-
አጽናፈ ዓለም የሚተዳደርበትን ሕግ ያወጣው ማን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2011 | ሐምሌ 1
-
-
1. አጽናፈ ዓለም ምንም ለውጥ አያደርግም?
አርስቶትል በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ክበቦች ምንም ዓይነት ለውጥ የማይታይባቸው እንደሆኑ አድርጎ ያስብ ነበር። እንደ አርስቶትል አስተሳሰብ ከሆነ ከዋክብትን የያዘው ክበብም ሆነ ሌሎቹ ክበቦች እየሰፉም ሆነ እያነሱ መሄድ አይችሉም።
በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? እንዲህ የመሰለ ግምታዊ ሐሳብ ይሰነዝራል? በፍጹም! የአምላክ ቃል በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ቀጥተኛ መግለጫ የለም። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሚከተለውን አስገራሚ መግለጫ ልብ በል፦ “እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦቿም እንደ አንበጣ ናቸው። ሰማያትን እንደ ድባብ [“ስስ ጨርቅ፣” NW] ይዘረጋቸዋል፤ እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይተክላቸዋል።”—ኢሳይያስ 40:22a
ታዲያ ዛሬ ይበልጥ ትክክል ሆኖ የተገኘው የአርስቶትል ሐሳብ ነው ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ? ዘመናዊው የጠፈር ጥናት አጽናፈ ዓለምን በተመለከተ ምን ይላል? በ20ኛው መቶ ዘመን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አጽናፈ ዓለም ባለበት የሚቀጥል ሳይሆን እየተለጠጠ የሚሄድ መሆኑን ሲያውቁ በጣም ተደንቀዋል። እንዲያውም ጋላክሲዎች በከፍተኛ ፍጥነት አንዳቸው ከሌላው በመሸሽ ላይ ያሉ ይመስላል። አጽናፈ ዓለም እየሰፋ እንደሚሄድ የገመቱ ሳይንቲስቶች አልነበሩም፤ ካሉም በጣም ጥቂት ቢሆኑ ነው። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የኮስሞሎጂ ባለሙያዎች አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ ላይ አነስተኛና ጥቅጥቅ ያለ እንደነበረ እንዲሁም ከዚያን ጊዜ አንስቶ አለማቋረጥ እየሰፋ እንደመጣ ያምናሉ። በሌላ አባባል አርስቶትል አጽናፈ ዓለምን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ የተሳሳተ መሆኑን ሳይንስ አረጋግጧል።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው መግለጫስ ምን ማለት ይቻላል? ነቢዩ ኢሳይያስ ራሱን ቀና አድርጎ በከዋክብት ያሸበረቀውን ሰማይ ሲመለከት ሁኔታውን ከተዘረጋ ድንኳን ጋር ማመሳሰሉ ምንም አያስገርምም።b እንዲያውም ኢሳይያስ ፍኖተ ሐሊብ የተባለው ጋላክሲ “ስስ ጨርቅ” እንደሚመስል ሳያስተውል አልቀረም።
ከዚህም በላይ ኢሳይያስ የተጠቀመበት መግለጫ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችን እንድንስለው የሚያደርግ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች ከጠንካራ ጨርቅ የተሠራና ተጠቅልሎ የተቀመጠን ድንኳን ሲፈቱ፣ በእንጨት ሲወጥሩ እናም ትንሽ የሚመስለው ጨርቅ ተዘርግቶ ትልቅ ቤት ሲሆን በአእምሯችን ማሰብ እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ነጋዴ ስስ ጨርቅ ሊገዛ ለመጣ ሰው ትንሽ የሚመስል አንድ ጣቃ አንስቶ እየተረተረ ሲያሳየው በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን። በሁለቱም ሁኔታ እንዳየነው ከሆነ ተጠቅልሎ ሲቀመጥ ትንሽ ይመስል የነበረው ነገር ሲዘረጋ ትልቅ ሆኗል።
እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን በአእምሯችን እንድንስለው በሚያደርግ መንገድ ስለ ድንኳንና ስለ ስስ ጨርቅ የተናገረው አጽናፈ ዓለም እየሰፋ መሄዱን ለማመልከት ነው ማለታችን አይደለም። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አጽናፈ ዓለም የሚሰጠው መግለጫ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር የሚጣጣም መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም? ኢሳይያስ የኖረው አርስቶትል ከኖረበት ዘመን ሦስት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ እንዲሁም ሳይንስ በዚህ ጉዳይ ላይ አሳማኝ ማስረጃ ከማቅረቡ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ነው። ያም ቢሆን ይህ ተራ ዕብራዊ ነቢይ የጻፈው መግለጫ አርስቶትል እንዳዘጋጀው ድንቅ ሞዴል ማሻሻያ ወይም ማስተካከያ ማድረግ አላስፈለገውም።
-
-
አጽናፈ ዓለም የሚተዳደርበትን ሕግ ያወጣው ማን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2011 | ሐምሌ 1
-
-
a መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን ክበብ ብሎ መጥራቱ የሚያስደንቅ ነው፤ ክበብ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ድቡልቡል ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አርስቶትልና ሌሎች ጥንታዊ የግሪክ ሊቃውንት ምድር ድቡልቡል እንደሆነች ያስቡ ነበር፤ ይሁን እንጂ ምድር ድቡልቡል ናት የሚለው ሐሳብ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላም እንኳ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ነበር።
-