ደስተኞች ናችሁ የተባሉ የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች
“እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል።”— ኢሳይያስ 35:10
1. ዓለም የሚያስፈልገው አንገብጋቢ ነገር ምንድን ነው?
የሰው ልጅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ የምስራች መልእክተኛ ያስፈልገዋል። ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን የሚናገር፣ ክፉ ሰዎችን ስለሚመጣው ጥፋት የሚያስጠነቅቅና ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አምላካዊ ሰላም እንዲያገኙ የሚረዳ ደፋር ምሥክር በአስቸኳይ ያስፈልጋል።
2, 3. ይሖዋ በአሞጽ 3:7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ቃሉን ለእስራኤላውያን የፈጸመላቸው እንዴት ነው?
2 በእስራኤላውያን ዘመን ይሖዋ እንዲህ ዓይነት መልእክተኞች እንደሚያስነሳ ቃል ገብቶ ነበር። በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ላይ ነቢዩ አሞጽ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም።” (አሞጽ 3:7) ይህ ቃል ከተነገረ በኋላ ባሉት መቶ ዘመናት ይሖዋ ብዙ ታላላቅ ድርጊቶችን ፈጽሟል። ለምሳሌ ያህል በ607 ከዘአበ ምርጥ ሕዝቦቹ ዓመፀኞችና ደም አፍሳሾች በመሆናቸው ቁጣውን አፍስሶባቸዋል። በተጨማሪም በእስራኤል ዙሪያ የነበሩት ብሔራት በእስራኤል መከራ ደስ በመሰኘታቸውና በመፈንጠዛቸው ቀጥቷቸዋል። (ኤርምያስ ምዕራፍ 46-49) ከዚያም ይሖዋ በ539 ከዘአበ ብርቱ የነበረው የባቢሎን የዓለም ኃይል እንዲወድቅ በማድረግ በ537 ከዘአበ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሱን ዳግመኛ የሚሠሩ እስራኤላውያን ቀሪዎች ወደ ምድራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።— 2 ዜና መዋዕል 36:22, 23
3 እነዚህ ሁሉ ምድርን ያናወጡ ክንውኖች ሲሆኑ ይሖዋም አሞጽ በተናገረው መሠረት መልእክተኞቹ ሆነው ባገለገሉ ነቢያት አማካኝነት እስራኤላውያንን ስለሚመጣባቸው ሁኔታ አስጠንቅቋቸዋል። በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ ኢሳይያስን አስነሳ። በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አጋማሽ ላይ ኤርምያስን አስነሳ። ከዚያም በዚያው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ሕዝቅኤልን አስነሳ። እነዚህና ሌሎች ታማኝ ነቢያት ስለ ይሖዋ ዓላማዎች የተሟላ ምሥክርነት ሰጥተዋል።
ዛሬ ያሉትን የአምላክ መልእክተኞች ለይቶ ማወቅ
4. የሰው ልጅ የሰላም መልእክተኛ እንደሚያስፈልገው የሚያሳየው ምንድን ነው?
4 ዛሬስ? በዓለም የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የሰብዓዊውን ኅብረተሰብ መፈራረስ በመመልከት ታላቅ መዓት ሊመጣ እንደተቃረበ ይሰማቸዋል። የጽድቅ ፍቅር ያላቸው ሰዎች የሕዝበ ክርስትናን ግብዝነትና ክፋት ሲመለከቱ በጣም ያዝናሉ። ይሖዋ በሕዝቅኤል በኩል እንደተነበየው ‘በመካከልዋ እየተሠራ ባለው ርኩሰት ሁሉ እያለቀሱና እየተከዙ’ ነው። (ሕዝቅኤል 9:4) ይሁን እንጂ ብዙዎች የይሖዋ ዓላማ ምን እንደሆነ አልተገነዘቡም። ሊነገራቸው ያስፈልጋል።
5. ኢየሱስ በዘመናችን መልእክተኞች እንደሚኖሩ የገለጸው እንዴት ነው?
5 ታዲያ ዛሬ የኢሳይያስን፣ የኤርምያስንና የሕዝቅኤልን በመሰለ የድፍረት መንፈስ የሚናገር ሰው አለን? ኢየሱስ ይህን የሚያደርግ እንደሚኖር አመልክቷል። በዘመናችን ስለሚፈጸሙ ክንውኖች በተነበየ ጊዜ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) በዛሬው ጊዜ መልእክተኛና የምስራች ሰባኪ በመሆን ይህን ትንቢት በመፈጸም ላይ የሚገኘው ማን ነው? በዚህ በእኛ ዘመንና በጥንትዋ እስራኤል ዘመን ያሉ ተመሳሳይ ሁኔታዎች የዚህን ጥያቄ መልስ ይጠቁሙናል።
6. (ሀ) በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ‘የአምላክ እስራኤል’ ምን እንደ ደረሰባቸው ግለጽ። (ለ) ሕዝቅኤል 11:17 በጥንቷ እስራኤል ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
6 በመጀመሪያው ዓለም ጦርነት የጨለማ ዓመታት ዘመናዊ የይሖዋ ሕዝቦች የነበሩት ‘የአምላክ እስራኤል’ ቅቡዓን ቀሪዎች እስራኤላውያን በባቢሎን ከነበሩበት ሁኔታ ጋር በሚመሳሰል ግዞት ይገኙ ነበር። (ገላትያ 6:16) ሕዝበ ክርስትና ዋነኛ አባልና ተነቃፊ በሆነችበት በዓለም የሐሰት ሃይማኖት ኅብረት ማለትም በታላቂቱ ባቢሎን መንፈሳዊ ግዞት ሥር ነበሩ። ቢሆንም ይሖዋ ለሕዝቅኤል የተናገራቸው ቃላት ፈጽመው የተጣሉ እንደማይሆኑ ያመለክታሉ። እንዲህ ብሏል:- “ከአሕዛብ ዘንድ አከማቻችኋለሁ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች እሰበስባችኋለሁ፣ የእስራኤልንም ምድር እሰጣችኋለሁ።” (ሕዝቅኤል 11:17) ይሖዋ ይህን ለጥንት እስራኤላውያን የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል የባቢሎንን የዓለም ኃያል መንግሥት ገልብጦ እስራኤላውያን ቀሪዎች ወደ ምድራቸው የሚመለሱበትን መንገድ የከፈተውን የፋርሱን ቂሮስን አስነስቷል። ዛሬስ?
7. በ1919 ኢየሱስ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እርምጃ እንደወሰደ የሚያሳይ ምን ነገር ተከናውኗል? አብራራ።
7 በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ታላቁ ቂሮስ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንዳለ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ታይቷል። ታላቁ ቂሮስ ማን ነው? በ1914 በሰማያዊ መንግሥት ዙፋን ላይ ከተቀመጠው ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ይህ ታላቅ ንጉሥ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 ከመንፈሳዊ ግዞት ወጥተው ወደ ‘ምድራቸው፣’ ማለትም ወደ መንፈሳዊ ርስታቸው እንዲመለሱ በማድረግ በምድር ላይ ይገኙ ለነበሩት ቅቡዓን ወንድሞቹ በጎ ፈቃዱን አሳይቷቸዋል። (ኢሳይያስ 66:8፤ ራእይ 18:4) በዚህ መንገድ ሕዝቅኤል 11:17 ዘመናዊ ፍጻሜ አግኝቷል። ጥንት እስራኤላውያን ወደ ምድራቸው እንዲመለሱ ባቢሎን መውደቅ ነበረባት። በዚህ ዘመን ደግሞ “የአምላክ እስራኤል” ዳግመኛ መቋቋም ታላቂቱ ባቢሎን በታላቁ ቂሮስ እጅ መውደቋን ያመለክታል። ይህን ውድቀትዋን በራእይ ምዕራፍ 14 ላይ የተገለጸው ሁለተኛው መልአክ “አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቊጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች” በማለት አብስሯል። (ራእይ 14:8) ይህ ለታላቂቱ ባቢሎን፣ በተለይም ለሕዝበ ክርስትና እንዴት ያለ ከፍተኛ ውድቀት ነው! ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ታላቅ በረከት ነው!
8. የሕዝቅኤል መጽሐፍ የአምላክ ሕዝቦች በ1919 ነፃ ከወጡ በኋላ ያገኙትን ደስታ የሚገልጸው እንዴት ነው?
8 በሕዝቅኤል 11:18-20 ላይ የአምላክ ሕዝቦች ተመልሰው በመቋቋማቸው የሚሰማቸውን ደስታ ነቢዩ ገልጾታል። ይህ ትንቢት ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመው እስራኤላውያን በዕዝራና በነህምያ ዘመን ራሳቸውን ባነጹበት ጊዜ ነበር። ዘመናዊው ፍጻሜ ደግሞ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል መሆን አለበት። እስቲ እንመልከት። ይሖዋ “ወደዚያም [ወደ ምድራቸው] ይመጣሉ፣ ጸያፉንና ርኩሱንም ነገር ሁሉ ከእርስዋ ያወጣሉ” ይላል። በዚህ ትንቢት መሠረት ይሖዋ ከ1919 ጀምሮ ሕዝቦቹን አጥርቶ እርሱን ለማገልገል የሚያስፈልጋቸውን ብርታት እንዲያገኙ አድርጓል። ከመንፈሳዊ አካባቢያቸው በአምላክ ፊት የተበከሉ ሆነው እንዲታዩ ያደረጓቸውን ባቢሎናዊ ልማዶችና መሠረተ ትምህርቶች ማስወገድ ጀመሩ።
9. ይሖዋ ከ1919 አንስቶ ለሕዝቦቹ ምን ጎላ ብለው የሚታዩ በረከቶችን አፍስሷል?
9 ከዚያም ይሖዋ በመቀጠል ቁጥር 19 ላይ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፣ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ እሰጣለሁ። ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ።” ይሖዋ በእነዚህ ቃላት መሠረት በ1919 ቅቡዓን አገልጋዮቹ ‘እጅ ለእጅ ተያይዘው’ እንዲያገለግሉት አንድነት እንዲኖራቸው በማድረግ በምሳሌያዊ አነጋገር “አንድ ልብ” ሰጥቷቸዋል። (ሶፎንያስ 3:9) በተጨማሪም ለሕዝቦቹ በምሥክርነቱ ሥራ የሚያበረታቸውንና በገላትያ 5:22, 23 ላይ የተዘረዘሩትን መልካም ፍሬዎች እንዲያፈሩ የሚያስችላቸውን መንፈስ ቅዱስ ሰጥቷቸዋል። እንደ ድንጋይ የጠነከረውንና አዎንታዊ ምላሽ የማይሰጠውን ልባቸውን አስወግዶ ገር፣ ታዛዥና ተቀባይ ልብ፣ ለፈቃዱ የሚገዛ ልብ እንዲኖራቸው አድርጓል።
10. ይሖዋ ተመልሰው የተቋቋሙትን ሕዝቦቹን ከ1919 አንስቶ የባረካቸው ለምንድን ነው?
10 ይህን ያደረገው ለምን ነበር? ይሖዋ ራሱ መልሱን ይሰጠናል። ሕዝቅኤል 11:20 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ . . . እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።” የአምላክ እስራኤል አባላት የራሳቸውን ሐሳብ ከመከተል ይልቅ የይሖዋን ሕግ መታዘዝን ተምረዋል። ሰዎችን ሳይፈሩ የአምላክን ፈቃድ ማድረግን ተምረዋል። ይህን በማድረጋቸውም ከሕዝበ ክርስትና አስመሳይ ክርስቲያኖች የተለዩ ሆነው ታይተዋል። የይሖዋ ሕዝቦች ሆነዋል። በመሆኑም ይሖዋ መልእክተኛው አድርጎ ሊጠቀምባቸው ማለትም “ታማኝና ልባም” ባሪያው ሊያደርጋቸው ተዘጋጅቶ ነበር።— ማቴዎስ 24:45-47
የአምላክ መልእክተኞች ያገኙት ደስታ
11. የኢሳይያስ መጽሐፍ የይሖዋ ሕዝቦች ያገኙትን ደስታ የሚገልጸው እንዴት ነው?
11 እንዴት ያለ ታላቅ መብት እንደተሰጣቸው ሲገነዘቡ የተሰማቸውን ደስታ ልትገምቱ ትችላላችሁ? በቡድን ደረጃ በኢሳይያስ 61:10 ላይ የሚገኘውን “በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፣ ነፍሴም በአምላኬ ሐሴት ታደርጋለች” የሚለውን ቃል አስተጋብተዋል። በኢሳይያስ 35:10 ላይ የተገባው ቃል በእነርሱ ላይ ፍጻሜ አግኝቶአል:- “እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፣ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፣ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።” የይሖዋ አምላካዊ ሰላም መልእክተኞች በ1919 ምሥራቹን ለሰው ዘር ሁሉ ለመስበክ በተነሱ ጊዜ የሚገኙበት ደስታ ይህን ይመስል ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይህን ሥራቸውን ከመፈጸም ወደ ኋላ አላሉም፣ ደስታቸውም እየጨመረ መጥቷል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ “ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው፣ ‘የአምላክ ልጆች’ ይባላሉና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:9 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።) “የአምላክ ልጆች” ቅቡዓን ቀሪዎች የዚህን ቃል እውነተኝነት ከ1919 ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ አይተዋል።
12, 13. (ሀ) ከአምላክ እስራኤል አባላት ጎን ይሖዋን ለማገልገል የተሰለፉት እነማን ናቸው? የትኛውንስ ሥራ አከናውነዋል? (ለ) የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች ምን ታላቅ ደስታ አግኝተዋል?
12 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ቁጥር እየጨመረ ሄዶ በ1930ዎቹ ዓመታት የቀሩትን ቅቡዓን የመሰብሰቡ ሥራ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቦ ነበር። ታዲያ የምስራቹ ሰባኪዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ በዚያ ጊዜ አቁሟልን? በፍጹም አላቆመም። በዚያን ጊዜ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ክርስቲያኖች ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህም ከቅቡዓን ወንድሞቻቸው ጋር በመተባበር የስብከቱን ሥራ ማከናወን ቀጠሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ እነዚህን እጅግ ብዙ ሰዎች በራእይ የተመለከታቸው ሲሆን ስለ እነርሱ የሰጠው መግለጫ ሊስተዋል ይገባል:- “በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፣ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል” ብሏል። (ራእይ 7:15) አዎን፣ እጅግ ብዙ ሰዎች አምላካቸውን በማገልገሉ ሥራ ተጠምደዋል። በዚህም ምክንያት ከ1935 አንስቶ የቅቡዓኑ ቁጥር መቀነስ ሲጀምር እነዚህ ታማኝ ባልደረቦቻቸው የምስክርነቱን ሥራ እያፋጠኑት ነው።
13 በዚህ መንገድ ኢሳይያስ 60:3, 4 ፍጻሜውን አግኝቷል:- “አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ፣ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ። ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፣ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፣ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል።” እነዚህ ክንውኖች ‘ለአምላክ እስራኤል’ ያስገኙት ደስታ በኢሳይያስ 60:5 ላይ ውብ በሆኑ ቃላት ተገልጿል። እንዲህ እናነባለን:- “በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፣ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፣ አይተሽ ደስ ይልሻል፣ ልብሽም ይደነቃል፣ ይሰፋማል።”
በእንቅስቃሴ ላይ ያለው የይሖዋ ድርጅት
14. (ሀ) ሕዝቅኤል ምን ሰማያዊ ራእይ አይቷል? ምንስ ትእዛዝ ተቀብሏል? (ለ) በዘመናችን ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች ያስተዋሉት ነገር ምንድን ነው? ምን ግዴታ እንዳለባቸውስ ይሰማቸዋል?
14 በ613 ከዘአበ ሕዝቅኤል ሠረገላ መሰሉ የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት በእንቅስቃሴ ላይ እንዳለ የሚያሳይ አስደናቂ ራእይ ተመልክቶ ነበር። (ሕዝቅኤል 1:4-28) በኋላም ይሖዋ እንዲህ አለው:- “የሰው ልጅ ሆይ፣ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፣ ቃሌንም ተናገራቸው።” (ሕዝቅኤል 3:4) በዚህ በ1997 ዓመትም የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም አንዳች ነገር ሳይገታው ወደ ፊት በመገስገስ ላይ እንዳለ እናስተውላለን። ስለዚህም ስለ እነዚህ ዓላማዎች ለሰዎች የመናገር ግዴታ እንዳለብን ይሰማናል። ሕዝቅኤል በዘመኑ በቀጥታ በይሖዋ መንፈስ የተነገረውን ቃል ይናገር ነበር። ዛሬ ደግሞ በመንፈስ ከተጻፈው የይሖዋ ቃል፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣ ቃል እንናገራለን። ይህ መጽሐፍ ለሰው ልጆች በጣም አስደናቂ የሆነ መልእክት ይዟል! ብዙ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ሁኔታ የሚጨነቁ ቢሆንም ሁኔታዎቹ በአንድ በኩል እነርሱ ከሚያስቡት በላይ በጣም አስከፊ እንደሚሆኑና በሌላ በኩል ደግሞ እነርሱ ከሚገምቱት በጣም የተሻለ ሁኔታ እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል።
15. ሁኔታዎቹ ዛሬ ብዙዎቹ ሰዎች ከሚያስቡት ይበልጥ የከፉት ለምንድን ነው?
15 ሁኔታዎቹ አስከፊ የሚሆኑት ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ እንደተማርነው ሕዝበ ክርስትናና የቀሩት የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በ607 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ዓይነት ጥፋት በቅርቡ ስለሚደርስባቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ባሉት አውሬ የተመሰለው ምድር አቀፍ ፖለቲካዊ ሥርዓት የኢየሩሳሌም አጎራባቾች እንደነበሩት አረማውያን ብሔራት ተጠራርጎ ይጠፋል። (ራእይ 13:1, 2፤ 19:19-21) በሕዝቅኤል ዘመን ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ የሚደርሰው ጥፋት የሚያስከትለውን ፍርሐትና ድንጋጤ ቁልጭ አድርጎ ገልጾት ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎች እየቀረበ ያለውን የዚህ ዓለም ጥፋት ሲያስተውሉ እሱ የተናገራቸው ቃላት ከዚህ የበለጠ ትርጉም ይኖራቸዋል። ይሖዋ ለሕዝቅኤል እንዲህ ብሎታል:- “ስለዚህም፣ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፣ አልቅስ፤ ወገብህን በማጉበጥ በፊታቸው ምርር ብለህ አልቅስ። እነርሱም:- ስለ ምን ታለቅሳለህ? ቢሉህ፣ አንተ እንዲህ በላቸው:- ወሬ ስለሚመጣ ነው። ልብም ሁሉ ይቀልጣል፣ እጆችም ሁሉ ይዝላሉ፣ ነፍስም ሁሉ ትደክማለች፣ ጉልበትም እንደ ውኃ ይፈስሳል። እነሆ ይመጣል፣ ይፈጸምማል፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” (ሕዝቅኤል 21:6, 7፤ ማቴዎስ 24:30) በጣም አስፈሪ የሆነ ሁኔታ ከፊታችን ይጠብቀናል። ለሰዎች ያለን ጥልቅ የሆነ አሳቢነት ማስጠንቀቂያውን እንድናሰማ፣ ስለ መጪው የይሖዋ ቁጣ የሚገልጸውን “ወሬ” እንድንናገር ይገፋፋናል።
16. ቅን የሆኑ ሰዎች ብዙዎቹ ሰዎች ከሚያስቡት የበለጠ የተሻለ ሁኔታ የሚያገኙት ለምንድን ነው?
16 በሌላው በኩል ደግሞ ቅን የሆኑ ሰዎች አብዛኞቹ ከሚያስቡት በጣም የተሻለ ሁኔታ ይጠብቃቸዋል። በምን መንገድ? ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአታችን ቤዛ ሆኖ በመሞቱና አሁን ደግሞ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆኑ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:15፤ ራእይ 11:15) በሰው ልጆች አመለካከት መፍትሔ ሊያገኙ የማይችሉ መስለው የሚታዩት የሰው ልጅ ችግሮች በቅርቡ በዚህ ሰማያዊ መንግሥት አማካኝነት ይወገዳሉ። ሞት፣ በሽታ፣ ሙስና፣ ረሐብ፣ ወንጀልና የአካባቢ መበከል የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ። የአምላክ መንግሥት ገነት የምትሆነውን ምድር ያለምንም ተቀናቃኝ ያስተዳድራል። (ራእይ 21:3, 4) የሰው ዘር ከይሖዋ አምላክ ጋርና እርስ በርሱ ሰላማዊ ዝምድና በመመስረት አምላካዊ ሰላም ያገኛል።— መዝሙር 72:7
17. የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞችን ልብ ደስ የሚያሰኙት የትኞቹ ጭማሪዎች ናቸው?
17 በአንዳንድ የዓለም አካባቢዎች ብዙ ቅን ሰዎች ይህን የአምላካዊ ሰላም መልእክት በመቀበል ላይ ናቸው። ጥቂቶቹን ብቻ እንጥቀስ ብንል ባለፈው ዓመት ዩክሬይን 17 በመቶ የሆነ የአስፋፊዎች ጭማሪ ሪፖርት አድርጋለች። ሞዛምቢክ 17 በመቶ፣ ሊትዋንያ 29 በመቶ ጭማሪ ሪፖርት አድርገዋል። ሩሲያ 31 በመቶ፣ አልባኒያ ደግሞ 52 በመቶ የሆነ የአስፋፊዎች ጭማሪ አግኝታለች። እነዚህ ጭማሪዎች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አምላካዊ ሰላም ማግኘት የሚፈልጉና ከጽድቅ ጎን የተሰለፉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ያመለክታሉ። እንዲህ ያለው ፈጣን እድገት ለመላው የክርስቲያኖች ወንድማማች ማኅበር ደስታ ያመጣል።
18. ሰዎች ሰሙም አልሰሙ የእኛ አመለካከት ምን መሆን አለበት?
18 በክልላችሁ የሚኖሩ ሰዎች ይህን የመሰለ ፈጣን ምላሽ እያሳዩ ነውን? ከሆነ በጣም ያስደስታል። በአንዳንድ ክልሎች ግን ፍላጎት ያለው አንድ ሰው እንኳን ለማግኘት የበርካታ ሰዓቶች ድካም ይጠይቃል። ታዲያ እንዲህ ባሉት ክልሎች የሚያገለግሉ ወንድሞች ሥራቸውን ቸል ይላሉ ወይም ተስፋ ይቆርጣሉን? በፍጹም እንዲህ አያደርጉም። የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ ወጣቱን ሕዝቅኤልን ለአይሁዳውያን ወገኖቹ እንዲሰብክ ነቢይ አድርጎ ሲሾመው የተናገረውን ቃል ያስታውሳሉ። “እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ” ብሎታል። (ሕዝቅኤል 2:5) እኛም እንደ ሕዝቅኤል ሰዎች ሰሙም አልሰሙ ስለ አምላካዊ ሰላም መናገራችንን እንቀጥላለን። ቢያዳምጡን ደስ ይለናል። ጀርባቸውን ሲሰጡን፣ ሲቀልዱብን፣ ከዚህም አልፈው ሲያሳድዱን ደግሞ እንጸናለን። ይሖዋን እንወዳለን፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “ፍቅር . . . በሁሉ ይጸናል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7) በጽናት ስለምንሰብክ የይሖዋ ምሥክሮች እነማን እንደሆኑ ሰዎች ያውቃሉ። መልእክታችን ምን እንደሆነ ያውቃሉ። መጨረሻው ሲመጣ የይሖዋ ምሥክሮች አምላካዊ ሰላም እንዲያገኙ ለመርዳት ሞክረው እንደነበረ ይገነዘባሉ።
19. የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ምን ውድ መብት አግኝተናል?
19 ይሖዋን ከማገልገል የሚበልጥ መብት ሊኖር ይችላልን? በፍጹም የለም! ከሁሉ የበለጠ ደስታ የምናገኘው ከአምላክ ጋር ባለን ዝምድናና የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ እንዳለን በማወቃችን ነው። “እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው። አቤቱ፣ [ይሖዋ] በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ።” (መዝሙር 89:15) ስለዚህ ለሰው ልጆች የአምላክ የሰላም መልእክተኞች መሆናችን ያስገኘልንን ደስታ ምንጊዜም እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንመልከተው። ይሖዋ ይብቃ እስኪል ድረስ በዚህ ሥራ በትጋት እንሳተፍ።
ታስታውሳለህን?
◻ በዛሬው ጊዜ የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች እነማን ናቸው?
◻ ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 እንደ ወደቀች እንዴት እናውቃለን?
◻ ‘እጅግ ብዙ ሰዎችን’ የሚያሳስባቸው ዋነኛው ነገር ምንድን ነው?
◻ የወደፊቱ ጊዜ ብዙ ሰዎች ከሚያስቡት ይበልጥ የጨለመው ለምንድን ነው?
◻ ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች የወደፊቱ ጊዜ እነርሱ ከሚገምቱት ይበልጥ የተሻለ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዛሬ ብዙ ሰዎች የሰብዓዊውን ኅብረተሰብ መፈራረስ ሲመለከቱ ታላቅ መዓት ሊመጣ እንዳለ ይሰማቸዋል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች ዛሬ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ደስተኞች ናቸው