“ሊነቀሉ የማይችሉ ሥሮች”
ዓለም ካሏት ግዙፍና በዕድሜ አንጋፋ የሆኑ ሕያዋን ነገሮች መካከል በካሊፎርኒያ የሚገኙት የሴኮያ ዛፎች ይገኙበታል። እነዚህ ዛፎች ወደ መጨረሻ የእድገት ደረጃቸው ሲደርሱ 90 ሜትር የሚሆን አስገራሚ ቁመት ሲኖራቸው እስከ 3,000 ዓመት ሊኖሩ ይችላሉ።
ምንም እንኳ ከምድር በላይ የሚታየው የሴኮያ ዛፍ ግዝፈት በጣም አስገራሚ ቢሆንም የማይታየው ሥሩም የዚያኑ ያህል አስገራሚ ነው። የሴኮያ ዛፍ ከ12,000 እስከ 16,000 ካሬ ሜትር ሊሸፍኑ የሚችሉ እርስ በርሳቸው የተጠላለፉ ሥሮች አሉት። ይህ በሰፊው የተዘረጋው ሥር ጎርፍ ወይም አውሎ ነፋስ በሚመጣበት ጊዜ ዛፉን እንዳይወድቅ ቀጥ አድርጎ ይይዘዋል። የሴኮያ ዛፍ ሌላው ቀርቶ ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ እንኳ ሊቋቋም ይችላል!
ንጉሥ ሰሎሞን ከምሳሌዎቹ በአንዱ ውስጥ የዛፍን ጠንካራ ሥር በሰምና ወርቅ አነጋገሩ ላይ ተጠቅሞበታል። “በክፋት ራሱን አጽንቶ መቆም የሚችል ሰው የለም፤ ጥሩ ሰዎች ግን ሊነቀሉ የማይችሉ ሥሮች አሏቸው” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 12:3 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) አዎን፣ ክፉዎች በሚያረገርግ መሬት ላይ እንዳሉ ያህል ናቸው። ክፉዎች የተሳካላቸው የሚመስለው ማንኛውም ነገር ጊዜያዊ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ “የኀጥኣን ተስፋ ግን ይጠፋል” ሲል ተናግሯል።—ምሳሌ 10:28
ኢየሱስ አንዳንዶች በራሳቸው “ሥር” ስለሌላቸው ይሰናከላሉ ብሎ ስለተናገረ ይህ ክርስቲያን ነን ለሚሉ ሰዎች ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው። (ማቴዎስ 13:21) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በሐሰት ትምህርት ነፋስ ወዲያና ወዲህ ስለሚንሳፈፉ’ ሰዎች ጽፏል። (ኤፌሶን 4:14) ይህን መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?
የሴኮያ ዛፍ ሥሮች ለም በሆነው የምድር አፈር ላይ እንደሚስፋፉ ሁሉ አእምሮአችንና ልባችንም ሕይወት አድን የሆነውን የአምላክን ቃል ውሃ በጥልቀት ገብተው መቅዳት ያስፈልጋቸዋል። ይህም በደንብ ሥር የሰደደ እምነት ለማዳበር ይረዳናል። እርግጥ ነው፣ እንደ ማዕበል አስቸጋሪ የሆኑ ፈተናዎች የሚያደርሱብን ተጽዕኖ ይሰማናል። በመከራ ጊዜ ምናልባትም እንደ ዛፍ ወዲያና ወዲህ ልንወዛወዝ እንችላለን። ነገር ግን እምነታችን በሚገባ ሥር የሰደደ ከሆነ “የማይነቀሉ ሥሮች” አሉን ማለት ነው።—ከዕብራውያን 6:19 ጋር አወዳድር።