-
“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”ወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
17, 18. (ሀ) ኢሳይያስ ያየው ራእይ መጀመሪያ ላይ ምን ስሜት አሳደረበት? (ለ) ይሖዋ በአንድ መልአክ አማካኝነት ኢሳይያስን ያጽናናው እንዴት ነው? መልአኩ ያደረገው ነገርስ ምን ትርጉም አለው?
17 ይሁን እንጂ አምላክ ቅዱስ መሆኑ ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንድንመለከት ሊያደርገን ይገባል? አዎን፣ በሚገባ። ከይሖዋ አንጻር ስንታይ እዚህ ግቡ የምንባል አይደለንም፤ ይህ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። ታዲያ ይህን መገንዘባችን ከእሱ እንድንርቅ ያደርገናል? ሱራፌል የይሖዋን ቅድስና ባወጁበት ጊዜ ኢሳይያስ ምን ተሰምቶት እንደነበር ተመልከት። “በዚህ ጊዜ እንዲህ አልኩ፦ ‘ወዮልኝ! ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ስለሆንኩና የምኖረውም ከንፈራቸው በረከሰ ሕዝብ መካከል ስለሆነ በቃ መሞቴ ነው፤ ዓይኖቼ ንጉሡን፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ራሱን አይተዋልና!’” (ኢሳይያስ 6:5) አዎን፣ ወደር የሌለው የይሖዋ ቅድስና ኢሳይያስ ምን ያህል ኃጢአተኛና ከፍጽምና የራቀ መሆኑን እንዲያስብ አድርጎታል። ይህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ መጀመሪያ ላይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮበት ነበር። ይሁንና ይሖዋ ዝም ብሎ አልተመለከተውም።
18 ከሱራፌል አንዱ ወዲያውኑ እየበረረ መጥቶ ነቢዩን አጽናናው። እንዴት? መልአኩ ከመሠዊያው ላይ ፍም ወስዶ የኢሳይያስን ከንፈር በፍሙ ነካው። ‘ታዲያ ይህ ያቃጥለዋል እንጂ እንዴት ያጽናናዋል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ራእይ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብሃል። ታማኝ አይሁዳዊ የነበረው ኢሳይያስ የኃጢአት ስርየት ለማግኘት በቤተ መቅደሱ መሠዊያ ላይ በየዕለቱ መሥዋዕቶች እንደሚቀርቡ ያውቃል። መልአኩ ቀጥሎ ለነቢዩ አንድ የሚያጽናና ሐሳብ ነገረው። ፍጽምና የጎደለውና ‘ከንፈሮቹ የረከሱ’a ቢሆንም እንኳ በአንጻራዊ ሁኔታም ቢሆን ይሖዋ እሱን ንጹሕ ወይም ቅዱስ አድርጎ ለመመልከት ፈቃደኛ እንደሆነ ገለጸለት።—ኢሳይያስ 6:6, 7
-
-
“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”ወደ ይሖዋ ቅረብ
-
-
a ከንፈር ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ ንግግርን ወይም ቋንቋን ለማመልከት ስለሚሠራበት “ከንፈሮቼ የረከሱ” የሚለው አገላለጽ ተስማሚ ነው። ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ኃጢአት የሚሠሩት በአንደበት አጠቃቀማቸው ነው።—ምሳሌ 10:19፤ ያዕቆብ 3:2, 6
-