-
ብርሃን አብሪዎች የሆንነው ለምን ዓላማ ነው?መጠበቂያ ግንብ—1993 | ጥር 15
-
-
“ለአሕዛብ ብርሃን” እንዲሆን የተሰጠ
6. ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እንድናገኘው ያስቻለን ምን አስደናቂ ተስፋ ነው?
6 ገና አዳምና ሔዋን ከገነት ከመባረራቸው በፊት ይሖዋ ጽድቅ ወዳዶችን ነጻ የሚያወጣ “ዘር” እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:15) ይህ ተስፋ የተደረገው ዘር ሰው ሆኖ እንደ ተወለደ ይሖዋ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረው ስምዖን የተባለ አረጋዊ ሕፃኑ “ለአሕዛብ ሁሉ [መሸፈኛውን አዓት] የሚገልጥ ብርሃን” ይሆናል ብሎ በመናገር ማንቱን እንዲያሳውቅ አድርጓል። (ሉቃስ 2:29–32) የሰው ልጆች ፍጹሙ የኢየሱስ ሰብዓዊ ሕይወት መሥዋዕት መሆኑን በማመን በወረሱት ኃጢአት ምክንያት ከመጣባቸው ኩነኔ ነፃ ሊወጡ ይችላሉ። (ዮሐንስ 3:36) ከዚህ በኋላ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ የሰማያዊ መንግሥት ክፍል ሆነው ወይም በገነቲቱ ምድር የሚኖሩ የመንግሥቲቱ ተገዢዎች በመሆን ፍጹም የሆነ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። ምንኛ አስደናቂ ዝግጅት ነው!
7. በኢሳይያስ 42:1–4 ላይ ያለው ተስፋም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ትንቢቱ ያገኘው ፍጻሜ በተስፋ እንድንሞላ የሚያደርገን ለምንድን ነው?
7 እነዚህ አስደናቂ ተስፋዎች የሚፈጸሙ ለመሆናቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ዋስትና ሆኗል። ሐዋርያው ማቴዎስ ኢየሱስ በሥቃይ ላይ የነበሩትን ሰዎች ከመፈወሱ ጋር በማያያዝ በኢሳይያስ 42:1–4 ላይ የተጻፈው ትንቢት በእርሱ ላይ እንደሚሠራ ገልጿል። ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይላል:- “እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፣ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል።” ታዲያ ለምድር ወገኖች የሚያስፈልገው ነገር ይህ አይደለምን? ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፣ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። የተቀጠቀጠን ሸንበቆ አይሰብርም፣ የሚጤስንም ክር አያጠፋም።” ኢየሱስ ከዚህ ትንቢት ጋር የሚስማማ ነገር አድርጓል፤ በሥቃይ የሚገኙትን ሰዎች አላስጨነቀም። አዘነላቸው፣ ስለ ይሖዋ ዓላማዎች አስተማራቸው፣ ከሕመማቸውም ፈወሳቸው። — ማቴዎስ 12:15–21
8. ይሖዋ ኢየሱስን “ለሕዝብ ቃል ኪዳን” እንዲሁም “ለአሕዛብ ብርሃን” አድርጎ የሰጠው በምን መንገድ ነው?
8 የዚህ ትንቢት ሰጭ ለአገልጋዩ ለኢየሱስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፣ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፣ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ።” (ኢሳይያስ 42:6, 7) አዎን፣ ይሖዋ ኢየሱስ ክርስቶስን “ቃል ኪዳን” ወይም የተስፋ ዋስትና አድርጎ ሰጥቷል። ይህ እንዴት የሚያበረታታ ነው! ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የሰው ልጆች ሁኔታ ከልብ እንደሚያሳስበው አሳይቷል። እንዲያውም ሕይወቱን ለሰው ልጆች ሲል አሳልፎ ሰጥቷል። ይሖዋ አሕዛብን በሙሉ የመግዛት ሥልጣን የሰጠው ለእርሱ ነው። ይሖዋ እርሱን “የአሕዛብ ብርሃን” ብሎ መጥራቱ አያስደንቅም። ኢየሱስ ራሱም በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሏል። — ዮሐንስ 8:12
9. ኢየሱስ በዚያን ጊዜ የነበረውን የነገሮች ሥርዓት ለማሻሻል በመድከም ጊዜውን ያላጠፋው ለምን ነበር?
9 ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” ሆኖ ያገለገለው ለምን ዓላማ ነበር? ሥጋዊ ወይም ቁሳዊ የሆነ ዓላማ ለማሳካት እንዳልነበረ የተረጋገጠ ነው። የዚህ ዓለም ገዢ ከሆነው ከሰይጣንም ሆነ ከሕዝቦቹ የቀረበለትን የንግሥና ሥልጣንም ሆነ በጊዜው የነበረውን የፖለቲካ ሥርዓት ለማቃናት የቀረበለትን ግብዣ አልተቀበለም። (ሉቃስ 4:5–8፤ ዮሐንስ 6:15፤ 14:30) ኢየሱስ በሥቃይና በመከራ ላይ ለነበሩ ሰዎች ታላቅ ርኅራኄ አሳይቷል። እንዲሁም ሌሎች ሊያደርጉት ባልቻሉት መንገድ ከሥቃይ እንዲገላገሉ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ በውርሻ በመጣ ኃጢአት ምክንያት በመለኮታዊ ኩነኔ ውስጥ በሚገኝና በማይታዩት የክፋት መናፍስታዊ ኃይላት ቁጥጥር ሥር በሚገኝ ማኅበረሰብ ውስጥ ዘላቂ የሆነ እፎይታና ፈውስ ሊገኝ እንደማይችል ያውቅ ነበር። አምላካዊ ማስተዋል ስለነበረው መላ ሕይወቱን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ተጠቅሞበታል። — ዕብራውያን 10:7
10. ኢየሱስ የዓለም ብርሃን ሆኖ ያገለገለው በምን መንገዶችና ለምን ዓላማ ነበር?
10 ታዲያ ኢየሱስ “የዓለም ብርሃን” ሆኖ ያገለገለው በምን መንገዶችና ለምን ዓላማ ነበር? ጊዜውን የአምላክን መንግሥት የምሥራች በመስበኩ ሥራ ላይ አውሏል። (ሉቃስ 4:43፤ ዮሐንስ 18:37) በተጨማሪም ኢየሱስ የይሖዋን ዓላማ በተመለከተ ስለ እውነት በመመስከሩ የሰማዩ አባቱን ስም ክብር አጎናጽፎታል። (ዮሐንስ 17:4, 6) ከዚህ በተጨማሪም የዓለም ብርሃን እንደመሆኑ መጠን ሃይማኖታዊ ውሸቶችን አጋልጧል። ይህንን በማድረጉም በሃይማኖታዊ እስራት ውስጥ ለነበሩት ሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት አስገኝቶላቸዋል። ሰይጣን እርሱ እንዲጠቀምባቸው ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች በማይታይ ሁኔታ እየተቆጣጠረ እንዳለ ኢየሱስ አጋልጧል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ የጨለማ ሥራዎችን በግልጽ ለይቶ አመልክቷል። (ማቴዎስ 15:3–9፤ ዮሐንስ 3:19–21፤ 8:44) ከሁሉ በላይ ደግሞ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የዓለም ብርሃን ሆኖ ተገኝቷል። ይህን በማድረጉም በዚህ ዝግጅት ለሚያምኑ ሰዎች ሁሉ የኃጢአት ሥርየት የማግኘት፣ ከአምላክ ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና የመመሥረትና የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ክፍል ሆኖ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) በመጨረሻም ኢየሱስ በሕይወቱ በሙሉ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ለአምላክ በማደሩ ለይሖዋ ሉዓላዊነት ደጋፊ ሆኖ ቆሟል፤ ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑንም አረጋግጧል። ይህም ጽድቅ ወዳድ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ የዘላለም ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። ይሁን እንጂ ብርሃን አብሪ የሆነው ኢየሱስ ብቻ ነበርን?
-
-
ብርሃን አብሪዎች የሆንነው ለምን ዓላማ ነው?መጠበቂያ ግንብ—1993 | ጥር 15
-
-
12. (ሀ) መንፈሳዊው ብርሃን እስከ ምን ድረስ መብራት ይኖርበታል? (ለ) የይሖዋ መንፈስ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኢሳይያስ 42:6 ምን እንዲገነዘብ አስቻለው? ይህ ትንቢት የእኛንስ ሕይወት እንዴት ሊነካው ይገባል?
12 ይሁን እንጂ የምሥራቹ ስብከት በዚህ የምድር ክፍል ብቻ ተወስኖ የሚቀር አልነበረም። ኢየሱስ ተከታዮቹን “አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል አዟል። (ማቴዎስ 28:19) የጠርሴሱ ሳውል (በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው) ወደ ክርስትና በተለወጠበት ጊዜ ጌታ ለአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ለአሕዛብም እንደሚሰብክ በግልጽ ነግሮታል። (ሥራ 9:15) ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ይህ ትዕዛዝ ምን ማድረግን እንደሚጠይቅ ተገንዝቧል። በዚህም ምክንያት በኢየሱስ ላይ በቀጥታ የተፈጸመው የኢሳይያስ 42:6 ትንቢት በክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ በተዘዋዋሪ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን ተገንዝቧል። ስለዚህ በሥራ 13:47 ላይ ከኢሳይያስ ትንቢት ጠቅሶ “ጌታ [ይሖዋ አዓት] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና” ብሏል። አንተስ? ይህንን ብርሃን አብሪ የመሆን ግዴታ በቁም ነገር አስበህበታልን? እንደ ኢየሱስና እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወትህ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ እንዲያተኩር አድርገሃልን?
-