ምዕራፍ 2
ክርስቶስ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያለውን ሚና መቀበል
“በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ”፤ የፈጠረውም ነገር ሁሉ “እጅግ መልካም” ነበር። (ዘፍ. 1:1, 31) ይሖዋ ሰውን ሲፈጥር ከፊቱ አስደሳች ተስፋ ዘርግቶለት ነበር። ይሁን እንጂ በኤደን የተከሰተው ዓመፅ ለሰው ልጆች የተዘረጋው አስደሳች ሕይወት ለጊዜውም ቢሆን እንዲስተጓጎል አድርጓል። ሆኖም ይሖዋ ለምድርም ሆነ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ አልተለወጠም። አምላክ ታዛዥ የሆኑ የአዳም ዘሮች መዳን የሚያገኙበት ዝግጅት እንደሚኖር ጠቁሟል። እውነተኛው አምልኮ ዳግመኛ የሚቋቋምበት ጊዜ እንደሚመጣና አምላክ ዲያብሎስን ከክፋት ድርጊቶቹ ጋር ጠራርጎ እንደሚያጠፋው አመልክቷል። (ዘፍ. 3:15) በዚያን ጊዜ ሁሉም ነገር እንደቀድሞው “እጅግ መልካም” ይሆናል። ይሖዋ ይህን የሚያከናውነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው። (1 ዮሐ. 3:8) በመሆኑም ክርስቶስ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና መቀበላችን ወሳኝ ነው።—ሥራ 4:12፤ ፊልጵ. 2:9, 11
የክርስቶስ ሚና ምንድን ነው?
2 ክርስቶስ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የሚጫወተው ሚና ብዙ ገጽታዎች እንዳሉት መገንዘብ ይኖርብናል። ኢየሱስ ሊቀ ካህናትና የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም ሌላ የሰው ልጆችን የሚቤዠው እሱ ነው፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኗል። ክርስቶስ በሚጫወተው የተለያየ ሚና ላይ ስናሰላስል ለአምላክ ዝግጅት ያለን አድናቆት ያድጋል፤ እንዲሁም ለክርስቶስ ኢየሱስ ያለን ፍቅር ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የሚጫወተውን የተለያየ ሚና ይገልጻል።
ይሖዋ ለሰው ዘር ባለው ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ኢየሱስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል
3 ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት፣ ታዛዥ የሰው ልጆችን ከአምላክ ጋር የሚያስታርቀው እሱ እንደሆነ በግልጽ ታውቆ ነበር። (ዮሐ. 14:6) ኢየሱስ የሰው ልጆችን የሚቤዥ እንደመሆኑ መጠን ራሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ማቴ. 20:28) ስለዚህ ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አኗኗር መምራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ከማሳየት ያለፈ ነገር አድርጓል። ይሖዋ ለሰው ዘር ባለው ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ኢየሱስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። የአምላክን ሞገስ መልሰን ማግኘት የምንችለው በእሱ በኩል ብቻ ነው። (ሥራ 5:31፤ 2 ቆሮ. 5:18, 19) የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞትና ትንሣኤው ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሰማይ ባለው የአምላክ መንግሥት አገዛዝ አማካኝነት ዘላለማዊ በረከቶች ማግኘት የሚችሉበትን በር ከፍቷል።
4 ኢየሱስ ሊቀ ካህናት ስለሆነ ‘በድካማችን ሊራራልን’ ይችላል፤ እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ተከታዮቹ የሚሠሩትን ኃጢአት ያስተሰርይላቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ያለን ሊቀ ካህናት በድካማችን ሊራራልን የማይችል አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁንና እሱ ኃጢአት የለበትም” ሲል ገልጿል። ጳውሎስ በመቀጠል በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ የሚያስችላቸውን ይህን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙበት ለማበረታታት እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲህ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ ያለ ምንም ፍርሃት ወደ ጸጋው ዙፋን እንቅረብ።”—ዕብ. 4:14-16፤ 1 ዮሐ. 2:2
5 በተጨማሪም ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት እውነተኛ ተከታዮቹ ሁሉ እኛም ሰብዓዊ መሪ አያስፈልገንም። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና ብቃት ባላቸው የበታች እረኞች አማካኝነት አመራር ይሰጣል፤ እነዚህ እረኞች የአምላክን መንጋ ስለሚይዙበት መንገድ በእሱም ሆነ በሰማይ ባለው አባቱ ዘንድ ተጠያቂ ናቸው። (ዕብ. 13:17፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) ይሖዋ ኢየሱስን በተመለከተ “እነሆ፣ ለብሔራት ምሥክር፣ መሪና አዛዥ አድርጌዋለሁ” የሚል ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳ. 55:4) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ” ብሎ በነገራቸው ጊዜ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን አረጋግጧል።—ማቴ. 23:10
6 ኢየሱስ የሚከተለውን ግብዣ ማቅረቡ አመለካከቱንና እኛን ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን ያሳያል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።” (ማቴ. 11:28-30) ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስቲያን ጉባኤን በገርነትና እረፍት በሚያስገኝ መንገድ መምራቱ በሰማይ የሚኖረውን የአባቱን፣ የይሖዋ አምላክን አርዓያ በመከተል “ጥሩ እረኛ” እንደሆነ ያሳያል።—ዮሐ. 10:11፤ ኢሳ. 40:11
7 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጫወተውን ሚና ተጨማሪ ገጽታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ጠላቶችን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ንጉሥ ሆኖ ሊገዛ ይገባዋልና። ይሁንና ሁሉም ነገር ከተገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር ላስገዛለት ራሱን ያስገዛል፤ ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር እንዲሆን ነው።” (1 ቆሮ. 15:25, 28) ኢየሱስ የአምላክ የመጀመሪያ ፍጥረት እንደመሆኑ መጠን ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በአምላክ ዘንድ “የተዋጣለት ሠራተኛ” ነበር። (ምሳሌ 8:22-31) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣም በኋላ ምንጊዜም የአምላክን ፈቃድ ያደርግ ነበር። የደረሰበትን ከሁሉ የከፋ ፈተና በጽናት በመቋቋም እስከ ሞት ድረስ ለአባቱ ታማኝ ሆኗል። (ዮሐ. 4:34፤ 15:10) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነቱን በመጠበቁ አምላክ ከሞት አስነስቶ በሰማይ የመንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። (ሥራ 2:32-36) በመሆኑም ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ኃያላን መንፈሳዊ ፍጥረታት በመምራት የሰውን አገዛዝ ከምድር ላይ እንዲያስወግድና ክፋትን በሙሉ ከዓለም ላይ ጠራርጎ እንዲያጠፋ አምላክ ትልቅ ኃላፊነት ሰጥቶታል። (ምሳሌ 2:21, 22፤ 2 ተሰ. 1:6-9፤ ራእይ 19:11-21፤ 20:1-3) ከዚያ በኋላ በመላው ምድር ላይ የሚገዛው በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ብቻ ይሆናል።—ራእይ 11:15
የክርስቶስን ሚና መቀበል ሲባል ምን ማለት ነው?
8 ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ነው። እኛን የመንከባከብ ተልእኮም ተሰጥቶታል። ኢየሱስ ፍቅራዊ እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርግልን ከፈለግን ለይሖዋ ታማኝ መሆንና ወደፊት እየገሰገሰ ካለው ድርጅቱ ጋር እኩል መጓዝ ይኖርብናል።
9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች ክርስቶስ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ሙሉ በሙሉ ተቀብለዋል። በክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆነው በአንድነት በመሥራት እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለሚሰጠው አመራር በመገዛት ይህንን በተግባር አሳይተዋል። (ሥራ 15:12-21) ሐዋርያው ጳውሎስ በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ መካከል ስላለው አንድነት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “እውነትን በመናገር በሁሉም ነገር ወደ እሱ ይኸውም የአካሉ ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ በፍቅር እንደግ። በእሱ አማካኝነት የአካል ክፍሎች ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሚያሟላው በእያንዳንዱ መገጣጠሚያ አማካኝነት እርስ በርስ ተስማምተው ተገጣጥመዋል። እያንዳንዱ የአካል ክፍል በአግባቡ ሥራውን ማከናወኑ አካሉ ራሱን በፍቅር እያነጸ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል።”—ኤፌ. 4:15, 16
10 በጉባኤው ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ግለሰብ ከሌሎቹ ጋር ሲተባበርና ሁሉም በክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆነው ተስማምተው ሲሠሩ እድገት የሚገኝ ከመሆኑም በላይ “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” የሆነው ፍቅር ይሰፍናል።—ዮሐ. 10:16፤ ቆላ. 3:14፤ 1 ቆሮ. 12:14-26
11 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ የሆኑት በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉት ሁኔታዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ከ1914 አንስቶ የመንግሥቱን ሥልጣን እንደተረከበ በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣሉ። አዎ፣ በአሁኑ ጊዜ በጠላቶቹ መካከል እየገዛ ነው። (መዝ. 2:1-12፤ 110:1, 2) ይህ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ምን ትርጉም አለው? ኢየሱስ በጠላቶቹ ላይ የተበየነውን መለኮታዊ ፍርድ በቅርቡ ሲያስፈጽም የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ሆኖ የሚጫወተውን ሚና በሚገባ ያሳያል። (ራእይ 11:15፤ 12:10፤ 19:16) ከዚያም የክርስቶስን ሞገስ አግኝተው በቀኙ የሚቆሙ ሰዎች፣ ይሖዋ የሰው ልጅ ባመፀበት ጊዜ ሰዎችን ለማዳን የገባው ቃል ሲፈጸም ያያሉ። (ማቴ. 25:34) በእርግጥም ክርስቶስ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና በመቀበላችን ደስተኞች ነን! በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በዓለም ዙሪያ በክርስቶስ አመራር ሥር እየተከናወነ ያለውን አገልግሎት ለመፈጸም በአንድነት መሥራታችንን እንቀጥል።