አምላክ ለአንተ እውን ነውን?
የሚያስጨንቁ ነገሮች በሚያጋጥሙህ ጊዜ ቶሎ ብለህ በጸሎት ወደ አምላክ ትቀርባለህን? በምትጸልይበት ጊዜ ከአንድ እውን ከሆነ አካል ጋር እየተነጋገርክ እንዳለህ ሆኖ ይሰማሃል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አባቱን አስመልክቶ ሲናገር “የላከኝ እውነተኛ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 7:28) አዎን፣ ይሖዋ እውን አምላክ ነው፤ በመሆኑም በጸሎት አማካኝነት ወደ እርሱ መቅረብ ከቅርብ ጓደኛችን እርዳታ ወይም ምክር እንደመጠየቅ ያክል ነው። እርግጥ ነው፣ አምላክ ጸሎታችንን እንዲሰማ ከፈለግን የምናቀርበው ጸሎት ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙትን መሥፈርቶች የሚያሟላ መሆን ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነውን አምላክ ራሳችንን ዝቅ አድርገን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መቅረብ አለብን።—መዝሙር 65:2፤ 138:6፤ ዮሐንስ 14:6
አምላክ በዓይን ስለማይታይ አንዳንዶች አካል እንደሌለው አድርገው ያስቡ ይሆናል። አምላክ ለእነርሱ ረቂቅ ነገር ነው። የአምላክን አስደናቂ ባሕርያት የተማሩ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንኳ ሳይቀሩ አንዳንድ ጊዜ የአምላክን እውንነት መረዳት አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል። ሕያው አካል መሆኑን ለመቀበል የሚያዳግታቸው ወቅት አለ። አንተ እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃል? ተሰምቶህ የሚያውቅ ከሆነ ይሖዋ አምላክ እውን እንዲሆንልህ ምን ሊረዳህ ይችላል?
ቅዱሳን ጽሑፎችን አጥና
ቅዱሳን ጽሑፎችን ዘወትር ታጠናለህ? መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር በተመስጦ የምታጠና ከሆነ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እውን እየሆነልህ ይሄዳል። በዚህ መንገድ እምነትህ ይጠናከራል፤ ከዚህም የተነሳ ‘የማይታየው አምላክ እንደሚታይ’ ያክል እውን ይሆንልሃል። (ዕብራውያን 11:6, 27) በሌላው በኩል ደግሞ የማይዘወተር ወይም አልፎ አልፎ ብቻ የሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በእምነትህ ላይ የሚያሳድረው የጎላ ተጽእኖ እንደማይኖር የታወቀ ነው።
በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ሐኪምህ በቆዳህ ላይ የወጣ ቁስል ለማጥፋት በቀን ሁለት ጊዜ የምትቀባው መድኃኒት አዘዘልህ እንበል። መድኃኒቱን በወር አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ብትቀባው ቁስሉ ሊድን የሚችል ይመስልሃል? እንደማይድን የታወቀ ነው። በተመሳሳይም መዝሙራዊው መንፈሳዊ ጤንነታችን ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያደርግ “መድኃኒት አዞልናል።” የአምላክን ቃል “በቀንና በሌሊት” አንብብ። (መዝሙር 1:1, 2) እያደር እየጨመረ የሚሄድ ጥቅም ለማግኘት እንድንችል በክርስቲያን ጽሑፎች በመታገዝ የአምላክን ቃል በመመርመር “የታዘዘልንን መድኃኒት” በየዕለቱ መውሰድ ይኖርብናል።—ኢያሱ 1:8
የምታጠናበትን ክፍለ ጊዜ እምነትህን ይበልጥ የሚያጠነክርልህ እንዲሆን ማድረግ ትፈልጋለህ? የምትፈልግ ከሆነ አንድ ሐሳብ እናካፍልህ:- የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ወይም ማጣቀሻ ያለው ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም አንድ ምዕራፍ ካነበብክ በኋላ አንድ ትኩረት የሚስብ ቁጥር ምረጥና በማጣቀሻው ላይ የሰፈሩትን ጥቅሶች ተመልከት። ይህ ዘዴ ጥናትህን ይበልጥ ከማበልጸጉም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ባለው ስምምነት በጣም ትደነቃለህ። ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ የሆነው ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እውን እንዲሆንልህ ያደርጋል።
ማጣቀሻዎችን መጠቀም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈሩት ትንቢቶችና ፍጻሜዎች ጋር እንድትተዋወቅ ሊረዳህ ይችላል። በባቢሎናውያን ስለ ጠፋችው ስለ ኢየሩሳሌም ውድቀት የሚተርከውን የመሰሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጎላ ብለው የሚጠቀሱ ትንቢቶችን ታውቅ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሳቸው ተዛማጅነት ያላቸው ትንቢቶችንና ፍጻሜዎቻቸውን በውስጡ አካቶ ይዟል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እምብዛም የሚታወቁ አይደሉም።
ለምሳሌ ያህል ኢያሪኮን ማደስ ስለሚያስከትለው ቅጣት የሚናገረውን ትንቢት አንብብና ከዚያም የትንቢቱን ፍጻሜ መርምር። ኢያሱ 6:26 እንዲህ ይላል:- “በዚያን ጊዜም ኢያሱ:- ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኩር ልጁ ይጥፋ፣ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ ብሎ ማለ።” ይህ ትንቢት ከተነገረ ከ500 ዓመት በኋላ ፍጻሜውን ያገኘ ሲሆን በ1 ነገሥት 16:34 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “በእርሱም [በንጉሥ አክዓብ] ዘመን የቤቴል ሰው አኪኤል ኢያሪኮን ሠራ፤ በነዌም ልጅ በኢያሱ እጅ እንደ ተነገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፣ በበኩር ልጁ በአቢሮን መሠረትዋን አደረገ፣ በታናሹ ልጁም በሠጉብ በሮችዋን አቆመ።”a እንዲህ ያለውን ትንቢት ሊናገርና ፍጻሜውንም ሊከታተል የሚችለው እውን የሆነ አምላክ ብቻ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን እያነበብክ ሳለ ስለ አንድ ነጥብ ለማወቅ ጉጉት ያድርብህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አንድ ትንቢት በተነገረበትና ትንቢቱ ፍጻሜውን ባገኘበት ጊዜ መካከል ምን ያክል ዓመታት እንዳለፉ በአእምሮህ ውስጥ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ሌላ ሰው ከመጠየቅ ይልቅ ለምን ራስህ መልሱን ለማግኘት ጥረት አታደርግም? አንድ የተቀበረ ሀብት ፈልጎ ለማግኘት በካርታ የተደገፈ ፍለጋ እንደሚደረግ ሁሉ አንተም ሰንጠረዦችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መርጃ መሣሪያዎችን በመጠቀም መልሶቹን ለማግኘት ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 2:4, 5) መልሶቹን ማግኘትህ በእምነትህ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እውን ይሆንልሃል።
ዘወትር ከልብ በመነጨ ስሜት ጸልይ
የጸሎትንና የእምነትን አስፈላጊነት አቅልለህ አትመልከት። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “እምነት ጨምርልን” በማለት ቀጥታ ጠይቀዋል። (ሉቃስ 17:5) ይሖዋ እውን ሆኖ የማይታይህ ከሆነ ተጨማሪ እምነት እንዲሰጥህ ለምን በጸሎት አትጠይቀውም? ራሱን ለአንተ እውን በማድረግ ይረዳህ ዘንድ የሰማዩ አባትህን ለመጠየቅ አታመንታ።
አእምሮህን የሚያስጨንቅ ችግር ገጥሞህ ከሆነ በቂ ጊዜ ወስደህ ለሰማዩ ወዳጅህ ጭንቀትህን ግልጥልጥ አድርገህ ንገረው። ኢየሱስ ሊሞት በተቃረበበት ወቅት አምርሮ ጸልዮአል። ለታይታ ሲባል ረዥም ጸሎት የማቅረብን ሃይማኖታዊ ልማድ ቢያወግዝም 12ቱን ደቀ መዛሙርቱን ከመምረጡ በፊት ለብቻው ሆኖ አንድ ሙሉ ሌሊት ጸልዮአል። (ማርቆስ 12:38–40፤ ሉቃስ 6:12–16) ከጊዜ በኋላ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ከሆነችው ከሐናም ትምህርት መቅሰም እንችላለን። ወንድ ልጅ ለማግኘት በጣም ጓጉታ ስለነበረ ‘ጸሎትዋን በእግዚአብሔር ፊት አብዝታለች።’—1 ሳሙኤል 1:12
ከዚህ ሁሉ የምንማረው ቁም ነገር ምንድን ነው? ለጸሎትህ መልስ ለማግኘት ተስፋ የምታደርግ ከሆነ ደጋግመህ፣ ከልብ በመነጨ ስሜት፣ ያለማቋረጥ እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መጸለይ አለብህ። (ሉቃስ 22:44፤ ሮሜ 12:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17፤ 1 ዮሐንስ 5:13–15) እንዲህ ማድረግህ አምላክ እውን ሆኖ እንዲታይህ ይረዳሃል።
ፍጥረታትን ተመልከት
የአንድ ሠዓሊ ባሕርይ በሚሥላቸው ሥዕሎች ላይ ሊንጸባረቅ ይችላል። በተመሳሳይም የአጽናፈ ዓለሙ ንድፍ አውጪና ፈጣሪ የሆነው የይሖዋ “የማይታየው ባሕርይ” በፍጥረታቱ ግልጽ ሆኖ ይታያል። (ሮሜ 1:20) ይሖዋ የሠራቸውን ነገሮች ትኩር ብለን በምንመለከትበት ጊዜ ስለ እርሱ ባሕርያት የተሻለ ግንዛቤ እንጨብጣለን፤ ይህ ደግሞ ይሖዋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልን ያደርጋል።
አምላክ የፈጠራቸውን ነገሮች በጥልቀት ብትመረምራቸው በእነዚህ የፍጥረት ሥራዎች ላይ በተንጸባረቁት ባሕርያቱ በጥልቅ መነካትህ አይቀርም። ለምሳሌ ያህል አእዋፍ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በመጓዝ ረገድ ስላላቸው ችሎታ ማወቅ ስለ ይሖዋ ጥበብ ያለህ አድናቆት ይበልጥ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ስለ አጽናፈ ዓለም ስታነብ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ ለማቋረጥ 100,000 የብርሃን ዓመት የሚፈጅ ርቀት ያለው ፍኖተ ሃሊብ በጠፈር ውስጥ በቢልዮን ከሚቆጠሩ ጋላክሲዎች መካከል አንዱ ብቻ መሆኑን ትገነዘባለህ። ታዲያ ይህ ፈጣሪ ያለውን ጥበብ እንድታደንቅ አያደርግህምን?
የይሖዋ ጥበብ እውን ሆኖ የሚታይ ስለመሆኑ ምንም የሚያሻማ ነገር የለም! ታዲያ ይህ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ማንኛችንም ብንሆን በጸሎት አማካኝነት ለምናቀርበው ችግር መፍትሄ ማግኘት እንደማይከብደው ያረጋግጥልናል። አዎን፣ ስለ ፍጥረት የምታውቀው ኢምንት እውቀት እንኳ ይሖዋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልህ ያደርጋል።
አካሄድህን ከይሖዋ ጋር አድርግ
ይሖዋ ለአንተ በግልህ እውን ሊሆንልህ ይችላልን? አዎን፣ በጥንት ጊዜ ይኖር እንደነበረው የእምነት አባት እንደ ኖኅ ሆነህ ከተገኘህ እውን ሊሆንልህ ይችላል። ኖኅ ምንጊዜም ይሖዋን ይታዘዝ ስለነበር “ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” ተብሎ ተነግሮለታል። (ዘፍጥረት 6:9) ኖኅ ይመላለስ የነበረው ልክ ይሖዋ ከጎኑ እንዳለ ያክል ነበር። አምላክ ለአንተም ያንን ያክል እውን ሊሆንልህ ይችላል።
አካሄድህን ከአምላክ ጋር ካደረግህ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሰፈሩት ተስፋዎች ላይ ትታመናለህ፤ እንዲሁም ሕይወትህን ከተስፋዎቹ ጋር አስማምተህ ትመራለህ። ለምሳሌ ያህል “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ [አስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮች] ይጨመርላችኋል” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ታምናለህ። (ማቴዎስ 6:25-33) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የሚያስፈልጉህን ነገሮች ሁልጊዜ አንተ በጠበቅከው መንገድ ላይሰጥህ ይችላል። ሆኖም ጸልየህ የአምላክን እርዳታ ስታገኝ ልክ ከጎንህ እንዳለ አንድ ሰው እውን ይሆንልሃል።
አንድ ሰው አካሄዱን ከአምላክ ጋር ማድረጉን በቀጠለ መጠን ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁማ ያለፈችውን የስፓንኛ ቋንቋ ተናጋሪ የይሖዋ ምሥክር የሆነችውን የማንዌላን ሁኔታ ተመልከት። እንዲህ ትላለች:- “ችግር በሚያጋጥመኝ ወይም እርዳታ በሚያስፈልገኝ ጊዜ በምሳሌ 18:10 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በተግባር ላይ አውላለሁ። ለእርዳታ ወደ ይሖዋ እሮጣለሁ። ይሖዋ ምንጊዜም ‘ጽኑ መሸሸጊያዬ’ ነው።” ማንዌላ ለ36 ዓመታት በይሖዋ ላይ ከተደገፈችና የእርሱን እርዳታ ከቀመሰች በኋላ ይህን ለመናገር ችላለች።
ይሖዋን መታመኛህ ማድረግን የጀመርከው በቅርብ ጊዜያት ነውን? ከእርሱ ጋር የመሠረትከው ወዳጅነት አንተ የፈለግከውን ያህል ባይሆን ተስፋ አትቁረጥ። በእያንዳንዱ ቀን ከአምላክ ጋር መመላለስህን ቀጥል። በታማኝነት ላይ የተመሠረተ የአኗኗር መንገድ በተከተልክ መጠን ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ትመሠርታለህ።—መዝሙር 25:14፤ ምሳሌ 3:26, 32
አካሄድክን ከአምላክ ጋር ማድረግ የምትችልበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ በአገልግሎቱ በሙሉ ነፍስ መካፈል ነው። በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ስትካፈል የይሖዋ የሥራ ባልደረባ ትሆናለህ። (1 ቆሮንቶስ 3:9) ይህን መገንዘብህ አምላክ እውን እንዲሆንልህ ይረዳሃል።
መዝሙራዊው “መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፣ በእርሱም ታመን፣ እርሱም ያደርግልሃል” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። (መዝሙር 37:5) ማንኛውንም ሸክምህን ወይም ጭንቀትህን በአምላክ ላይ ከመጣል ወደኋላ አትበል። እርዳታና መመሪያ ለማግኘት ዘወትር ወደ እርሱ ዘወር በል። በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ አምላክ ላይ የምትደገፍና ሙሉ በሙሉ በእርሱ የምትታመን ከሆነ እርሱ አንተን የሚጠቅምህን ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል ስለምታውቅ ያለ ሥጋት ትኖራለህ። የሚያስጨንቁህን ነገሮች ይዘህ ወደ ይሖዋ በምትቀርብበት ጊዜ እንደሚሰማህ እርግጠኛ ነህን? አምላክ እውን ከሆነልህ እርግጠኛ ትሆናለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ምሳሌ ለመመልከት ያክል ደግሞ 1 ነገሥት 13:1–3 ላይ የሰፈረውን ስለ ኢዮርብዓም መሠዊያ መርከስ የሚናገረውን ትንቢት አንብብ። ከዚያም በ2 ነገሥት 23:16–18 ላይ የተመዘገበውን የትንቢቱን አፈጻጸም ተመልከት።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥናትህ ክፍለ ጊዜ እምነት የሚያጠነክር ይሁን
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዘወትር ከልብ በመነጨ ስሜት ለመጸለይ ጊዜ መድብ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአምላክ ባሕርያት በፍጥረት ሥራዎች ላይ እንዴት እንደሚንጸባረቁ ተመልከት
[ምንጮች]
Hummingbird: U.S. Fish and Wildlife Service, Washington, D.C./Dean Biggins; stars: Photo: Copyright IAC/RGO 1991, Dr. D. Malin et al, Isaac Newton Telescope, Roque de los Muchachos Observatory, La Palma, Canary Islands