የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 58—ዕብራውያን
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- ሮም
ተጽፎ ያለቀው:- በ61 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ጳውሎስ በሰፊው የሚታወቀው ‘የአሕዛብ’ ሐዋርያ በመሆኑ ነው። ይሁን እንጂ አገልግሎቱ አይሁዳውያን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር? በፍጹም አልነበረም! ጳውሎስ ከመጠመቁና የሥራ ምድቡን ከመቀበሉ በፊት ጌታ ኢየሱስ ለሐናንያ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ይህ ሰው [ጳውሎስ] በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው።” (ሥራ 9:15፤ ገላ. 2:8, 9) በእርግጥም፣ ጳውሎስ የዕብራውያንን መጽሐፍ መጻፉ የኢየሱስን ስም በእስራኤል ልጆች ፊት እንዲሸከም ከተሰጠው ተልእኮ ጋር የሚስማማ ነበር።
2 ይሁን እንጂ አንዳንድ ተቺዎች የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ ጳውሎስ መሆኑን ይጠራጠራሉ። ለዚህ የሚያቀርቡት አንዱ ምክንያት የጳውሎስ ስም በደብዳቤው ውስጥ አለመጠቀሱ ነው። ሆኖም ይህ መከራከሪያ ነጥብ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ጸሐፊውን በስም የማይጠቅሱ ሌሎች በርካታ ቅዱሳን መጻሕፍት ያሉ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የጸሐፊው ማንነት ተለይቶ የሚታወቀው በጽሑፉ ውስጥ በሚገኙ ማስረጃዎች ነው። ከዚህም በላይ አንዳንዶች፣ ጳውሎስ በይሁዳ ለሚገኙ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በሚጽፍበት ጊዜ ስሙን ያልጠቀሰው በዚያ የሚገኙት አይሁዳውያን ለእሱ ጥላቻ ስለነበራቸው ሆን ብሎ መሆኑን ይገልጻሉ። (ሥራ 21:28) የአጻጻፍ ስልቱ ሌሎቹን መልእክቶቹን ለመጻፍ ከተጠቀመበት የተለየ መሆኑም የጳውሎስን ጸሐፊነት ላለመቀበል በቂ ምክንያት አይሆንም። ጳውሎስ የጻፈው ለአረማውያንም ይሁን ለአይሁዶች አሊያም ለክርስቲያኖች ምን ጊዜም “ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር” የመሆን ችሎታ እንዳለው አስመስክሯል። እዚህ ላይ እንደ አንድ አይሁዳዊ በመሆን አይሁዳውያንን እያስረዳ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሊረዷቸውና ሊያደንቋቸው የሚችሏቸውን የመከራከሪያ ነጥቦች አስፍሯል።—1 ቆሮ. 9:22
3 በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘው ማስረጃ፣ ጸሐፊው ጳውሎስ መሆኑን ሙሉ በሙሉ የሚደግፍ ነው። ጸሐፊው ጣሊያን የነበረ ሲሆን የጢሞቴዎስ ወዳጅ ነበር። እነዚህ እውነታዎች ጳውሎስ ከነበረበት ሁኔታ ጋር ይስማማሉ። (ዕብ. 13:23, 24) ከዚህም በተጨማሪ ምንም እንኳ በመልእክቱ ውስጥ ያሉት የመከራከሪያ ነጥቦች፣ ደብዳቤው የተላከለትን ዕብራውያን ብቻ የሚገኙበትን ጉባኤ ለመማረክ ሲባል ከአይሁዳውያን አመለካከት አንጻር የቀረቡ ቢሆኑም ትምህርቶቹ የጳውሎስ መሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ነጥብ ላይ ክላርክስ ኮሜንተሪ፣ ጥራዝ 6 ገጽ 681 የዕብራውያንን መጽሐፍ አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “የመልእክቱ አጠቃላይ ይዘት ለአይሁዳውያን የተጻፈ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ለአሕዛብ የተጻፈ ቢሆን ኖሮ የተናገራቸውን የማሳመኛ ነጥቦች ከአሥር ሺህ ሰዎች ውስጥ አንዱ እንኳ ባልተረዳቸው ነበር። ምክንያቱም አሕዛብ፣ የመልእክቱ ጸሐፊ ደጋግሞ ይጠቅሰው ስለነበረው የአይሁድ ሥርዓት የሚያውቁት ነገር አልነበረም።” ይህ ሐሳብ፣ የዕብራውያን መጽሐፍ አጻጻፍ ከሌሎቹ የጳውሎስ ደብዳቤዎች የተለየው ለምን እንደሆነ እንድንረዳ ያስችለናል።
4 በ1930 ገደማ የተገኘው ቼስተር ቢቲ ፓፒረስ ቁጥር 2 (P46) ጸሐፊው ጳውሎስ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ያቀርባል። ብሪታንያዊው ታዋቂ የሥነ ጽሑፍ ገምጋሚ ሰር ፍሬደሪክ ኬንየን ጳውሎስ ከሞተ ከአንድ ምዕተ ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ ስለተጻፈው ስለዚህ የፓፒረስ ኮዴክስ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “የዕብራውያን መጽሐፍ ከሮሜ መጽሐፍ ቀጥሎ መገኘቱ (ሊገኝ ይችላል ተብሎ በማይታሰብበት ቦታ) ትኩረት የሚስብ ሲሆን ቀደም ባሉት ጊዜያትም ከጳውሎስ መልእክቶች መካከል ይቆጠር እንደነበረ የሚያሳይ ነው።”a ከዚሁ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ የሚከተለውን ብሏል:- “ከመጽሐፉ ውጭም ይሁን ውስጥ፣ ከጳውሎስ በቀር ሌላ ግለሰብ ይህን መልእክት መጻፉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊያቀርብ የሚችል ሰው የለም።”b
5 የዕብራውያን መጽሐፍ በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘቱም ሌላ ይዘቱ ‘የአምላክ መንፈስ’ ያለበት መሆኑን ያረጋግጣል። የዕብራውያን መጽሐፍ ጥንታዊ ከሆኑት መጻሕፍት በተደጋጋሚ በመጥቀስ አንባቢዎቹን በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ወደሚገኙ ትንቢቶች የሚመራ ሲሆን ትንቢቶቹ በሙሉ እንዴት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ያሳያል። በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ልጅ ከመላእክት የሚበልጥ መሆኑን ለማስረዳት በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ብቻ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ ከሰባት ያላነሱ ጥቅሶች ይገኛሉ። መጽሐፉ የይሖዋን ቃልና ስሙን በተደጋጋሚ ጎላ አድርጎ የሚገልጽ ሲሆን ኢየሱስ ዋነኛው የሕይወት መገኛ መሆኑንና በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ደግሞ ብቸኛው የሰው ልጅ ተስፋ መሆኑን ይገልጻል።
6 መጽሐፉ የተጻፈበትን ጊዜ በሚመለከት፣ ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ጣሊያን በነበረበት ጊዜ መሆኑ ቀደም ሲል ተገልጿል። ጳውሎስ በደብዳቤው ማጠቃለያ ላይ “ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደተፈታ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ፤ ቶሎ ከመጣ፣ ከእርሱ ጋር ላያችሁ እመጣለሁ” ብሏል። (13:23) ይህ አባባል ጳውሎስ በቅርቡ ከእስር ለመውጣት እየተጠባበቀ እንዳለና ከእስር ከተፈታው ከጢሞቴዎስ ጋር አብሮ ለመሄድ ማሰቡን የሚያመለክት ይመስላል። በመሆኑም መጽሐፉ የተጻፈው ጳውሎስ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ ታስሮ በነበረበት ወቅት በመጨረሻው ዓመት ላይ ማለትም በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሳይሆን እንደማይቀር ይታሰባል።
7 በአይሁድ ሥርዓት ማብቂያ ላይ በይሁዳ፣ በተለይም ደግሞ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ላይ ከባድ ፈተና ደርሶባቸው ነበር። ምሥራቹ በመስፋፋቱ ምክንያት አይሁዳውያን ይበልጥ አክራሪ እየሆኑና ጥላቻቸው እየጨመረ በመሄዱ በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱት ተቃውሞ እያየለ መጣ። ከጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም መታየቱ ብቻ እንኳ ሁከት ያስነሳ ሲሆን ሃይማኖተኛ የሆኑ አይሁዳውያን “ይህስ ከምድር ገጽ ይወገድ! በሕይወት መኖር አይገባውም!” በማለት ጮኸውበት ነበር። ከ40 የሚበልጡ አይሁዳውያን ጳውሎስን ሳይገድሉ እህልና ውኃ ላለመቅመስ ስለተማማሉ ጳውሎስን በምሽት ወደ ቂሣርያ ለመውሰድ በደንብ የታጠቁ ወታደሮች እንዲያጅቡት ማድረግ አስፈልጎ ነበር። (ሥራ 22:22፤ 23:12-15, 23, 24) በዚያ የነበረው ጉባኤ አባላት እንዲህ ባለው ሃይማኖታዊ አክራሪነት በነገሠበትና ለክርስቲያኖች ጥላቻ በነበረው ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር፣ መስበክና እምነታቸውን አጥብቀው መያዝ ነበረባቸው። በተጨማሪም እነዚህ ክርስቲያኖች ወደ አይሁድ እምነት እንዲሁም የእንስሳ መሥዋዕቶችን ማቅረብንና በዚያ ወቅት ምንም ሊጠቅሙ የማይችሉ ልማዶችን መከተልን ወደሚያካትተው የሙሴ ሕግ እንዳይመለሱ ክርስቶስ ሕጉን እንዴት እንደፈጸመ በደንብ ማወቅና በጥልቀት መረዳት ነበረባቸው።
8 አይሁዳውያን የሆኑ ክርስቲያኖች እየደረሰባቸው ያለውን ተጽዕኖና መከራ የሚረዳላቸው ከሐዋርያው ጳውሎስ የተሻለ ሰው አልነበረም። ቀደም ሲል ፈሪሳዊ ከነበረው ከጳውሎስ ሌላ የአይሁድን ወግ በተመለከተ ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥቦችንና ማስረጃዎችን ሊያቀርብ የሚችል የተሻለ እውቀት ያለው ሰው አልነበረም። ጳውሎስ በገማልያል እግር ሥር ሆኖ ስለ ሙሴ ሕግ ካገኘው ሰፊ እውቀት በመጥቀስ፣ ክርስቶስ የሕጉ (ደንቦቹንና መሥዋዕቶቹን ጨምሮ) ፍጻሜ መሆኑን የማያሻማ ማረጋገጫ አቅርቧል። እነዚህ ነገሮች ታላላቅ ጥቅሞችን በሚያስገኝ አዲስና የተሻለ ቃል ኪዳን ሥር በሚገኙ ብልጫ ባላቸው አስደናቂ ነገሮች እንዴት እንደተተኩ አሳይቷል። ንቁ በሆነ አእምሮው ተጠቅሞ ማስረጃዎቹን ግልጽና አሳማኝ በሆነ መንገድ ደረጃ በደረጃ አቅርቧል። የሕጉ ቃል ኪዳን መፈጸምንና የአዲሱ ቃል ኪዳን መምጣትን፣ የክርስቶስ ክህነት ከአሮን ክህነት ያለውን ብልጫ፣ የክርስቶስ መሥዋዕት ከበሬዎችና ከፍየሎች መሥዋዕት ጋር ሲወዳደር ያለውን ከፍተኛ ዋጋ፣ ክርስቶስ ወደ ምድራዊ ድንኳን ሳይሆን ይሖዋ ወደሚገኝበት ወደ ሰማይ መግባቱን የመሳሰሉ ትኩረት የሚስቡ አዳዲስ ትምህርቶች በማያምኑ አይሁዶች ዘንድ እጅግ የሚጠሉ ቢሆኑም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ግን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለውን ማንኛውንም አይሁዳዊ ሊያሳምን በሚችል መልኩ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ከተወሰዱ በርካታ ማስረጃዎች ጋር ቀርበውላቸዋል።
9 ይህ ደብዳቤ፣ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች አይሁዳውያን አሳዳጆቻቸውን አፍ የሚያስይዙበት አዲስና ኃይለኛ መሣሪያ የሆነላቸው ሲሆን የአምላክን እውነት የሚፈልጉ ቅን ልቦና ያላቸውን አይሁዶች ለማሳመንና ለመለወጥ የሚያስችል የመከራከሪያ ነጥብም ይዟል። ደብዳቤው፣ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የነበረውን ጥልቅ ፍቅርና በችግራቸው ጊዜ ተግባራዊ በሆነ መንገድ ለመርዳት የነበረውን ከፍተኛ ፍላጎት ያሳያል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
23 ለዕብራውያን የተላከው ደብዳቤ ክርስቶስን በመደገፍ የቀረበ ሕጋዊ የመከራከሪያ ሐሳብ ሲሆን በሚገባ የተቀናጀና ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ብዙ ማስረጃዎችን ያካተተ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ድንቅ ጽሑፍ ነው። የሙሴ ሕግ ያሉትን የተለያዩ ገጽታዎች ማለትም ቃል ኪዳኑን፣ ደሙን፣ መካከለኛውን፣ የአምልኮ ድንኳኑን፣ የክህነት አገልግሎቱንና መሥዋዕቶቹን ከገለጸ በኋላ እነዚህ ነገሮች ወደፊት የሚመጡትን ብልጫ ያላቸው ነገሮች ለማመልከት አምላክ እንደ ጥላ አድርጎ የተጠቀመባቸው እንደነበሩ እንዲሁም ሁሉም የሕግ ፍጻሜ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስና በእሱ መሥዋዕትነት ላይ እንደተፈጸሙ ያሳያል። ጳውሎስ ስለ ሕጉ ሲናገር “ያረጀ ያፈጀው የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቦአል” ብሏል። “ኢየሱስ ክርስቶስ [ግን] ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው።” (8:13፤ 13:8፤ 10:1) እነዚያ ዕብራውያን የተላከላቸውን ደብዳቤ በሚያነቡበት ጊዜ ምንኛ ተደስተው ይሆን!
24 ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ፣ በተለየ ሁኔታ ውስጥ ለምንገኘው ለእኛ ይህ ምን ጥቅም አለው? በሙሴ ሕግ ሥር ስላልሆንን ጳውሎስ ካቀረበው የማሳመኛ ሐሳብ ጠቃሚ የሆነ ነገር ማግኘት እንችል ይሆን? አዎን፣ እንችላለን። የምድር ቤተሰቦች በሙሉ በዘሩ አማካኝነት ራሳቸውን እንደሚባርኩ ለአብርሃም በተሰጠው የተስፋ ቃል ላይ ስለተመሠረተውና ታላቅ ስለሆነው ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን የሚገልጸውን ዝግጅት የምናገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ሕይወት ለማግኘት ያለን ብቸኛ ተስፋ፣ ይሖዋ የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በረከት እንደሚያመጣ በሚገልጸው ጥንት በገባው ቃል መፈጸም ላይ የተመሠረተ ነው። በሕጉ ሥር ባንሆንም እንኳ የአዳም ዘሮች ስለሆንን ኃጢአተኞች ሆነን ተወልደናል። ስለሆነም ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው የኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የሚችልና በሰማይ ወደ ይሖዋ በቀጥታ ገብቶ ስለ እኛ ሊማልድልን የሚችል ርኅሩኅ ሊቀ ካህናት ያስፈልገናል። ይሖዋ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ ወደሚገኘው ሕይወት ሊመራን የሚችል፣ ድካማችንን አይቶ የሚራራልን፣ “እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ፣” “ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት” እንድንቀርብ የሚጋብዘን ሊቀ ካህናት እንዳለን የምናነበው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ነው።—4:15, 16
25 ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በላከው ደብዳቤ ላይ፣ ከረጅም ጊዜ በፊት በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ትንቢቶች ከጊዜ በኋላ አስደናቂ ፍጻሜ ማግኘታቸውን የሚያሳይ ልብ የሚነካ ማስረጃ እናገኛለን። እነዚህ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው መመሪያና ማጽናኛ ይሰጡናል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ በመዝሙር 110:1 ላይ የሚገኙትን ስለ መንግሥቱ ተስፋ የሚናገሩትን ሐሳቦች በዕብራውያን መጽሐፍ ላይ አምስት ጊዜ በመጥቀስ እነዚህ ትንቢቶች “ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ” ‘በአምላክ ዙፋን ቀኝ በተቀመጠው’ በመንግሥቱ ዘር ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደሚሠሩ ገልጿል። (ዕብ. 12:2፤ 10:12, 13፤ 1:3, 13፤ 8:1) በተጨማሪም ጳውሎስ መዝሙር 110:4ን ጠቅሶ፣ የአምላክ ልጅ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት” መሆኑን በመግለጽ ኢየሱስ ያለውን ቁልፍ የሥራ ድርሻ ያብራራል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው ‘አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ አሊያም ለዘመኑ መጀመሪያም ሆነ ለሕይወቱም ፍጻሜ እንደሌለው’ እንደ ጥንቱ መልከ ጼዴቅ፣ ኢየሱስ ለአመራሩ በፈቃደኝነት ለሚገዙ ሰዎች በሙሉ ቤዛዊ መሥዋዕቱ የሚያስገኛቸውን ዘላለማዊ ጥቅሞች የሚሰጥ ንጉሥና ‘የዘላለም ካህን’ ነው። (ዕብ. 5:6, 10፤ 6:20፤ 7:1-21) ጳውሎስ፣ መዝሙር 45:6, 7ን ጠቅሶ እንደሚከተለው ሲል የተናገረውም ስለዚሁ ንጉሥና ካህን ነበር:- “አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም ዙፋንህ ነው፤ የመንግሥትህ በትርም የጽድቅ በትር ነው። ጽድቅን ወደድክ፣ ዓመፅን ጠላህ። አምላክ ይኸውም አምላክህ ከመሰሎችህ ይበልጥ በደስታ ዘይት የቀባህ ለዚህ ነው።” (ዕብ. 1:8, 9 NW) ጳውሎስ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት መጥቀሱና እነዚህ ጥቅሶች በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ እንዴት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ማብራራቱ መለኮታዊውን አሠራር እንድንረዳ አስችሎናል።
26 የዕብራውያን መልእክት በግልጽ እንደሚናገረው አብርሃም የአምላክን መንግሥት ማለትም “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር።” ይህች ከተማ “ሰማያዊ አገር” ናት። አብርሃም “በእምነት” የአምላክን መንግሥት አሻግሮ የተመለከተ ሲሆን “የተሻለውን ትንሣኤ” አግኝቶ በረከቶችን ማጨድ ይችል ዘንድ ታላላቅ መሥዋዕቶችን ከፍሏል። የአብርሃም እምነትም ሆነ ጳውሎስ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የዘረዘራቸው ‘እንደ ደመና በዙሪያችን ያሉ’ ብዙ ታማኝ ምስክሮች ያሳዩት እምነት እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል! ይህን ዘገባ ስናነብ፣ እነዚህ ንጹሕ አቋም ጠባቂዎች ያላቸው ዓይነት መብትና ተስፋ እኛም በማግኘታችን ልባችን በምስጋናና በደስታ ይሞላል። በመሆኑም “በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት [እንድንሮጥ]” ተበረታተናል።—11:8, 10, 16, 35፤ 12:1
27 ጳውሎስ የሚከተለውን የሐጌ ትንቢት በመጥቀስ ትኩረታችንን አምላክ ወደ ሰጠው ተስፋ እንድናዞር ያደርገናል:- “ምድርን ብቻ ሳይሆን፣ ሰማያትንም አንድ ጊዜ ደግሜ አናውጣለሁ።” (ዕብ. 12:26፤ ሐጌ 2:6) በዘሩ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። “ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሰኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው።” ይህ ስሜት ቀስቃሽ ዘገባ ክርስቶስ ‘ኀጢአትን ለመሸከም ሳይሆን ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚገለጥ’ ማረጋገጫ ይሰጣል። እንግዲያው “ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ።” የይሖዋ አምላክ ታላቅ ስም፣ ንጉሥና ካህን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለዘላለም ይቀደስ!—ዕብ. 12:28፤ 9:28፤ 13:15
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዘ ስቶሪ ኦቭ ዘ ባይብል፣ 1964 ገጽ 91
b በ1981 በድጋሚ የታተመ፣ ጥራዝ አራት ገጽ 147