የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 2/15 ገጽ 13-18
  • አሁንና ለዘላለም ደስተኛ መሆን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አሁንና ለዘላለም ደስተኛ መሆን
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በዘመናችን ያለው ፍጻሜ
  • ትንቢቱ በአንተም ላይ እየተፈጸመ ነውን?
  • የትንቢቱ ፍጻሜ አላበቃም!
  • ተመልሶ የተቋቋመ ገነት!
    የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
  • በደስታ እልል የምንልበት ምክንያት አለን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • “እጅግ ብዙ ሰዎች” ወደ አምላክ ድርጅት የሚወስደውን “ጐዳና” ያዙ
    “የሰላሙ መስፍን“ ሲገዛ በምድር ዙሪያ የሚገኝ ዋስትና ያለው ሕይወት
  • በገነት ተስፋ እንድታምን የሚያደርግ ምክንያት አለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 2/15 ገጽ 13-18

አሁንና ለዘላለም ደስተኛ መሆን

“ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፣ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና።”—ኢሳይያስ 65:18

1. ባለፉት መቶ ዘመናት እውነተኛው አምልኮ የሰዎችን ሕይወት የነካው እንዴት ነበር?

ባለፉት መቶ ዘመናት እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን በማምለክ ከፍተኛ ደስታ ያገኙ በጣም ብዙ ሰዎች ነበሩ። ዳዊት በእውነተኛው አምልኮ ደስታ ካገኙ ከእነዚህ በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ “ዳዊትና መላው እስራኤል በደስታ እልል” እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ሳሙኤል 6:15 የ1980 ትርጉም) ዛሬም ቢሆን ይሖዋን በማገልገል እንዲህ ያለ ደስታ ማግኘት ይቻላል። አንተም ይህንን ደስታ ልታገኝ ትችላለህ። እንዲያውም በቅርቡ ሌላ ዓይነት ደስታ ማግኘት ትችላለህ!

2. ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ከምርኮ ከተመለሱት አይሁዶች በተጨማሪ በሌላ መንገድ በእነማን ላይ እየተፈጸመ ነው?

2 ባለፈው ርዕስ ላይ በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ላይ የተመዘገበውን የሚያበረታታ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜ መርምረን ነበር። ይህ ትንቢት በጥንቶቹ አይሁዶች ላይ ተሐድሶ አስከትሎ ስለነበር የተሐድሶ ትንቢት ልንለው እንችላለን። በዘመናችንም ቢሆን ተመሳሳይ ፍጻሜ አለው። እንዴት? ይሖዋ ከኢየሱስ ሐዋርያትና በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ከተገኙት ደቀ መዛሙርት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር ግንኙነት ሲያደርግ ቆይቷል። እነዚህ መንፈሳዊ እስራኤላውያን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ የተቀቡና ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የአምላክ እስራኤል’ ብሎ የጠራው ቡድን ክፍል የሆኑ ሰዎች ናቸው። (ገላትያ 6:16፤ ሮሜ 8:15-17) እነዚህ ክርስቲያኖች በ1 ጴጥሮስ 2:9 ላይ “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” ተብለው እንደተጠሩም አስታውስ። ጴጥሮስ መንፈሳዊ እስራኤላውያን የተሰጣቸውን የሥራ ምድብ ሲገልጽ “ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ” ነው ብሏል።

በዘመናችን ያለው ፍጻሜ

3, 4. ኢሳይያስ ምዕራፍ 34 በዘመናችን መፈጸም ሲጀምር ምን ዓይነት ሁኔታ ነበር?

3 መንፈሳዊ እስራኤላውያን በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይህን መልእክት በትጋትና በንቃት አላወጁም ነበር። አምላክ የሚሰጠው መንፈሳዊ ብርሃን የሚያስገኘውን ደስታ ሙሉ በሙሉ በማጣጣም ላይ አልነበሩም። እንዲያውም ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነበሩ። ይህ የሆነው መቼ ነበር? አምላክስ የነበሩበትን ሁኔታ በተመለከተ ምን አደረገ?

4 ይህ የሆነው የአምላክ መንግሥት በሰማይ ከተቋቋመበት ከ1914 ወዲህ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር። በዚህ ጊዜ ብሔራት የአብያተ ክርስቲያናት ቀሳውስት በሚያደርጉላቸው ድጋፍ በመታገዝ እርስ በርሳቸው ይናቆሩ ነበር። (ራእይ 11:17, 18) አምላክ በትዕቢተኛው የኤዶም ብሔር ላይ እንዳደረገው ሁሉ ከዳተኛይቱን ሕዝበ ክርስትናንና ከፍተኛ ቦታ የነበረውን የቀሳውስት ቡድን ተቃውሞ ነበር። በዚህ ምክንያት በኢሳይያስ ምዕራፍ 34 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዘመናችን በምሳሌያዊ ኤዶም ላይ ተፈጻሚነት ያገኛል። ይህ ትንቢት በጥንትዋ ኤዶም ላይ እንደተፈጸመ ሁሉ ዛሬም ሕዝበ ክርስትና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስትደመሰስ ይፈጸማል።—ራእይ 18:4-8, 19-21

5. ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 በዘመናችን ምን ፍጻሜ አግኝቷል?

5 ስለ ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 እና ደስተኞች እንድንሆን ስለሚያስችሉን ምክንያቶቸስ ምን ለማለት ይቻላል? ይህም በዘመናችን ተፈጽሟል። እንዴት? መንፈሳዊ እስራኤላውያን ከነበሩበት ምርኮ ሲመለሱ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። በዛሬው ጊዜ በሕይወት ያሉ ብዙ ሰዎች የተመለከቷቸውን በቅርቡ ባሳለፍነው ቲኦክራሲያዊ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙትን እውነታዎች እንመርምር።

6. የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች በግዞት ሥር እንደነበሩ ያህል ሆነው ነበር ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?

6 የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለተወሰነ ጊዜ መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን ሙሉ በሙሉ ካለመጠበቃቸውም በተጨማሪ ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሙሉ ልባቸው አልተስማሙም ነበር። አንዳንዶቹ የመሠረተ ትምህርት እድፈት የታየባቸው ከመሆኑም በላይ ጦረኛ ብሔራትን እንዲደግፉ ተጽዕኖ ሲደርስባቸው ግልጽ የሆነ የገለልተኝነት አቋም ይዞ በይሖዋ ጎን ከመቆም ይልቅ አቋማቸውን አላልተው ነበር። በእነዚያ የጦርነት ዓመታት የተለያየ ዓይነት ስደት ደርሶባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸው በተለያዩ አገሮች ታግደውባቸዋል። በመጨረሻም ሥራውን በግንባር ቀደምትነት ከሚያካሂዱት ወንድሞች መካከል አንዳንዶቹ የሐሰት ክስ ቀርቦባቸው ታሠሩ። በዚህ የተነሣ የአምላክ ሕዝቦች ነፃ ሳይሆኑ በግዞት እንደነበሩ ያህል መሆናቸው አያሻማም። (ከዮሐንስ 8:31, 32 ጋር አወዳድር።) መንፈሳዊ እይታቸው ጠፍቶ ነበር። (ኤፌሶን 1:16-18) በመንፈሳዊ ፍሬያማ ስላልነበሩ አምላክን በማወደስ ረገድ በአንጻራዊ ሁኔታ ድዳዎች መሆናቸውን አሳይተው ነበር። (ኢሳይያስ 32:3, 4፤ ሮሜ 14:11፤ ፊልጵስዩስ 2:11) ይህ ሁኔታ የጥንቶቹ አይሁዶች በባቢሎን ምርኮ ከነበሩበት ሁኔታ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰል ትመለከታለህን?

7, 8. በዘመናችን ያሉት ቀሪዎች መልሰው የተቋቋሙት በምን ዓይነት ሁኔታ ነው?

7 ታዲያ አምላክ በአሁኑ ዘመን ያሉት አገልጋዮቹን በዚሁ ሁኔታቸው እንዲቀጥሉ ይተዋቸው ይሆን? አምላክ በኢሳይያስ አማካኝነት እንደተነበየው መልሶ ሊያቋቁማቸው ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። ስለዚህ ይህ በምዕራፍ 35 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዘመናችንም በግልጽ ሊታይ በሚችል ሁኔታ ይፈጸማል። የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች መንፈሳዊ ብልጽግናና ጤንነት አግኝተው በመንፈሳዊ ገነት ይኖራሉ። ጳውሎስ በዕብራውያን 12:12 ላይ ኢሳይያስ 35:3ን በምሳሌያዊ መንገድ ተጠቅሞበታል። ይህ ሁኔታ የኢሳይያስ ትንቢት ክፍል የሆነውን ይህን ትንቢት በመንፈሳዊ መንገድ እንደሚፈጸም አድርገን ማቅረባችን ትክክል እንደሆነ ያረጋግጣል።

8 ቅቡዓን የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ከጦርነቱ በኋላ በነበሩት ዓመታት ከነበሩበት እንደ ግዞት ያለ ሁኔታ ነፃ ወጡ። ይሖዋ አምላክ በታላቁ ቂሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠቅሞ ነፃ አወጣቸው። በዚህ ምክንያት ቀሪዎቹ በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ ለመገንባት የተመለሱት የጥንት አይሁዶች እንዳደረጉት የመልሶ ግንባታ ሥራ ለማካሄድ ችለዋል። በተጨማሪም በጊዜያችን የሚገኙት እነዚህ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ከፍተኛ ልምላሜ ያለው መንፈሳዊ ገነት ይኸውም ምሳሌያዊ የኤደን ገነት መኮትኮትና ማበጀት ችለዋል።

9. በኢሳይያስ 35:1, 2, 5-7 ላይ እንደተገለጹት ያሉ ሁኔታዎች በጊዜያችን የተፈጸሙት እንዴት ነው?

9 ከላይ ያለውን በአእምሯችን ይዘን ኢሳይያስ ምዕራፍ 35ን እንደገና እንመርምር፤ በመጀመሪያ ቁጥር 1 እና 2ን ተመልከት። ውኃ የሌለው ደረቅ ምድረ በዳ ሆኖ የታየው ሁኔታ በጣም ለምልሞ እንደ ጥንቱ የሳሮን ማሳዎች ፍሬያማ መሆን ጀምሮ ነበር። አሁን ደግሞ ከ5 እስከ 7 ያሉትን ቁጥሮች ተመልከት። እስከ አሁን ድረስ በሕይወት ያሉትና በይሖዋ አገልግሎት በንቃት የሚሳተፉት ቅቡዓን የማስተዋል ዓይናቸው ተከፍቶላቸዋል። በ1914ም ሆነ ከዚያ በኋላ የተፈጸሙትን ሁኔታዎች ትርጉም በተሻለ መንገድ ለመረዳት ችለዋል። ይህም ደግሞ ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ አባል በሆንነውና ከቅቡዓን ጎን በምንሠራው አብዛኞቻችን ላይ ያስከተለው ለውጥ አለ።—ራእይ 7:9

ትንቢቱ በአንተም ላይ እየተፈጸመ ነውን?

10, 11. (ሀ) ኢሳይያስ 35:5-7 በአንተ ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) ስለ እነዚህ ለውጦች በግልህ ምን ይሰ ­ማሃል?

10 ለምሳሌ ራስህን ውሰድ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከመገናኘትህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ታነብ ነበርን? የምታነብ ከነበርክስ ከምታነበው ውስጥ ምን ያህሉን ትረዳ ነበር? ለምሳሌ አሁን ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ ታውቃለህ። ስለዚህ ጉዳይ ለማወቅ ለሚፈልግ ሰው በዘፍጥረት ምዕራፍ 2፣ በመክብብ ምዕራፍ 9 እና በሕዝቅኤል ምዕራፍ 18 ላይ ያሉትንና ሌሎች ብዙ አግባብነት ያላቸው ጥቅሶች አውጥተህ ማሳየት ትችላለህ። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸውን የተለያዩ ትምህርቶችና ጉዳዮች ተገንዝበሃል። በአጭሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረውን ስታስተውል ከመጽሐፉ ያገኘኸውን አብዛኛውን ነገር ለሌሎች ማካፈል ትችላለህ። ይህን ደግሞ እስካሁን እያደረግከው እንዳለ አያጠራጥርም።

11 ይሁን እንጂ እያንዳንዳችን ራሳችንን እንዲህ እያልን ብንጠይቅ ጥሩ ነው፦ ‘የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማርኩት እንዴት ነው? ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ከማጥናቴ በፊት እነዚህን ሁሉ ጥቅሶች አግኝቻቸው ነበርን? የጥቅሶቹን ትርጉም ተረድቼ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ችዬ ነበርን?’ እነዚህን ጥያቄዎች ‘አይ’ ብለህ እንደምትመልስ ግልጽ ነው። በአባበሉ ቅር እንዳትሰኝ እንጂ በእነዚህ ጥቅሶችና በጥቅሶቹ ትርጉም ረገድ ዕውር ነበርክ ሊባል ይቻላል። አይደለም እንዴ? ጥቅሶቹ እዚያው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢኖሩም አንተ ግን ልታያቸውም ሆነ ትርጉማቸውን ልትረዳ አልቻልክም። ታዲያ ዓይኖችህ ለመንፈሳዊ ነገሮች የተከፈቱት እንዴት ነው? ይሖዋ በኢሳይያስ 35:5 ላይ የሰጠውን ተስፋ ለቅቡዓን ቀሪዎች ስለ ፈጸመላቸው ነው። በዚህ ምክንያት ዓይኖችህ ተገለጡ። በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ መኖርህ አበቃ። አሁን ማየት ትችላለህ።—ከራእይ 3:17, 18 ጋር አወዳድር።

12. (ሀ) ያለንበት ጊዜ በተአምር አካላዊ ፈውስ የሚደረግበት ጊዜ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የወንድም ፍራንዝ ተሞክሮ ኢሳይያስ 35:5 በጊዜያችን የሚፈጸምበትን መንገድ የሚያሳየው እንዴት ነው?

12 መጽሐፍ ቅዱስንና አምላክ ባለፉት መቶ ዓመታት ያደረጋቸውን ነገሮች በጥሩ ማስተዋል የሚያጠኑ ሰዎች ይህ የምንኖርበት የታሪክ ወቅት በተአምር አካላዊ ፈውስ የሚገኝበት ዘመን እንዳልሆነ አውቀዋል። (1 ቆሮንቶስ 13:8-10) ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሕና የአምላክ ነቢይ መሆኑን ለማሳየት የታወሩ ዓይኖችን ያበራል ብለን አንጠብቅም። (ዮሐንስ 9:1-7, 30-33) የደነቆሩ ጆሮችም እንዲሰሙ ያደርጋል ብለን አንጠብቅም። ከቅቡዓን አንዱ የሆነውና በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ፕሬዚዳንት የነበረው ፍሬደሪክ ፍራንዝ ወደ 100 ዓመት ዕድሜ እየተጠጋ ሲሄድ የማየት ችሎታው ጨርሶ ከመድከሙም በተጨማሪ ለመስማት የሚረዳ መሣሪያ ለመጠቀም ተገድዶ ነበር። ለጥቂት ዓመታት ሌሎች ካላነበቡለት በስተቀር ራሱ ማንበብ አቅቶት ነበር። ይሁን እንጂ በኢሳይያስ 35:5 ትርጉም መሠረት እርሱን ዕውር ወይም ደንቆሮ ብሎ ሊጠራው የሚችል ሰው ይኖራልን? ጥርት አድርጎ የሚያይ መንፈሳዊ ዓይን ስለነበረው በመላው ዓለም ለሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች ትልቅ በረከት ሆኖ ኖሯል።

13. በጊዜያችን የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ምን የተለወጠላቸው ነገር ወይም መልሰው ያገኙት ነገር አለ?

13 ስለ ምላስህስ ምን ለማለት ይቻላል? የአምላክ ቅቡዓን በመንፈሳዊ ግዞት በነበሩባቸው ዓመታት ድዳ ሆነው ነበር። አምላክ ያን የነበሩበትን ሁኔታ ከለወጠላቸው በኋላ ግን ስለ ተቋቋመው የአምላክ መንግሥትና አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ስለሰጠው ተስፋ ባገኙት እውቀት በመደሰታቸው ምላሳቸው የደስታ እልልታ ማሰማት ጀመረ። የአንተም ምላሶች እንዲፈቱ ረድተዋል። ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ምን ያህል ለሰዎች ተናግረሃል? ምናልባት በምታጠናበት ጊዜ ‘ማጥናቱ ደስ ይለኛል። ግን ወጥቼ የማላውቀውን ሰው አላናግርም’ ብለህ አስበህ ይሆናል። ቢሆንም “የድዳ ምላስ” አሁን ‘በመዘመር ላይ’ አይደለምን?—ኢሳይያስ 35:6

14, 15. ባለንበት ጊዜ ብዙ ሰዎች ‘በቅድስና ጎዳና’ የተመላለሱት እንዴት ነው?

14 ከባቢሎን ነፃ ወጥተው የነበሩት የጥንት አይሁዶች ወደ አገራቸው ለመመለስ ረዥም መንገድ መጓዝ ነበረባቸው። እኛስ ምን ዓይነት ጉዞ መጓዝ ይፈለግብናል? ኢሳይያስ 35:8ን ተመልከት፦ “በዚያም ጎዳናና መንገድ ይሆናል፣ እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል። ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም።”

15 በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሌሎች በጎች የታጀቡት ቅቡዓን ቀሪዎች ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ከታላቂቱ ባቢሎን ወጥተው ወደ መንፈሳዊ ገነት በሚመራ ንጹሕ የሆነ የቅድስና መንገድ በመጓዝ ላይ ናቸው። እኛም በዚህ የቅድስና ጎዳና ለመጓዝ የሚያስችለንን ብቃት ለማግኘትና ከዚህ መንገድ ሳንወጣ ለመኖር ብርቱ ጥረት በማድረግ ላይ ነን። እስቲ ስለ ራስህ ሁኔታ አስብ። በአሁኑ ጊዜ የምትመራባቸውና የምትከተላቸው የሥነ ምግባር ደንቦችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በዓለም ውስጥ በነበርክበት ጊዜ ከነበሩህ በጣም የላቁ አይደሉምን? አስተሳሰብህንና ምግባርህን ከይሖዋ መስፈርቶች ጋር ለማስማማት የበለጠ ጥረት አታደርግም?—ሮሜ 8:12, 13፤ ኤፌሶን 4:22-24

16. በቅድስና ጎዳና ስንመላለስ ምን ነገሮች ማግኘት እንችላለን?

16 በዚህ የቅድስና ጎዳና ስትመላለስ እንደ አራዊት ያሉ ሰዎች ያጋጥሙኛል ብለህ አትሰጋም። በዓለም ውስጥ በቁምህ ሊውጡህ የሚፈልጉ ስግብግብና በጥላቻ የተሞሉ ሰዎች ስለሚያጋጥሙህ ሁልጊዜ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። አልጠግብ ባዮች እየበዙ ሄደዋል። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው ሁኔታ ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው! በአምላክ ሕዝቦች መካከል ስትሆን ከዚህ ሁሉ በተጠበቀ አካባቢ ትኖራለህ። ክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ ፍጹማን አለመሆናቸው አይካድም። አንዳንድ ጊዜ ስህተት ሊሠሩ ወይም የሚያስቀይም ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። ቢሆንም ወንድሞችህ አንተን ሆን ብለው ለመጉዳትና ለማጥፋት እንደማይነሱ ታውቃለህ። (መዝሙር 57:4፤ ሕዝቅኤል 22:25፤ ሉቃስ 20:45-47፤ ሥራ 20:29፤ 2 ቆሮንቶስ 11:19, 20፤ ገላትያ 5:15) ከዚህ ይልቅ ስለ ደህንነትህ ያስባሉ፣ ከዚህ በፊት ረድተውሃል፣ ወደፊትም አብረውህ ይሖዋን ለማገልገል ይፈልጋሉ።

17, 18. ገነት በአሁኑ ጊዜ ያለው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? ይህስ የእኛን ሕይወት እንዴት ይነካል?

17 ከቁጥር 1 እስከ 8 የሚገኙት ትንቢቶች በጊዜያችን በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ሳንዘነጋ ኢሳይያስ ምዕራፍ 35ን መመርመር እንችላለን። በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ እንደምንኖር ግልጽ አይደለምን? ይህ ገነት ገና ፍጹም አልሆነም። ቢሆንም ቁጥር 2 እንደሚናገረው በዚህ ገነት ውስጥ “የእግዚአብሔር ክብር፣ የአምላካችንንም ግርማ” ለማየት ስለቻልን እውነተኛ ገነት ነው። ውጤቱ ምንድን ነው? ቁጥር 10 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመላለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፣ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።” ከሐሰት ሃይማኖት ወጥተንና እውነተኛውን አምልኮ ተቀብለን በአምላክ ሞገስ ሥር መኖራችን በእርግጥም በእጅጉ የሚያስደስት ነገር ነው።

18 ከእውነተኛው አምልኮ ጋር ግንኙነት ያለው ይህ ደስታ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የሚሄድ ነው። አይደለም እንዴ? አዳዲስ ሰዎች ለውጥ ሲያደርጉና በእውነት ላይ ጽኑ መሠረት ሲጥሉ ትመለከታለህ። ወጣቶች ለውጥ አድርገው በጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ መሻሻል ሲያደርጉ ታያለህ። በጥምቀት ሥነ ሥርዓቶች ላይ የምታውቃቸው ሰዎች ሲጠመቁ ትመለከታለህ። ታዲያ እነዚህ ሁሉ ደስታችንን የሚያበዙ ምክንያቶች አይደሉምን? አዎን፣ ሰዎች ካገኘነው መንፈሳዊ ነፃነትና መንፈሳዊ ገነት ሲካፈሉ ማየት ምንኛ ያስደስታል!

የትንቢቱ ፍጻሜ አላበቃም!

19. ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ምን ተስፋ ይሰጠናል?

19 እስካሁን ድረስ ኢሳይያስ 35 በመጀመሪያ እንዴት እንደተፈጸመና በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊ ሁኔታ እንዴት በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አያበቃም። ከዚህ የበለጠ ፍጻሜም አለው። ይህ ትንቢት መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ምድር ላይ ቃል በቃል ስለሚኖረው ገነታዊ ሁኔታ ከሚሰጠው ማረጋገጫ ጋር የተያያዘ ነው።—መዝሙር 37:10, 11፤ ራእይ 21:4, 5

20, 21. ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ከዚህ ሌላም ፍጻሜ አለው ብሎ ማመኑ ምክንያታዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ እንደነዚህ ባሉ ሥዕላዊ ቃላት ገነታዊ ሁኔታዎችን ገልጾ ትንቢቱ በመንፈሳዊ ፍጻሜ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ቢያደርግ ከባሕርዩ ጋር የሚስማማ አይሆንም። ይህ ሲባል መንፈሳዊ ፍጻሜው በጣም አስፈላጊ አይደለም ለማለት አይደለም። በሚያምር ገነታዊ አካባቢና ሰላማዊ በሆኑ እንስሳትና አራዊት መካከል ሆነን የአራዊት ጠባይ ባላቸውና በመንፈሳዊ በተበከሉ ሰዎች ብንከበብ እንዲህ ካለው ገነት ምንም ያህል እርካታ አናገኝም። (ከቲቶ 1:12 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ መንፈሳዊ ገነት ይበልጥ አስፈላጊ ስለሆነ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

21 ወደፊት የሚመጣው ገነት በአሁኑ ጊዜ ባገኘናቸውና ወደፊት በበለጠ መጠን በምንደሰትባቸው መንፈሳዊ ፍጻሜዎች ብቻ የተወሰነ አለመሆኑ በእጅጉ ያስደስተናል። እንደ ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ያሉት ትንቢቶች ቃል በቃል እንደሚፈጸሙ ለማመን የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች አሉን። እንዴት? ኢሳይያስ በምዕራፍ 65 ላይ “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚመጡ ተንብዮአል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከይሖዋ ቀን በኋላ ስለሚመጣው ሁኔታ ሲገልጽ ይህን ጥቅስ ጠቅሷል። (ኢሳይያስ 65:17, 18፤ 2 ጴጥሮስ 3:10-13) ‘አዲሱ ምድር’ እውን ሲሆን ኢሳይያስ የገለጻቸው ሁኔታዎች በእርግጥ እንደሚመጡ ጴጥሮስ አመልክቷል። ትንቢቱ ቤቶችን ሠርቶ ለመኖሪያነት ስለ መጠቀም፣ ወይን ተክሎ ፍሬውን ስለ መብላት፣ በሠሩት ሥራ ረዥም ዘመን ስለ መደሰት፣ ተኩላና ጠቦት በአንድነት ስለ መሰማራታቸውና በዓለም ዙሪያ ጎጂ ነገር እንደማይኖር የሚናገር ሲሆን እነዚህ ሁኔታዎች የምታውቃቸው ናቸው። በሌላ አነጋገር ሰዎች ረዥም ዕድሜ፣ ምቹ መኖሪያ ቤት፣ የተትረፈረፈ ጤናማ ምግብ፣ የሚያረካ ሥራ ያገኛሉ። እንስሳትና አራዊት እርስ በርሳቸውና ከሰዎች ጋር ተስማምተው ይኖራሉ።

22, 23. ወደፊት ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ሲፈጸም ምን የደስታ ምክንያት ይኖረናል?

22 እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ ልብህ በደስታ እንዲፈነድቅ አያደርግምን? አምላክ የፈጠረን እንደዚህ ባለው አካባቢ ለመኖር በመሆኑ ልንደሰት ይገባል። (ዘፍጥረት 2:7-9) ስለዚህ እየመረመርን ያለነው በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ውስጥ የሚገኘው ትንቢት ምን ትርጉም አለው? ትንቢቱ በደስታ እልል የምንልበትን ተጨማሪ ምክንያት ይሰጣል። ቃል በቃል በረሀና ደረቅ የነበሩ አካባቢዎች ይለመልማሉ። ሰማያዊ፣ ቡናማ ወይም ሌላ ዓይነት ቀለም ያለው ዓይን ኖሯቸው በአሁኑ ጊዜ በዓይነ ስውርነት መጋረጃ የተያዙ ሰዎች በዚያ ጊዜ እንደገና ለማየት ይችላሉ። መስማት የተሳናቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ አጥርተን መስማት የሚቸግረን ጭምር በዚያ ጊዜ ጥርት ያለ ድምፅ መስማት እንችላለን። የአምላክ ቃል ሲነበብና ሲብራራ ማዳመጥ፣ አስደሳች የሆነውን የዛፎች ሽውሽውታ፣ የሕፃናት ሳቅ፣ የአእዋፍ ዝማሬ መስማት መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነገር ይሆናል!

23 በተጨማሪም አንካሶችና ሽባዎች፣ አርትራይትስ በተባለው የመገጣጠሚያ አካላት በሽታ እጅና እግራቸው የተሳሰረባቸው ጭምር እንደልባቸው መንቀሳቀስ ይችላሉ። እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል! በዚያ ጊዜ ምድረ በዳዎች በቀላሉ ምንጭ ይፈልቅባቸዋል። ውኃው እየተንዶለዶለ ሲወርድ እናያለን፣ የሚፈጥረውንም ድምፅ እንሰማለን። በእግራችን እየተዘዋወርን አረንጓዴውን ሣርና በየወንዙ ዳርቻ የበቀለውን ደንገል በእጃችን ለመዳሰስ እንችላለን። በእርግጥም ምድር ተመልሳ ገነት ትሆናለች። አለምንም ፍርሃት ወደ አንበሳ ወይም ወደ ሌላ አውሬ በመቅረብ የምናገኘው ደስታስ? ሁላችንም ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን በዓይነ ልቦናችን ያጣጣምን ስለሆነ ሁኔታውን በቃላት መግለጽ አያስፈልገንም።

24. በኢሳይያስ 35:10 ላይ የተሰጠውን ሐሳብ የምትቀበለው ለምንድን ነው?

24 ኢሳይያስ “እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል” በማለት ያረጋግጥልናል። ስለዚህ በደስታ እልል የምንልባቸው ምክንያቶች እንዳሉን ሁላችንም እንስማማለን። ይሖዋ በመንፈሳዊ ገነታችን ውስጥ ለሕዝቡ በማድረግ ላይ ባለውና በቅርቡ በሚቋቋመው ምድራዊ ገነት ውስጥ ያደርጋል ብለን ተስፋ በምናደርጋቸው ነገሮች የተነሳ ደስ ይለናል። ኢሳይያስ ደስተኞች የሆንነውን እኛን በተመለከተ “ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፣ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ” በማለት ጽፏል።—ኢሳይያስ 35:10

አስተውለኸዋል?

◻ የኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ሁለተኛ ፍጻሜ ምንድን ነው?

◻ ኢሳይያስ የተነበያቸው ተአምራዊ ለውጦች በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚፈጸሙት እንዴት ነው?

◻ ይህ ትንቢት በአንተ ላይ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

◻ ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ይሰጠናል ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰኔ 1918 ሥራውን በግንባር ቀደምትነት ያካሂዱ የነበሩ ሰባት ወንድሞች የታሰሩበት በብሩክሊን ሬመንድ ጎዳና የሚገኘው እስር ቤት

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድም ፍራንዝ ሊሞት አቅራቢያ ዓይኑ ቢታወርም መንፈሳዊ ዓይኑ አጥርቶ ይመለከት ነበር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

መንፈሳዊ እድገትና መሻሻል ደስታ ያስገኛል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ