ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
የፈለግሁትን ሁሉ ማግኘት የማልችለው ለምንድን ነው?
“እንዲኖሩኝ የምፈልጋቸው በጣም ምርጥ የሆኑ ነገሮች አሉ፤ ሆኖም ወላጆቼ እነዚህን ነገሮች የመግዛት አቅም የላቸውም።”—ማይክ
እንዲኖሩህ የምትፈልጋቸው ሆኖም ሊኖሩህ ያልቻሉ ነገሮች አሉ? ምናልባት አንድ አዲስ ቴፕ፣ ልጆች ሁሉ ያደረጉት ዓይነት ጫማ ወይም ታዋቂ የልብስ ሞድ አውጪ ምልክት የተለጠፈበት አዲስ ጂንስ ሱሪ እንዲኖርህ ትመኝ ይሆናል። አንዳንድ እኩዮችህ እነዚህ ነገሮች ሊኖራቸውና ለሌሎችም በኩራት ሲያሳዩ ትመለከት ይሆናል። ስለዚህ ወላጆችህ እነዚህን ነገሮች የመግዛት አቅም እንደሌላቸው ሲነግሩህ ልትበሳጭ ትችላለህ።
አንዳንድ ቁሳዊ ነገሮች እንዲኖሩህ መፈለግህ በራሱ ስህተት ባይኖረውም ብዙ ወጣቶች ግን እነዚህን ነገሮች የማግኘት ፍላጎታቸው ከልክ ያለፈ ነው። ይህ ደግሞ በአብዛኛው በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፈው ፕሮፓጋንዳ ውጤት ነው። ማራኪ የሆኑ የቴሌቪዥን፣ የመጽሔትና የራዲዮ ማስታወቂያዎች የተወሰኑ የልብስ ዓይነቶችን ካልለበሳችሁ ወይም ታዋቂ የንግድ ምልክት በተለጠፈባቸው እቃዎች ካልተጠቀማችሁ አሳዛኝ ፍጥረቶች ናችሁ የሚል መልእክት የሚያስተላልፉ ይመስላሉ። በመሆኑም በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በአሥራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች በዓመት ከ100 ቢልዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ የሚያጠፉ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም!
በዚያ ላይ ደግሞ የእኩዮች ተጽእኖ አለ። ማርኬቲንግ ቱልስ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “ባለህበት ማኅበረሰብ ውስጥ ባሉት ወጣቶች ዘንድ እንደ ኋላ ቀር ተደርገህ መታየትህ እኩዮችህ ያወጡትን የአቋም ደረጃ አለማሟላትህን ወይም ተቀባይነት ማጣትህን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ማንነትህን ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት ሊሆን ይችላል።” ታዲያ “አሪፍ” ለመሆን የሚያስፈልገው ምንድን ነው? ለብዙዎች ምርጥና ዘመናዊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮችን ማግኘት ነው። እነዚህን ነገሮች ማግኘት የማትችል ከሆነስ? አንድ ክርስቲያን ወጣት “በጣም፣ በጣም አስቸጋሪ ነው” ብሏል። “ታዋቂ የልብስ ሞድ አውጪ ምልክት ያልተለጠፈበት ልብስ ለብሰህ ወደ ትምህርት ቤት ትሄዳለህ፤ እናም ሰው ሁሉ ይሳለቅብሃል።” አንዲት ሌላ ወጣት ደግሞ “አንዳንድ ጊዜ ገሸሽ እንደተደረግሁ ሆኖ ይሰማኛል” ስትል ተናግራለች።
ሰዎች የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ለረዥም ሰዓታት ደፋ ቀና በሚሉባቸው ታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶችም ተመሳሳይ የሆነ ተጽእኖ ሊገጥማቸው ይችላል። እንዲህ ባለ ቤተሰብ ውስጥ የምትኖር ከሆነ የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ትናፍቅ ይሆናል። በበለጸጉ አገሮች የተሠሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችንና ፊልሞችን ማየትህ በእነዚህ ፕሮግራሞችና ፊልሞች ውስጥ የታዩትን ውድ ልብሶች፣ ቤቶችና መኪናዎች የማግኘት ፍላጎት አሳድሮብህ ይሆናል። እነዚህን ነገሮች የማግኘቱ ጉዳይ የሕልም እንጀራ ሲሆንብህ ታማርር አልፎ ተርፎም በሐዘን ስሜት ትዋጥ ይሆናል።
የምትኖረው በድሃ አገርም ይሁን በበለጸገ አገር የተወሰኑ ነገሮችን ለማግኘት ባለመቻልህ መበሳጨትህ ወይም ተስፋ መቁረጥህ ይጎዳሃል እንጂ አይጠቅምህም። ከዚህም በተጨማሪ ከወላጆችህ ጋር ዘወትር እንድትጨቃጨቅ ሊያደርግህ ይችላል። አሁን የሚነሳው ጥያቄ ይህን ችግር እንዴት ልትወጣው ትችላለህ? የሚለው ነው።
ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
በመጀመሪያ፣ ይሖዋ አምላክ ሕዝቡ በድህነት እንዲኖሩ ወይም በእርግጥ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሳያገኙ እንዲኖሩ እንደማይፈልግ መገንዘብ አለብህ። አምላክ አዳምንና ሔዋንን ያስቀመጣቸው ለማየት ደስ የሚያሰኙ ዛፎች በሞሉበት ውብ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንጂ በቆሻሻ መጣያ ቦታ አልነበረም። (ዘፍጥረት 2:9) ከጊዜ በኋላ እንደ አብርሃም፣ ኢዮብና ሰሎሞን የመሳሰሉ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ብዙ ንብረት አካብተው ነበር። (ዘፍጥረት 13:2፤ ኢዮብ 1:3) እንዲያውም ሰሎሞን እጅግ ብዙ ወርቅ ስለነበረው በንግሥናው ዘመን ብር ከቁብ “አይቆጠርም” ነበር!—1 ነገሥት 10:21, 23
በጥቅሉ ሲታይ ግን አብዛኞቹ የአምላክ ሕዝቦች ያላቸው ገቢ መጠነኛ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ድሀ ነበር፤ ‘ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ’ እንኳን አልነበረውም። (ማቴዎስ 8:20) ሆኖም ኢየሱስ የሚፈልገውን ነገር ማግኘት ባለመቻሉ እንዳማረረ የሚናገር አንድም ሐሳብ አናገኝም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ሲል አስተምሯል:- “ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ . . . ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:31-33
ይህ ማለት ግን አንድ ሰው የፋሽን ልብሶች ወይም የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች የማግኘት ፍላጎቱን አምላክ የማሟላት ግዴታ አለበት ማለት አይደለም። አምላክ የሚሰጠን የሚያስፈልገንን እንጂ የምንፈልገውን ሁሉ አይደለም። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ባለን “ምግብና ልብስ” እንድንረካ የሚያሳስበን። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ሆኖም ግልጹን ለመናገር ባለን ነገር ረክቶ መኖር ቀላል አይደለም። ማይክ የተባለ አንድ ወጣት “በምትፈልጋቸውና በሚያስፈልጉህ ነገሮች መካከል የማያቋርጥ ትግል አለብህ” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ራስ ወዳድ ከሆነው ዝንባሌያችን በተጨማሪ የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ የሚያሳድረውንም ተጽእኖ መዋጋት አለብን። (1 ዮሐንስ 5:19) ረዥም ዕድሜ ካስቆጠሩት የማታለያ ዘዴዎቹ መካከል አንደኛው ደግሞ ሰዎች የቀረባቸው ነገር እንዳለ ሆኖ እንዲሰማቸው ማድረግ ነው። ሔዋን ፍጹም በሆነ ገነት ውስጥ ብትኖርም እንኳ የተነፈገችው ነገር እንዳለ ሆኖ እንዲሰማት ተደርጋ ነበር።—ዘፍጥረት 3:2-6
ባለህ ነገር ረክተህ እንዳትኖር በሚያደርግ ወጥመድ ውስጥ እንዳትወድቅ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ነገሩ ተደጋግሞ የተነገረ ቢመስልም ያሉህን ነገሮች ቆም ብለህ እንድታስብ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ስለሌሉህ ነገሮች በማሰብ በአፍራሽ አመለካከት ማጥ ውስጥ እንዳትገባ ተጠንቀቅ። አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ፤ ስላሉህ ነገሮች አስብ። (ከፊልጵስዩስ 4:8 ጋር አወዳድር።) ማይክ “የምፈልጋቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ስለ እነሱ ሳውጠነጥን አልውልም” ብሏል።
በተጨማሪም ስሜትህን የሚቀሰቅሱ መሠሪ ማስታወቂያዎችን በጥርጣሬ ዓይን መመልከቱ ጠቃሚ ነው።a (ምሳሌ 14:15) እነዚያን የስኒከር ጫማዎች ወይም ያንን የሲዲ ማጫወቻ ካላገኘሁ “ሞቼ እገኛለሁ” ወደሚል መደምደሚያ ከመድረስህ በፊት ስለ ጉዳዩ በርጋታ አስብ። ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘ይህ ነገር በእርግጥ ያስፈልገኛል? ተግባራዊ ጠቀሜታ አለው? ያለኝ ነገር በቂ አይደለም?’ በተለይ ደግሞ ሁሉን ማግበስበስን የሚያራምዱ ማስታወቂያዎችን በጥርጣሬ ዓይን መመልከቱ ጥሩ ነው። በ1 ዮሐንስ 2:16 ላይ የሚገኙት የሐዋርያው ዮሐንስ ቃላት ሊታሰብባቸው የሚገባቸው ናቸው:- “በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም . . . እንጂ ከአባት [አይደለም]።”
አንድ ነገር የግድ እንደሚያስፈልግህ በሚሰማህ ጊዜ
የግድ የሚያስፈልግህ ነገር ቢኖርስ? ስለ ጉዳዩ ለወላጆችህ ከመንገርህ በፊት አስቀድመህ በጉዳዩ ላይ አንዳንድ ጥናቶች አካሂድ። ይህ ዓይነቱ እቃ ለምን እንደሚያስፈልግህ፣ እንዴት ልትጠቀምበት እንዳሰብክና ይጠቅመኛል ብለህ የምታስበው ለምን እንደሆነ ግልጽ በሆነ መንገድ ለማብራራት ተዘጋጅ። ምናልባት ወላጆችህ በቤተሰቡ ባጀት ውስጥ ሊያስገቡት ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለጊዜውም ቢሆን የመግዛቱ አቅም ባይኖራቸውስ? በትእግሥት ከመጠበቅ ሌላ ምንም አማራጭ ላይኖርህ ይችላል። (መክብብ 7:8) በእነዚህ ‘አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት’ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው የሚጠይቋቸውን ሁሉ ማሟላት አይችሉም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ወላጆችህን የሆነ ያልሆነውን በመጠየቅ የማታስቸግራቸው ከሆነ አድካሚ ሥራቸውን በትንሹም ቢሆን ልታቀልላቸው ትችላለህ።
ይሁን እንጂ አንተም ቅድሚያውን ልትወስድ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል የኪስ ገንዘብ ታገኛለህ? እንግዲያው ገንዘብህን በባጀት መጠቀምን በመማር በየወሩ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ ለማስቀመጥ ጥረት አድርግ። ምናልባትም በአቅራቢያችሁ በሚገኝ ባንክ የቁጠባ ሒሳብ ልትከፍት ትችል ይሆናል። (ከሉቃስ 19:23 ጋር አወዳድር።) አቢጋኤል የምትባል አንዲት ልጃገረድ ያደረገችው ይህንኑ ነበር። እንዲህ ትላለች:- “ገንዘቤን ለሁለት ከፍዬ አስቀምጣለሁ፤ አንደኛው በባንክ ሒሳቤ ላይ የምጨምረው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለወጪዎቼ መሸፈኛ የማውለው ነው።” ዕድሜህ የሚፈቅድ ከሆነ ምናልባት ጊዜያዊ ሥራዎችን ወይም በትርፍ ሰዓት የሚሠሩ ሥራዎችን ለመሥራት ትችል ይሆናል።b በዚያም ሆነ በዚህ ወላጆችህ የግድ ለመግዛት የምትፈልገው ነገር እንዳለና ለዚያም የሚሆን ገንዘብ እያጠራቀምህ መሆኑን ሲመለከቱ የሚችሉ ከሆነ የተወሰነውን ወጪ እንዲሸፍኑ ይገፋፉ ይሆናል።
እቃዎችን በምትሸምትበት መንገድ ላይ አንዳንድ ለውጦች ማድረጉም ሊጠቅምህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የአንድ እቃ ዋጋ በጣም ውድ ከሆነ ተከራክረህ ዋጋውን ልታስቀንስ ትችል ይሆናል። ይህ ካልሆነ ደግሞ እቃው ይረክስ እንደሆነ ቆየት ብሎ ማየቱ ጥሩ ነው። ይህንኑ እቃ በቅናሽ ዋጋ ለማግኘት ትችል እንደሆነ ሌሎች ሱቆችን እየተዘዋወርክ ተመልከት። የእቃዎችን ጥራት ለማወቅ አገላብጠህ ተመልከታቸው፤ አንዳንድ ጊዜ ጥራት ያላቸው የአገር ውስጥ ምርቶች በጥሩ ዋጋ ሊገኙ ይችላሉ።c
ባለህ መርካትን ተማር
ምሳሌ 27:20 እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “ሲኦልና ጥፋት እንዳይጠግቡ፣ እንዲሁ የሰው ዓይን አይጠግብም።” አዎን፣ በቃኝ እንደማያውቀው መቃብር አንዳንድ ሰዎች ምንም ያህል ብዙ ነገር ቢኖራቸው ሁልጊዜ ተጨማሪ ነገር ለማግኘት ይፈልጋሉ። እንዲህ ያለውን የራስ ወዳድነት አስተሳሰብ አስወግድ። ስስት የኋላ ኋላ ጭንቀትና ሐዘን ማስከተሉ የማይቀር ነው። ዮናታን የሚባል አንድ ወጣት እንዲህ ይላል:- “ደስታህ የተመካው የተለያዩ ነገሮችን በማግኘት ላይ ብቻ ከሆነ በፍጹም ደስተኛ አትሆንም። ሁልጊዜ እንዲኖርህ የምትፈልገው አንድ አዲስ ነገር ይኖራል። ባለህ ነገር መደሰትን መማር ያስፈልግሃል።”
ባለህ የምትረካ ከሆነ ከእኩዮችህ የሚመጣብህን ተጽእኖ ልታሸንፍ ትችላለህ። ወጣቱ ቪንሰንት እንዲህ ይላል:- “በአንድ ሰው እግር ላይ አንድ አዲስ ስኒከር ጫማ ስላየሁ ብቻ እኔም መግዛት አለብኝ ማለት አይደለም።” እርግጥ አንዳንድ ጊዜ የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት አለመቻልህ ያበሳጭህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚያውቅ በፍጹም አትርሳ። (ማቴዎስ 6:32) በቅርቡም ‘ሕይወት ላለው ሁሉ መልካሙን ያጠግባል።’—መዝሙር 145:16
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በየካቲት 1999 ንቁ! ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ገንዘብ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b በነሐሴ 22, 1998 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ማስታወቂያ—ምን ያህል ተጽእኖ አሳድሮብሃል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ለማግኘት በጥር 22, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” የሚለውን አምድ ተመልከት።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ታዋቂ የልብስ ሞድ አውጪ ምልክት ያልተለጠፈበት ልብስ ለብሰህ ወደ ትምህርት ቤት ትሄዳለህ፤ እናም ሰው ሁሉ ይሳለቅብሃል።”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ባታገኝም ደስተኛ መሆን ትችላለህ