የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g93 10/8 ገጽ 27-29
  • “አባትህንና እናትህን አክብር”​—ግን ለምን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “አባትህንና እናትህን አክብር”​—ግን ለምን?
  • ንቁ!—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ማክበር ማለት ምን ማለት ነው?
  • ወላጆችህን ማክበር የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
  • አስቸጋሪ ወላጆች
  • ‘አባቴ ያለኝ ሁሉ ትክክል ነበር’
  • ‘ወላጆቼን ማክበር’ የሚኖርብኝ ለምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች
  • ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ማክበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • “አባትህንና እናትህን አክብር”
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2018
  • “አባትህንና እናትህን አክብር” ሲባል ምን ማለት ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1993
g93 10/8 ገጽ 27-29

የወጣቶች ጥያቄ . . .

“አባትህንና እናትህን አክብር”​—ግን ለምን?

የቬዳ አባት በጣም ተበሳጭቶ “ከአንቺ ጋር ምንም ነገር ለማድረግ አልችልም። ፈጽሞ አታከብሪኝም። በራስሽ ላይ ችግር እየጠራሽ ነው” አላት። ቬዳ የአደንዛዥ ዕጽና የመጠጥ ሱስ ካለበት ልጅ ጋር ተወዳጅታ ነበር። ሙሉ ሌሊት በዲስኮ ቤቶች ስትጨፍር ታድር ነበር። አባትዋ አጥብቆ ቢከለክላትም ቬዳ የአባትዋን ተቃውሞ ከጉዳይ አልቆጠረችውም።

“አባቴ ከመጠን በላይ ጥብቅ የሆነ ይመስለኝ ነበር” በማለት ቬዳ ትገልጻለች። “በዚያ ጊዜ አሥራ ስምንት ዓመት ሆኖኝ ስለነበረ ሙሉ ሰው የሆንኩና ሁሉንም ነገር ያወቅሁ ይመስለኝ ነበር። አባቴ ክፉና እኔ እንድደሰት የማይፈልግ ይመስለኝ ስለነበረ ከፈቃዱ ወጥቼ የፈለግሁትን አደርግ ነበር።”

ሌላዋ ጂና የተባለች ወጣት ደግሞ “አባቴ ከመጠን በላይ ይጠጣ ነበር። ወላጆቼ እርስ በርሳቸው ይጨቃጨቁና ይጯጯሁ ስለነበረ መተኛት አልችልም ነበር። አልጋዬ ላይ ሆኜ አለቅስ ነበር። እናቴ ትመታኛለች ብዬ ስለምፈራ እንዴት እንደሚሰማኝ ልነግራቸው አልቻልኩም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ ይላል። እኔ ግን ላከብራቸው አልችልም።”

አንተም እንደ ቬዳና ጂና ወላጆችህን ማክበር ያስቸግርህ ይሆናል። ምክንያታዊ እንዳልሆነ የሚሰማህን ነገር እንድታደርግ ያዝህ ወይም በጠባያቸው መጥፎ ምሳሌ እያሳዩህ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ “አባትህንና እናትህን አክብር” ብሎ ያዝዛል። (ኤፌሶን 6:2) አባትንና እናትን ማክበር ምን ነገሮችን ያካትታል? ወላጆች ራሳቸው እነርሱን ማክበር አስቸጋሪ እንዲሆን በሚያደርጉበት ጊዜ እንኳን እነርሱን የምናከብርበት በቂ ምክንያት አለንን?

ማክበር ማለት ምን ማለት ነው?

“ማክበር” ማለት ሕጋዊነት ያለውን ሥልጣን ማወቅና መቀበል ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች “ንጉሥን አክብሩ” የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:17) የአንድ አገር አስተዳዳሪ ከሚያደርገው ጋር ሁልጊዜ ልትስማማ ባትችልም ሥልጣኑን ወይም ቦታውን ማክበር ይኖርብሃል። በቤተሰብ ክልል ውስጥ አምላክ ለወላጆች ወኪሎቹ እንዲሆኑ የተወሰነ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። ፈሪሀ አምላክ ያላቸው ልጆች ይህን ሥልጣን ማክበር ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ልጆች የታይታ አክብሮት ብቻ ማሳየት አይገባቸውም።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማክበር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግሥ መሠረታዊ ትርጉም አንድን ሰው ትልቅ ዋጋ እንዳለው መቁጠር ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ወላጅ ውድ፣ ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው የሚገባና በጣም የሚወደድ ሆኖ መታየት ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ለእነርሱ ሞቅ ያለና አድናቆት የተሞላበት ስሜት እንዲኖረን ይጠይቅብናል። ‘ይሁን እንጂ ይህን ያህል እያስቸገሩኝ እንዴት ለእነርሱ ይህን የመሰለ ስሜት ሊኖረኝ ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

ወላጆችህን ማክበር የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ ምሳሌ 23:22 “የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህንም . . . አትናቃት” ይላል። በየዓመቱ በመላው ዓለም 55 ሚልዮን የሚያክሉ ውርጃዎች እንደሚፈጸሙ ይገመታል። ወላጆችህ እንድትወለድ መፍቀዳቸው ብቻ እንኳን እነርሱን ለማክበር አንድ ምክንያት ይሆናል። አንድ ጊዜ ወላጆቹን ይዳፈር የነበረው ግሪጎሪ ይህን ለመገንዘብ ችሏል። “እናቴ ያደረገችልኝን በሙሉ መገንዘብ ጀመርኩ። ስላላስወረደችኝ ወይም ገና ሕጻን እያለሁ ከቆሻሻ ጋር ስላልጣለችኝ ይሖዋ አምላክን አመሰግነዋለሁ። ስድስታችንን ያሳደገችን ብቻዋን ያለ አባት ነበር። በጣም ከብዶባት እንደነበረ አስታውሳለሁ።

ልጆችን ማሳደግ በጣም ከባድ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው። አንድ በካናዳ የተደረገ ጥናት እንደገለጸው አንድን ልጅ አባትም እናትም ባሉበትና አንድ ልጅ ብቻ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ እስከ 18 ዓመት ድረስ ለማሳደግ ቢያንስ 66,400 ዶላር ወይም ከ330,000 ብር በላይ ይጠይቃል። ወላጆችህ ለአንተ የሚያስፈልገውን ምግብና ልብስ ለማቅረብ ምን ያህል ራሳቸውን መሥዋዕት እንደሚያደርጉ አስብ። ግሪጎሪ እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል:- “አንድ ወቅት ላይ የቀረን ምግብ አንድ ጣሳ በቆሎና ጥቂት ፍርፋሪ ብቻ ነበር። እናታችን ይህንኑ አብስላ ለእኛ ለልጆች ሰጠችን። እርስዋ ግን አልበላችም። ሆዴን ሞልቼ ተኛሁ። ግን እማዬ ለምን አልበላችም ብዬ ሳስብ አደርኩ። አሁን የራሴን ትዳር ከመሠረትኩ በኋላ ግን ለእኛ ስትል መሥዋዕት ማድረግዋ እንደሆነ ተገነዘብሁ። እኔስ ለልጆቼ ስል ጦሜን አድር ይሆን? ብዬ አስባለሁ። ያን ሁሉ እንዴት ችላ እንዳሳለፈች ይገርመኛል።”

የአንተም ወላጆች አንተን ሲያስታምሙ እንቅልፍ በአይናቸው ሳይዞር ያደሩባቸው ብዙ ቀናት እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። የሽንት ጨርቆችህን በየጊዜው መቀየርና የቆሸሹ ልብሶችህን ማጠብ ነበረባቸው። ከ200,000 የሚበልጡ አሜሪካውያን ድጋሚ ምርጫ ቢሰጣቸው ምን ያህል ልጆች እንደሚወልዱ ተጠይቀው ነበር። 54 በመቶ የሚያክሉት ወላጆች አሁን የወለዷቸውን ያህል ልጆች እንደሚወልዱ ተናግረዋል። አንድም ልጅ አልወልድም ያሉት 6 በመቶ የሚያክሉት ብቻ ነበሩ።

ስለዚህ ወላጆችህ ሕይወት ከመስጠታቸውም በላይ ተንከባክበው አሳድገውሃል። በእርግጥም ልታከብራቸው ይገባል።

አስቸጋሪ ወላጆች

ወላጆችህ ቁጡዎች፣ ሰካራሞችና አመንዝሮች በመሆን መጥፎ ምሳሌ የሚሆኑ ከሆነስ? በዚህ ምክንያት ብዙ ችግር ሊደርስብህ እንደሚችል መረዳት አያስቸግርም። እንደነዚህ ያሉትን ወላጆች እንዴት ማክበር ይቻላል?a

ወላጆችህ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ከባድ የሆነ ችግር ወይም የባሕርይ ጉድለት ሊኖራቸው ይችላል። (መክብብ 7:20) ይሁን እንጂ ጉድለት ቢኖራቸውም ሕይወትህን በተወሰነ መጠን እንዲቆጣጠሩ አምላክ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። ሥልጣናቸውንም እንድታከብር አምላክ ይፈልግብሃል። ገዥዎች እንኳን እንዲከበሩ አምላክ እንዳዘዘ አስታውስ። (ሮሜ 13:7) ይህን ለማድረግ የግል ጠባያቸውን ሳንመለከት ሥልጣናቸውን ወይም ቦታቸውን ብቻ ማየት ያስፈልገናል። ስለዚህ ወላጅህ ሥልጣኑን አለአግባብ እንደሚጠቀም ከተሰማህ እሱን ከማቃለል ይልቅ ረጋ ብለህ ለማሳለፍ ሞክር። (ከመክብብ 10:4 ጋር አወዳድር።) ጉዳዩን ለአምላክ ተወው። ምክንያቱም “የሚበድልም የበደለውን በብድራት ይቀበላል፣ ለሰው ፊትም አድልዎ የለም።”​—ቆላስይስ 3:25

ለኑሮ የሚያስፈልግህን የምታገኘው ከወላጅህ እስከሆነ ድረስ የቤተሰቡ ኃላፊ ወላጅህ ከመሆኑ ሐቅ ልትሸሽ አትችልም። መክብብ 8:3, 4 እንዲህ ይላል:- “[ሥልጣን ያለው ሰው] የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና።” በማመጽ ልታሸንፍ አትችልም።

ይሁን እንጂ በወላጆችህ ላይ የሚሰማህን ቅሬታ እንዴት ለማስወገድ ትችላለህ? ወላጆች ለምን እንደዚህ እንዳደረጉ ለመረዳት ሞክር። በተጨማሪም ምን ዓይነት ጥቅሞች እንደሚሰጡህ አስብ። ለምሳሌ ያህል ግድየለሽ የሆነች እናትና ሰካራም የሆነ እንጀራ አባት የነበራት ዶዲ እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “እናቴ ፍቅር አሳይታን የማታውቀው ራስዋ ልጅ ሳለች ብዙ በደል ተፈጽሞባት ስለነበረና እንዴት ፍቅር እንደምታሳይ ያስተማራት ሰው ስላልነበረ ሳይሆን አይቀርም። እንጀራ አባቴም ቢሆን ባልሰከረበት ጊዜ የምናደርጋቸው ነገሮች ያስደስቱታል። የማይሰክርበት ጊዜ ግን ብዙ አይደለም። ይህም ሆኖ ግን እኔና እህቴ መጠለያና ምግብ ያጣንበት ጊዜ የለም።” ስለዚህ ዶዲ ወላጆችዋን ለማክበር የተቻላትን ሁሉ እንዳደረገች ስለምታውቅ ሕሊናዋ ንጹሕ ነው።

አንድን ሰው ካከበርክ የግዴታ ከእርሱ ጋር መስማማት አለብህ ማለት አይደለም። መክብብ 8:2 “በእግዚአብሔር መሐላ ምክንያት የንጉሥን [ወይም የወላጅን] ትዕዛዝ ጠብቅ” በማለት ይመክራል። የአምላክን ሕግ የሚጥስ እስካልሆነ ድረስ ትዕዛዛቸውን በማክበር ለአምላክ ያለህን ፍቅር አሳይ። “ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።”​—ቆላስይስ 3:20

ከዚህም በላይ የአንድ ወላጅ ጠባይ መጥፎ ቢሆንም እንኳን የሚነግርህ ሁሉ ስህተት ነው ብለህ መደምደም አይኖርብህም። በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን የአምላክን ቃል የማስተማር ሥልጣን የተሰጣቸው ሃይማኖታዊ መሪዎች በጣም ምግባረ ብልሹዎች ሆነው ነበር። ኢየሱስ ግን ለሕዝቡ “ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ፣ ጠብቁትም። ነገር ግን . . . እንደ ሥራቸው አታድርጉ” ብሏል። (ማቴዎስ 23:1–3, 25, 26) ሕዝቡ ከአምላክ ቃል የተሰጣቸውን ምክር ቢያከብሩ አምላክ ይባርካቸዋል። አንተም ወላጆችህ የሚሰጡህን አምላካዊ ምክር ብታከብር አምላክ ይባርክሃል።

‘አባቴ ያለኝ ሁሉ ትክክል ነበር’

ከጊዜ በኋላ ቬዳ ለወላጆችዋ የነበራት ዝንባሌ ተለወጠ። ይሁን እንጂ ይህን ትምህርት ያገኘችው ብዙ ችግር ካሳለፈች በኋላ ነበር። በማሪዋናና በቢራ ሰክሮ ይነዳ ከነበረው የወንድ ጓደኛዋ ጋር በመኪና እየሄደች ሳለ መኪናዋ ከቁጥጥር ውጭ ሆነች። በሰዓት መቶ ኪሎ ሜትር ትበር የነበረችው መኪና ከመብራት ምሰሶ ጋር ተጋጨች። መኪናዋ ከጥቅም ውጭ ስትሆን ቬዳ ግንባርዋ ላይ ተፈንክታ ብዙ ደም ፈሰሳት። ልጁ ከዚያ ቦታ ከመጥፋቱም በላይ ሆስፒታል እንኳን መጥቶ አልጠየቃትም።

“ወላጆቼ ሆስፒታል ሲመጡ አባቴ ይለኝ የነበረው ሁሉ ትክክል እንደሆነና ቀድሞውንም ሰምቼአቸው ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ እንደማይደርስብኝ ነገርኳቸው” በማለት ቬዳ ትተርካለች። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቬዳ ወላጆችዋን ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ አደረገች። “ይህ ቀላል አልነበረም” ስትል አምናለች። “ምክንያቱም አሁንም ወደ ዲስኮዎች የመሄድ ፍላጎት ነበረኝ። ቤት መቀመጥ ደግሞ ይሰለቸኝ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክን ለማስደሰት ፈልግሁ። የሠራሁት ከባድ ስህተት ሕይወቴን አሳጥቶኝ ነበር። በዚህም ምክንያት ዝንባሌዬን እንድለውጥ ይሖዋ እንዲረዳኝ አጥብቄ ጸለይኩ።”

ቬዳ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት አግኝታለች። ሥልጣን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን አውቃለች። ብዙዎች ይህን ትምህርት ሳያገኙ በመቅረታቸው በትምህርት ቤት የተሳካ ውጤት ለማግኘት፣ በሥራቸው ለመቆየት፣ ወይም ደስተኛ ትዳር ለመመሥረት ሳይችሉ ቀርተዋል። በአሁኑ ጊዜ ደስተኛ ትዳር መሥርታ የምትገኘው ቬዳ “ቀላል በማይሆንበት ጊዜ እንኳን አባቴን ማክበርን መለማመዴ ለባሌ እንድገዛ በሚገባ ረድቶኛል” ትላለች። ከሌሎች ጋር አስደሳች ዝምድና መመሥረትና በአምላክ ዘንድ ንጹሕ ሕሊና ማግኘት ወላጆችን ከማክበር የሚገኙ ሽልማቶች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ ጽሑፍ አንድ ልጅ ፈጽሞ ሊቋቋም የማይችለውንና አካላዊ ወይም ጾታዊ በደል የሚፈጸምበትን ሁኔታ አይጨምርም። እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎች ልጁ ከቤተሰቡ ውጭ የባለሞያዎችን እርዳታ መጠየቅ ሊያስፈልገው ይችላል። በየካቲት 8, 1981 የእንግሊዝኛ እትም ላይ “በቅርብ ዘመዶች መካከል የሚፈጸም ሩካቤ ሥጋ​—ድብቁ ወንጀል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለፉት ዓመታት ወላጆችህ ያደረጉልህን ሁሉ ማሰላሰልህ እነሱን እንድታከብራቸው ሊገፋፉህ ይገባል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ