በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ያለው ቦታ ምንድን ነው?
ኢየሱስ ምን ይመስል እንደነበረ ማወቅ የሚያጓጓ ነገር ቢሆንም የበለጠ አስፈላጊነት ያለው ግን በአሁኑ ጊዜ ምን ቦታ እንዳለውና የት እንዳለ ማወቅ ነው። አምላክ ለሰው ልጅ ቤተሰብ ባለው ዓላማ ረገድ ምን የሥራ ድርሻ አለው?
ዓለማዊ ታሪክ እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ ሊሰጥ አይችልም። እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ ልናገኝ የምንችለው አምላክ ለእውነት ፈላጊዎች ሲል ባስጻፈው ሰነድ ውስጥ ብቻ ነው። ይህ ሰነድ በዓለም ታሪክ ውስጥ ከተሰራጩት መጻሕፍት ሁሉ የበለጠ ስርጭት ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ልጆች የተጻፈ ተራ መጽሐፍ አይደለም። አምላክ ሰዎችን እንደ ጸሐፊ አድርጎ ይጠቀም እንጂ ደራሲው እርሱ ራሱ ነው። “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፣ በእውነት እንዳለ . . . እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ [አልተቀበላችሁትም]” ሲል ስለጻፈ የቅዱሳን ጽሑፎችን ምንነት ተገንዝቦ ነበር።—1 ተሰሎንቄ 2:13
ለኃይሉና ለሥልጣኑ ዳርቻ የሌለው፣ እያንዳንዳቸው በቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት ያሏቸውን በቢልዮን የሚቆጠሩ የከዋክብት ረጨቶች የፈጠረው አምላክ ነው። ይህን ሁሉ ለመፍጠር የቻለው ምን ያህል ታላቅ ኃይል ቢኖረው ነው! በእርግጥ አስደናቂውን ጽንፈ ዓለም የፈጠረው ሁሉን ቻይ አምላክ እውነትን ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው አስተማማኝ መመሪያ ሊሰጥ የሚችል መጽሐፍ ማስጻፍ አያቅተውም።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የአምላክ ቃል ስለ ኢየሱስ የተነገሩት በርካታ ንድፈ ሐሳቦችና ግምታዊ አስተያየቶች ሐሰት መሆናቸውን ያጋልጣል። ስለ ኢየሱስ ከሚሰጣቸው ዝርዝር መግለጫዎች መካከል አንዳንዶቹን ልብ በል:-
• ኢየሱስ ሕልቆ መሳፍርት ከሌላቸው ዘመናት በፊት መላእክትና ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ከመፈጠራቸው አስቀድሞ አምላክ በቀጥታ የፈጠረው ብቸኛ ፍጡር ነው። የአምላክ “አንድያ ልጅ” የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው። ሌሎቹ ፍጥረታት በሙሉ የተፈጠሩት በዚህ የአምላክ “ዋና ሠራተኛ” በሆነው ልጅ በኩል ነው። ይህ የሆነው ሰው ከመሆኑ በፊት ነው።—ዮሐንስ 3:16፤ 6:38፤ 8:58፤ ምሳሌ 8:30፤ ቆላስይስ 1:16
• ሁለት ሺህ ከሚያክል ዓመት በፊት አምላክ የኢየሱስ ሕይወት ወደ አንዲት አይሁዳዊት ድንግል ማሕጸን እንዲዛወርና ሰው ሆኖ እንዲወለድ አደረገ። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች እንኳን በሰው ሠራሽ ዘዴ ጽንስ እንዲፈጠር ስለሚያደርጉ በአንዳንድ መንገዶች ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ድርጊት ሊፈጽሙ ችለዋል።—ማቴዎስ 1:18፤ ዮሐንስ 1:14
• ኢየሱስ ተራ የሆነ ጥሩ ሰው ብቻ አልነበረም። ሙሉ ሰው ከሆነ በኋላ የሰማይ አባቱን የይሖዋ አምላክን የፍቅር፣ የርህራሄና የጽድቅ ባሕርያት ፍጹም በሆነ ሁኔታ አንጸባርቋል።—ዮሐንስ 14:9, 10፤ ዕብራውያን 1:3፤ 1 ዮሐንስ 4:7-11, 20, 21
• በምድር ላይ የአምላክ ወኪል ሆኖ በኖረባቸው ዓመታት ለችግረኞችና ለጭቁኖች የሚያስፈልገውን እንክብካቤ ቢያደርግም በባለጠጋዎች ላይ አድልዎ አልፈጸመም። በጣም ኃያል በሆነው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ በሽተኞችን በተአምራዊ ሁኔታ ፈውሷል፣ ሙታንን እንኳን አስነስቷል። እንደነዚህ ያሉትን አስደናቂ ተአምራት በመፈጸም ከሙታን ተነስቶ ሰማያዊ ሕይወቱን ካገኘና የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ከሆነ በኋላ በመላው ምድር ላይ ምን እንደሚያደርግ አነስተኛ በሆነ መንገድ አሳይቷል።—ማቴዎስ 11:4-6፤ ሉቃስ 7:11-17፤ ዮሐንስ 11:5-45
• ኢየሱስ ተከታዮቹ በሙሉ እንዲጸልዩለትና በሕይወታቸው ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲሰጡ ያስተማረው ለዚህ ሰማያዊ የአምላክ መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት ሙሉ በሙሉ በሚቋቋምበት ጊዜ “እነዚያንም [የዛሬዎቹን] መንግሥታት ሁሉ ይፈጫቸዋል፣ ያጠፋቸውማል፣ ለዘላለምም ይቆማል።” ከዚያ በኋላ የመላው ምድር ብቸኛ አስተዳዳሪ ይሆናል። በጭንቀት ለተዋጠው የሰው ልጅ ከዚህ መንግሥት ሌላ ምንም ዓይነት ተስፋ የለም።—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10
• አምላክ የኢየሱስ አባት ሲሆን ኢየሱስም ለአምላክ ታማኝ ነበር። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ በተገደለበት ጊዜ ፍጹም የሆነ ሰው ነበር። አዳም በአምላክ ላይ ባመፀ ጊዜ ያጣውን መብት ለማስመለስ ሲል ፍጹም ሕይወቱን በፈቃዱ ለአምላክ ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ይህን በማድረጉም በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ ከፈተ።—ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 3:23, 24፤ 1 ዮሐንስ 2:2
• ኢየሱስ በአምላክ የተሾመ ሰማያዊ ንጉሥ በመሆኑ አምላክ ክፋትን ከምድር ገጽ ላይ ጠራርጎ ለማጥፋትና ታዛዥ የሆነውን የሰው ልጅ ወደ አእምሮአዊና አካላዊ ፍጽምና ለመመለስ ያለውን ዓላማ ያስፈጽማል። ከዚያ በኋላ የሰው ልጅ የተመቻቸ መኖሪያ ቤትና የተትረፈረፈ ምግብ አግኝቶ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ በሰላምና በደስታ ይኖራል። በሽታ፣ ሐዘንና ሞት ለዘላለም ጠፍተው ይቀራሉ። የሞቱ ሰዎች እንኳን ተነስተው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ።—ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:8፤ መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ምሳሌ 2:21, 22፤ ኢሳይያስ 25:6፤ 65:21-23፤ ሉቃስ 23:43፤ ሥራ 24:15፤ ራእይ 21:3, 4
ስለዚህ አምላክ በዚህች ምድር ላይ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማቋቋም ባለው ዓላማ ውስጥ ኢየሱስ ቁልፍ የሆነ የሥራ ድርሻ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ይህን የመሰለ በጣም አስፈላጊ ሚና ስላለው “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ሊል ችሏል።—ዮሐንስ 14:6፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
ርኅሩኅ የሆነ ገዥ
ትሑታን ሁሉ ኢየሱስ በአዲሱ ዓለም ገዥያቸው እንዲሆን ይፈልጋሉ። በእርግጥም ከዛሬዎቹ ገዥዎች በጣም የተለየና አስደሳች ገዥ ይሆናል። ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በጣም አስደናቂ የሆኑ ተአምራት በመፈጸም ይህን በተግባር አሳይቷል። (ማቴዎስ 15:30, 31) ከዚህ በተጨማሪ ግን ወደፊት ምን ዓይነት ገዥ እንደሚሆን ልብ በል።
በመጀመሪያ የዚህ ዓለም ገዥዎች ምን ዓይነት እንደነበሩ ተመልከት። ባለፉት ዘመናት በሙሉ አብዛኛውን ጊዜ ጨካኞችና ግፈኞች እንደነበሩ፣ ሕዝቦቻቸውን ቁጥር ሥፍር ወደሌላቸው ጦርነቶች፣ እልቂቶችና ግድያዎች መርተው እንዳስገቡ ታሪክ ያረጋገጠው ሐቅ ነው። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ብቻ ከ100 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በጦርነት አልቀዋል።
የዚህ ዓለም ገዥዎች ያላቸውን አመለካከትና ታሪክ ኢየሱስ ለድሆች፣ ለምስኪኖችና ለአቅመ ደካሞች ከነበረው አመለካከትና ታሪክ ጋር አስተያይ። “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” ከዚያም “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” አላቸው።—ማቴዎስ 9:36፤ 11:28-30
ኢየሱስ ለሰዎች አዛኝና ርኅሩኅ ነበር! በዚህ ረገድ ሰማያዊ አባቱን መስሏል። ኢየሱስ የፍቅር አብነት ከመሆኑም በላይ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርሳቸው እውነተኛ የሆነና በሥርዓት የሚገዛ ፍቅር እንዲኖራቸው አስተምሯል። ስለዚህ ዘር፣ ብሔር፣ የኢኮኖሚ ደረጃ፣ የቀድሞ ሃይማኖት ወይም ማንኛውም ሌላ ነገር ጣልቃ ገብቶ ዓለም አቀፋዊ አንድነታቸውን እንዲያደፈርስባቸው አይፈቅዱም። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ ሥራ 10:34, 35) በእርግጥም ኢየሱስ የገዛ ራሱን ሕይወት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ የሰው ልጆችን ወዷል። (ኤፌሶን 5:25) ለዚህ ዓለም የሚያስፈልገውና የተዘጋጀው እንዲህ ያለ ገዥ ነው።
ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ‘የተዋበ’ ንጉሥ ነው
የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ኃያል የሆነ ሰማያዊ ንጉሥ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። መዝሙራዊው ስለ ኢየሱስ ሲተነብይ እንዲህ ብሏል:- “ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል፣ . . . ስለ ቅንነትና ስለ የዋህነት ስለ ጽድቅም አቅና፣ ተከናወን፣ ንገሥም። . . . ጽድቅን ወደድህ፣ ዓመፃንም ጠላህ፣ ስለዚህ . . . እግዚአብሔር አምላክህ የደስታ ዘይትን ቀባህ።”—መዝሙር 45:2, 4, 7
ኢየሱስ በአምላክ የተቀባ ሰማያዊ ንጉሥ እንደመሆኑ ለጽድቅ ያለውን ፍቅርና ለክፋት ያለውን ጥላቻ የሚያሳይ እርምጃ እንዲወስድ ሥልጣን ተሰጥቶታል። በዚህም ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይሞት ድል አድራጊና “የነገሥታት ንጉሥ” እንደሆነ ተገልጿል። በቅርቡ የአምላክን ጠላቶች በሙሉ ያጠፋል። ከዚህም በላይ ምድርን ወደ ገነትነት ይመልሳል፣ ከቤዛው ተጠቃሚ የሆኑ የሰው ልጆችንም ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ያደርሳል።—ራእይ 19:11-16
አዲሱ የኢየሱስ የሥራ ድርሻ የሚዘበትበት፣ የሚደበደብና በተቃዋሚዎች የሚገደል ‘መከረኛ መሲሕ’ ከመሆን ፈጽሞ የተለየ ነው። ከዚህ ይልቅ አዲሱ ሥራው “ኃያል አምላክ፣” የምድር ገዥ በመሆን የሚፈጽመው ነው። (ኢሳይያስ 9:6) ይህ ለአብዛኛዎች ሰብዓዊ ገዥዎች ተወዳጅነት ያለው ዜና አይደለም። ምክንያቱም ዳንኤል 2:44 እንደሚተነብየው መንግሥቶቻቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተንኮታኩተው ይጠፋሉ። አምላክ ክርስቶስን ፍርድ ፈጻሚ አድርጎ በመጠቀም “ነገሥታትን በቁጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል። በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል።”—መዝሙር 110:5, 6
ክርስቶስ ይህን ሲያደርግ “ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፤ . . . ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ” በማለት ኢሳይያስ ተንብዮአል። ለምን? “ያልተነገረላቸውንም [ሃይማኖታዊ ምሥጢረኞቻቸው ያልነገሯቸውን] ያያሉና፣ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና።”—ኢሳይያስ 52:15
“አውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ”
ኢሳይያስ ሃይማኖታዊ መሪዎች የተሰጣቸውን የሥራ ግዴታ ገሸሽ አድርገው እንደሚጥሉ መተንበዩ ነበር። ለምሳሌ፣ ለመንጎቻቸው ስለ ዘላለማዊ የሲኦል እሳት ሥቃይ፣ አንድነት በሦስትነት ስላለው ሥላሴ፣ ነፍስ የማትሞት ስለመሆኗ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት ያስተምራሉ እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አያስተምሩም። ከዚህም በላይ ቀሳውስት የየብሔሮቻቸውን ጦርነቶች፣ የራሳቸው ሃይማኖት ተከታዮች በሆኑ ሰዎች ላይ እልቂት የሚያስከትል በሚሆንበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር ደግፈዋል። ይህ የአምላክን ትእዛዝ በቀጥታ የሚቃወም ነው።—1 ዮሐንስ 2:3, 4፤ 3:10-12፤ 4:8, 20, 21
ከዚህም በላይ ቀሳውስት ለመንጎቻቸው የሚያቀርቡት በአምላክ ዘንድ ምንም ዓይነት ዋጋ የሌላቸውን ግን ለሰው ዓይን ብቻ ደስ የሚያሰኙትን ሃይማኖታዊ ምስሎች፣ ልብሰ ተክህኖዎች፣ ብዙ ሀብት የፈሰሰባቸው ካቴድራሎችና የፀሐይ አምላክን አክሊለ ብርሃን ጨምሮ በተለያዩ የአረማውያን ጽንሰ ሐሳቦች ያሸበረቁ ሥዕሎችንና የመሳሰሉትን ብቻ ነው። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት “እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፣ እልፍ በሉ፣ እልፍ በሉ፣ ከዚያ ውጡ ርኩስን ነገር አትንኩ” የሚለውን አምላክ ለአገልጋዮቹ የሰጠውን ትእዛዝ እያወቁ ነው።—ኢሳይያስ 52:11፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14-18
የአምላክ ወኪሎች ነን እያሉ የአምላክን ትእዛዝ የሚጥሱና ሌሎችም እንዲጥሱ የሚያስተምሩ ሁሉ የዘሩትን ያጭዳሉ። ይህ የነገሮች ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ ዋጋቸውን ይቀበላሉ። ነቢዩ ሆሴዕ እንዳለው “ነፋስን ዘርተዋል፣ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ።”—ሆሴዕ 8:7፤ በተጨማሪም ራእይ 17:1-3, 15, 16ን ተመልከት።
ልበ ቅን ሰዎች እውነቱን ይማራሉ
ቀሳውስት አምላክንና ኢየሱስን በትክክል አለመወከላቸው ልበ ቅን ሰዎችን ስለ ኢየሱስ እውነቱን ከመማር ሊያግዳቸው አይችልም። በመጀመሪያው መቶ ዘመንም ቢሆን አልቻለም። ፖል ባርነት ዘ ቱ ፌስስ ኦቭ ጂሰስ በተባለው መጽሐፋቸው እንደጻፉት “ኢየሱስ ማስታወቂያ ሳይነገርለት ድንገት ከሰማይ ዱብ ያለ ሰው አልነበረም።” አዎን፣ በዚያ የጥንት ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የመሲሑን ማንነት በሚገባ ‘አስታውቀው’ ስለነበረ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መምጣቱ በቂ ማረጋገጫ አግኝተው ነበር። ዛሬ ደግሞ ኢየሱስ በሰማይ “የነገሥታት ንጉሥ” ሆኖ እንዲገዛ በአምላክ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን የሚያስታውቁ በጣም ብዙ ማስረጃዎች አሉ።—ማቴዎስ 24:3-13፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13
በእርግጥም “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት [ክርስቶስ ገዥ ሆኖ የተሾመበት የአምላክ መንግሥት] ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) ይህ የስብከት ሥራ በአሁኑ ጊዜ ከአምስት ሚልዮን በላይ በሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም በመከናወን ላይ ይገኛል። ስለዚህ ትክክለኛውን ኢየሱስ ለማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ ሊያውቁት ይችላሉ። (ዮሐንስ 10:14፤ 1 ዮሐንስ 5:20) በቅርቡ መላይቱን ምድር ከሚያጥለቀልቀው “ታላቅ መከራ” ለመዳን ደግሞ እርሱን ማወቅና መታዘዝ የግድ አስፈላጊ ነው።—ራእይ 7:9-14፤ ዮሐንስ 17:3፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-10
ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ልጅ የሚሰጠውን አስደሳች መግለጫ እንድትመረምር በደስታ ይረዱሃል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶስ በንጉሣዊ ክብሩ ሲመጣ ክፋትን በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህች ምድር በክርስቶስ ፍቅራዊ አገዛዝ ሥር ገነት ትሆናለች