በሕይወት መንገድ ላይ የሚመራችሁ መብራት
“አቤቱ፣ [“ይሖዋ፣” NW] የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” (ኤርምያስ 10:23) ኤርምያስ በእነዚህ ቃላት አማካኝነት ሰዎች እርዳታ እስካላገኙ ድረስ በሕይወት መንገድ ላይ በትክክል መጓዝ እንደማይችሉ ገልጿል። እንዲህ ዓይነቱ እርዳታ ከየት ሊገኝ ይችላል? መዝሙራዊው ለይሖዋ አምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ በማለት ይመልሳል:- “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴ ብርሃን ነው።”—መዝሙር 119:105
የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑና የሚለውን በተግባር የሚያውሉ ሰዎች ሊነጋጋ ሲል ጉዞ ከጀመረ ሰው ጋር ይመሳሰላሉ። በመጀመሪያ ጨለማ በመሆኑ ምክንያት በደንብ ለመመልከት አይችልም። ነገር ግን ፀሐይ መውጣት ስትጀምር የማየት ችሎታው እየጨመረ ይሄዳል። በመጨረሻም ፀሐይዋ አናት ላይ ትሆናለች። ሰውየው ማንኛውንም ነገር በግልጽ ሊመለከት ይችላል። ይህ ሁኔታ “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ ያስታውሰናል።—ምሳሌ 4:18
የአምላክን አመራር አልቀበልም የሚሉ ሰዎችስ? መጽሐፍ ቅዱስ “የኀጥአን መንገድ እንደ ጨለማ ነው፣ እንዴት እንደሚሰናከሉም አያውቁም” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 4:19) አዎን፣ ክፉዎች በጨለማ እንደሚደናበር ሰው ናቸው። ሌላው ቀርቶ አግኝተናል ብለው የሚያስቡት ስኬት ሊቆይ የሚችለው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው። ምክንያቱም “ጥበብ ወይም ማስተዋል ወይም ምክር በእግዚአብሔር ላይ የለም።”—ምሳሌ 21:30
ስለዚህ የአምላክ ቃል የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስን አመራር ተቀበሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ በምሳሌ 3:5, 6 ላይ የሚገኙት ቃላት እውነት ሆነው ታገኟቸዋላችሁ:- “በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።”