ከፍተኛና አነስተኛ የብርሃን ብልጭታዎች (ክፍል ሁለት)
“በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን።”—መዝሙር 36:9
1. ቀደም ሲል የራእይን መጽሐፍ ምሳሌያዊ አገላለጽ ለመረዳት ምን ጥረት ተደርጎ ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ከጥንት ጀምሮ የክርስቲያኖችን ትኩረት ሲስብ ቆይቷል። የእውነት ብርሃን እንዴት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ እንደሄደ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። የይሖዋ ሕዝቦች የራእይን መጽሐፍ የሚያብራራ ያለቀለት ምሥጢር የተባለ መጽሐፍ በ1917 አሳተሙ። ይህ መጽሐፍ የሕዝበ ክርስትናን ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መሪዎች በድፍረት የሚያጋልጥ ነበር፤ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ማብራሪያዎች ከተለያዩ ምንጮች የተወሰዱ ነበሩ። ሆኖም ያለቀለት ምሥጢር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋ እየተጠቀመበት ለነበረው የሚታይ የመገናኛ መስመር የነበራቸውን ታማኝነት ለመፈተን አገልግሎ ነበር።
2. “የአንድ ሕዝብ መወለድ” የተባለው ርዕስ በራእይ መጽሐፍ ላይ ምን ብርሃን ፈንጥቆ ነበር?
2 በመጋቢት 1, 1925 የወጣው መጠበቂያ ግንብ ላይ “የአንድ ሕዝብ መወለድ” የሚል ርዕስ ሲወጣ በራእይ መጽሐፍ ላይ አስደናቂ የብርሃን ብልጭታ ፈነጠቀ። ራእይ ምዕራፍ 12 የሚገልጸው በአረማዊው የሮም መንግሥትና በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል የሚደረገውን ጦርነት እንደሆነና ወንዱ ልጅ ጵጵስናን እንደሚያመለክት ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ሆኖም ይህ ርዕስ ራእይ 11:15–18 ስለ አምላክ መንግሥት መወለድ እንደሚናገር በመጠቆም በትርጉም ደረጃ ከምዕራፍ 12 ጋር ግንኙነት እንዳለው አሳይቷል።
3. በራእይ መጽሐፍ ላይ ተጨማሪ ብርሃን የፈነጠቁት የትኞቹ ጽሑፎች ናቸው?
3 ይህ ሁሉ የራእይ መጽሐፍን ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ ለመረዳት አስችሏል፤ ይህም በ1930 ብርሃን በተባለ ሁለት ጥራዞች ባሉት መጽሐፍ ላይ ታትሞ ወጥቷል። ከዚያም “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች!” የአምላክ መንግሥት ትገዛለች! (1963) እና “ከዚያ በኋላ የአምላክ ምሥጢር ተፈጸመ” (1969) በተባሉት መጻሕፍት ላይ ተጨማሪ ማሻሻያዎች ወጡ። ሆኖም ስለ ትንቢታዊው የራእይ መጽሐፍ መታወቅ የነበረባቸው ሌሎች ነገሮች ነበሩ። አዎን፣ በ1988 ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለው መጽሐፍ ሲወጣ ይበልጥ ቦግ ያለ ብርሃን ወጣ። ለዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የእውቀት ብርሃን ቁልፉ የራእይ ትንቢት በ1914 በጀመረው “በጌታ ቀን” ውስጥ የሚፈጸም መሆኑ ነው ሊባል ይችላል። (ራእይ 1:10) ስለዚህ ይህ የጌታ ቀን እየገፋ ሲሄድ የራእይን መጽሐፍ ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ መረዳት ይቻላል።
“ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት” እነማን እንደሆኑ ተብራራ
4, 5. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለ ሮሜ 13:1 ምን አመለካከት ነበራቸው? (ለ) “ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት” ያላቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ቦታ በተመለከተ ቆየት ብሎ ምን ማስተዋል ተገኝቶ ነበር?
4 በ1962 “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች [“ለከፍተኛ ባለ ሥልጣናት” ኪንግ ጀምስ ቨርሽን] ይገዛ” ከሚለው ከሮሜ 13:1 ጋር በተያያዘ መንገድ ደማቅ የብርሃን ብልጭታ ታየ። የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ ጥቅስ ላይ “ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት” ተብለው የተጠቀሱት ዓለማዊ ባለ ሥልጣናት እንደሆኑ ተረድተው ነበር። ይህን ጥቅስ የተረዱት አንድ ክርስቲያን በጦርነት ወቅት ለወታደርነት ከተመለመለ የደንብ ልብስ ለመልበስ፣ ጠመንጃ ለማነገትና ወደ ጦር ግንባር ዘምቶ ምሽግ ለመያዝ ይገደዳል ማለት እንደሆነ አድርገው ነበር። አንድ ክርስቲያን ሰዎችን መግደል ስለማይችል ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር ካጋጠመው ወደ ሰማይ ለመተኮስ ይገደዳል የሚል ስሜት ነበራቸው።a
5 የኅዳር 15 እና የታኅሣሥ 1, 1962 መጠበቂያ ግንብ በማቴዎስ 22:21 ላይ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት በማብራራት በዚህ ጉዳይ ላይ ብሩህ የሆነ ብርሃን ፈንጥቋል። “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚሉት በሥራ 5:29 ላይ የሚገኙት የሐዋርያት ቃላት ከዚህ ጋር ይስማማሉ። ክርስቲያኖች ለቄሣር ማለትም “ለከፍተኛ ባለ ሥልጣናት” የሚገዙት ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጻረር ነገር እስካልተጠየቁ ድረስ ነው። ለቄሣር የምንገዛው በአንፃራዊ መንገድ እንጂ ሙሉ በሙሉ እንዳልሆነ ተስተውሎ ነበር። ክርስቲያኖች የቄሣርን ለቄሣር የሚከፍሉት ነገሩ አምላክ ካወጣቸው ብቃቶች ጋር ካልተጋጨ ብቻ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ ማስተዋል ማግኘት ምንኛ የሚያስደስት ነበር!
በድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ የፈነጠቁ የብርሃን ብልጭታዎች
6. (ሀ) በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ተስፋፍቶ ከሚገኘው ዓይነት የሥልጣን መዋቅር ለመራቅ ምን መሠረታዊ ሥርዓት መጠቀም ተጀምሮ ነበር? (ለ) በመጨረሻ ለጉባኤው የበላይ ጥበቃ እንዲያደርጉ የሚመረጡ ሰዎችን በተመለከተ ምን ግንዛቤ ተገኘ?
6 በጉባኤ ውስጥ እነማን ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሆነው ማገልገል እንዳለባቸው ጥያቄ ተነሥቶ ነበር። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ተስፋፍቶ ከሚገኘው የሥልጣን መዋቅር ለመራቅ ሲባል እያንዳንዱ ጉባኤ እነዚህን አገልጋዮች በአባሎቹ ድምፅ ብልጫ በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲመርጣቸው ተወስኖ ነበር። ይሁን እንጂ በመስከረም 1 እና ጥቅምት 15, 1932 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው እየጨመረ የሄደ ብርሃን ሽማግሌዎችን በድምፅ ብልጫ መምረጥን የሚደግፍ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት እንደሌለ ጠቆመ። ስለዚህ እነዚህ ሽማግሌዎች በአንድ የአገልግሎት ኮሚቴ ተተኩና ማኅበሩ አንድ የአገልግሎት ዲሬክተር መምረጥ ጀመረ።
7. የፈነጠቁት የብርሃን ብልጭታዎች የጉባኤ አገልጋዮች በሚሾሙበት መንገድ ላይ ምን ማሻሻያዎች እንዲደረጉ አስ ችሏል?
7 በሰኔ 1 እና በሰኔ 15, 1938 የወጣው መጠበቂያ ግንብ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አገልጋዮች መሾም ማለትም በቲኦክራሲያዊ መንገድ መሾም እንጂ መመረጥ እንደሌለባቸው የሚጠቁሙ የብርሃን ብልጭታዎች ፈንጥቆ ነበር። በ1971 የወጣ ሌላ የብርሃን ብልጭታ እያንዳንዱ ጉባኤ በአንድ የጉባኤ አገልጋይ ብቻ መመራት እንደሌለበት ጠቆመ። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ጉባኤ በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል የተሾመ አንድ የሽማግሌዎች ወይም የበላይ ተመልካቾች አካል ሊኖረው እንደሚገባ ተገለጸ። ስለዚህ ከ40 ለሚልቁ ዓመታት ያህል እየጨመረ በመጣው ብርሃን ሳቢያ ሽማግሌዎችም ሆኑ ዲያቆናት በአስተዳደር አካሉ በኩል “በታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት መሾም እንዳለባቸው ታወቀ። (ማቴዎስ 24:45–47) ይህ በሐዋርያት ዘመን ይፈጸም ከነበረው ጋር የሚስማማ ነበር። እንደ ጢሞቴዎስና ቲቶ ያሉት ወንዶች የበላይ ተመልካቾች ሆነው የተሾሙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 3:1–7፤ 5:22፤ ቲቶ 1:5–9) ይህ ሁሉ ላይ “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም [“የበላይ ተመልካቾችሽንም” አዓት] ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ” የሚለው የኢሳይያስ 60:17 ትንቢት አስደናቂ ፍጻሜ ነው።
8. (ሀ) እየጨመረ የመጣው እውነት በማኅበሩ አሠራር ላይ ምን ማሻሻያዎች እንዲደረጉ አስችሏል? (ለ) የአስተዳደር አካል ኮሚቴዎች የትኞቹ ናቸው? እያንዳንዳቸው ያላቸው ተግባር ወይም በበላይነት የሚመሩት ነገር ምንድን ነው?
8 በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አሠራር በኩልም ብርሃን ፈንጥቋል። ለብዙ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል ከፔንሲልቫንያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የዲሬክተሮች ቦርድ ተነጥሎ የማይታይና አብዛኞቹ ጉዳዮች የሚያዙት በፕሬዘዳንቱ ነበር። በ1977 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (ገጽ 258–9) ላይ እንደተገለጸው ከ1976 ጀምሮ የአስተዳደር አካሉ በስድስት ኮሚቴዎች መሥራት ጀመረ፤ እያንዳንዱ ኮሚቴ የዓለም አቀፉን ሥራ የተወሰኑ ተግባሮች እንዲያከናውን ተመድቧል። ፐርሶኔል ኮሚቴ የግለሰቦችን ጉዳይ ይከታተላል፤ ይህም በመላው ዓለም የቤቴል ቤተሰብ ውስጥ የሚያገለግሉትን ይጨምራል። የኅትመት ኮሚቴ ንብረትንና ኅትመትን የመሳሰሉት ሃይማኖታዊ ያልሆኑና ሕጋዊ ጉዳዮችን የማከናወን ኃላፊነት አለው። የአገልግሎት ኮሚቴ የምሥክርነቱን ሥራ ይከታተላል፤ የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ የአቅኚዎችንና የጉባኤ አስፋፊዎችን ሥራ ይከታተላል። የትምህርት ኮሚቴ የጉባኤ ስብሰባዎችን እንዲሁም የልዩ ስብሰባ ቀናትን፣ የወረዳ ስብሰባን፣ የአውራጃና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎችንም ሆነ ለአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ትምህርት የሚሰጡ ልዩ ልዩ ትምህርት ቤቶችን ይከታተላል። የጽሑፍ አዘጋጅ ኮሚቴ ሁሉም ነገር ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚስማማ መሆኑን በማረጋገጥ የሁሉንም ጽሑፎች ዝግጅትና የትርጉም ሥራ ይቆጣጠራል። የሊቀመንበሩ ኮሚቴ ድንገት የሚያጋጥሙ ችግሮችንና ሌሎች አስቸኳይ ጉዳዮችን ይከታተላል።b በተጨማሪም ከ1970ዎቹ ዓመታት አንሥቶ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮዎች በአንድ የበላይ ተመልካች ከመመራት ይልቅ በኮሚቴ መመራት ጀምረዋል።
ከክርስቲያናዊ ጠባይ ጋር የሚዛመድ ብርሃን
9. የእውነት ብርሃን ክርስቲያኖች ከዓለም መንግሥታት ጋር ያላቸውን ግንኙነት የነካው እንዴት ነው?
9 ክርስቲያናዊ ጠባይን የሚመለከቱ ብዙ የብርሃን ብልጭታዎች ፈንጥቀዋል። ለምሳሌ ያህል የገለልተኝነትን ጉዳይ እንውሰድ። በተለይ “ገለልተኝነት” በሚል ርዕስ በኅዳር 1, 1939 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው ትምህርት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ደማቅ ብርሃን ፈንጥቆ ነበር። ይህ ብርሃን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ በኋላ መገለጡ ምንኛ ወቅታዊ ነበር! ይህ ርዕስ ለገለልተኝነት ፍቺ ሰጠና ክርስቲያኖች በፖለቲካዊ ጉዳዮችና በብሔራት መካከል በሚደረጉት ግጭቶች ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው ጠቆመ። (ሚክያስ 4:3, 5፤ ዮሐንስ 17:14, 16) ይህም ክርስቲያኖች በመላው ዓለም በሚገኙ ብሔራት ዘንድ እንዲጠሉ አድርጓቸዋል። (ማቴዎስ 24:9) ኢየሱስ በማቴዎስ 26:52 ላይ ግልጽ እንዳደረገው የጥንት እስራኤላውያን ያካሄዷቸው ውጊያዎች ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌ ሊሆኑ አይችሉም። ከዚህም በላይ እንደ ጥንቷ እስራኤል በቲኦክራሲ ማለትም በአምላክ የሚገዛ አንድም ፖለቲካዊ ብሔር የለም።
10. የፈነጠቁት የብርሃን ብልጭታዎች ክርስቲያኖች ደምን በምን ዓይነት መንገድ ሊመለከቱት እንደሚገባ ገልጠዋል?
10 በደም ቅድስና ላይም ብርሃን ፈንጥቋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሥራ 15:28, 29 ላይ ያለው ደም መብላትን የሚከለክለው ሕግ ለአይሁድ ክርስቲያኖች ብቻ የሚሠራ ሕግ ነው ብለው ያስቡ ነበር። ይሁን እንጂ በሐዋርያት ዘመን ባመኑት አሕዛብ ላይም ይህ ትእዛዝ ይሠራ እንደነበር ሥራ 21:25 ያሳያል። ስለዚህ በሐምሌ 1, 1945 መጠበቂያ ግንብ ላይ እንደተገለጸው የደም ቅድስና በሁሉም ክርስቲያኖች ላይ ይሠራል። ይህም ማለት ከሥጋ ጋር ተቀላቅሎ የሚዘጋጀውን ዓይነት የእንስሳ ደም የሚቀላቀልባቸውን ምግቦች ከመብላት መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ደምን በደም ሥር ባለ መውሰድ ጭምር ከሰው ደም መራቅ ማለት ነው።
11. ክርስቲያኖች ትንባሆ ማጨስን በተመለከተ ሊኖራቸው ስለሚገባው አመለካከት ምን ተስተውሎ ነበር?
11 ብርሃኑ እየጨመረ በመምጣቱ ሳቢያ ቀደም ሲል እንዲሁ ይጠሉ የነበሩ ልማዶች የኋላ ኋላ ፈጽሞ መደረግ የሌለባቸው ነገሮች ተደርገው መታየት ጀመሩ። ለዚህ አንዱ ምሳሌ ሲጋራ ስለ ማጨስ የነበረው አመለካከት ነው። በነሐሴ 1, 1895 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ወንድም ራስል በ1 ቆሮንቶስ 10:31 እና በ2 ቆሮንቶስ 7:1 ላይ በማተኮር “አንድ ክርስቲያን ትንባሆን በማንኛውም ዓይነት መልኩ መጠቀሙ ለአምላክ ክብር የሚያመጣበትና ለራሱ ለተጠቃሚው ጥቅም የሚያስገኝበት መንገድ አይታየኝም” ሲል ጽፎ ነበር። ከ1973 ጀምሮ ማንኛውም የትንባሆ አጫሽ የይሖዋ ምሥክር ሊሆን እንደማይችል በግልጽ ተስተዋለ። በ1976 ማንኛውም የይሖዋ ምሥክር በቁማር ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሠራ በጉባኤው ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ ተደረገ።
ሌሎች ማሻሻያዎች
12. (ሀ) የፈነጠቀው የብርሃን ብልጭታ ጴጥሮስ ስለተሰጡት የመንግሥቱ ቁልፎች ቁጥር የገለጠው ምን ነበር? (ለ) ጴጥሮስ እያንዳንዱን ቁልፍ ሲጠቀም የነበሩት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
12 ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ለጴጥሮስ በሰጠው ምሳሌያዊ ቁልፎች ቁጥር ረገድ ተጨማሪ ብርሃን ፈንጥቆ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጴጥሮስ ሰዎች የመንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ መንገድ የከፈቱ ሁለት ቁልፎች ተቀብሎ ነበር፤ አንዱ በ33 እዘአ ለአይሁዶች የተጠቀመበት ሲሆን ሌላውን ደግሞ ለቆርኔሌዎስ ሲሰብክ በ36 እዘአ ተጠቅሞበታል የሚል እምነት ነበራቸው። (ሥራ 2:14–41፤ 10:34–48) ከጊዜ በኋላ ግን ሌላ ሦስተኛ ቡድን ማለትም ሳምራውያንም ጭምር እንዳሉበት ተስተዋለ። ጴጥሮስ ሁለተኛውን ቁልፍ የተጠቀመው ወደ መንግሥቱ የመግባት አጋጣሚ ለሳምራውያን በከፈተላቸው ወቅት ነበር። (ሥራ 8:14–17) ስለዚህ ጴጥሮስ ሦስተኛውን ቁልፍ የተጠቀመበት ለቆርኔሌዎስ በሰበከበት ወቅት ነበር።—ጥቅምት 1, 1979 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16–22, 26
13. የፈነጠቁት የብርሃን ብልጭታዎች በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ላይ ስለ ተጠቀሱት በረቶች የገለጡት ነገር ምን ነበር?
13 ነገሩን ከሌላ አቅጣጫ በመመልከት ኢየሱስ የጠቀሰው ሁለት በረቶችን ብቻ ሳይሆን ሦስት በረቶችን እንደሆነ ተስተዋለ። (ዮሐንስ ምዕራፍ 10) እነርሱም (1) አጥማቂው ዮሐንስ ጠባቂ የነበረበት የአይሁዶች በረት (2) የመንግሥቱ ወራሾች የሆኑት የቅቡዓን በረትና (3) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የ“ሌሎች በጎች” በረት ነበሩ።—ዮሐንስ 10:2, 3, 15, 16፤ የካቲት 15, 1984 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 10–20
14. እየጨመረ የመጣው ብርሃን የኢዮቤልዩ ጥላ የሚጀምርበትን ጊዜ በተመለከተ ሁኔታውን ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው?
14 ታላቁን ኢዮቤልዩ አስመልክቶ በነበረው እውቀት ላይም ተጨማሪ ማብራሪያ ተስጥቷል። በሕጉ መሠረት በየ50ኛው ዓመት ንብረት ለመጀመሪያ ባለቤቱ የሚመለስበት ታላቅ ኢዮቤልዩ ይደረግ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:10) ይህ ኢዮቤልዩ ለክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ጥላ እንደሆነ ቀደም ሲል ተስተውሎ ነበር። ሆኖም በቅርቡ ታላቁ ኢዮቤልዩ የጀመረው መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉ ሰዎች ከሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ነፃ ከወጡበት ከ33 እዘአ ጀምሮ እንደሆነ ተስተዋለ።—መጠበቂያ ግንብ 1–108 ገጽ 1–7
በቃላት አጠቃቀም ላይ የፈነጠቀ ተጨማሪ ብርሃን
15. “እቅድ” በተባለው ቃል አጠቃቀም ላይ ምን ብርሃን በርቶ ነበር?
15 “ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ።” (መክብብ 12:10) ብርሃን የበራልን በጣም አስፈላጊ በሆኑት እንደ መሠረተ ትምህርትና ጠባይ በመሳሰሉት ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በክርስቲያናዊ ቃላት አጠቃቀምና በትክክለኛ ትርጉማቸው ላይም ጭምር ስለሆነ እነዚህ ቃላት ከያዝነው ርዕሳችን ጋር ሊስማሙ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በጣም ተወዳጅ ከነበሩት ጽሑፎች መካከል የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ጥራዝ አንድ የሆነው መለኮታዊው የዘመናት እቅድ የተባለው መጽሐፍ ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ የአምላክ ቃል እቅድ ያቅዳሉ ብሎ የሚናገረው ሰዎችን ብቻ እንደሆነ ተስተዋለ። (ምሳሌ 19:21) ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ እቅድ እንደሚያወጣ በጭራሽ አይናገሩም። እቅድ ማውጣት አያስፈልገውም። በኤፌሶን 1:9, 10 (አዓት) ላይ እንደምናነበው ወሰን የሌለው ጥበብና ኃይል ስላለው ዓላማው ሁሉ ስኬታማ ይሆናል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ዓላማው የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ . . . ለማስተዳደር ነው” ስለዚህ ስለ ይሖዋ ስንናገር “ዓላማ” በሚለው ቃል መጠቀማችን ይበልጥ ትክክለኛ እንደሆነ ከጊዜ በኋላ መገንዘብ ተቻለ።
16. ከጊዜ በኋላ ሉቃስ 2:14ን በተመለከተ የተገኘው ትክክለኛ እውቀት ምን ነበር?
16 ከዚያም የሉቃስ 2:14 ትርጉምን በግልጽ የመረዳት ሁኔታም ነበር። ጥቅሱ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” ይላል። የአምላክ በጎ ፈቃድ ለክፉዎች ስላልተገለጠ ይህ ሐሳብ ትክክለኛ መልእክት እንደማያስተላልፍ ተስተውሎ ነበር። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ጥቅሱን ለአምላክ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ስለሚያገኙት ሰላም እንደሚናገር አድርገው ይመለከቱት ነበር። ስለዚህ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ይሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ በጎ ፈቃድ የተባለው የአምላክ በጎ ፈቃድ እንጂ የሰው በጎ ፈቃድ እንዳልሆነ ተስተዋለ። ስለዚህ ለሉቃስ 2:14 የተሰጠው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ “[በአምላክ] ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሰዎች” ይላል። ራሳቸውን ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ክርስቲያኖች በሙሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው።
17, 18. ይሖዋ የሚያረጋግጠው የምኑን ትክክለኛነት ነው? የሚያስቀድሰውስ?
17 በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች ለአያሌ ዓመታት ስለ ይሖዋ ስም ትክክለኛነት መረጋገጥ ይናገሩ ነበር። ይሁን እንጂ ሰይጣን በይሖዋ ስም ላይ አጠያያቂ ሁኔታ አስነስቷልን? ከሰይጣን ወኪሎች መካከል ይሖዋ በዚህ ስም የመጠራት መብት የለውም የሚል አጠያያቂ ሁኔታ ያስነሳ አለን? በጭራሽ የለም። ግድድር የተነሳበትና ትክክለኛነቱ መረጋገጥ ያስፈለገው የይሖዋ ስም አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጡት የማኅበሩ ጽሑፎች ስለ ይሖዋ ስም ትክክለኛነት መረጋገጥ የማይናገሩት ለዚህ ነው። ጽሑፎቹ የሚናገሩት ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት መረጋገጥ እና ስለ ስሙ መቀደስ ነው። ይህም ኢየሱስ “ስምህ ይቀደስ” ብለን እንድንጸልይ ካዘዘን ትእዛዝ ጋር የሚስማማ ነው። (ማቴዎስ 6:9፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በተደጋጋሚ ጊዜያት ይሖዋ እስራኤላውያን የተገዳደሩትን ሳይሆን ያረከሱትን ስሙን እንደሚቀድስ ተናግሯል።—ሕዝቅኤል 20:9, 14, 22፤ 36:23
18 የሚያስገርመው፣ በ1971 የታተመው “አሕዛብ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”—እንዴት? የተባለው መጽሐፍ “ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት እንዲረጋገጥና የይሖዋ ስም እንዲከበር . . . ይዋጋል” ሲል በሁለቱ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ይገልጻል። (ገጽ 364–5) በ1973 የታተመው የአምላክ የሺህ ዓመት መንግሥት ቀርቧል የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ “መጪው ‘ታላቅ መከራ’ ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ የጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥበትና ውድ ስሙን የሚቀድስበት ጊዜ ይሆናል” ብሎ ነበር። (ገጽ 409) ከዚህ ቀጥሎም በ1975 የታተመው የሰው ልጅ ከዓለም መከራ የሚገላገልበት ጊዜ ቀርቧል! የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ “በዚያን ጊዜ የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት የሚረጋገጥበትና ቅዱስ ስሙ የሚቀደስበት በአጽናፈ ዓለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ድርጊት ይከሰታል” በማለት ይገልጻል።—ገጽ 281
19, 20. ለመንፈሳዊ የብርሃን ብልጭታዎች አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
19 የይሖዋ ሕዝቦች ይህ ሁሉ መንፈሳዊ ብርሃን ስለተገለጠላቸው ምንኛ የተባረኩ ናቸው! ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎች የሚገኙበትን መንፈሳዊ ጨለማ አንድ ቄስ የተናገሩት የሚከተለው ቃል ይጠቁማል፦ “ኃጢአት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? መከራ ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? ዲያብሎስ ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? ሰማይ ስሄድ ጌታን መጠየቅ የምፈልገው እነዚህን ጥያቄዎች ነው።” ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ይህ የሆነው ለምን እንደሆነ ሊነግሯቸው ይችላሉ። ይህ የሆነው በይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ላይ በተነሳው አከራካሪ ጉዳይና ሰዎች ዲያብሎስ ተቃውሞ ቢያደርስባቸውም እንኳ ለአምላክ ያላቸውን ንጹሕ አቋም ሳያጎድፉ መኖር ስለመቻላቸው በተነሳው ጥያቄ ምክንያት መሆኑን ሊገልጹላቸው ይችላሉ።
20 ለብዙ ዓመታት የፈነጠቁት አነስተኛና ከፍተኛ የብርሃን ብልጭታዎች የይሖዋ ውስን አገልጋዮች የሚጓዙበትን መንገድ ብሩህ ሲያደርጉላቸው ቆይተዋል። እንደ መዝሙር 97:11 እና ምሳሌ 4:18 ያሉት ጥቅሶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ በብርሃን መመላለስ ማለት እየጨመረ የመጣውን ብርሃን ማድነቅና ከብርሃኑ ጋር ተስማምቶ መኖር ማለት መሆኑን በጭራሽ አንዘንጋ። ከዚህ በፊት እንደተመለከትነው እየጨመረ የመጣው ይህ ብርሃን ጠባያችንንም ሆነ የስብከት ተልእኳችንን ይነካል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከዚህ አመለካከት በተቃራኒ በሰኔ 1 እና ሰኔ 15, 1929 የታተመው መጠበቂያ ግንብ “ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት” ተብለው የተጠሩት ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆኑ አብራርቶ ነበር። በ1962 በመጀመሪያ ደረጃ የታረመው ይህ አቋም ነበር።
b ሚያዝያ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ በዕዝራ ዘመን ከነበሩት ናታኒም ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ከ“ሌሎች በጎች” የተመረጡ አንዳንድ ወንድሞች የአስተዳደር አካል ኮሚቴዎችን ለመርዳት እንደተመደቡ አስታውቆ ነበር።—ዮሐንስ 10:16፤ ዕዝራ 2:58
ታስታውሳለህን?
◻ “ለከፍተኛ ባለ ሥልጣናት” መገዛትን በተመለከተ የፈነጠቀው ብርሃን ምን ነበር?
◻ የፈነጠቁት የብርሃን ብልጭታዎች ምን ድርጅታዊ ማሻሻያዎችን አስገኝተዋል?
◻ እየጨመረ የመጣው ብርሃን ክርስቲያናዊ ጠባይን የነካው እንዴት ነው?
◻ መንፈሳዊ ብርሃን ለአንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጉዳዮች በነበረን እውቀት ላይ ምን ማሻሻያዎችን አምጥተዋል?
[ምንጭ]
በገጽ 24 ላይ ያሉት ቁልፎች፦ Drawing based on photo taken in Cooper-Hewitt, National Design Museum, Smithsonian institution