በቤትህ መቃኖች በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው” ይላል። (ዘዳግም 6:8, 9) ይህ ሲባል ግን ወላጆች የአምላክን ሕግጋት ቃል በቃል በቤታቸው መቃንና በግቢያቸው በር ላይ ይጽፋሉ ወይም ሕጎቹን ገልብጠው በልጆቻቸው እጅ ላይ ያስራሉ እንዲሁም በዓይኖቻቸው መካከል ያደርጋሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዋነኝነት ለማሳሰብ የተፈለገው ወላጆች የአምላክን ትእዛዛት ዘወትር ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ ነው። አዘውትረው ልጆቻቸውን የማስተማሩ ጉዳይ በቋሚነት መደረግ የሚገባው በመሆኑ የአምላክ ትምህርት ሁልጊዜ ከልጆቹ ፊት እንደማይጠፋ ነገር ነበር።

      23. የሚቀጥለው ሳምንት ጥናት በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ይሆናል?

      23 ወላጆች ልጆቻቸውን ሊያስተምሯቸው ከሚገቡት በጣም አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ልጆች ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንዲችሉ ትምህርትም ሆነ ሥልጠና ማግኘታቸው በተለይ በዛሬው ጊዜ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ወላጆች ልጆቻቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተማር እንዲችሉ ለመርዳት ምን ጠቃሚ ዝግጅት ተደርጎላቸዋል? በርካታ ወላጆችን የሚያሳስቡ እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል።

  • ወላጆች፣ ውድ ለሆኑት ስጦታዎቻችሁ ጥበቃ አድርጉላቸው
    መጠበቂያ ግንብ—2005 | ሚያዝያ 1
    • ወላጆች፣ ውድ ለሆኑት ስጦታዎቻችሁ ጥበቃ አድርጉላቸው

      ‘ጥበብ ጥላ ከለላ ናት፤ የባለቤቷን ሕይወት ትጠብቃለች።’—መክብብ 7:12

      1. ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ ስጦታ መመልከት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

      ወላጆች በአካላዊ ገጽታና በባሕርይ እነርሱን የሚመስሉ ልጆች ይወልዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉትን ልጆች “የእግዚአብሔር ስጦታ” በማለት ይጠራቸዋል። (መዝሙር 127:3) ዋነኛው የሕይወት ምንጭ ይሖዋ ስለሆነ ንብረቱ የሆኑትን ልጆች ለወላጆች በአደራ ሰጥቷቸዋል። (መዝሙር 36:9) ወላጆች፣ እነዚህን የመሰሉ ውድ ስጦታዎች ከአምላክ በማግኘታችሁ ምን ይሰማችኋል?

      2. ማኑሄ ልጅ እንደሚወልድ በተነገረው ጊዜ ምን አደረገ?

      2 ወላጆች እንዲህ ያለውን ስጦታ በትሕትናና በአድናቆት መቀበል እንደሚኖርባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ከ3,000 ዓመታት በፊት እስራኤላዊው ማኑሄ፣ አንድ መልአክ ልጅ እንደሚወልዱ ለሚስቱ በነገራት ጊዜ እንዲህ ያለ ስሜት አሳይቶ ነበር። ማኑሄ ምሥራቹን ሲሰማ “ጌታ ሆይ፤ የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ እንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ” በማለት ጸልዮአል። (መሳፍንት 13:8) ወላጆች ከማኑሄ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ?

      በዛሬው ጊዜ መለኮታዊ እርዳታ ያስፈለገበት ምክንያት

      3. በተለይ በዛሬው ጊዜ ልጆችን ለማሳደግ የአምላክ እርዳታ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      3 በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የይሖዋ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰይጣን ዲያብሎስና መላእክቱ ከሰማይ ወደ ምድር ስለተጣሉ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርና ባሕር . . . ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቊጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ራእይ 12:7-9, 12) በተጨማሪም ሰይጣን “የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ” በመዞር ላይ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 5:8) አብዛኛውን ጊዜ አንበሳ ማደን የሚፈልገው ራሳቸውን የመከላከል አቅም የሌላቸውን በተለይ ደግሞ ትንንሽ እንስሳትን ነው። በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠበቅ የሚያስችል መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር ማለታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ታዲያ ልጆቻችሁን ለመጠበቅ ምን ያህል ጥረት እያደረጋችሁ ነው?

      4. (ሀ) ወላጆች በሰፈራቸው ውስጥ አንበሳ እንደተለቀቀ ቢሰሙ ምን እርምጃ ለመውሰድ ይነሳሳሉ? (ለ) ልጆች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ምን ማግኘት ያስፈልጋቸዋል?

      4 በሰፈራችሁ ውስጥ አንበሳ እንደተለቀቀ ብትሰሙ ከምንም በላይ የሚያሳስባችሁ ልጆቻችሁን ከአደጋ የመጠበቁ ጉዳይ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ሰይጣን ልክ እንደ አዳኝ አውሬ ነው። የአምላክ ሕዝቦች አቋማቸውን አጉድፈው የአምላክን ሞገስ እንዲያጡ ለማድረግ ይፈልጋል። (ኢዮብ 2:1-7፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ለዚህ ጥቃት ይበልጥ የተጋለጡት ደግሞ ልጆች ናቸው። ልጆች በዲያብሎስ ወጥመድ እንዳይያዙ ይሖዋን ማወቅና እርሱን መታዘዝ ይኖርባቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) ከዚህም በላይ ልጆች ጥበብ ማለትም የተማሩትን የመረዳትና ተግባራዊ የማድረግ ችሎታ ያስፈልጋቸዋል። ‘ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ስለምትጠብቅ’ ወላጆች በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ እውነትን መትከል ያስፈልጋችኋል። (መክብብ 7:12) ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

      5. (ሀ) ጥበብን ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) የምሳሌ መጽሐፍ ጥበብ ምን ጥቅም እንዳላት ይገልጻል?

      5 ለልጆቻችሁ የአምላክን ቃል ልታነቡላቸው ትችላላችሁ፤ ደግሞም እንደዚያ ማድረግ ይኖርባችኋል። ይሁን እንጂ ልጆች ይሖዋን እንዲወዱትና እንዲታዘዙት ለማድረግ ከዚህም የበለጠ ነገር ያስፈልጋል፤ ልጆቹ የሚማሩትን መረዳት ይኖርባቸዋል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ልጅ ግራና ቀኝ ሳይመለከት የመኪና መንገድ እንዳያቋርጥ ይነገረው ይሆናል። ሆኖም አንዳንድ ልጆች እንደታዘዙት አያደርጉም። ለምን? በመኪና መገጨት የሚያስከትለው አደጋ በሚገባ ስለማይገለጽላቸው ወይም የአደጋው ውጤት በደንብ እንዲታያቸው ስለማይደረግ ሊሆን ይችላል። በዚህ መንገድ ትምህርት ቢሰጣቸው ግን ለአደጋ የሚያጋልጥ ‘የሞኝነት’ እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይችላሉ። ጥበብን ለሌሎች ለማስተማር ጊዜና ከፍተኛ ትዕግሥት ይጠይቃል። ይሁንና ጥበብ እጅግ ጠቃሚ ናት! መጽሐፍ ቅዱስ “መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ” ይላል።—ምሳሌ 3:13-18፤ 22:15

      ጥበብ የሚሰጥ ትምህርት

      6. (ሀ) ልጆች ብዙውን ጊዜ ስህተት የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? (ለ) ምን ዓይነት ጦርነት በመካሄድ ላይ ነው?

      6 ብዙውን ጊዜ ልጆች ስህተት የሚሠሩት ትክክል የሆነውን ስላልተማሩ ሳይሆን ትምህርቱ ልባቸውን ስላልነካ ወይም ውስጣቸው ስላልዘለቀ ሊሆን ይችላል። ዲያብሎስ የልጆችን ልብ ለመቆጣጠር ፍልሚያ እያካሄደ ነው። የሚፈልገው በእርሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ለሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ ሲጋለጡ ማየት ነው። ከዚህም በላይ ከአዳም በወረሱት ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ ተገፋፍተው መጥፎ ነገሮችን እንዲፈጽሙ ለማድረግ ይጥራል። (ዘፍጥረት 8:21፤ መዝሙር 51:5) ወላጆች፣ የልጆቻቸውን ልብ ለመማረክ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደተከፈተ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

      7. ለአንድ ልጅ ትክክል ወይም ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ብቻ መንገሩ በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው?

      7 ወላጆች ለልጃቸው አንድ ዓይነት የሥነ ምግባር መመሪያ ለማስተማር ሲሉ ብዙውን ጊዜ ትክክልና መጥፎ ስለሆኑ ነገሮች ይነግሩታል። ለምሳሌ ያህል መዋሸት፣ መስረቅ ወይም ካላገቡት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም ትክክል እንዳልሆነ ለልጁ ይነግሩት ይሆናል። ይሁን እንጂ የተሰጠውን ትእዛዝ የማክበር ብርቱ ፍላጎት እንዲያድርበት ሌላም ነገር ማወቅ ያስፈልገዋል። ትእዛዙን የሰጡት ወላጆቹ ቢሆኑም ሕጉን ያወጣው ይሖዋ እንደሆነ ማወቅ ይኖርበታል። ልጁ የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ የጥበብ መንገድ መሆኑን መማር ይገባዋል።—ምሳሌ 6:16-19፤ ዕብራውያን 13:4

      8. ልጆች የጥበብ እርምጃ የሚወስዱት ምን ከተማሩ ነው?

      8 አንድ ልጅ ውስብስብ ስለሆነው አጽናፈ ዓለም፣ ስለተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታት፣ ስለ ወቅቶች መፈራረቅና እነዚህን ስለመሳሰሉ ነገሮች ማወቁ ለጥበቡ አቻ የሌለው ፈጣሪ መኖሩን እንዲገነዘብ ያደርገዋል። (ሮሜ 1:20፤ ዕብራውያን 3:4) ከዚህ በተጨማሪ አምላክ እንደሚወደው፣ ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት የዘላለም ሕይወት የሚያገኝበትን መንገድ እንደከፈተለትና የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅ እርሱን ማስደሰት እንደሚችል መማር ይኖርበታል። ልጁ እንዲህ ያለውን ትምህርት ማግኘቱ፣ ዲያብሎስ እንቅፋት ሊሆንበት ቢጥርም እንኳ ይሖዋን ለማገልገል እንዲወስን ሊያደርገው ይችላል።—ምሳሌ 22:6፤ 27:11፤ ዮሐንስ 3:16

      9. (ሀ) ሕይወት አድን የሆነውን ትምህርት መስጠት ምን ይጠይቃል? (ለ) አባቶች ምን እንዲያደርጉ ታዘዋል? ይህስ ምን ማድረግን ይጨምራል?

      9 አንድ ልጅ ራሱን ከክፉ እንዲጠብቅም ሆነ ትክክል የሆነውን የማድረግ ፍላጎት እንዲያድርበት የሚያስችለውን ትምህርት ማስተማር ጊዜ፣ ትኩረትና እቅድ ማውጣት ይጠይቃል። ወላጆችም የአምላክን አመራር ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን . . . በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” ይላል። (ኤፌሶን 6:4) ይህ ምን ማለት ነው? እዚህ ጥቅስ ላይ “ተግሣጽ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አስተሳሰብን መክተት” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። በመሆኑም አባቶች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ የይሖዋን አስተሳሰብ መክተት አለባቸው ማለት ነው። ይህም ለልጆች ትልቅ ጥበቃ እንደሚሆንላቸው እሙን ነው! የአምላክ አስተሳሰብ በልጆች አእምሮ ላይ መቀረጹ ከመጥፎ ድርጊት እንዲጠበቁ ያደርጋቸዋል።

      ፍላጎታችሁ ከፍቅር የመነጨ መሆን አለበት

      10. ልጆቻችሁን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር ምን ማወቅ ያስፈልጋችኋል?

      10 ይሁን እንጂ ልጆቻችሁን በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ ያላችሁን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ የምታደርጉት ጥረት፣ ከፍቅር የመነጨ መሆን ይኖርበታል። ለዚህ አንዱ አስፈላጊ ነገር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ነው። በልጆቻችሁ ሕይወት ውስጥ ምን እየተከሰተ እንዳለና ምን አመለካከት እንዳላቸው ለመገንዘብ ጥረት አድርጉ። ዘና እንዲሉ በማድረግ በዘዴ የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ አድርጓቸው። አንዳንድ ጊዜ የሚያስደነግጥ ነገር ይነግሯችሁ ይሆናል። ሆኖም ስሜታችሁ እንዳይለዋወጥ ጥንቃቄ አድርጉ። ከዚህ ይልቅ በአዘኔታ ስሜት አዳምጧቸው።

      11. አንድ ወላጅ የአምላክን አስተሳሰብ በልጁ አእምሮ ውስጥ መቅረጽ የሚችለው እንዴት ነው?

      11 እርግጥ ነው፣ ለልጆቻችሁ የጾታ ብልግና መፈጸም የሚከለክለውን የአምላክ ሕግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ደጋግማችሁ አንብባችሁላቸው ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ኤፌሶን 5:5) እንደዚህ ማድረጋችሁ ልጆቻችሁ ይሖዋን ምን እንደሚያስደስተውና እንደሚያሳዝነው በሚገባ እንዲገነዘቡ አድርጓቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የይሖዋን አስተሳሰብ በልጆች አእምሮ ውስጥ መቅረጽ ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ልጆች የይሖዋ ሕግ ያለውን ጠቀሜታ እንዲያገናዝቡ መረዳት ያስፈልጋቸዋል። ሕጎቹ ትክክልና ጠቃሚ ስለመሆናቸው እንዲሁም ሕጎቹን መታዘዝ ተገቢና አስደሳች ስለመሆኑ አሳማኝ ትምህርት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። የአምላክን አስተሳሰብ በልጆቻችሁ አእምሮ ውስጥ ቀርጻችኋል ሊባል የሚችለው፣ ልጆቹ የአምላክን አመለካከት እንዲቀበሉ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅማችሁ በሚገባ ካስረዳችኋቸው ብቻ ነው።

      12. አንድ ወላጅ ልጁ ስለ ጾታ ግንኙነት ተገቢ አመለካከት እንዲኖረው መርዳት የሚችለው እንዴት ነው?

      12 ከልጃችሁ ጋር ስለ ጾታ ጉዳይ ስትነጋገሩ “አንድ ሰው፣ ይሖዋ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት እንዳይደረግ የሰጠውን ሕግ መከተሉ ደስታ የሚያሳጣው ይመስልሃል?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ አበረታቱት። ልጅ ለመውለድ ስለሚያስችለው አስደናቂ የአምላክ ዝግጅት ከነገራችሁት በኋላ “አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ሕግ የሚያወጣው ለምን ይመስልሃል? እኛን ደስታ ለማሳጣት ነው ወይስ ደስተኛ እንድንሆንና ከክፉ እንድንጠበቅ?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። (መዝሙር 119:1, 2፤ ኢሳይያስ 48:17) ልጃችሁ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት እንዳለው ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ከዚያም የጾታ ብልግና መፈጸም ሐዘንና ችግር እንደሚያስከትል የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ልትነግሩት ትችላላችሁ። (2 ሳሙኤል 13:1-33) ልጁን በጥሩ ሁኔታ በማስረዳት የአምላክን አመለካከት እንዲገነዘብና እንዲቀበል የምታደርጉ ከሆነ የአምላክን አስተሳሰብ በአእምሮው ውስጥ ለመቅረጽ የሚያስችለውን ትልቅ እርምጃ ወስዳችኋል ለማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ ሌላም ልታደርጉ የምትችሉት ነገር አለ።

      13. አንድ ልጅ ይሖዋን የመታዘዝ ፍላጎት እንዲያድርበት ምን መማር ይኖርበታል?

      13 ይሖዋን አለመታዘዝ የሚያስከትለውን መዘዝ ብቻ ሳይሆን አኗኗራችን ይሖዋን እንዴት እንደሚነካው ጭምር ለልጆቻችሁ ማስተማራችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋ ፈቃዱን ሳናደርግ ስንቀር ሊያዝንብን እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳዩት። (መዝሙር 78:41) ልጃችሁን “ይሖዋን ማሳዘን የሌለብህ ለምንድን ነው?” ብላችሁ ልትጠይቁትና “የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ይሖዋን የምናገለግለው ስለምንወደው ሳይሆን ለግል ጥቅማችን ብለን እንደሆነ ይከራከራል” በማለት ልታስረዱት ትችላላችሁ። ከዚያም ኢዮብ ከአቋሙ ፍንክች ባለማለት የአምላክን ልብ እንዳስደሰተ፣ በዚህም ሰይጣን ላነሳው የሐሰት ክስ መልስ እንዳስገኘ ልትገልጹለት ትችላላችሁ። (ኢዮብ 1:9-11፤ 27:5) ልጃችሁ በሚያንጸባርቀው ባሕርይ ይሖዋን ሊያሳዝን ወይም ሊያስደስት የሚችል መሆኑን ማወቅ ይገባዋል። (ምሳሌ 27:11) ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅማችሁ ይህንንና ይህን የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለልጆቻችሁ ማስተማር ትችላላችሁ።a

      አርኪ ውጤቶች

      14, 15. (ሀ) ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ ልጆችን ለተግባር ያነሳሱት አንዳንዶቹ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) መጽሐፉን መጠቀምህ ምን ጥሩ ውጤቶች አስገኝቶልሃል? (በገጽ 18ና 19 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

      14 ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለውን ይህን መጽሐፍ ከሰባት ዓመት የልጅ ልጃቸው ጋር ያነበቡ በክሮኤሺያ የሚኖሩ አንድ አያት “እማዬ አንድ ነገር እንድሠራ አዝዛኝ ነበር፤ ሆኖም መጀመሪያ ላይ ያለችኝን ማድረግ አልፈለግሁም ነበር። ከዚያም ‘ታዛዥነት ይጠብቅሃል’ የሚለው ምዕራፍ ትዝ ሲለኝ ተመልሼ ሄድኩና እንደምታዘዛት ነገርኳት” በማለት ልጁ እንደነገራቸው ጽፈዋል። በፍሎሪዳ፣ ዩ ኤስ ኤ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት “መዋሸት የሌለብን ለምንድን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ምዕራፍ ልጆች የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩና ሌላ ጊዜ ቢሆን ኖሮ የሚክዱትን ጥፋት እንዲያምኑ የሚያደርጉ ጥያቄዎችን ያነሳል” በማለት ተናግረዋል።

      15 ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ከ230 የሚበልጡ ሥዕሎች ያሉት ሲሆን ለእያንዳንዱ ሥዕል ለማለት ይቻላል መግለጫ ተሰጥቷል። አንዲት እናት እንዲህ በማለት የተሰማትን አድናቆት ገልጻለች:- “ብዙውን ጊዜ ልጄ አንድ ሥዕል ትኩር ብሎ ስለሚመለከት ገጹን ቶሎ አይገልጥም። ሥዕሎቹ ማራኪ ከመሆናቸውም በላይ ትምህርት ይሰጣሉ፤ ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ ልጆች ጥያቄ እንዲጠይቁ ያነሳሷቸዋል። ልጄ አንድ ትንሽ ልጅ ጨለምለም ባለ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን ሲመለከት የሚያሳየውን ሥዕል ሲያይ፣ ትክክል ያልሆነ ነገር እያደረገ መሆኑን እንደተገነዘበ በሚያሳይ የድምፅ ቃና ‘እማዬ ይህ ልጅ ምን እያደረገ ነው?’ ሲል ጠየቀኝ።” ለሥዕሉ የተሰጠው መግለጫ “የምናደርገውን ሁሉ ማን ያያል?” ይላል።

      ለዘመናችን የሚሆን በጣም አስፈላጊ ትምህርት

      16. በዛሬው ጊዜ ልጆችን ስለ ምን ጉዳይ ማስተማር ያስፈልጋል? ለምንስ?

      16 ልጆች የአካል ክፍሎቻቸውን ተገቢ በሆነ መንገድ እንዴት ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባና በምን ዓይነት መንገድ ቢጠቀሙባቸው ደግሞ ተገቢ እንደማይሆን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ስለ እነዚህ ነገሮች መነጋገር ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። የአንድ ጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ የሆነች አንዲት ሴት የጾታ ብልቶችን በስም መጥራት እንደ ነውር ይታይ በነበረበት ዘመን እንዳደገች ገልጻ “የሚሰማኝን የሃፍረት ስሜት ማሸነፍ ይኖርብኛል” በማለት ልጆቿን ስታስተምር ያጋጠማትን ጽፋለች። በእርግጥም ወላጆች ሃፍረት ተሰምቷቸው ስለ ጾታ ጉዳዮች የማያነሱ ከሆነ ልጆቹ ከአደጋ ሊጠበቁ አይችሉም። አንድ ልጅ ስለ ጾታ ጉዳይ ምንም የማያውቅ መሆኑ በጾታ ለሚያስነውሩ ሰዎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ይህን ርዕሰ ጉዳይ በትክክለኛና ጨዋነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ያነሳል። ልጆችን ስለ ጾታ ጉዳይ ማስተማር የማያውቁትን ነገር አውቀው እንዲበላሹ አያደርጋቸውም፤ እንዲያውም እንዲበላሹ የሚያደርጋቸው አለማወቃቸው ነው።

      17. ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ጾታ ጉዳይ እንዲያስተምሩ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

      17 መጽሐፉ በምዕራፍ 10 ላይ ወደ ምድር ወርደው ልጅ ስለወለዱ ክፉ መላእክት በሚገልጽበት ጊዜ “ስለ ጾታ ግንኙነት ምን የምታውቀው ነገር አለ?” የሚል ጥያቄ ያነሳል። ከዚያም ለዚህ ጥያቄ ቀላልና ጨዋነት የተንጸባረቀበት መልስ ይሰጣል። በምዕራፍ 32 ላይ ደግሞ ልጆች ወሲባዊ ጥቃት ሊፈጽሙባቸው ከሚፈልጉ ሰዎች እንዴት ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ ይናገራል። ለዚህ መጽሐፍ አዘጋጆች የደረሱት በርካታ ደብዳቤዎች እንዲህ ያለው ትምህርት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ። አንዲት እናት “ባለፈው ሳምንት ልጄን ጄቫንን ሐኪም ቤት ይዤው ሄጄ በነበረበት ወቅት ዶክተሯ ስለ አካል ክፍሎቹ ተገቢ የሆነ አጠቃቀም አስተምረነው እንደሆነ ጠየቀችኝ። አዲሱን መጽሐፍ ተጠቅመን እንዳስተማርነው ስታውቅ በጣም ተገረመች” በማለት ጽፋለች።

      18. መጽሐፉ ለባንዲራ ሰላምታ መስጠት ጣዖት አምልኮ መሆኑን የሚያስረዳው እንዴት ነው?

      18 ሌላው ምዕራፍ ደግሞ የባቢሎንን መንግሥት ለሚወክለው ምስል ለመስገድ ፈቃደኛ ስላልሆኑ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ስለተባሉ ዕብራውያን ወጣቶች የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይዟል። (ዳንኤል 3:1-30) ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ እንደሚጠቁመው አንዳንዶች በጣዖት አምልኮና ለባንዲራ ሰላምታ በመስጠት መካከል ያለውን ግንኙነት በግልጽ አያውቁ ይሆናል። ይሁን እንጂ ኤድዋርድ ጋፍኒ የተባሉ ደራሲ ዩ ኤስ ካቶሊክ ከተባለ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ የተናገሩትን ልብ በል። ሴት ልጃቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት ቤት ውላ ስትመለስ “በትምህርት ቤት አንድ አዲስ ጸሎት” እንደተማረች ትነግራቸዋለች፤ እርሳቸውም ጸሎቱን እንድትደግምላቸው ይጠይቋታል። ጋፍኒ ልጅቷ ያደረገችውን አስመልክተው ሲናገሩ “እጅዋን በደረቷ ላይ አደረገችና ኮስተር ብላ ‘ለባንዲራችን ታማኝ ለመሆን ቃል እገባለሁ . . .’ በማለት መዘመር ጀመረች” ብለዋል። አክለውም “ወዲያውኑ አንድ ነገር ብልጭ አለልኝ። ለካስ የይሖዋ ምሥክሮች ትክክል ናቸው። በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ የብሔራዊ ስሜት አምልኮ በልጆች አእምሮ ላይ የሚቀረጸው ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነው፤ ከምንም በላይ ለአገራቸው ታማኝ እንዲሆኑ ትምህርት ይሰጣቸዋል” በማለት ተናግረዋል።

      ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም

      19. ልጆችን ማስተማር ምን ውጤት ያስገኛል?

      19 በእርግጥም ልጆቻችሁን ማስተማር ምንም ያህል ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም። በካንሳስ፣ ዩ ኤስ ኤ የምትኖር አንዲት እናት ከልጅዋ ደብዳቤ ደርሷት ስታነብ እንባዋን መቆጣጠር አልቻለችም። ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነበር:- “በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ የተረጋጋና ሚዛናዊ የሆነ ስሜታዊ አቋም እንዲኖረኝ አድርጋችሁ ስላሳደጋችሁኝ የታደልኩ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል። አንቺም ሆንሽ አባዬ በእርግጥ ልትመሰገኑ ይገባችኋል።” (ምሳሌ 31:28) ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ ሌሎች በርካታ ወላጆች ውድ ለሆኑ ስጦታዎቻቸው አስፈላጊውን ትምህርት በመስጠት ሊደርስባቸው ከሚችለው አደጋ እንዲጠብቋቸው ሊረዳቸው ይችላል።

      20. ወላጆች ሁልጊዜ ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል? ይህስ ምን ያስከትልባቸዋል?

      20 ለልጆቻችን የቻልነውን ያህል ጊዜና ትኩረት ልንሰጣቸው፣ እንዲሁም ልንደክምላቸው ይገባል። በልጅነት የሚያሳልፉት ዕድሜ በጣም አጭር ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በተቻላችሁ መጠን አብራችኋቸው ለመሆንና እነርሱን ለመርዳት ጥረት አድርጉ። እንዲህ በማድረጋችሁ ፈጽሞ አትጸጸቱም። የኋላ ኋላ ይወዷችኋል። ምንጊዜም ቢሆን ልጆቻችሁ የይሖዋ ስጦታዎች መሆናቸውን አስታውሱ። በእርግጥም እንዴት ያሉ ውድ ስጦታዎች ናቸው! (መዝሙር 127:3-5) ስለዚህ እንዴት እንዳሳደጋችኋቸው አምላክ እንደሚጠይቃችሁ በማሰብ ጥሩ እንክብካቤ አድርጉላቸው፤ በእርግጥም በኃላፊነት ትጠየቁበታላችሁ!

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። “አምላክን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 40ን ተመልከት።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ