የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • pe ምዕ. 8 ገጽ 76-80
  • ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?
  • በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ነፍስ ትሞታለች
  • አልዓዛር— ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረው ሰው
  • ስንሞት ምን እንሆናለን?
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?
    እናፈቅራቸው የነበሩ ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?
  • ከሞት በኋላ ሕይወት —መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
ለተጨማሪ መረጃ
በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
pe ምዕ. 8 ገጽ 76-80

ምዕራፍ 8

ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?

1. ሰዎች ስለ ሙታን ብዙ ጊዜ ምን ብለው ይጠይቃሉ?

የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን የከንቱነት ስሜት ምናልባት ታውቀው ይሆናል። ይህ ቢደርስብህ እንዴት በጣም ታዝንና ተስፋ ትቆርጥ ነበር! እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ሊመጡብን ይችላሉ:- አንድ ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? በሌላ ቦታ ሕያው ሆኖ ይኖራልን? በሕይወት ያሉትስ ከሞቱት ጋር ወደፊት በምድር ላይ እንደገና ተገናኝተው ይደሰቱ ይሆን?

2. የመጀመሪያው ሰው አዳም ሲሞት ምን ሆነ?

2 እንደነዚህ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ አዳም ሲሞት ምን እንደሆነ ማወቁ ይረዳናል። ኃጢአት በሠራ ጊዜ አምላክ:- “ወደ ወጣህበት መሬት ትመለሳለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” አለው። (ዘፍጥረት 3:19) እስቲ ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስበው። አምላክ እርሱን ከአፈር ከመሥራቱ በፊት አዳም የትም አልነበረም። ሕልውና አልነበረውም። ስለዚህ አዳም ሲሞት ቀድሞ ወደነበረበት ያለመኖር ሁኔታ ተመለሰ።

3. (ሀ) ሞት ምንድን ነው? (ለ) መክብብ 9:5, 10 ስለ ሙታን ሁኔታ ምን ይላል?

3 በቀላል አነጋገር ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 9:5, 10 ላይ ነገሩ እንደዚያ መሆኑን ያሳያል። እነዚህ ጥቅሶች እንዲህ ይላሉ:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።”

4. (ሀ) አንድ ሰው ሲሞት የማሰብ ችሎታው ምን ይሆናል? (ለ) አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ የስሜት ሕዋሳቶቹ በሙሉ መሥራት የሚያቆሙት ለምንድን ነው?

4 ይህም ሙታን ምንም ነገር ሊያደርጉ ወይም ሊሰማቸው አይችልም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ከዚያ ወዲያ ምንም ዓይነት አሳብ የላቸውም:- “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ። [መንፈሱ (አዓት)] ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ ያን ጊዜ [አሳቡ (አዓት)] ሁሉ ይጠፋል።” (መዝሙር 146:3, 4) አንድ ሰው በመተንፈስ ጠብቆ ያቆየው መንፈሱ ማለትም የሕይወቱ ኃይል በሚሞትበት ጊዜ ከእርሱ ‘ይወጣል’። ከዚያ በኋላ ያ መንፈስ አይኖርም። በዚህም ምክንያት በማሰብ ችሎታው ላይ የተመኩት የመስማት፣ የመዳሰስ፣ የማሽተትና የመቅመስ የስሜት ሕዋሳቱ ሁሉ መሥራት ያቆማሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሙታን ምንም ዓይነት ስሜት የሌላቸው በድኖች ይሆናሉ።

5. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎችና የሞቱ እንስሳት ሁኔታ አንድ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ሰዎችንም ሆነ እንስሳትን ሕያው የሚያደርጋቸው “መንፈስ” ምንድን ነው?

5 ሰዎችም ሆኑ እንስሳት በሚሞቱበት ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በድን ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ነጥብ እንዴት እንደሚገልጸው ልብ በል:- “አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም [መንፈስ (አዓት)] አንድ ነው፤ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል።” (መክብብ 3:19, 20) እንስሳትን ሕያዋን የሚያደርጋቸው “መንፈስ” ሰዎችን ሕያዋን ከሚያደርገው መንፈስ ጋር አንድ ነው። ይህ “መንፈስ” ወይም የማይታይ የሕይወት ኃይል ሲወጣ ሰዎችም ሆኑ እንስሳት ወደ ተሠሩበት አፈር ይመለሳሉ።

ነፍስ ትሞታለች

6. መጽሐፍ ቅዱስ እንስሳት ነፍስ መሆናቸውን የሚያሳየው እንዴት ነው?

6 አንዳንድ ሰዎች ሰውን ከእንስሳት የሚለየው ነገር ሰው ነፍስ ሲኖረው እንስሳት ግን የሌላቸው መሆኑ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ዘፍጥረት 1:20, 30 አምላክ በባሕር ውስጥ እንዲኖሩ “ሕያው ነፍሳትን” እንደፈጠረና እንስሳት ‘ሕይወት ያለባቸው ነፍሳት’ መሆናቸውን ይገልጻል። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ‘በነፍስ’ ፋንታ “ፍጥረት” እና “ሕይወት” የሚሉትን ቃላት አስገብተዋል፤ ይሁን እንጂ በኅዳጉ ላይ የሚሰጡት መግለጫ በመጀመሪያው ቋንቋ የገባው “ነፍስ” የሚለው ቃል መሆኑን ይስማማል። መጽሐፍ ቅዱስ እንስሳትን እንደ ነፍስ አድርጎ ከጠቀሰባቸው ቦታዎች አንዱ ዘኁልቁ 31:28 ነው። ይህ ጥቅስ እንዲህ ይላል:- “ለእግዚአብሔርም ፈንታ አውጣ ከለዚያ ከተዋጉት ወደ ሰልፍም ከወጡት ካምስት መቶ ሁሉ አንድ ነፍስ። ከሰዎች እንዲሁም ከላም ካህያም ከበግም።” (የ1879 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም)

7. መጽሐፍ ቅዱስ የእንስሳት ነፍሳትም ሆኑ የሰዎች ነፍሳት እንደሚሞቱ ለማረጋገጥ ምን ይላል?

7 እንስሳት ነፍሳት ስለሆኑ በሚሞቱበት ጊዜ ነፍሳቸውም ይሞታል። መጽሐፍ ቅዱስ “በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ” ይላል። (ራእይ 16:3) የሰዎች ነፍሳትስ ምን ይሆናሉ? ባለፈው ምዕራፍ ላይ እንደተማርነው አምላክ ሰውን በውስጡ ነፍስ ያለበት አድርጎ አልፈጠረውም። ሰው ራሱ ነፍስ ነው። ሁኔታው እንደዚህ በመሆኑ አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ይሞታል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ እውነት መሆኑን በብዙ ቦታ ላይ ደጋግሞ ይናገራል። ነፍስ የማትሞት ወይም ልትሞት የማትችል ነገር ነች ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ በፍጹም አይናገርም። መዝሙር 22:29 “ወደ መሬት የሚወርዱ ሁሉ በፊቱ ይንበረከካሉ፤ ማንም የራሱን ነፍስ ሕያው አድርጎ አይጠብቅም” ይላል። (አዓት) ሕዝቅኤል 18:4, 20 “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” ሲል ያብራራል። እንዲሁም ኢያሱ 10:28-39⁠ን ብትመለከት ነፍስ ልትገደል ወይም ልትጠፋ እንደምትችል ሆኖ የተገለጸባቸውን ሰባት ቦታዎች ታገኛለህ።

8. ሰብዓዊ ነፍስ ሆኖ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሞተ እንዴት እናውቃለን?

8 ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በተነገረ በአንድ ትንቢት ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷልና . . . እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ።” (ኢሳይያስ 53:12) የቤዛው ትምህርት ኃጢአት የሠራው አንድ ነፍስ (አዳም) እንደ ሆነ ያሳያል፤ ስለዚህም ሰዎችን ለመዋጀት ከዚህ ተመጣጣኝ የሆነ ነፍስ (አንድ ሰው) መሥዋዕት መሆን አስፈልጎታል። ክርስቶስ ‘ነፍሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት’ የቤዛውን ዋጋ ከፍሏል። ሰብዓዊ ነፍስ ሆኖ የመጣው ኢየሱስ ሞተ።

9. ‘መንፈስም ወደሰጠው ወደ አምላክ ይመለሳል’ የሚሉት ቃላት ምን ማለት ናቸው?

9 ቀደም ብለን እንዳየነው “መንፈስ” ከነፍሳችን የተለየ ነገር ነው። መንፈስ የሕይወታችን ኃይል ነው። ይህ የሕይወት ኃይል በእያንዳንዱ የሰዎችና የእንስሳት የአካል ሴሎች ውስጥ ይገኛል። እርሱም የሚኖረው ወይም ሕያው ሆኖ የሚቀጥለው በመተንፈስ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ በሞት ጊዜ “መሬትም ወደ ነበረበት ምድር ይመለሳል፤ መንፈስም ወደሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል” ሲል ምን ማለቱ ነው? (መክብብ 12:7 የ1879 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም) በሞት ጊዜ የሕይወት ኃይል ቀስ በቀስ ከሰውነት ሴሎች ውስጥ እየወጣ ይሄዳል፣ አካልም መበስበስ ይጀምራል። ይሁን እንጂ ይህ የሕይወታችን ኃይል ቃል በቃል ምድርን በመልቀቅ ጠፈርን አቋርጦ ወደ አምላክ ይጓዛል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መንፈሱ ወደ አምላክ ይመለሳል ሲባል ከዚህ በኋላ ሕይወት ለማግኘት የሚኖረን ተስፋ ሙሉ በሙሉ በአምላክ ላይ የተመካ ነው ማለት ነው። እንደገና ለመኖር እንድንችል ይህ መንፈስ ወይም የሕይወት ኃይል ተመልሶ ሊሰጠን የሚችለው በአምላክ ኃይል ብቻ ነው።— መዝሙር 104:29, 30

አልዓዛር— ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረው ሰው

10. አልዓዛር ሞቶ እያለ እርሱ ስላለበት ሁኔታ ኢየሱስ ምን አለ?

10 ለአራት ቀናት ሞቶ በነበረው በአልዓዛር ላይ የደረሰው ነገር ሙታን ያሉበት ሁኔታ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቷል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው።” ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ መልሰው:- “ጌታ ሆይ ተኝቶስ እንደሆነ ይድናል አሉት።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጽ “አልዓዛር ሞተ” አላቸው። አልዓዛር ሞቶ ሳለ ኢየሱስ ተኝቷል ያለው ለምን ነበር? እስቲ እንመልከት።

11. ኢየሱስ ሞቶ የነበረውን አልዓዛርን ምን አደረገው?

11 ኢየሱስ አልዓዛር ወደሚኖርበት መንደር አቅራቢያ ሲደርስ ከአልዓዛር እኅት ከማርታ ጋር ተገናኘ። ወዲያውም እነርሱና ሌሎች ብዙ ሰዎች ሆነው አልዓዛርን ወዳኖሩበት መቃብር ሄዱ። ይህም ዋሻ ነበር፣ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡ” አለ። አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ስለ ነበር ማርታ “ጌታ ሆይ . . . አሁን ይሸታል” በማለት ተቃወመች። ሆኖም ድንጋዩን አነሡት፤ ኢየሱስም “አልዓዛር ሆይ ወደ ውጭ ና ብሎ ጮኸ።” እርሱም ወጣ! በተገነዘበት ጨርቅ እንደተጠመጠመ ሕያው ሆኖ ወጣ። “ኢየሱስም ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው።”— ዮሐንስ 11:11–44

12, 13. (ሀ) አልዓዛር ሞቶ በነበረበት ጊዜ ምንም የማይሰማ በድን እንደነበረ እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) አልዓዛር በእርግጥ ሞቶ እያለ ኢየሱስ ተኝቷል ያለው ለምንድን ነው?

12 እስቲ አሁን ስለዚህ ነገር አስብ:- አልዓዛር ሞቶ በቆየባቸው አራት ቀናት ውስጥ የነበረበት ሁኔታ ምን ነበር? ወደ ሰማይ ሄዶ ነበርን? እርሱ ጥሩ ሰው ነበር። ሆኖም ወደ ሰማይ ስለመሄዱ ምንም ነገር አልተናገረም፤ ወደዚያ ሄዶ ቢሆን ኖሮ ስለ መሄዱ እንደሚናገር ምንም አያጠራጥርም። አዎን፣ ልክ ኢየሱስ እንደተናገረው አልዓዛር ሞቶ ነበር። ታዲያ በመጀመሪያው ላይ ኢየሱስ አንቀላፍቷል ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረው ለምንድን ነው?

13 መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” ይላል። ስለዚህ አልዓዛር ምንም የማይሰማ በድን እንደነበረ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። (መክብብ 9:5) በሕይወት ያለውን ሰው ግን ከከባድ እንቅልፍ እንዲነቃ ማድረግ ይቻላል። ስለዚህ ኢየሱስ ከአምላክ በተሰጠው ኃይል አማካኝነት ወዳጁ አልዓዛር ከሞት ሊነሣ እንደሚችል ሊያሳያቸው እንደሆነ መናገሩ ነበር።

14. ክርስቶስ ሙታንን ለማስነሣት ስላለው ኃይል ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?

14 አንድ ሰው በከባድ እንቅልፍ ላይ ካለ ምንም ነገር ለማስታወስ አይችልም። የሙታንም ሁኔታ እንደዚሁ ነው። ምንም ዓይነት ስሜት የላቸውም። ከዚያ በኋላ ሕልውናቸው ጠፍቷል። ይሁን እንጂ አምላክ በወሰነው ጊዜ በአምላክ የተዋጁት ሙታን ሕይወት አግኝተው ይነሣሉ። (ዮሐንስ 5:28) ይህ እውቀት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት እንድንጥር ሊገፋፋን እንደሚገባ የተረጋገጠ ነው። ይህንን ካደረግን ብንሞትም እንኳ አምላክ ያስታውሰናል፤ ወደ ሕይወትም መልሶ ያመጣናል።— 1 ተሰሎንቄ 4:13, 14

[በገጽ 76 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳም ከአፈር ተሠርቶ. . .ወደ አፈር ተመለሰ

[በገጽ 78 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ከሞት ሳያስነሳው የአልዓዛር ሁኔታ ምን ነበር?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ