በአምላክ ፊት ያለባችሁን ሁለንተናዊ ግዴታ እየፈጸማችሁ ነውን?
“እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፣ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፣ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።”—መክብብ 12:14
1. ይሖዋ ለሕዝቦቹ ምን ዝግጅቶችን አድርጓል?
ይሖዋ እንደ ታላቅ ፈጣሪያቸው አድርገው ዘወትር የሚያስቡትን ሰዎች ይደግፋቸዋል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ እሱን ከልብ ማስደሰት የሚችሉበትን እውቀት ይሰጣቸዋል። መለኮታዊውን ፈቃድ እንዲያደርጉና ‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እንዲያፈሩ’ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ይመራቸዋል። (ቆላስይስ 1:9, 10) ከዚህም በላይ ይሖዋ “በታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብና ቲኦክራሲያዊ መመሪያ ያቀርባል። (ማቴዎስ 24:45-47) ስለዚህ የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን በሚያገለግሉበትና በጣም አንገብጋቢ የሆነውን የመንግሥቱን ምሥራች ስብከት ሥራ በሚያከናውኑበት ወቅት መለኮታዊ በረከት ያገኛሉ።—ማርቆስ 13:10
2. ለይሖዋ የሚቀርበውን አገልግሎት በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ?
2 እውነተኛ ክርስቲያኖች በይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት በመጠመዳቸው ደስተኞች ናቸው። ይሁንና አንዳንዶች ተስፋ ሊቆርጡና ጥረታቸው ሁሉ ትርጉም የለሽ ሊሆንባቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች አንዳንድ ጊዜ የማደርገው ልባዊ ጥረት ፋይዳው ምኑ ላይ ነው ብለው ያስቡ ይሆናል። አንድ የቤተሰብ ራስ ስለ ቤተሰብ ጥናታቸውና ስለ ሌሎች እንቅስቃሴዎቻቸው ሲያስብ ‘በምናደርገው ነገር በእርግጥ ይሖዋ ይደሰት ይሆን? ለአምላክ ያለብንን ሁለንተናዊ ግዴታ እየተወጣን ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች በአእምሮው ውስጥ ሊጉላሉ ይችላሉ። ሰባኪው የተናገራቸው የጥበብ ቃላት እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሊረዱ ይችላሉ።
ሁሉም ነገር ከንቱ ነውን?
3. በመክብብ 12:8 መሠረት ከሁሉ የከፋው ከንቱ ነገር ምንድን ነው?
3 አንዳንድ ሰዎች ጠቢቡ ሰው የተናገራቸው ቃላት ለማንም ሰው ለወጣትም ሆነ ለአረጋዊ ተስፋ የሚያስቆርጡ ናቸው ብለው ያስቡ ይሆናል። “ሰባኪው:- ከንቱ፣ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል።” (መክብብ 12:8) በወጣትነት ታላቁን ፈጣሪ ቸል ማለትና ካረጁ በኋላ ይህን ለሚያክል ዓመት ኖሬያለሁ እያሉ እንደ ትልቅ ነገር መናገር በእርግጥ የከንቱ ከንቱ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ምንም እንኳ በክፉው ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ስር ባለው በዚህ ዓለም ውስጥ ሀብትና ዝና አትርፎ ቢሞትም እንኳ ሁሉ ከንቱ ነበር።—1 ዮሐንስ 5:19
4. ሁሉ ነገር ከንቱ አይደለም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
4 በታማኝነት ይሖዋን በማገልገል በሰማይ ሀብት ሲያከማቹ ለኖሩ ሰዎች ግን ሁሉ ነገር ከንቱ አይደለም። (ማቴዎስ 6:19, 20) በሚክሰው የጌታ ሥራ ሊያከናውኑት የሚችሉት በርካታ ሥራ አላቸው፤ ደግሞም ይህ ድካማቸው በፍጹም ከንቱ አይሆንም። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ሆኖም ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች ከሆንን አምላክ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ እንድንሠራው የሰጠንን ሥራ በትጋት እየሠራን ነውን? (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ወይስ ሌሎች ጎረቤቶቻችን ከሚከተሉት የአኗኗር ዘይቤ እምብዛም ያልተለየ አኗኗር እየተከተልን ነው? እነሱ ምናልባትም በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ የተጠላለፉና ለእምነታቸው ያደሩ፣ የአምልኮ ሥርዓታቸው በሚካሄድበት ቦታ ዘወትር በመገኘት አምልኮታቸው የሚጠይቅባቸውን ሁሉ ለማከናወን የሚጥሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ እነሱ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች አይደሉም። ያለንበት ጊዜ ‘የፍጻሜ ዘመን’ መሆኑን በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት የላቸውም። እንዲሁም የምንኖርበትን ዘመን በተመለከተ ምንም ዓይነት የጥድፊያ ስሜት የላቸውም።—ዳንኤል 12:4
5. በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የተለመደ የዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳይ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
5 ኢየሱስ ክርስቶስ የምንኖርበትን አስጨናቂ ዘመን በተመለከተ እንደሚከተለው ብሏል:- “የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:37-39) በልከኝነት እስከሆነ ድረስ መብላትም ሆነ መጠጣት ምንም ስህተት የለውም። ጋብቻም ቢሆን አምላክ ራሱ ያቋቋመው ዝግጅት ነው። (ዘፍጥረት 2:20-24) ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው የተለመደ የዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳይ እንደሆነ ከተገነዘብን ለምን ይህን በተመለከተ አንጸልይም? ይሖዋ የመንግሥቱን ጉዳዮች እንድናስቀድም፣ ትክክል የሆነውን ነገር እንድናደርግና በእሱ ፊት ያለብንን ግዴታ እንድንፈጽም ሊረዳን ይችላል።—ማቴዎስ 6:33፤ ሮሜ 12:12፤ 2 ቆሮንቶስ 13:7
ራስን መወሰንና በአምላክ ፊት ያለብን ግዴታ
6. አንዳንድ የተጠመቁ ግለሰቦች በአምላክ ፊት ያለባቸውን ግዴታ ሳይፈጽሙ የሚቀሩት በምን መንገድ ነው?
6 አንዳንድ የተጠመቁ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የገቡትን ግዴታ መፈጸም እየተሳናቸው ስለሆነ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ያስፈልጋቸዋል። እስከ አሁን ድረስ በየዓመቱ ከ300,000 በላይ ይጠመቃሉ፤ ሆኖም አጠቃላዩ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከዚህ ጋር በሚመጣጠን ሁኔታ እየጨመረ ሲሄድ አይታይም። አንዳንድ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ምሥራቹን ማወጃቸውን አቁመዋል። ሆኖም ግለሰቦች ከመጠመቃቸው በፊት በክርስቲያናዊ አገልግሎት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው። እንዲህ ካደረጉ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠውን የሚከተለውን ተልእኮ ይገነዘባሉ:- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ይሁን እንጂ በጤና ወይም ከአቅማቸው በላይ በሆኑ ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ የተለየ የአቅም ገደብ ያለባቸው ካልሆኑ በስተቀር የአምላክና የክርስቶስ ምሥክሮች በመሆን ማገልገላቸውን ያቆሙ የተጠመቁ ግለሰቦች በታላቁ ፈጣሪያችን ፊት ያለባቸውን ሁለንተናዊ ግዴታ እየፈጸሙ አይደሉም።—ኢሳይያስ 43:10-12
7. ለአምልኮ ዘወትር አንድ ላይ መሰብሰብ ያለብን ለምንድን ነው?
7 የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ለአምላክ የተወሰነ ብሔር ነበር። በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ሆነው በይሖዋ ፊት የሚፈጽሙት ግዴታ ነበረባቸው። ለምሳሌ ያህል ወንዶች በሙሉ በሦስት ዓመታዊ በዓላት ላይ መሰብሰብ ነበረባቸው፤ እንዲሁም የማለፍን በዓል ሆን ብሎ ሳያከብር የቀረ ሰው ከሕዝቡ ‘ተለይቶ መጥፋት’ ነበረበት። (ዘኁልቊ 9:13፤ ዘሌዋውያን 23:1-43፤ ዘዳግም 16:16) እስራኤላውያን ለአምላክ የተወሰነ ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን በአምላክ ፊት ያለባቸውን ግዴታ ለመፈጸም ሲሉ ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብ ነበረባቸው። (ዘዳግም 31:10-13) በሕጉ ውስጥ ‘ከተመቻችሁ አድርጉት’ የሚል ሐሳብ ፈጽሞ አናገኝም። ይህ ትእዛዝ ዛሬ ያሉ ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት ክብደት እንዲገነዘቡ እንደሚረዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:24, 25) አዎን፣ ከእምነት ባልደረቦች ጋር ዘወትር አብሮ መሰብሰብ አንድ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን በአምላክ ፊት ያለበት ግዴታ ክፍል ነው።
ውሳኔዎቻችሁን በጥንቃቄ መዝኑ!
8. ራሱን ለአምላክ የወሰነ አንድ ወጣት ስለሚያቀርበው ቅዱስ አገልግሎት በጸሎት ማሰብ ያለበት ለምንድን ነው?
8 ምናልባት ራስህን ለይሖዋ የወሰንክ ወጣት ነህ እንበል። በሕይወትህ ውስጥ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ማስቀደምህን ከቀጠልክ የተትረፈረፉ በረከቶችን ታገኛለህ። (ምሳሌ 10:22) በጸሎትና ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ በማውጣት ቢያንስ የወጣትነት ዕድሜህን በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ማሳለፍ ትችል ይሆናል። ይህ ደግሞ ታላቁን ፈጣሪህን እንደምታስብ የምታሳይበት ግሩም አጋጣሚ ነው። አለዚያ ግን ጊዜህና ትኩረትህ ሁሉ በቁሳዊ ነገር ሊያዝ ይችላል። አንተም እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ቶሎ ልታገባና ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ስትል ዕዳ ውስጥ ልትዘፈቅ ትችላለህ። ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለማግኘት ስትል አብዛኛውን ጊዜህንና ጉልበትህን በምትሠራው ሥራ ላይ ልታጠፋ ትችላለህ። ልጆች ካሉህ ደግሞ ለአሥርተ ዓመታት የቤተሰብ ኃላፊነቶችን መሸከም ግድ ይሆንብሃል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ታላቁን ፈጣሪህን ረስተሃል ማለት ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም አስቀድመህ ዕቅድ ማውጣትህ ወይም አለማውጣትህ በጎልማስነት ዕድሜህ ለምትመራው ሕይወት ወሳኝ እንደሆነ መገንዘብህ ጥበብ ነው። በኋለኞቹ ዘመናት ወደኋላ መለስ ብለህ ምነው ቢያንስ የወጣትነት ዕድሜዬን ለታላቁ ፈጣሪያችን ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ በተጠቀምኩበት ኖሮ ብለህ ልትቆጭ ትችላለህ። በወጣትነት ዕድሜህ ለይሖዋ በምታቀርበው ቅዱስ አገልግሎት እርካታ እንድታገኝ ለምን የወደፊት ዕቅድህን በጸሎት አታስብበትም?
9. በአንድ ወቅት በጉባኤ ውስጥ ከባድ ኃላፊነት የነበረው አሁን በዕድሜ የገፋ ወንድም ምን የማድረግ አጋጣሚ ሊኖረው ይችላል?
9 አሁን ደግሞ በአንድ ወቅት ‘የእግዚአብሔር መንጋ’ እረኛ የነበረን ሰው ሁኔታ ተመልከት። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) በሆነ ምክንያት ይህን መብት በፈቃደኝነት ይተዋል። አሁን ዕድሜው ስለገፋ የአምላክን አገልግሎት ማከናወን ይበልጥ አዳጋች ሊሆንበት እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ እንደገና ለቲኦክራሲያዊ መብቶች መጣጣር ይችላልን? ይህ ሰው በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መሸከም ቢችል ለሌሎች ብዙ በረከት ሊያስገኝ ይችላል! ማንም ሰው ለራሱ ብቻ ስለማይኖር ይህ ሰው ለአምላክ ክብር አገልግሎቱን ከፍ ማድረግ ቢችል ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ደስ ይላቸዋል። (ሮሜ 14:7, 8) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ ማንም ሰው እሱን በማገልገል ያከናወነውን ተግባር አይረሳም። (ዕብራውያን 6:10-12) ታዲያ ታላቁን ፈጣሪያችንን እንድናስብ ምን ነገር ሊረዳን ይችላል?
ታላቁ ፈጣሪያችንን ለማሰብ የሚረዱን ነገሮች
10. ታላቁን ፈጣሪያችንን በማሰብ ረገድ መመሪያ ለመስጠት ሰባኪው በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
10 ሰባኪው ታላቁን ፈጣሪያችንን ማሰብ የምንችልበትን መመሪያ ለመስጠት በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኝ ነበር። ይሖዋ አስደናቂ ጥበብ በመስጠት ሰባኪው ላቀረበው ልባዊ ጸሎት መልስ ሰጥቶታል። (1 ነገሥት 3:6-12) ሰሎሞን የሰውን ልጅ ሕይወት ሁለንተናዊ ገጽታ በተመለከተ ጥልቅ ምርምር አድርጎ ነበር። ከዚህም በላይ ሌሎች ሰዎች መጠቀም ይችሉ ዘንድ በምርምሩ የደረሰበትን ሁሉ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት በጽሑፍ አስፍሮታል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሰባኪውም ጠቢብ ስለ ሆነ ለሕዝቡ እውቀትን አስተማረ፤ እርሱም ብዙ ምሳሌዎችን መረመረና ፈላለገ አስማማም። ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ።”—መክብብ 12:9, 10
11. የሰሎሞንን የጥበብ ምክር መቀበል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
11 በግሪክ ሰፕቱጀንት ትርጉም እነዚህ ቃላት እንደሚከተለው ይነበባሉ:- “ከዚህም በላይ ሰባኪው ጠቢብ ስለነበረ ለሰዎች ጥበብን ያስተምር ነበር፤ ከምሳሌዎች ውስጥ ለጆሮ የሚጥመውን ያገኝ ዘንድ ሰባኪው አስደሳች የሆነውንና የታመነውን የእውነት ቃል ለማግኘት በትጋት መረመረ።” (የሰፕቱጀንት መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትርጉም በቻርልስ ቶምሰን) ሰሎሞን ለጆሮ በሚጥሙ ቃላትና ማራኪና ቁምነገር አዘል በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች አማካኝነት የአንባቢዎቹን ልብ ለመንካት ጥሯል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት የሰሎሞን ቃላት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፉ ስለሆኑ ሰሎሞን መርምሮ የደረሰበትንና የሰጠውን የጥበብ ምክር ሳናቅማማ መቀበል እንችላለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
12. በመክብብ 12:11, 12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የሰሎሞን አነጋገር በራስህ አባባል እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ?
12 ምንም እንኳ ዘመናዊ የማተሚያ ዘዴዎች ያልነበሩ ቢሆንም በሰሎሞን ዘመን በጣም ብዛት ያላቸው መጻሕፍት ነበሩ። እንዲህ ዓይነቱ ሥነ ጽሑፍ እንዴት መታየት ነበረበት? ሰሎሞን እንዲህ ይላል:- “የጠቢባን ቃል እንደ በሬ መውጊያ ነው፣ የተሰበሰቡትም ከአንድ እረኛ የተሰጡት ቃላት እንደ ተቸነከሩ ችንካሮች ናቸው። ከዚህም ሁሉ በላይ፣ ልጄ ሆይ፣ ተግሣጽን ስማ፤ ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፣ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል።”—መክብብ 12:11, 12
13. አምላካዊ ጥበብ ያላቸው ሰዎች የሚናገሯቸው ቃላት እንደ በሬ መውጊያ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? እንደ “ተቸነከሩ ችንካሮች” የሆኑትስ እነማን ናቸው?
13 አምላካዊ ጥበብ ያላቸው ሰዎች የሚናገሯቸው ቃላት እንደ በሬ መውጊያ ናቸው። እንዴት? እነዚህ የጥበብ ቃላት አንባቢዎቻቸውን ወይም አድማጮቻቸውን ባነበቡት ወይም በሰሙት መሠረት እርምጃ እንዲወስዱ የመገፋፋት ኃይል አላቸው። ከዚህም በላይ ‘የተሰበሰቡ ቃላትን’ ወይም ጥበብ ያለባቸውንና ጠቃሚ ምሳሌዎችን በመመርመር ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ‘እንደ ተቸነከረ’ ወይም ጥሩ ተደርጎ እንደተተከለ ችንካር ናቸው። ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች የተናገሯቸው ግሩም የሆኑ ቃላት የይሖዋን ጥበብ ስለሚያንጸባርቁና አንባቢዎቻቸውንም ሆነ አድማጮቻቸውን ለማጽናናትና ለመደገፍ ስለሚያገለግሉ ነው። ፈሪሃ አምላክ ያለህ ወላጅ ከሆንክ እንዲህ ዓይነቱን ጥበብ በልጆችህ አእምሮና ልብ ውስጥ ለመቅረጽ የተቻለህን ያህል ጥረት ማድረግ አይኖርብህም?—ዘዳግም 6:4-9
14. (ሀ) ‘ብዙ ትኩረት’ መስጠት የማያስፈልገው ለምን ዓይነት መጻሕፍት ነው? (ለ) ይበልጥ ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለየትኛው ዓይነት ጽሑፍ ነው? ለምንስ?
14 ታዲያ ሰሎሞን መጻሕፍትን በተመለከተ እንዲህ ዓይነት አስተያየት የሰጠው ለምንድን ነው? ይህ ዓለም የሚያቀርባቸው ማለቂያ የሌላቸው መጻሕፍት ከይሖዋ ቃል ጋር ሲነጻጸሩ በሰብዓዊ አመለካከት የተሞሉ ናቸው። ይህ ሰብዓዊ አስተሳሰብ ደግሞ በአብዛኛው የሰይጣንን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ስለዚህ እንዲህ ያሉትን መጻሕፍት ‘እጅግ መመርመር’ ምንም ዓይነት ዘላቂ ጥቅም አያስገኝም። እንዲያውም እንዲህ ያሉ መጻሕፍትን ማብዛት መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ልክ እንደ ሰሎሞን የአምላክ ቃል ስለ ሕይወት በሚናገረው ነገር ላይ እናሰላስል። እንዲህ ማድረጋችን እምነታችንን ያጠነክርልናል፤ ወደ ይሖዋም ይበልጥ ያቀርበናል። ለሌሎች መጻሕፍት ወይም የመመሪያ ምንጮች ከመጠን ያለፈ ትኩረት መስጠት ሊያደክመን ይችላል። በተለይ እነዚህ በሰብዓዊ ጥበብ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ከአምላካዊ ጥበብ ጋር የሚጋጩ ከሆኑ መጥፎ ከመሆናቸውም በላይ በአምላክና በዓላማዎቹ ላይ ያለንን እምነት ያጠፉብናል። ስለሆነም በሰሎሞን ዘመንም ሆነ በእኛ ዘመን የላቀ ጥቅም ያላቸው መጻሕፍት ‘የአንዱን እረኛ’ ማለትም የይሖዋ አምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቁ መጻሕፍት መሆናቸውን እናስታውስ። 66 የቅዱሳን ጽሑፎች መጻሕፍትን ሰጥቶናል፤ ትልቅ ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለእነዚህ መጻሕፍት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ‘ታማኙ ባሪያ’ የሚያዘጋጃቸው ጠቃሚ የሆኑ ጽሑፎች ‘የአምላክን እውቀት’ እንድናገኝ ያስችሉናል።—ምሳሌ 2:1-6
በአምላክ ፊት ያለብን ሁለንተናዊ ግዴታ
15. (ሀ) ሰሎሞን ስለ ‘ሰው ሁለንተናዊ ግዴታ’ የተናገራቸውን ቃላት እንዴት ትገልጻቸዋለህ? (ለ) በአምላክ ፊት ያለብንን ግዴታ ለመፈጸም ከፈለግን ምን ማድረግ አለብን?
15 ሰባኪው ሰሎሞን ያደረገውን ምርምር ሲያጠቃልል እንዲህ አለ:- “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፣ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፣ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።” (መክብብ 12:13, 14) ለታላቁ ፈጣሪያችን ጤናማ ወይም አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳደራችን እኛንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች ይህ ነው ወደማይባል ችግርና ሐዘን ውስጥ ሊከት የሚችል አጓጉል የሞኝነት ጎዳና እንዳንከተል እኛንም ሆነ ምናልባትም ቤተሰቦቻችንን ይጠብቃል። ለአምላክ የምናሳድረው ጤናማ ፍርሃት ንጹህ ከመሆኑም ሌላ የጥበብና የእውቀት መጀመሪያ ነው። (መዝሙር 19:9፤ ምሳሌ 1:7) በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ጥልቅ ማስተዋል ካለንና በማንኛውም ረገድ ምክሩን በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ በአምላክ ፊት ያለብንን ‘ሁለንተናዊ ግዴታ’ እንፈጽማለን። ይህ ማለት ግዴታዎቻችንን በዝርዝር መጻፍ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት በምንጥርበት ጊዜ ወደ ቅዱሳን ጽሑፎች ዞር በማለት ምንጊዜም ነገሮችን በአምላክ መንገድ መሥራት ማለት ነው።
16. ፍርድን በተመለከተ ይሖዋ ምን ያደርጋል?
16 ታላቁ ፈጣሪያችን ሳያስተውለው የሚቀር ምንም ነገር እንደሌለ መገንዘብ ይኖርብናል። (ምሳሌ 15:3) አምላክ ‘ማንኛውንም ሥራ ወደ ፍርድ’ ያመጣዋል። አዎን፣ ልዑሉ አምላክ ከሰብዓዊ ዓይን የተሰወረውን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ወደ ፍርድ ያመጣዋል። ይህን መገንዘባችን የአምላክን ትእዛዛት እንድንጠብቅ ይበልጥ ሊያነቃን ይችላል። ሆኖም ሐዋርያው ዮሐንስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” ሲል ስለጻፈ የአምላክን ትእዛዛት እንድንጠብቅ የሚያነሳሳን ከሁሉ የላቀው ነገር ለሰማያዊ አባታችን ያለን ፍቅር መሆን ይኖርበታል። (1 ዮሐንስ 5:3) እንዲሁም የአምላክ ትእዛዛት ለዘላቂ ደህንነታችን ጠቃሚዎች ስለሆኑ እነዚህን ትእዛዛት መጠበቅ ተገቢ ከመሆኑም በላይ በእርግጥ ጥበብ ነው። ታላቁን ፈጣሪ ለሚያፈቅሩ ሰዎች ይህ ሸክም አይደለም። በአምላክ ፊት ያለባቸውን ግዴታ መፈጸም ይፈልጋሉ።
ሁለንተናዊ ግዴታችሁን ፈጽሙ
17. በእርግጥ በአምላክ ፊት ያለብንን ሁለንተናዊ ግዴታ ለመፈጸም ከፈለግን ምን እናደርጋለን?
17 ጥበበኛ ከሆንንና በአምላክ ፊት ያለብንን ሁለንተናዊ ግዴታ ለመፈጸም የምንፈልግ ከሆነ ትእዛዛቱን ከመጠበቃችንም በተጨማሪ እሱን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት ይኖረናል። በእርግጥም “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።” እንዲሁም ትእዛዛቱን የሚጠብቁ “ደህና ማስተዋል” አላቸው። (መዝሙር 111:10፤ ምሳሌ 1:7) ስለሆነም በማንኛውም ነገር ይሖዋን በመታዘዝ በጥበብ እንመላለስ። ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ስለያዘና በአምላክ የተሾመ ዳኛ እንደ መሆኑ መጠን ፍርድ የሚያስፈጽምበት ጊዜ ስለቀረበ ይህ ጉዳይ ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነው አሁን ነው።—ማቴዎስ 24:3፤ 25:31, 32
18. በይሖዋ አምላክ ፊት ያለብንን ሁለንተናዊ ግዴታ ከፈጸምን ውጤቱ ምን ይሆናል?
18 በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዳችን በአምላክ እየተመረመርን ነን። መንፈሳዊ ዝንባሌ አለን ወይስ ዓለማዊ ተጽእኖዎች ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና እንዲያዳክሙብን ፈቅደንላቸዋል? (1 ቆሮንቶስ 2:10-16፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) ወጣትም ሆን አረጋዊ ታላቁን ፈጣሪያችንን ለማስደሰት የቻልነውን ሁሉ እናድርግ። ይሖዋን የምንታዘዝና ትእዛዛቱን የምንጠብቅ ከሆነ ይህ የሚያልፍ አሮጌ ዓለም በሚያቀርባቸው ከንቱ ነገሮች አንታለልም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ቃል በገባው አዲስ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሊኖረን ይችላል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በአምላክ ፊት ያለባቸውን ሁለንተናዊ ግዴታ ለሚፈጽሙ ሁሉ ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ነው!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ሁሉም ነገር ከንቱ አይደለም የምትለው ለምንድን ነው?
◻ አንድ ወጣት ክርስቲያን የሚያቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት በጸሎት መመርመር ያለበት ለምንድን ነው?
◻ ‘ብዙ ትኩረት’ መስጠት አስፈላጊ ያልሆነው ለምን ዓይነት መጻሕፍት ነው?
◻ ‘የሰው ሁለንተናዊ ግዴታ’ ምንድን ነው?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን ለሚያገለግሉ ሰዎች ሁሉም ነገር ከንቱ አይደለም
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ቃል ይህ ዓለም ከሚያቀርባቸው መጻሕፍት በተለየ መንገድ አእምሮን የሚያድስና ጠቃሚ ነው