የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 11/15 ገጽ 13-18
  • ታላቁን ፈጣሪህን አስብ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታላቁን ፈጣሪህን አስብ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በቀደሙት ዘመናት የነበሩ ግሩም ምሳሌዎች
  • አሁኑኑ ይሖዋን አስብ!
  • እርጅና የሚያስከትለው ውጤት
  • ፈጣሪያቸውን የሚያስቡ ሰዎች የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው?
  • ሕይወታችሁን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • በአምላክ ፊት ያለባችሁን ሁለንተናዊ ግዴታ እየፈጸማችሁ ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • “በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ”
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ (2016)
  • የጭንቀት ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ይሖዋን ማገልገል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 11/15 ገጽ 13-18

ታላቁን ፈጣሪህን አስብ!

“የጭንቀት ቀን ሳይመጣ . . . [“ታላቁን፣” NW] ፈጣሪህን አስብ።”​—⁠መክብብ 12:​1

1. ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ወጣቶች የወጣትነት ሕይወታቸውንና ጉልበታቸውን እንዴት ሊጠቀሙበት ይገባል?

ይሖዋ ፈቃዱን እንዲያደርጉ ለአገልጋዮቹ ኃይል ይሰጣል። (ኢሳይያስ 40:​28-31) በየትኛውም ዕድሜ ላይ ለሚገኙ አገልጋዮቹ ኃይል ይሰጣል። ሆኖም ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ወጣቶች በተለይ የወጣትነት ሕይወታቸውንና ጉልበታቸውን በይሖዋ አገልግሎት ላይ ለማዋል መፈለግ ይኖርባቸዋል። እንዲህ በማድረግ ‘ሰባኪው’ ማለትም የጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን የሰጠውን ምክር ልብ እንዳሉት ያሳያሉ። “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት [“ታላቁን፣” NW] ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ” በማለት አጥብቆ አሳስቧል።​—⁠መክብብ 1:​1፤ 12:​1

2. ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያን ወላጆች ያሏቸው ልጆች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

2 በወጣትነት ዕድሜ ታላቁን ፈጣሪ ስለማሰብ ሰሎሞን የሰጠው ምክር በቅድሚያ የተነገረው በእስራኤል ይገኙ ለነበሩ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ነበር። እነዚህ ወጣቶች ለይሖዋ በተወሰነ ብሔር መካከል የተወለዱ ነበሩ። ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያን ወላጆች ስላሏቸው ልጆችስ ምን ለማለት ይቻላል? ታላቁን ፈጣሪያቸውን ማሰብ እንዳለባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ካደረጉ አምላካቸውን ያስከብራሉ ራሳቸውንም ይጠቅማሉ።​—⁠ኢሳይያስ 48:​17, 18

በቀደሙት ዘመናት የነበሩ ግሩም ምሳሌዎች

3. ዮሴፍ፣ ሳሙኤልና ዳዊት ምን ምሳሌ ትተውልናል?

3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ ብዙ ወጣቶች ታላቁን ፈጣሪያቸውን በማሰብ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ፈጣሪውን አስቧል። የጶጢፋር ሚስት ከእርሷ ጋር የጾታ ብልግና እንዲፈጽም በተፈታተነችው ጊዜ “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” በማለት በጽኑ ተቃውሟታል። (ዘፍጥረት 39:​9) ሌዋዊው ሳሙኤል በልጅነቱ ብቻ ሳይሆን ዕድሜውን በሙሉ ፈጣሪውን አስቧል። (1 ሳሙኤል 1:​22-28፤ 2:​18፤ 3:​1-5) በቤተ ልሔም ይኖር የነበረው ወጣቱ ዳዊትም ፈጣሪውን እንዳሰበ ምንም ጥርጥር የለውም። ግዙፉን ፍልስጥኤማዊ ጎልያድን በገጠመበት ጊዜ ምን ያህል በአምላክ እንደሚታመን አሳይቷል። እንዲህ አለ:- “አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፣ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፤ . . . ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደለ ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ወዲያው ጎልያድ ተገደለ፤ ፍልስጥኤማውያንም እግሬ አውጪኝ ብለው ፈረጠጡ።​—⁠1 ሳሙኤል 17:​45-51

4. (ሀ) በምርኮ የተወሰደችው እስራኤላዊት ልጃገረድና ወጣቱ ንጉሥ ኢዮስያስ ታላቁን ፈጣሪያችንን እንዳሰቡ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ጊዜ ፈጣሪውን እንዳሰበ ያሳየው እንዴት ነው?

4 ታላቁን ፈጣሪ ያሰበች ሌላዋ ወጣት በምርኮ የተወሰደች አንዲት እስራኤላዊት ልጃገረድ ነች። ይህች ልጃገረድ ንዕማን ለሚባል የሶርያ ሠራዊት አለቃ ሚስት ግሩም ምስክርነት በመስጠቷ ይህ ሰው ወደ አምላክ ነቢይ ዘንድ በመሄድ ከያዘው የሥጋ ደዌ በሽታ ሊፈወስና የይሖዋ አምላኪ ሊሆን ችሏል። (2 ነገሥት 5:​1-19) ወጣቱ ንጉሥ ኢዮስያስም የይሖዋን ንጹህ አምልኮ በቆራጥነት አስፋፍቷል። (2 ነገሥት 22:​1 እስከ 23:​25) ሆኖም ገና በለጋ ዕድሜው ታላቁን ፈጣሪውን በማሰብ የላቀ ምሳሌ የሚሆነው የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው። የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ምን ነገር እንደተከሰተ ልብ በል። ወላጆቹ የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ሄደው ነበር። ከዚያም ወደ አገራቸው ለመመለስ በጉዞ ላይ ሳሉ ኢየሱስ አብሯቸው እንደሌለ አወቁ። ስለዚህም ሊፈልጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በሦስተኛው ቀን በቤተ መቅደስ ውስጥ ከአስተማሪዎች ጋር ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆኑ ጥያቄዎች ላይ ሲወያይ አገኙት። እናቱ በመጥፋቱ ምን ያህል እንደተጨነቁ ስትነግረው እርሱም “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” አላት። (ሉቃስ 2:​49) በቤተ መቅደስ ማለትም ‘በአባቱ ቤት’ ተቀምጦ መንፈሳዊ ቁምነገር መገብየት ለኢየሱስ ጠቃሚ ነገር ነበር። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ታላቁ ፈጣሪያችን የሚሰጠውን ትክክለኛ እውቀት መቅሰም የምንችልበት በጣም ግሩም ቦታ ነው።

አሁኑኑ ይሖዋን አስብ!

5. በመክብብ 12:​1 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን ሰባኪው የተናገራቸውን ቃላት በራስህ አባባል እንዴት ብለህ ትገልጻቸዋለህ?

5 በሙሉ ልቡ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ነገ ዛሬ ሳይል የይሖዋን አገልግሎት ለመጀመርና በቀረው የሕይወት ዘመኑ በሙሉ አምላክን ለማገልገል ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ፈጣሪን ሳያስብ የወጣትነት ሕይወቱን በከንቱ ያሳለፈ ሰውስ ምን ተስፋ አለው? ሰባኪው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት እንደሚከተለው ብሏል:- “የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ።”​—⁠መክብብ 12:​1

6. አረጋዊው ስምዖንና አረጋዊቱ ሐና ታላቁን ፈጣሪያቸውን እንዳሰቡ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

6 መቼም “የጭንቀት ቀን” የሆነው እርጅና ሲመጣ ማንም የሚደሰት የለም። ሆኖም አምላክን የሚያስቡ አረጋውያን ደስተኞች ናቸው። ለምሳሌ ያህል አረጋዊው ስምዖን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሕፃኑን ኢየሱስን በእቅፉ ይዞ እንደሚከተለው ሲል በደስታ ተናግሯል:- “ጌታ ሆይ፣ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” (ሉቃስ 2:​25-32) የሰማንያ አራት ዓመቷ ሐናም ፈጣሪዋን አስባለች። ከቤተ መቅደስ ተለይታ ስለማታውቅ ሕፃኑን ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደስ ባመጡት ጊዜ በዚያ ነበረች። “በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።”​—⁠ሉቃስ 2:​36-38

7. መላ ዕድሜያቸውን በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፉ ሰዎች ሁኔታ ምን ይመስላል?

7 መላ ዕድሜያቸውን በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፉ ዛሬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የዕድሜ መግፋት ባስከተለባቸው ድካምና የአቅም ገደብ ሊሰቃዩ ይችላሉ። ቢሆንም ምንኛ ደስተኞች ናቸው! እኛም ቢሆን ያሳለፉትን የታማኝነት አገልግሎት በጣም እናደንቃለን። ይሖዋ በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል ምንም የማይበግረውን ኃይሉን እየተጠቀመ እንዳለና ኢየሱስ ክርስቶስን ኃያል ሰማያዊ ንጉሥ አድርጎ እንደሾመ ስለሚያውቁ ‘የይሖዋ ደስታ’ አላቸው። (ነህምያ 8:​10) ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን የሚከተለውን ምክር ሰምተው እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ አሁን ነው:- “ጕልማሶችና ቈነጃጅቶች፣ ሽማግሌዎችና ልጆች፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፤ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፣ ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው።”​—⁠መዝሙር 148:​12, 13

8, 9. (ሀ) “የጭንቀት ቀን” ምንም እርካታ የሌለው የሚሆነው ለእነማን ነው? እንዲህ የሚሆንባቸውስ ለምንድን ነው? (ለ) መክብብ 12:​2ን እንዴት ብለህ ታብራራለህ?

8 “የጭንቀት ቀን” ማለትም የእርጅና ዕድሜ ታላቁን ፈጣሪያቸውን ለማያስቡና ክብራማ ዓላማዎቹን ለማያውቁ ሰዎች ምንም እርካታ የሌለው ምናልባትም አስጨናቂ ይሆንባቸዋል። እርጅና የሚያስከትላቸውን መከራዎችና ሰይጣን ከሰማይ ከተባረረበት ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጅ ላይ እየደረሱ ያሉትን ወዮታዎች መቋቋም የሚያስችል መንፈሳዊ ማስተዋል የላቸውም። (ራእይ 12:​7-12) በመሆኑም ሰባኪው “ፀሐይና ብርሃን ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፣ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ” ፈጣሪያችንን እንድናስብ አጥብቆ ይመክረናል። (መክብብ 12:​2) እነዚህ ቃላት የያዙት ቁምነገር ምንድን ነው?

9 ሰሎሞን የወጣትነት ዕድሜን ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ጥርት ባለ ሰማይ ላይ ብርሃናቸውን ከሚፈነጥቁበት ከፍልስጤም ምድር የበጋ ወቅት ጋር አመሳስሎታል። በዚህ ወቅት ሁሉ ነገር ብሩህ ሆኖ ይታያል። ሆኖም አንድ ሰው በሚያረጅበት ጊዜ ቅዝቃዜና ዝናብ እንደማይለየው የክረምት ወቅት ቀኖቹ ሁሉ ችግር የሚፈራረቅባቸው ይሆኑበታል። (ኢዮብ 14:​1) አንድ ሰው ፈጣሪን ቢያውቅና በበጋ በተመሰለው የሕይወት ዘመኑ እርሱን ሳያገለግል ቢቀር ምንኛ ያሳዝናል! በተለይ ከንቱ የሆኑ ነገሮችን ሲያሳድዱ በወጣትነት ዕድሜያቸው ይሖዋን የማገልገል አጋጣሚ ያመለጣቸው ሰዎች በክረምት በተመሰለው የእርጅና ዘመን ሁሉም ነገር ጨለማ ይሆንባቸዋል። በየትኛውም የዕድሜ ክልል እንገኝ የነቢዩ ሙሴ ታማኝ ጓደኛ እንደነበረው እንደ ካሌብ ‘ይሖዋን ፈጽመን እንከተል።’​—⁠ኢያሱ 14:​6-9

እርጅና የሚያስከትለው ውጤት

10. (ሀ) “ቤት ጠባቆች” (ለ) “ኃያላን ሰዎች” ምን ያመለክታሉ?

10 ቀጥሎ ሰሎሞን “ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፣ ኃያላን ሰዎችም በሚጎብጡበት፣ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፣ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት” በማለት እርጅና የሚያስከትላቸውን ችግሮች ጠቅሷል። (መክብብ 12:​3) እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ቤት” የሰውን አካል ያመለክታል። (ማቴዎስ 12:​43-45፤ 2 ቆሮንቶስ 5:​1-8) “ጠባቆች” የተባሉት ደግሞ አካልን ከጉዳት የሚጠብቁትና የሚያስፈልገውን ነገር የሚያቀርቡለት እጆች ናቸው። በእርጅና ወቅት ከድካም፣ ከመንፈስ መረበሽና ከመዛል የተነሳ ይንቀጠቀጣሉ። “ኃያላን ሰዎች” ማለትም እግሮች ብርቱ ድጋፍ ከመሆን ይልቅ ስለሚብረከረኩና አሸብርከው ስለሚቀሩ መጎተት ይጀምራሉ። ይሁን እንጂ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በዕድሜ የገፉ የእምነት ባልደረቦችን ስታይ ደስ አይልህም?

11. “ፈጭታዎች” እና ‘በመስኮት ሆነው የሚመለከቱ’ የተባሉት በምሳሌያዊ አነጋገር ምን ያመለክታሉ?

11 ‘ጥቂት በመሆናቸው ምክንያት ፈጭታዎች ሥራ ይፈታሉ።’ ግን ይህ ምን ማለት ነው? በእርጅና ወቅት ጥርስ ስለሚበሰብስ ወይም ስለሚወልቅ የሚቀረው ጥቂት ብቻ ይሆናል። ጠንከር ያለ ምግብ ማኘክ በጣም አስቸጋሪ ወይም ከናካቴው የማይቻል ይሆናል። “በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ” ማለትም ዓይኖች ይደክማሉ ወይም ጭራሹኑ ይጨልማሉ።

12. (ሀ) ‘ወደ አደባባይ የሚያስወጡት ደጆች የተዘጉት’ እንዴት ነው? (ለ) አረጋውያን ስለሆኑት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ምን ይሰማሃል?

12 ሰባኪው “በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን፤ የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፣ ከወፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፣ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ” በማለት ይቀጥላል። (መክብብ 12:​4) ሁለቱ የአፍ ደጆች ማለትም ከንፈሮች “በቤት” ወይም በአካል ውስጥ ያለውን ነገር ለመግለጽ በሰፊው ወይም ሙሉ በሙሉ አይከፈቱም። ምንም ነገር ወደ ‘አደባባይ’ አያወጡም። ሆኖም የአምላክን መንግሥት በቅናት ስለሚያውጁ አረጋውያን ምን ለማለት ይቻላል? (ኢዮብ 41:​14 የ1980 ትርጉም) እንደምንም እያዘገሙ ከቤት ወደ ቤት ይሄዱ እንዲሁም በጭንቅ ይናገሩ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ያህን ያወድሳሉ!​—⁠መዝሙር 113:​1

13. ሰባኪው አረጋውያን የሚገጥሟቸውን ሌሎች ችግሮች የገለጸው እንዴት ነው? ሆኖም የክርስቲያን አረጋውያን ሁኔታ ምንድን ነው?

13 ጥርሳቸው አልቆ በድዳቸው ምግብ ስለሚያላምጡ የወፍጮ ድምፅ ይላሻል። ያረጁ ሰዎች ሲተኙ ጥሩ እንቅልፍ አይወስዳቸውም። የወፍ ድምፅ እንኳ ያባንናቸዋል። የሚያንጎራጉሩት ዜማ ጥቂት ከመሆኑም ሌላ የድምፅ አወጣጣቸው ደካማ ነው። “ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች” ማለትም የዜማ ድምፆች ‘ዝግ’ ይላሉ። በዕድሜ የገፉ ሰዎች ሌሎች የሚያሰሙትን ዜማ መስማት ያቅታቸዋል። ሆኖም በዕድሜ የገፉት ቅቡዓንና ከእነሱ ብዙም ወጣት ያልሆኑት ጓደኞቻቸው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አምላክን በመዝሙር ያወድሳሉ። እነዚህ አረጋውያን ከጎናችን ሆነው በጉባኤ መካከል ይሖዋን ሲያወድሱ መስማት ምንኛ ያስደስታል!​—⁠መዝሙር 149:​1

14. ያረጁ ሰዎች ምን ነገር ይፈራሉ?

14 በተለይ ፈጣሪን ቸል ላሉ ብዙ አረጋውያን ሁኔታው እንዴት አሳዛኝ ነው! ሰባኪው እንዲህ ይላል:- “ከፍ ያለውን ደግሞ ሲፈሩ፣ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን፤ ለውዝም ሲያብብ፣ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፣ ፈቃድም ሲጠፋ፤ ሰው ወደ ዘላለም ቤት ሲሄድ፣ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ።” (መክብብ 12:​5) አብዛኞቹ አረጋውያን ከፍታ ያለው ነገር ላይ ሲሆኑ እወድቃለሁ ብለው በጣም ይፈራሉ። ሌላው ቀርቶ ከፍታ ያለው ነገር ቀና ብለው ሲመለከቱ ጭው ይልባቸዋል። ሕዝብ በሚበዛበት ጎዳና ላይ ሲጓዙ ሌባ ጉዳት ያደርስብኛል ወይም ጥቃት ይሰነዝርብኛል ብለው በማሰብ በፍርሃት ይዋጣሉ።

15. ‘ለውዝ አበበ’ እንዲሁም ‘አንበጣ ከበደ’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

15 “ለውዝም ሲያብብ” ሲል ያረጁ ሰዎች ፀጉራቸው እንደሚሸብትና ጥጥ እንደሚመስል ማመልከቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሸብቶ ጥጥ የመሰለው ፀጉር እንደ ለውዝ ዛፍ ነጭ አበባ ይረግፋል። ምናልባትም ጎብጠውና እጆቻቸው ወደታች ተንጠልጥለው ወይም ወገባቸውን ይዘው ክርኖቻቸው ወደ ላይ ሾለው ‘ሰውነታቸው ከብዷቸው ቀስ እያሉ ሲራመዱ’ አንበጣ ይመስላሉ። በመጠኑም ቢሆን እንደዚያ የመሰልን ብንኖር ብርቱና ፈጣን የሆነው የይሖዋ የአንበጣ ሠራዊት ክፍል መሆናችንን ሌሎች ሰዎች እንዲያዩ እናድርግ!​—⁠ግንቦት 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-13 ተመልከት።

16. (ሀ) ‘ፈቃድም ሲጠፋ’ የሚለው አባባል ምን ያመለክታል? (ለ) የሰው ‘የዘላለም ቤት’ ምንድን ነው? ወደ ሞት አፋፍ እየቀረበ መሆኑን የሚጠቁሙት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

16 የቀረበላቸው ምግብ የቱንም ያህል ጥሩ ጣዕም ያለው ቢሆን የምግብ ፍላጎታቸው እንደበፊቱ አይሆንም። “ፈቃድም ሲጠፋ” የሚለው አባባል አንድ ሰው ሲያረጅ የምግብ ፍላጎቱ እየቀነሰ እንደሚሄድና ምንም ዓይነት የምግብ ማጣፈጫ ቅመም ፍላጎቱን ሊቀሰቅሰው እንደማይችል ያመለክታል። እነዚህ ነገሮች “ወደ ዘላለም ቤት” ማለትም ወደ መቃብር አፋፍ እየቀረበ መሆኑን ያሳያሉ። ፈጣሪውን ሳያስብ የቀረና አምላክ በትንሣኤ እንዳያስታውሰው የሚያደርግ የክፋት ጎዳና ይከተል ከነበረ መቃብሩ የዘላለም ቤቱ ይሆናል። ያረጁ ሰዎች የሚያሰሙት የሐዘን እንጉርጉሮና የሰቆቃ ሮሮ ወደ ሞት አፋፍ መቅረባቸውን የሚያሳይ ነው።

17. “የብር ድሪ” ተበጠሰ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ‘የወርቅ ኩስኩስት’ ምንን ሊያመለክት ይችላል?

17 “የብር ድሪ ሳይበጠስ፣ የወርቅም ኩስኩስት ሳይሰበር፣ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፣ መንኮራኩሩም በጉድጓድ ላይ ሳይሰበር” ታላቁን ፈጣሪያችንን እንድናስብ በጥብቅ ተመክረናል። (መክብብ 12:6) “የብር ድሪ” አከርካሪን የሚያመልክት ሊሆን ይችላል። ወደ አንጎል መልእክት የሚተላለፍበት ይህ አስደናቂ መስመር ሊጠገን በማይችል ሁኔታ ጉዳት ከደረሰበት ሰውዬው እንደሚሞት የተረጋገጠ ነው። ‘የወርቅ ኩስኩስት’ ከአከርካሪ አጥንት ጋር ተጋጥሞ በሚገኘው በራስ ቅል ውስጥ የሚገኘውን አንጎልን ሊያመለክት ይችላል። እንደ ወርቅ ውድ የሆነው አንጎል ሲሰበር ማለትም ሥራውን ሲያቆም ሞትን ያስከትላል።

18. ‘በምንጭ አጠገብ ያለው’ ምሳሌያዊ ‘ማድጋ’ ምንድን ነው? ሲሰበርስ ምን ይከሰታል?

18 ‘ማድጋ በምንጭ አጠገብ’ የተባለው ደግሞ ደምን ተቀብሎ መልሶ ወደ ሰውነት የሚያሰራጨውን ልብን ያመለክታል። በሞት ጊዜ ልብ ለሰውነት እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ደምን መቀበል፣ መያዝና መርጨት ስለማይችል ልክ በምንጭ አጠገብ እንደተሰበረ ማድጋ ይሆናል። ‘መንኮራኩሩ በጉድጓድ ላይ በመሠበሩ’ ሕይወትን ጠብቆ የሚያቆየው ደም በሰውነት ውስጥ መዘዋወሩ ያከትምለታል። በ17ኛው መቶ ዘመን ሐኪሙ ዊልያም ሃርቬይ የደም ዝውውር እንዴት እንደሚካሄድ ከማስረዳታቸው ከረጅም ዘመን በፊት ይሖዋ የደም ዝውውርን በተመለከተ ለሰሎሞን ገልጦለት ነበር።

19. በሞት ጊዜ በመክብብ 12:​7 ላይ የሚገኙት ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው?

19 ሰባኪው ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፣ ነፍስም [“መንፈስም፣” NW] ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።” (መክብብ 12:​7) “መንኮራኩሩ” ሲሰበር መጀመሪያውኑ ከአፈር የተሠራው ሰብአዊ አካል ወደ አፈር ይመለሳል። (ዘፍጥረት 2:​7፤ 3:​19) ነፍስ ሟች የሆነበት ምክንያት ከአምላክ የተገኘው መንፈስ ወይም የሕይወት ኃይል ወደ ባለቤቱ ወደ ፈጣሪያችን የሚመለስ በመሆኑ ነው።​—⁠ሕዝቅኤል 18:​4, 20፤ ያዕቆብ 2:​26 NW

ፈጣሪያቸውን የሚያስቡ ሰዎች የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው?

20. ሙሴ በመዝሙር 90:​12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ጸሎት ሲያቀርብ ጥያቄው ምን ነበር?

20 ታላቁን ፈጣሪያችንን ማሰብ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሰሎሞን ቁልጭ አድርጎ ገልጾታል። ይሖዋን ለሚያስቡና በሙሉ ልባቸው ፈቃዱን ለሚያደርጉ ሰዎች ሕይወት ማለት ዛሬ ያለው በአንጻራዊ ሁኔታ አጭር የሆነና በመከራ የተሞላ ሕይወት ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ወጣትም ሆኑ በዕድሜ የገፉ “ጥበበኛ ልብ እንዲኖረን በሚያስችል መንገድ ዘመናችንን እንዴት መቁጠር እንዳለብን አሳየን” ሲል እንደ ጸለየው እንደ ሙሴ ያለ አመለካከት አላቸው። ይህ ትሑት የአምላክ ነቢይ እርሱም ሆነ የእስራኤል ሕዝብ ‘የሕይወት ዘመናቸውን’ በቁም ነገር በመመልከትና አምላክን በሚያስደስት መንገድ በመጠቀም ረገድ ጥበብ ማሳየት ይችሉ ዘንድ ይሖዋ እንዲመራቸው ወይም እንዲያስተምራቸው ከልቡ ተማጽኗል።​—⁠መዝሙር 90:​10, 12 NW

21. ቀኖቻችንን ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ መቁጠር ከፈለግን ምን ማድረግ አለብን?

21 በተለይ ወጣቶች ሰባኪው ፈጣሪን ስለማሰብ የሰጠውን ምክር ልብ ሊሉት ይገባል። ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ በጣም ግሩም የሆነ አጋጣሚ አላቸው! ሆኖም በየትኛውም ዕድሜ ላይ ብንገኝ በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ ቀኖቻችንን ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ መቁጠር ከተማርን እንደዚያ በማድረግ ለዘላለም መቀጠል እንችላለን። (ዳንኤል 12:​4፤ ዮሐንስ 17:​3) እርግጥ ነው እንዲህ ለማድረግ ታላቁን ፈጣሪያችንን ማሰብ አለብን። በተጨማሪም በአምላክ ፊት ያለብንን ሁለንተናዊ ግዴታችንን መወጣት አለብን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ ማሳሰቢያ የተሰጣቸው ለምንድን ነው?

◻ ታላቁን ፈጣሪያቸውን በማሰብ ረገድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች እነማን ናቸው?

◻ ሰሎሞን የጠቀሳቸው እርጅና የሚያስከትላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

◻ ይሖዋን የሚያስቡ ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዳዊት፣ በምርኮ የተወሰደችው እስራኤላዊት ልጃገረድ፣ ሐና እና ስምዖን ይሖዋን አስበዋል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በዕድሜ የገፉ የይሖዋ ምሥክሮች ለታላቁ ፈጣሪያችን በደስታ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ