-
መጽሐፍ ቅዱስን መማርህን እንድትቀጥል ምን ሊረዳህ ይችላል?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 12
መጽሐፍ ቅዱስን መማርህን እንድትቀጥል ምን ሊረዳህ ይችላል?
መጽሐፍ ቅዱስን መማር ወደ አንድ አስደሳች ቦታ ከምናደርገው ጉዞ ጋር ይመሳሰላል። ሆኖም እንዲህ ያለ ጉዞ ስናደርግ አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ስትማርም ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥምህ ይሆናል። ‘መጽሐፍ ቅዱስን መማሬን ማቆም ይኖርብኝ ይሆን?’ ብለህ እንድታስብ የሚያደርጉህ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። ይሁንና የጀመርከውን ጉዞ ለመቀጠል ጥረት ማድረግህ የሚክስ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህም እንድትጸና ሊረዳህ የሚችለው ምንድን ነው?
1. መጽሐፍ ቅዱስን መማርህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
“የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው።” (ዕብራውያን 4:12) መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ መጽሐፍ ነው፤ ምክንያቱም የአምላክን አስተሳሰብና እሱ ለአንተ ያለውን ስሜት እንድታውቅ ይረዳሃል። እውቀት ብቻ ሳይሆን ጥበብና አስተማማኝ ተስፋ እንዲኖርህ ያስችልሃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ወዳጅ እንድትሆን ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስን ስትማር፣ የአምላክ ቃል ያለው ኃይል ሕይወትህን ያሻሽልልሃል።
2. የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያላቸውን ውድ ዋጋ መገንዘባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት እውነቶች ልክ እንደ ውድ ሀብት ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነትን ግዛ፤ ፈጽሞም አትሽጣት” የሚል ማበረታቻ የሚሰጠን ለዚህ ነው። (ምሳሌ 23:23) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ምን ያህል ውድ እንደሆኑ የምናስታውስ ከሆነ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም መጽሐፍ ቅዱስን መማራችንን ለመቀጠል ጥረት እናደርጋለን።—ምሳሌ 2:4, 5ን አንብብ።
3. ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን መማርህን እንድትቀጥል ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
ሁሉን ቻይ ፈጣሪና ወዳጅህ የሆነው ይሖዋ ስለ እሱ እንድትማር ሊረዳህ ይፈልጋል። ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎትም ሆነ ኃይል’ ይሰጥሃል። (ፊልጵስዩስ 2:13ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ወይም የተማርከውን ነገር ተግባር ላይ ለማዋል ተጨማሪ ተነሳሽነት በሚያስፈልግህ ጊዜ ሊረዳህ ይችላል። ያጋጠመህን ተፈታታኝ ሁኔታ ወይም ተቃውሞ ለመቋቋም የሚያስችል ተጨማሪ ኃይልም ይሰጥሃል። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን መማርህን እንድትቀጥል እንዲረዳህ አዘውትረህ ይሖዋን በጸሎት ለምነው።—1 ተሰሎንቄ 5:17
ጠለቅ ያለ ጥናት
ጊዜህ የተጣበበ ቢሆንም ወይም ከሌሎች ተቃውሞ ቢያጋጥምህም መጽሐፍ ቅዱስን መማርህን እንድትቀጥል የሚረዳህ ምን እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ ረገድ የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ እንወያያለን።
4. ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ቅድሚያ ስጥ
አንዳንዴ ጊዜያችን በጣም ከመጣበቡ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር በቂ ጊዜ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። ታዲያ ምን ሊረዳን ይችላል? ፊልጵስዩስ 1:10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በሕይወታችን ውስጥ ‘ይበልጥ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች’ አንዳንዶቹ የትኞቹ ይመስሉሃል?
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ቅድሚያ ለመስጠት ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
ሀ. ባልዲው ውስጥ መጀመሪያ ላይ አሸዋ ከጨመርክ በኋላ ድንጋዮቹን ለመጨመር ብትሞክር ለሁሉም ድንጋዮች የሚሆን በቂ ቦታ አታገኝም
ለ. አስቀድመህ ድንጋዮቹን ካስገባህ ግን አብዛኛውን አሸዋ ለማስገባት የሚያስችል ቦታ ታገኛለህ። በተመሳሳይም በሕይወት ውስጥ ‘ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች’ ቅድሚያ ከሰጠህ ለሌሎች ነገሮችም የሚሆን ጊዜ ታገኛለህ
መጽሐፍ ቅዱስን መማራችን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማለትም አምላክን የማወቅና እሱን የማምለክ ፍላጎታችንን ለማሟላት ያስችለናል። ማቴዎስ 5:3ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ቅድሚያ መስጠታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
5. የሚያጋጥምህን ተቃውሞ በጽናት ተቋቋም
አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን መማርህን እንድታቆም ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ ይሞክራሉ። ፍራንሲስኮ የተባለ ሰው ያጋጠመውን ነገር ተመልከት። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ የፍራንሲስኮ ጓደኞችና ቤተሰቦች ፍራንሲስኮ ስለሚማረው ነገር ሲነግራቸው ምን ተሰማቸው?
መጽናቱ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል?
ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 2:24, 25ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ቤተሰቦችህና ጓደኞችህ ስለምትማረው ነገር ምን ይሰማቸዋል?
በዚህ ጥቅስ መሠረት አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በመማርህ ቢቃወምህ ምላሽ መስጠት ያለብህ እንዴት ነው? ለምን?
6. ይሖዋ እንደሚረዳህ ተማመን
ወደ ይሖዋ ይበልጥ በቀረብን መጠን እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎትም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። ያም ሆኖ ግን ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ስንል በሕይወታችን ላይ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። አንተም እንደዚህ ተሰምቶህ የሚያውቅ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ ይረዳሃል። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ እንደታየው፣ ጂም ይሖዋን ለማስደሰት ሲል ምን ለውጦች አድርጓል?
ከእሱ ታሪክ ትኩረትህን የሳበው ምንድን ነው?
ዕብራውያን 11:6ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ “ከልብ ለሚፈልጉት” ሰዎች ማለትም እሱን ለማወቅና ለማስደሰት ጥረት ለሚያደርጉ ሰዎች ምን ያደርግላቸዋል?
ከዚህ አንጻር ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር የምታደርገውን ጥረት ሲመለከት ምን የሚሰማው ይመስልሃል?
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “መጽሐፍ ቅዱስን የምትማረው ለምንድን ነው?”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ማጠቃለያ
አንዳንድ ጊዜ ተፈታታኝ ሊሆን ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስን መማርህ ለዘላለም በደስታ መኖር የምትችልበት አጋጣሚ ይከፍትልሃል። በይሖዋ መታመንህን ከቀጠልክ እሱ ወሮታህን ይከፍልሃል።
ክለሳ
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች እንደ ውድ ሀብት አድርገህ የምትመለከታቸው ለምንድን ነው?
‘ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች’ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን መማርህን እንድትቀጥል እንዲረዳህ መጸለይ ያለብህ ለምንድን ነው?
ምርምር አድርግ
ብዙ ሰዎች ጊዜያቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙ የረዱ አራት ዘዴዎች የትኞቹ ናቸው?
አንዲት ሴት አምላክን ለማስደሰት ጥረት ስታደርግ ባለቤቷ ይቃወማት ጀመር። ይሖዋ ይህችን ሴት የረዳት እንዴት ነው?
አንድ ሰው ባለቤቱ በመጽናቷ ምን ጥቅም አግኝቷል?
የይሖዋ ምሥክሮች ‘ቤተሰብ ይከፋፍላሉ’ የሚል ነቀፋ የሚሰነዘርባቸው ጊዜ አለ። ሆኖም ይህ እውነት ነው?
“የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን ያፈርሳሉ? ወይስ የቤተሰብ ትስስር እንዲጠናከር ይረዳሉ?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)
-
-
ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
-
-
ምዕራፍ 35
ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
ሁላችንም የተለያዩ ውሳኔዎችን ማድረግ ይጠበቅብናል። ከእነዚህ ውሳኔዎች መካከል ብዙዎቹ በእኛ ሕይወት ላይም ሆነ ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ። ለምሳሌ ከምንኖርበት ቦታ፣ ራሳችንን ከምናስተዳድርበት መንገድ ወይም ትዳር ከመመሥረት ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ጥሩ ውሳኔዎችን ስናደርግ ደስተኛ እንሆናለን፤ ይሖዋንም እናስደስታለን።
1. መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመህ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፤ እንዲሁም እሱ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን መርምር። (ምሳሌ 2:3-6ን አንብብ።) አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ ይሖዋ ግልጽ መመሪያ ሰጥቷል። እንዲህ ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሁሉ የተሻለው ውሳኔ የይሖዋን መመሪያ መታዘዝ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ግን ምን ማድረግ እንዳለብህ የሚገልጽ ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ላይኖር ይችላል። በዚህ ጊዜስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ‘ልትሄድበት በሚገባህ መንገድ ይመራሃል።’ (ኢሳይያስ 48:17) እንዴት? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልትመራባቸው የምትችል መሠረታዊ ሥርዓቶችን ልታገኝ ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አምላክ ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አስተሳሰብ ወይም ስሜት ለማወቅ የሚረዱ መሠረታዊ እውነቶች ናቸው። በአብዛኛው አምላክ ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አመለካከት የምናውቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝን ታሪክ ስናነብ ነው። ይሖዋ ያለውን አመለካከት ማወቃችን ደግሞ እሱን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ ይረዳናል።
2. ውሳኔ ከማድረግህ በፊት የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል?
መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ . . . አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ይህም ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት ጊዜ ወስደን ያሉንን አማራጮች በሚገባ ማሰብ እንዳለብን ይጠቁማል። ያሉህን አማራጮች ስትገመግም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው? ውስጣዊ ሰላም የማገኘው የትኛውን ምርጫ ባደርግ ነው? የማደርገው ውሳኔ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? ከሁሉ በላይ ይህ ውሳኔ ይሖዋን ያስደስተዋል?’—ዘዳግም 32:29
ይሖዋ ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር በተመለከተ መመሪያ የመስጠት መብት አለው። ስለ ይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለን እውቀት ሲጨምር እንዲሁም እነዚህን መመሪያዎች በተቻለን መጠን ተግባራዊ ለማድረግ ስንጥር ሕሊናችንን እያሠለጠንን እንሄዳለን። ሕሊና ማለት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የሚነግረን በውስጣችን ያለ ዳኛ ነው። (ሮም 2:14, 15) በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳል።
ጠለቅ ያለ ጥናት
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሕሊናችን ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
3. ውሳኔ ስታደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመራ
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን እንዴት ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
የመምረጥ ነፃነት ምንድን ነው?
ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት የሰጠን ለምንድን ነው?
ይሖዋ የመምረጥ ነፃነታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መጠቀም እንድንችል ምን ሰጥቶናል?
ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዱን ለማየት ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብቡ። ከዚያም የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ‘ጊዜህን በተሻለ መንገድ መጠቀም’ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተወያዩ፦
መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ለማንበብ
ጥሩ የትዳር ጓደኛ፣ ወላጅ ወይም ልጅ ለመሆን
በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት
4. ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ ሕሊናህን አሠልጥን
አንድን ጉዳይ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግልጽ መመሪያ ሲኖር ትክክለኛው ምርጫ የቱ እንደሆነ ለማወቅ አይከብድም። ሆኖም ግልጽ መመሪያ በማይኖርበት ጊዜስ? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
በቪዲዮው ላይ የታየችው እህት ሕሊናዋን ለማሠልጠንና ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ የትኞቹን እርምጃዎች ወስዳለች?
እኛ ልናደርግ የሚገባንን ውሳኔ ሌሎች እንዲያደርጉልን መጠየቅ የሌለብን ለምንድን ነው? ዕብራውያን 5:14ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
ሌሎች ለእኛ እንዲወስኑልን መጠየቅ ቀላል ሊመስል ቢችልም የትኛውን ነገር በራሳችን መለየት መቻል ይኖርብናል?
ጥሩ ውሳኔ ለማድረግና ሕሊናህን ለማሠልጠን የሚረዱህ ምን ዝግጅቶች አሉ?
ሕሊናችን ልክ እንደ ካርታ የምንጓዝበትን አቅጣጫ ለመወሰን ይረዳናል
5. የሌሎችን ሕሊና አክብር
ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ ውሳኔ ሊያደርጉ ይችላሉ። ታዲያ የሌሎችን ሕሊና እንደምናከብር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ ሁለት ሁኔታዎችን እንደ ምሳሌ እንመልከት፦
ምሳሌ 1፦ መኳኳል የምትወድ አንዲት እህት ወደ ሌላ ጉባኤ ተዛወረች፤ በአዲሱ ጉባኤዋ ያሉ ብዙ እህቶች መኳኳል ተገቢ እንደሆነ አይሰማቸውም።
ሮም 15:1ን እና 1 ቆሮንቶስ 10:23, 24ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት እህት ምን ውሳኔ ልታደርግ ትችላለች? አንተ ሕሊናህ የሚፈቅድልህን ነገር ሌላ ሰው ሕሊናው የማይፈቅድለት ከሆነ ምን ታደርጋለህ?
ምሳሌ 2፦ አንድ ወንድም፣ በመጠኑ እስከሆነ ድረስ የአልኮል መጠጥ መጠጣትን መጽሐፍ ቅዱስ እንደማይከለክል ያውቃል። ያም ሆኖ ጨርሶ አልኮል ላለመጠጣት ወስኗል። ይህ ወንድም አንድ ግብዣ ላይ ተገኝቶ ወንድሞች የአልኮል መጠጥ ሲጠጡ ይመለከታል።
መክብብ 7:16ን እና ሮም 14:1, 10ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦
በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት ወንድም ምን ውሳኔ ሊያደርግ ይችላል? አንተ ሕሊናህ የማይፈቅድልህን ነገር ሌላ ሰው ሲያደርግ ብታይ ምን ታደርጋለህ?
ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች
1. ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳህ ይሖዋን ለምን።—ያዕቆብ 1:5
2. ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች ላይ ምርምር አድርግ። ተሞክሮ ያላቸውን ክርስቲያኖችም ማማከር ትችላለህ።
3. የምታደርገው ውሳኔ በአንተም ሆነ በሌሎች ሕሊና ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አስብ።
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “የፈለግከውን ነገር ማድረግ መብትህ ነው። ስለ ሌሎች ሰዎች ምን ያስጨንቅሃል?”
የምናደርገው ነገር በአምላክም ሆነ በሌሎች ሰዎች ስሜት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?
ማጠቃለያ
ይሖዋ ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አመለካከት ማወቃችን እንዲሁም የምናደርገው ነገር በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን በጎ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ማሰባችን ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳናል።
ክለሳ
ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ሕሊናህን ማሠልጠን የምትችለው እንዴት ነው?
የሌሎች ሰዎችን ሕሊና እንደምታከብር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
ምርምር አድርግ
ከአምላክ ጋር ያለህን ወዳጅነት የሚያጠናክሩ ውሳኔዎችን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ ለእኛ ምክር ስለሚሰጥበት መንገድ ያለህን ግንዛቤ አሳድግ።
አንድ ሰው ከባድ ውሳኔ ከፊቱ በተደቀነበት ወቅት ጥሩ ምርጫ ለማድረግ የረዱት ነገሮች ምንድን ናቸው?
ቀጥተኛ መመሪያ ያልተሰጠበት ጉዳይ ሲያጋጥምህ ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
-