-
አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ምንድን ነው?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 25
አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ሕይወት “አጭርና በመከራ የተሞላ” እንደሆነ ይናገራል። (ኢዮብ 14:1) በእርግጥ አምላክ የፈጠረን እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንድንኖር ነው? ካልሆነስ አምላክ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሕይወት እንድንኖር ነው? አምላክ በሚፈልገው መንገድ የምንኖርበት ጊዜስ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ማወቅህ ያጽናናሃል።
1. ይሖዋ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሕይወት እንድንኖር ነው?
ይሖዋ አስደሳች ሕይወት እንድንኖር ይፈልጋል። የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ኤደን ገነት ተብሎ በሚጠራ ውብ የአትክልት ቦታ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ከዚያም “አምላክ ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም።’” (ዘፍጥረት 1:28) ይሖዋ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ፣ መላዋን ምድር ገነት እንዲያደርጉና እንስሳቱን እንዲንከባከቡ ይፈልግ ነበር። ዓላማው ሁሉም ሰዎች ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር።
በዛሬው ጊዜ ያለን ሕይወት ከዚህ የተለየ ቢሆንምa የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም። (ኢሳይያስ 46:10, 11) አሁንም ቢሆን ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ከችግር ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል።—ራእይ 21:3, 4ን አንብብ።
2. በዛሬው ጊዜ አስደሳች ሕይወት መምራት የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ የፈጠረን ‘መንፈሳዊ ፍላጎት’ ማለትም እሱን የማወቅና የማምለክ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። (ማቴዎስ 5:3-6ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት፣ ‘በመንገዶቹ ሁሉ እንድንሄድ፣ እንድንወደው’ እንዲሁም ‘በሙሉ ልባችን እንድናገለግለው’ ይፈልጋል። (ዘዳግም 10:12፤ መዝሙር 25:14) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ችግሮች ቢያጋጥሙንም እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንችላለን። ይሖዋን ማምለክ ሕይወታችን ትርጉም ያለውና አስደሳች እንዲሆንልን ያደርጋል።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ይሖዋ ምድርን ለእኛ ምቹ መኖሪያ እንድትሆን አድርጎ ያዘጋጀበት መንገድ ታላቅ ፍቅሩን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን፤ በተጨማሪም የአምላክ ቃል ስለተፈጠርንበት ዓላማ ምን እንደሚል እንመረምራለን።
3. ይሖዋ ሰዎች ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ ይፈልጋል
ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
አምላክ ውብ የሆነችውን ምድራችንን የፈጠረው ለምንድን ነው?
መክብብ 3:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይህ ጥቅስ ይሖዋ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ምን ያስተምርሃል?
4. የይሖዋ ዓላማ አልተለወጠም
መዝሙር 37:11, 29ን እንዲሁም ኢሳይያስ 55:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ለእኛ ያለው ዓላማ እንዳልተለወጠ በምን እናውቃለን?
በአግባቡ ባለመያዙ ምክንያት የፈራረሰ ቤት መልሶ ሊታደስ እንደሚችል ሁሉ አምላክም የሰው ዘር ያበላሻትን ምድር መልሶ ያድሳታል። ከዚያም እሱን የሚወዱ ሰዎች በምድር ላይ እንዲኖሩ ያደርጋል
5. ይሖዋን ማምለካችን ዓላማ ያለው ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል
የተፈጠርንበትን ዓላማ ማወቃችን ደስተኛ እንድንሆን ያደርገናል። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ቴሩሚ የተፈጠርንበትን ዓላማ ማወቋ የጠቀማት እንዴት ነው?
መክብብ 12:13ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ብዙ ነገሮችን አድርጎልናል፤ ታዲያ እኛ በምላሹ ምን ልናደርግ ይገባል?
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የተፈጠርንበት ዓላማ ምንድን ነው?”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ማጠቃለያ
ይሖዋ ከማንኛውም ችግር ነፃ ሆነን በምድር ላይ ለዘላለም እንድንኖር ይፈልጋል። በሙሉ ልባችን እሱን ስናመልከው በዛሬው ጊዜም እንኳ አስደሳች ሕይወት መምራት እንችላለን።
ክለሳ
ይሖዋ አዳምና ሔዋን ምን ዓይነት ሕይወት እንዲኖሩ ይፈልግ ነበር?
አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ እንዳልተለወጠ በምን እናውቃለን?
ሕይወትህ አስደሳችና ትርጉም ያለው እንዲሆን ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
ምርምር አድርግ
ኤደን ገነት አፈ ታሪክ ሳይሆን በትክክል የነበረ ቦታ እንደሆነ የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉ?
ምድር እንደማትጠፋ እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርገን ምክንያት ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለተፈጠርንበት ዓላማ ምን ይላል?
ሁሉ ነገር እንዳለው ያስብ የነበረ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የጎደለው ነገር እንዳለ ያወቀው እንዴት ነው?
a ይህ የሆነበትን ምክንያት በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።
-
-
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
2. ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት እነማን ናቸው?
ኢየሱስ የሚገዛው ብቻውን አይደለም። “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ” የተውጣጡ ሰዎች ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።’ (ራእይ 5:9, 10) ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት ሰዎች ምን ያህል ናቸው? ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ ወዲህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች የእሱ ተከታዮች ሆነዋል። ሆኖም ወደ ሰማይ ሄደው ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት 144,000 የሚያህሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። (ራእይ 14:1-4ን አንብብ።) በምድር ላይ የሚቀሩት ሌሎች ክርስቲያኖች በሙሉ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ይሆናሉ።—መዝሙር 37:29
-
-
የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?
የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀምሯል። በቅርቡ በምድር ላይ ሥር ነቀል ለውጦችን ያደርጋል። እስቲ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የምታገኛቸውን አንዳንድ በረከቶች እንመልከት።
1. የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያደርገው እንዴት ነው?
የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ ክፉ ሰዎችንና መንግሥታትን ያጠፋል። (ራእይ 16:14, 16) በዚያ ወቅት “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። (መዝሙር 37:10) ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት በመላዋ ምድር ላይ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል።—ኢሳይያስ 11:4ን አንብብ።
2. የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ በሚፈጸምበት ጊዜ ምን ዓይነት ሕይወት ይኖረናል?
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) ክፉዎች በሌሉበት እንዲሁም ይሖዋን የሚወዱና እርስ በርስ የሚዋደዱ ሰዎች ብቻ ባሉበት ዓለም ውስጥ መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው! በሕመም የሚሠቃይ ሰው አይኖርም፤ ሁሉም ሰው ለዘላለም ይኖራል።
3. ክፉዎች ከጠፉ በኋላ የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?
ክፉዎች ከጠፉ በኋላ ኢየሱስ ለ1,000 ዓመት ያህል ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። በዚያ ወቅት ኢየሱስና አብረውት የሚገዙት 144,000 ገዢዎች፣ ሰዎች ፍጹምና ከኃጢአት ነፃ እንዲሆኑ ይረዳሉ። የሺህ ዓመቱ ግዛት መጨረሻ ላይ ምድር የይሖዋን ሕጎች በሚታዘዙ ደስተኛ ሰዎች የተሞላች ውብ ገነት ትሆናለች። ከዚያም ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ ለይሖዋ ያስረክባል። የይሖዋ ስም ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ ‘ይቀደሳል።’ (ማቴዎስ 6:9, 10) ይሖዋ ለተገዢዎቹ የሚያስብ ጥሩ ገዢ እንደሆነ ይረጋገጣል። ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንንና አጋንንቱን ጨምሮ በእሱ አገዛዝ ላይ የሚያምፁትን ሁሉ ያጠፋል። (ራእይ 20:7-10) የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸው በረከቶች ለዘላለም ይቀጥላሉ።
ጠለቅ ያለ ጥናት
አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚፈጽም እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።
4. የአምላክ መንግሥት የሰዎችን አገዛዝ ያስወግዳል
“ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 8:9) ይሖዋ በፍትሕ መጓደል ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን በመንግሥቱ አማካኝነት ያስተካክላል።
ዳንኤል 2:44ን እና 2 ተሰሎንቄ 1:6-8ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ ሰዎች በሚያስተዳድሯቸው መንግሥታትና በደጋፊዎቻቸው ላይ ምን እርምጃ ይወስዳሉ?
ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ የተማርከው ነገር እነሱ የሚወስዱት እርምጃ ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደሆነ እንድትተማመን የሚያደርግህ እንዴት ነው?
5. ኢየሱስ ከሁሉ የተሻለ ንጉሥ ነው
ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ ላሉ ተገዢዎቹ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ያከናውናል። ኢየሱስ ከዚህ በፊት ያደረጋቸው ነገሮች እንዲህ ለማድረግ ፍላጎቱ እንዳለውና አምላክም ኃይል እንደሰጠው ያሳያሉ። ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ቪዲዮው ላይ ተመልከቱ።
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአምላክ መንግሥት ወደፊት የሚያከናውናቸውን ነገሮች በጥቂቱም ቢሆን አሳይቷል። አንተ በግልህ እዚህ ላይ ከተዘረዘሩት ነገሮች መካከል የትኛው ሲፈጸም ለማየት ትጓጓለህ? ከእያንዳንዱ ተስፋ ጋር አብረው የተጠቀሱትን ጥቅሶች አንብቡ።
ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ . . .
ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ . . .
የአየሩን ጠባይ ተቆጣጥሯል።—ማርቆስ 4:36-41
በፕላኔቷ ምድራችን ላይ የደረሰውን ጉዳት ያስተካክላል።—ኢሳይያስ 35:1, 2
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መግቧል።—ማቴዎስ 14:17-21
ከዓለም ላይ ረሃብን ያስወግዳል።—መዝሙር 72:16
ብዙዎችን ከሕመማቸው ፈውሷል።—ሉቃስ 18:35-43
ሁሉም ሰው ፍጹም ጤንነት እንዲኖረው ያደርጋል።—ኢሳይያስ 33:24
የሞቱ ሰዎችን አስነስቷል።—ሉቃስ 8:49-55
ሞትን ያስወግዳል፤ የሞቱትን ያስነሳል።—ራእይ 21:3, 4
6. የአምላክ መንግሥት ወደፊት አስደሳች ጊዜ ያመጣል
የአምላክ መንግሥት ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው የመጀመሪያ ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ያደርጋል። ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት ዓላማውን ዳር ለማድረስ እየሠራ ያለው እንዴት እንደሆነ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ።
መዝሙር 145:16ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ሁላችንም ተባብረን ከሠራን የዓለማችንን ችግሮች ማስወገድ እንችላለን።”
ሰዎች ከሚያስተዳድሯቸው መንግሥታት አቅም በላይ የሆኑ ሆኖም የአምላክ መንግሥት የሚያስወግዳቸው ችግሮች የትኞቹ ናቸው?
ማጠቃለያ
የአምላክ መንግሥት ዓላማውን ዳር ያደርሳል። መላዋ ምድር ይሖዋን ለዘላለም በሚያመልኩ ጥሩ ሰዎች እንድትሞላና ገነት እንድትሆን ያደርጋል።
ክለሳ
የአምላክ መንግሥት የይሖዋ ስም እንዲቀደስ የሚያደርገው እንዴት ነው?
የአምላክ መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ተስፋዎች እንዲፈጸሙ እንደሚያደርግ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
የአምላክ መንግሥት ከሚያመጣቸው በረከቶች መካከል አንተ ለማየት የምትጓጓው የትኛውን ነው?
ምርምር አድርግ
‘አርማጌዶን’ የሚለው ቃል ምን ያመለክታል?
ኢየሱስ “ታላቅ መከራ” ብሎ በጠራው ወቅት ምን ነገሮች ይከናወናሉ?—ማቴዎስ 24:21
የአምላክ መንግሥት ወደፊት በሚያመጣቸው በረከቶች ላይ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ማሰላሰል የሚቻለው እንዴት ነው?
“አእምሮዬን የሚረብሹ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ” በሚለው ርዕስ ሥር ዓማፂ የነበረ አንድ ሰው ለጥያቄዎቹ መልስ ያገኘው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።
-