የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | መጋቢት 1
    • በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ከላይ ያለውን ሐሳብ የጻፈው ጠቢቡ ሰለሞን የተናገረው የሰዎች ዕድል አስቀድሞ ስለመወሰኑ ሳይሆን ስለ አምላክ ዓላማና ይህ ዓላማ የሰው ልጆችን እንዴት እንደሚነካቸው ነው። በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ይህን ለመረዳት እንችላለን። ሰለሞን “ለሁሉም ነገር ጊዜ [እንዳለው]” በመግለጽ በርከት ያሉ ነገሮችን ከዘረዘረ በኋላ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “ሰዎች ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ከባድ የሥራ ጫና አየሁ። ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው።”—መክብብ 3:10, 11

      አምላክ የሰው ልጆች ሊሠሯቸው የሚችሉ በርካታ ነገሮችን የሰጣቸው ሲሆን ሰለሞንም ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን ጠቅሷል። በተጨማሪም አምላክ መሥራት የምንፈልገውን ነገር የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። ይሁን እንጂ እያንዳንዱን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችል ተስማሚ ወይም አመቺ ጊዜ አለ። በመክብብ 3:2 ላይ የሚገኘውን ሰለሞን የተናገረውን ሐሳብ እንደ ምሳሌ እንመልከት፦ “ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀልም ጊዜ አለው።” ገበሬዎች እያንዳንዱ ዘር ሊዘራበት የሚገባ ተስማሚ ጊዜ እንዳለው ያውቃሉ። አንድ ገበሬ ይህን ሐቅ ችላ በማለት አንድን ዘር አለጊዜው ወይም አለወቅቱ ቢዘራስ? ይህ ገበሬ ጥሩ ምርት ባያገኝ ዕድሉን ማማረር ይገባዋል? በጭራሽ! ገበሬው ጠንክሮ ሠርቶ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ዘሩን በተገቢው ጊዜ አልዘራም። ይህ ገበሬ፣ ፈጣሪ ባወጣው የተፈጥሮ ሕግ ተመርቶ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ምርት ማግኘት ይችል ነበር።

      በመሆኑም አምላክ የሰዎችን ዕድል ወይም የሚያከናውኗቸው ነገሮች የሚያስገኙትን ውጤት አስቀድሞ አልወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ሊመሩባቸው የሚገቡና ከዓላማው ጋር የሚስማሙ አንዳንድ ሥርዓቶችን አስቀድሞ አስቀምጧል። ሰዎች በሚያከናውኑት ነገር ስኬታማ ለመሆን ከፈለጉ አስተዋዮች በመሆን ከአምላክ ዓላማና ከወሰነው ጊዜ ጋር በሚስማማ መንገድ መሥራት ይገባቸዋል። አምላክ አስቀድሞ የወሰነው እንዲሁም ሊለወጥ የማይችለው ዓላማው ነው እንጂ የግለሰቦች ዕድል አይደለም። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።”—ኢሳይያስ 55:11

  • ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | መጋቢት 1
    • አምላክ የወሰነውን ጊዜ መረዳት

      ሰለሞን ፍንጭ ሰጥቶናል። “[አምላክ] ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” ብሎ ከተናገረ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።”—መክብብ 3:11

      ሰዎች ይህን ጥቅስ በተመለከተ ብዙ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የዚህ ጥቅስ ዋና መልእክት ግን ሁላችንም በሆነ ወቅት ላይ የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነና ወደፊት ምን እንደምንሆን የማወቅ ጉጉት እንደሚያድርብን የሚገልጽ ነው። ሰዎች ሕይወታቸውን ሙሉ ሲለፉ ኖረው መጨረሻቸው ሞት መሆኑ የሰው ልጆች በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሊዋጥላቸው ያልቻለ ነገር ነው። የሰው ልጆች፣ ሕይወት ካላቸው ሌሎች ፍጥረታት የምንለየው አሁን ስላለው ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን ስለ ሞት ብሎም ከዚያ በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ የምናስብ በመሆናችን ነው። ሌላው ቀርቶ ለዘላለም ለመኖር እንኳ እንመኛለን። እንዲህ ዓይነት ምኞት ሊኖረን የቻለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይህ የሆነው አምላክ ‘በሰዎች ልብ ዘላለማዊነትን ስላኖረ’ ነው።

      የሰው ልጆች ይህን ምኞታቸውን ለማርካት ሲሉ ‘ከሞት በኋላ ሕይወት አለ’ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ለመረዳት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። አንዳንዶች፣ በውስጣችን ያለ አንድ ነገር ከሞትን በኋላ መኖሩን ይቀጥላል ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል። ሌሎች ስንሞት እንደገና እየተወለድን ሕልውናችን ለዘላለም እንደሚቀጥል ያምናሉ። አንዳንዶች ደግሞ ዕድል ወይም አምላክ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውም ነገር እንደወሰኑትና ይህን ለመለወጥ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። የሚያሳዝነው ግን እነዚህ ሁሉ ማብራሪያዎች ለሰው ልጅ አጥጋቢ መልስ አልሰጡትም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ “[ሰዎች] እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም” ይላል።

      ባለፉት ዘመናት የኖሩ ምሑራንና ፈላስፎች ከላይ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም ይህን ማድረግ አለመቻላቸው አእምሯቸውን ሲበጠብጠው ቆይቷል። ወደፊት ምን እንደምንሆን የማወቅ ፍላጎት በልባችን ውስጥ እንዲኖር ያደረገው አምላክ እስከሆነ ድረስ ይህን ምኞታችንን ለማርካት የእሱን እርዳታ መሻታችን ተገቢ አይሆንም? መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።” (መዝሙር 145:16) የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ሕይወትንና ሞትን እንዲሁም አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያለውን ዘላለማዊ ዓላማ በተመለከተ አጥጋቢ መልስ ማግኘት ትችላለህ።—ኤፌሶን 3:11

  • የምትመርጥበት ጊዜ አሁን ነው
    መጠበቂያ ግንብ—2009 | መጋቢት 1
    • “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።”—ዘፍጥረት 1:27

      በመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ምዕራፎች ላይ የሚገኘው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው ይህ ሐሳብ፣ አምላክ ፍጹም የሆኑትን ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋንን መፍጠሩን ይገልጻል፤ እነዚህ ፍጥረታት አምላክ “በጊዜው ውብ አድርጎ [ከሠራቸው]” እጅግ ድንቅ ነገሮች መካከል የሚመደቡ ናቸው። (መክብብ 3:11) ፈጣሪያቸው የሆነው ይሖዋ አምላክ ለእነዚህ ባልና ሚስት እንዲህ አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው።”—ዘፍጥረት 1:28

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ