-
ይሖዋ አምላክ ለቀሪዎቹ ምሕረት አሳየየኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
-
-
“የእግዚአብሔር ቁጥቋጥ”
5, 6. (ሀ) ኢሳይያስ ከመጪው ዓውሎ ነፋስ በኋላ የሚኖረውን ሰላም የሰፈነበት ጊዜ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) “ቁጥቋጥ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ይህስ ስለ ይሁዳ ምድር ምን ይጠቁማል?
5 ኢሳይያስ ከፊታቸው ከሚጠብቃቸው ከባድ ጥፋት ባሻገር ስለሚያገኙት የበለጠ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ በማሰብ ፍቅራዊ በሆነ ስሜት መናገር ይጀምራል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቁጥቋጥ ለጌጥና ለክብር ይሆናል፣ ከእስራኤልም ወገን ላመለጡ ሰዎች የምድሪቱ ፍሬ ለትምክሕትና ለውበት ይሆናል።”—ኢሳይያስ 4:2
6 ኢሳይያስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ስለ መልሶ መቋቋም ነው። “ቁጥቋጥ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ‘እንደ ቀንበጥና ቅርንጫፍ ያለ የሚበቅልን ነገር’ ያመለክታል። ከይሖዋ ከሚገኝ ብልጽግና፣ ጭማሪ እና በረከት ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ መንገድ ኢሳይያስ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው የይሁዳ ባድማነት እስከ መጨረሻው እንደማይቀጥል የሚጠቁም ተስፋ ሰጥቷል። በአንድ ወቅት የበለጸገ የነበረው የይሁዳ ምድር በይሖዋ በረከት እንደገና የተትረፈረፈ ፍሬ መስጠት ይጀምራል።a—ዘሌዋውያን 26:3-5
7. የይሖዋ ቁጥቋጥ ‘ለጌጥና ለክብር’ የሚሆነው በምን መንገድ ነው?
7 ኢሳይያስ ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ለውጥ ታላቅ መሆኑን ለማመልከት ሕያው የሆኑ መግለጫዎችን ተጠቅሟል። የይሖዋ ቁጥቋጥ “ለጌጥና ለክብር” ይሆናል። “ጌጥ” የሚለው ቃል ይሖዋ የተስፋይቱን ምድር በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ለእስራኤላውያን በሰጠበት ጊዜ ምድሪቱ የነበራትን ውበት ያስታውሰናል። በጣም ውብ ከመሆኗ የተነሣ “የምድር ሁሉ ጌጥ [“ፈርጥ፣” ኒው አሜሪካን ባይብል]” እንደሆነች ተደርጋ ተቆጥራለች። (ሕዝቅኤል 20:6) ስለዚህ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት ይሁዳ መልሳ የቀድሞ ክብሯንና ውበቷን እንደምታገኝ ለሕዝቡ ማረጋገጫ የሚሰጡ ነበሩ። በእርግጥም ደግሞ በምድር ላይ እንደ ፈርጥ ትሆናለች።
8. ተመልሳ የተቋቋመችው ምድር የተላበሰችውን ውበት እያጣጣሙ የሚደሰቱት እነማን ይሆናሉ? ኢሳይያስስ ስሜታቸውን የገለጸው እንዴት ነው?
8 ይሁንና ምድሪቷ ዳግም በምትላበሰው ውበት የመደሰት አጋጣሚ የሚያገኙት እነማን ናቸው? ኢሳይያስ ‘ከእስራኤል ወገን ያመለጡት’ እንደሆኑ ጽፏል። አዎን፣ አስቀድሞ ከተነገረው የሚያዋርድ ጥፋት የሚተርፉ አንዳንዶች ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 3:25, 26) ከተራፊዎቹ መካከል የቀሩት ወደ ይሁዳ ተመልሰው በመልሶ ግንባታው ሥራ ይካፈላሉ። ለእነዚህ ተመላሾች ማለትም ‘ከእስራኤል ላመለጡት ሰዎች’ ተመልሳ የምትቋቋመው ምድራቸው የምትለግሰው የተትረፈረፈ ፍሬ ‘ለትምክህትና ለውበት’ ይሆንላቸዋል። (ኢሳይያስ 4:2 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ከተማዋ በባድማነት ያሳለፈችው የውርደት ወቅት በአዲስ የኩራት መንፈስ ይተካል።
9. (ሀ) ኢሳይያስ በተናገራቸው ቃላት ፍጻሜ መሠረት በ537 ከዘአበ ምን ነገር ተከናውኗል? (ለ) ‘ያመለጡ’ የተባሉት ሰዎች በግዞት እያሉ የተወለዱትን ይጨምራሉ ማለት የሚቻለው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
9 ልክ ኢሳይያስ እንደተናገረው በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ባጠፉና ብዙ እስራኤላውያን በተገደሉ ጊዜ እንደ ዓውሎ ነፋስ ያለው ፍርድ መጥቷል። አንዳንዶቹ በሕይወት ተርፈው ወደ ባቢሎን በግዞት ተወስደዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ ምሕረት ባይሆን ኖሮ ሰው የሚባል ባልቀረ ነበር። (ነህምያ 9:31) በመጨረሻ ይሁዳ ሙሉ በሙሉ ባድማ ሆነች። (2 ዜና መዋዕል 36:17-21) ከዚያም የምሕረት አምላክ በ537 ከዘአበ ‘ያመለጡት ሰዎች’ እውነተኛውን አምልኮ ለማቋቋም ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ ፈቀደ።b (ዕዝራ 1:1-4፤ 2:1) ከግዞት የተመለሱት እነዚህ ሰዎች ያሳዩት ልባዊ ንስሐ በመዝሙር 137 ላይ ውብ በሆነ መንገድ ተገልጿል። ይህ መዝሙር የተጻፈው በምርኮ እያሉ ወይም ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ሳይሆን አይቀርም። በይሁዳም መሬቱን አርሰው ዘር ዘርተዋል። አምላክ ምድሪቱ ፍሬያማ እንደነበረችው ‘ኤድን ገነት’ እንድታብብ በማድረግ ጥረታቸውን እየባረከላቸው እንዳለ ሲመለከቱ ምን እንደተሰማቸው ገምት!—ሕዝቅኤል 36:34-36
10, 11. (ሀ) በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ግዞት ሥር ነበሩ ማለት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎችን የባረካቸው እንዴት ነው?
10 በዘመናችንም ተመሳሳይ የመልሶ ማቋቋም ሥራ ተከናውኗል። በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ይታወቁ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ መንፈሳዊ ምርኮኛ ሆነው ነበር። (ራእይ 17:5) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ምንም እንኳ ብዙ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ትተው የነበረ ቢሆንም ከአንዳንድ ባቢሎናዊ ሐሳቦችና ድርጊቶች ገና አልተላቀቁም ነበር። ቀሳውስቱ በቆሰቆሱት ተቃውሞ ምክንያት አንዳንዶቹ ቃል በቃል ወኅኒ ወርደው ነበር። መንፈሳዊ ምድራቸው ማለትም ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ ርስታቸው ባድማ ሆኖ ነበር።
11 ይሁን እንጂ በ1919 የፀደይ ወቅት ይሖዋ ለእነዚህ የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ምሕረት አሳየ። (ገላትያ 6:16) ንስሐቸውንና እርሱን በእውነት ለማምለክ ያላቸውን ፍላጎት በመመልከት ቃል በቃል ከነበሩበት ወኅኒ ብቻ ሳይሆን ከመንፈሳዊውም ምርኮ ነፃ አውጥቷቸዋል። እነዚህ ‘ያመለጡ ሰዎች’ አምላክ ወደሰጣቸውና ብዙ ፍሬ እንዲያፈራ ወዳደረገው መንፈሳዊ ርስት ተመልሰዋል። ይህ መንፈሳዊ ርስት ጋባዥና ማራኪ እይታ ያለው በመሆኑ አምላክን የሚፈሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀሪዎቹ ጋር በአምልኮ ለመተባበር ተስበዋል።
12. የኢሳይያስ ቃላት ይሖዋ ለሕዝቡ ያሳየውን ምሕረት ጎላ አድርገው የሚገልጹት እንዴት ነው?
12 እዚህ ላይ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት አምላክ ለሕዝቡ ያሳየውን ምሕረት ጎላ አድርገው የሚገልጹ ናቸው። እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ለይሖዋ ጀርባቸውን ቢሰጡም እርሱ ግን ንስሐ ለገቡት ቀሪዎች ምሕረት አሳይቷል። ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችም እንኳ ተስፋ ኖሯቸው ወደ ይሖዋ መመለስ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ ማወቃችን ሊያጽናናን ይችላል። ይሖዋ የተሰበረውን ልብ ስለማይንቅ ንስሐ የሚገቡ ሰዎች በፍጹም የይሖዋን ምሕረት ሊያገኙ እንደማይችሉ ሊሰማቸው አይገባም። (መዝሙር 51:17) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፣ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል።” (መዝሙር 103:8, 13) በእርግጥም እንዲህ ያለውን መሐሪ አምላክ ሁላችንም ልናወድሰው ይገባል!
-
-
ይሖዋ አምላክ ለቀሪዎቹ ምሕረት አሳየየኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
-
-
a አንዳንድ ምሁራን “የእግዚአብሔር ቁጥቋጥ” የሚለው ሐረግ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚናገረው ከኢየሩሳሌም መልሶ መቋቋም በኋላ ስለሚገለጠው መሲሕ ነው ይላሉ። ይህ አገላለጽ በአረማይኩ ትርጉም ውስጥ “የይሖዋ መሲህ [ክርስቶስ]” በሚል ተብራርቶ ተቀምጧል። የሚያስገርመው ከጊዜ በኋላ ኤርምያስ መሲሁ ከዳዊት ዘር የተገኘ “ጻድቅ ቁጥቋጥ” መሆኑን ሲገልጽ የተጠቀመበት የዕብራይስጥ ስም (ጼማክ) ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ነው።—ኤርምያስ 23:5፤ 33:15
b “ያመለጡ” የተባሉት ሰዎች በግዞት እያሉ የተወለዱትንም ይጨምራሉ። ወላጆቻቸው ከጥፋቱ ባይተርፉ ኖሮ ሊወለዱ የሚችሉበት አጋጣሚ ስላልነበረ እነርሱም ‘እንዳመለጡ’ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ።—ዕዝራ 9:13-15፤ ከዕብራውያን 7:9, 10 ጋር አወዳድር።
-