-
‘የይሖዋ ሕግ’ የጸና ነውመጠበቂያ ግንብ—2004 | ሐምሌ 15
-
-
ብሔራት ያሴራሉ
4. የመዝሙር 2:1, 2ን ዋና ዋና ነጥቦች ተናገር።
4 መዝሙራዊው ሕዝቦችና ገዥዎቻቸው የሚወስዱትን እርምጃ በሚመለከት ያቀናበረውን መዝሙር የከፈተው እንደሚከተለው በማለት ነበር፦ “ሕዝቦች ለምን ያሤራሉ? ሰዎችስ ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ? የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ፣ ሊመክሩ ተሰበሰቡ።”—መዝሙር 2:1, 2a
5, 6. ሰዎች ‘ያውጠነጠኑት ከንቱ ነገር’ ምንድን ነው?
5 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብሔራት ‘የሚያውጠነጥኑት ከንቱ ነገር’ ምንድን ነው? ብሔራት አምላክ የቀባውን ማለትም መሢሑን ወይም ክርስቶስን ከመቀበል ይልቅ ሥልጣናቸውን የሚያራዝሙበትን መንገድ ‘ያውጠነጥናሉ’ ወይም ያሰላስላሉ። በሁለተኛው መዝሙር ላይ የሚገኙት እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአይሁድና የሮማ ገዥዎች ኅብረት ፈጥረው አምላክ ለማንገሥ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን በገደሉበት ጊዜም ፍጻሜአቸውን አግኝተዋል። ይሁን እንጂ በዋነኝነት መፈጸም የጀመሩት ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት በ1914 ነው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በምድር ላይ ያለ አንድም የፖለቲካ መንግሥት አምላክ ለሾመው ንጉሥ እውቅና አልሰጠም።
6 መዝሙራዊው ‘ሰዎች ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ?’ ብሎ ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነበር? ከንቱ የተባለው ዓላማቸው ሲሆን ይህ ዓላማቸው እርባና ቢስና ጠፊ ነው። ለምድር ሰላምና አንድነት ማምጣት አይችሉም። ያም ሆኖ ግን ሰዎች ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ መለኮታዊውን አገዛዝ የሚጻረር እርምጃ ከመውሰድ አይመለሱም። እንዲያውም ልዑሉንና እርሱ የቀባውን ገዥ አምርረው ለመቃወም ተባብረው ይነሳሉ። እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!
ድል አድራጊው ንጉሥ
7. የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መዝሙር 2:1, 2 በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ በጸሎታቸው ላይ የገለጹት እንዴት ነው?
7 የኢየሱስ ተከታዮች መዝሙር 2:1, 2 በእርሱ ላይ እንደተፈጸመ ተናግረዋል። በእምነታቸው ምክንያት ስደት በደረሰባቸው ጊዜ እንዲህ በማለት ጸልየው ነበር፦ “ልዑል ጌታ ሆይ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፤ በመንፈስ ቅዱስም አማካይነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ ተናግረሃል፤ ‘አሕዛብ ለምን በቁጣ ተነሣሡ? ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ? የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ ገዦችም በአንድነት ተሰበሰቡ፤ በጌታ ላይ፣ በተቀባውም ላይ ተከማቹ።’ በእርግጥም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ለማሤር ተሰበሰቡ።” (የሐዋርያት ሥራ 4:24-27፤ ሉቃስ 23:1-12)b አዎን፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምላክ በቀባው አገልጋዩ በኢየሱስ ላይ ሴራ ተጠንስሶ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ይህ መዝሙር ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሌላ ፍጻሜ ይኖረዋል።
8. መዝሙር 2:3 በዚህ ዘመን ባሉ ብሔራትም ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?
8 የጥንቷ እስራኤል፣ ዳዊትን በመሳሰሉ ሰብዓዊ ነገሥታት ትተዳደር በነበረበት ወቅት አረማውያን ብሔራትና ገዥዎቻቸው በአምላክና እርሱ በቀባው ንጉሥ ላይ ተነስተው ነበር። በዘመናችንስ? በዚህ ዘመን ያሉ ብሔራት ይሖዋና መሢሑ የሚፈልጉባቸውን ለማሟላት ፈቃደኛ ስላልሆኑ “ሰንሰለታቸውን እንበጥስ፣ የእግር ብረታቸውንም አውልቀን እንጣል” እንዳሉ ተደርጎ ተገልጿል። (መዝሙር 2:3) ገዥዎችና ሕዝቦች አምላክና እርሱ የሾመው ቅቡዕ የሚጥሉትን ማንኛውንም ማእቀብ ይቃወማሉ። እርግጥ ነው፣ ሰንሰለታቸውን ለመበጠስና የእግር ብረታቸውን ለመጣል ምንም ዓይነት ጥረት ቢያደርጉ አይሳካላቸውም።
-
-
‘የይሖዋ ሕግ’ የጸና ነውመጠበቂያ ግንብ—2004 | ሐምሌ 15
-
-
a በመጀመሪያ ‘መሢሕ’ (የተቀባ) የተባለው ንጉሥ ዳዊት ሲሆን “የምድር ነገሥታት” ደግሞ ሠራዊቶቻቸውን በእርሱ ላይ ያዘመቱ የፍልስጥኤም ገዥዎች ነበሩ።
b በሁለተኛው መዝሙር ላይ የተጠቀሰው፣ አምላክ የሾመው ቅቡዕ ወይም መሢሕ ኢየሱስ መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችም አሉ። መዝሙር 2:7ን ከሐዋርያት ሥራ 13:32, 33፣ ከዕብራውያን 1:5 እና 5:5 ጋር በማወዳደር ይህን በግልጽ ለማየት ይቻላል። በተጨማሪም መዝሙር 2:9ን እና ራእይ 2:27ን ተመልከት።
-