የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • kr ምዕ. 9 ገጽ 87-97
  • የስብከቱ ሥራ ያስገኘው ውጤት—‘አዝመራው ነጥቷል’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የስብከቱ ሥራ ያስገኘው ውጤት—‘አዝመራው ነጥቷል’
  • የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለሥራ የቀረበ ጥሪ እና የሚገኘው ደስታ
  • ንጉሣችን በታላቁ የመከር ሥራ በቀዳሚነት እየተካፈለ ነው
  • የመከሩ ሥራ የሚያስገኘው ውጤት ግሩም በሆነ ምሳሌ አስቀድሞ ተነግሯል
  • ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች የሚደሰቱበት ምክንያት
  • “ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ”
  • በመከሩ ሥራ ወደፊት ግፉ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2010
  • ደስተኛ የመከሩ ሠራተኞች ሁኑ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • በታላቁ መንፈሳዊ የመከር ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ይኑራችሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
ለተጨማሪ መረጃ
የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
kr ምዕ. 9 ገጽ 87-97

ምዕራፍ 9

የስብከቱ ሥራ ያስገኘው ውጤት—‘አዝመራው ነጥቷል’

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ይሖዋ የመንግሥቱ እውነት ዘር እንዲያድግ አድርጓል

1, 2. (ሀ) ደቀ መዛሙርቱ ግራ የተጋቡት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የተናገረው ስለ የትኛው የመከር ሥራ ነው?

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ግራ ተጋብተዋል። ኢየሱስ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” አላቸው። ኢየሱስ እየጠቆማቸው ወዳለው አቅጣጫ ሲመለከቱ ግን ዓይናቸው ውስጥ የገባው የነጣ አዝመራ ሳይሆን አረንጓዴ የሆነ ለምለም የገብስ ቡቃያ ነበር። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ‘ስለ የትኛው አዝመራ ነው የሚያወራው? መከር ሊገባ ገና የተወሰኑ ወራት ይቀሩ የለም እንዴ?’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል።—ዮሐ. 4:35

2 ኢየሱስ ግን ቃል በቃል ስለሚከናወነው የመከር ሥራ እየተናገረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ወቅት፣ ከመንፈሳዊው የመከር ሥራ ማለትም ሰዎችን ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ትምህርቶችን ለደቀ መዛሙርቱ እያስተማራቸው ነበር። እነዚህ ትምህርቶች ምንድን ናቸው? መልሱን ለማግኘት እስቲ ይህን ዘገባ በስፋት እንመርምር።

ለሥራ የቀረበ ጥሪ እና የሚገኘው ደስታ

3. (ሀ) ኢየሱስ “አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ብሎ የተናገረው ለምን ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) ኢየሱስ፣ የተናገረውን ነገር ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይህን ውይይት ያደረገው በ30 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ቦታው ሰማርያ ውስጥ በምትገኝ ሲካር የተባለች ከተማ አቅራቢያ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ኢየሱስ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። በዚያም ለአንዲት ሴት መንፈሳዊውን እውነት ነገራት፤ ይህች ሴት፣ ኢየሱስ ያስተማራት እውነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባትም። ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ሲመለሱ ሴትየዋ የተማረቻቸውን አስደናቂ እውነቶች ለምታውቃቸው ሰዎች ለመናገር በፍጥነት ወደ ሲካር ሄደች። ሴትየዋ የተናገረችው ነገር የሰዎቹን የማወቅ ጉጉት ስለቀሰቀሰው ብዙዎቹ ኢየሱስን ለማግኘት በጥድፊያ ወደ ውኃው ጉድጓድ መጡ። ኢየሱስ አሻግሮ በርቀት ያለውን ሜዳ ሲቃኝ በርካታ ሳምራውያን በብዛት ሆነው ሲመጡ ተመለከተ፤ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ብሎ የተናገረው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።a ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለ መንፈሳዊ አዝመራ መሆኑን ለመጠቆም “አጫጁ . . . ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው” በማለት አክሎ ተናገረ።—ዮሐ. 4:5-30, 36

4. (ሀ) ኢየሱስ የመከሩን ሥራ በተመለከተ የትኞቹን ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶች አስተምሯል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

4 ኢየሱስ መንፈሳዊውን የመከር ሥራ በተመለከተ ያስተማራቸው ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? የመጀመሪያው፣ ሥራው አጣዳፊ ነው የሚለው ነው። “አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ሲል ተከታዮቹን ለሥራ እንዲንቀሳቀሱ ማበረታታቱ ነበር። ኢየሱስ፣ ሥራው ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ደቀ መዛሙርቱ በደንብ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ሲል “አሁንም እንኳ አጫጁ ደሞዙን እየተቀበለ . . . ነው” አላቸው። በእርግጥም አዝመራው መሰብሰብ ጀምሯል፤ በመሆኑም ዛሬ ነገ ሳይሉ ወዲያውኑ ሥራ መጀመር አለባቸው። ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ ሠራተኞቹ ደስተኞች ናቸው የሚለው ነው። ኢየሱስ፣ ዘሪዎቹም ሆኑ አጫጆቹ “በአንድነት ደስ ይላቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 4:35ለ, 36) ኢየሱስ “ብዙ ሳምራውያን በእሱ [በማመናቸው]” ተደስቶ መሆን አለበት፤ ደቀ መዛሙርቱም በመከሩ ሥራ በሙሉ ነፍሳቸው መካፈላቸው ከፍተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል። (ዮሐ. 4:39-42) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸመው ይህ ታሪክ፣ እስከ ዛሬ ከተካሄዱት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ መንፈሳዊ የመከር ሥራ በሚከናወንበት በዚህ ዘመን የሚኖረውን ሁኔታ የሚያሳይ በመሆኑ በዛሬው ጊዜ ላለን ክርስቲያኖች ልዩ ትርጉም አለው። ታዲያ ይህ ዘመናዊ የመከር ሥራ የጀመረው መቼ ነው? በሥራው የሚካፈሉት እነማን ናቸው? ምን ውጤትስ ተገኝቷል?

ንጉሣችን በታላቁ የመከር ሥራ በቀዳሚነት እየተካፈለ ነው

5. ዓለም አቀፍ የሆነውን ሰዎችን የመሰብሰብ ሥራ ቅድሚያውን ወስዶ የሚያከናውነው ማነው? የዮሐንስ ራእይ የሥራውን አጣዳፊነት የሚያጎላው እንዴት ነው?

5 ዓለም አቀፍ በሆነው ሰዎችን የመሰብሰብ ሥራ ኢየሱስ ቅድሚያውን ወስዶ እንዲካፈል በይሖዋ እንደተሾመ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ተመልክቷል። (ራእይ 14:14-16⁠ን አንብብ።) በዚህ ራእይ ላይ ኢየሱስ አክሊል ደፍቶና ማጭድ ይዞ ታይቷል። ኢየሱስ “በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል” መድፋቱ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን ያሳያል። ‘በእጁ ስለታም ማጭድ’ መያዙ ደግሞ አዝመራውን በመሰብሰብ ረገድ የሚጫወተውን ሚና ይጠቁማል። ይሖዋ “የምድር መከር ደርሷል” በማለት በአንድ መልአክ አማካኝነት መናገሩ የሥራውን አጣዳፊነት የሚያጎላ ነው። በእርግጥም “የአጨዳው ሰዓት ስለደረሰ” ሥራው ወዲያውኑ መጀመር አለበት! ኢየሱስ፣ “ማጭድህን ስደድ” በማለት አምላክ የሰጠውን መመሪያ በመታዘዝ ማጭዱን ሰድዶ ምድርን ይኸውም በምድር ላይ ያሉትን ሰዎች አጨደ። ይህ አስገራሚ ራእይም “አዝመራው እንደነጣ” ያስታውሰናል። ታዲያ ይህ ራእይ በዓለም ዙሪያ የሚከናወነው የመከር ሥራ መቼ እንደጀመረ ለማወቅ የሚያስችል ፍንጭ ይሰጠናል? አዎን!

6. (ሀ) ‘የመከሩ ወቅት’ የጀመረው መቼ ነው? (ለ) “የምድር መከር” መሰብሰብ የጀመረው መቼ ነው? አብራራ።

6 በራእይ ምዕራፍ 14 ላይ በሚገኘው ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ አጫጁ ማለትም ኢየሱስ አክሊል ደፍቶ (ቁጥር 14) ስለታየ ራእዩ የተፈጸመው ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ መሆን አለበት። (ዳን. 7:13, 14) ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ አጨዳ እንዲጀምር ትእዛዝ ተሰጠው (ቁጥር 15)። ኢየሱስ ስለ ስንዴው መሰብሰብ በተናገረው ምሳሌ ላይም ነገሮች የተከናወኑበት ቅደም ተከተል ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ በዚህ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ “መከሩ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” እንደሆነ ተናግሮ ነበር። በመሆኑም የመከሩ ወቅት እና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ የሚጀምሩት በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ይኸውም በ1914 ነው። አዝመራውን የመሰብሰቡ ሥራ የጀመረው ግን “በመከር ወቅት” ውስጥ ይኸውም የመከሩ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ ነው። (ማቴ. 13:30, 39) ዛሬ ላይ ሆነን ወደኋላ ስንመለከት፣ የመከሩ ሥራ ወይም አዝመራውን የመሰብሰቡ ሥራ የጀመረው ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን። ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮቹን የማንጻት ሥራ አከናውኗል። (ሚል. 3:1-3፤ 1 ጴጥ. 4:17) ከዚያም በ1919 “የምድር መከር” መሰብሰብ ጀመረ። ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ፣ በዚያ ወቅት በተሾመው ታማኝ ባሪያ በመጠቀም ወንድሞቻችን የስብከቱን ሥራ አጣዳፊነት እንዲገነዘቡ አድርጓል። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

7. (ሀ) ወንድሞቻችን የስብከቱ ሥራ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ የረዳቸው ምን ነገር መመርመራቸው ነው? (ለ) ወንድሞቻችን ምን እንዲያደርጉ ማበረታቻ ተሰጣቸው?

7 የሐምሌ 1920 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሏል፦ “ቅዱሳን መጻሕፍትን ስንመረምር፣ ቤተ ክርስቲያን ስለ መንግሥቱ የሚገልጽ መልእክት ለሰዎች የማድረስ ታላቅ መብት እንደተሰጣት መረዳት እንችላለን።” ለምሳሌ የኢሳይያስ ትንቢት፣ ወንድሞች የመንግሥቱን ዜና በዓለም ዙሪያ ማድረስ እንዳለባቸው እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል። (ኢሳ. 49:6፤ 52:7፤ 61:1-3) ይህ ሥራ የሚከናወነው እንዴት እንደሆነ ባያውቁም ይሖዋ መንገዱን እንደሚከፍትላቸው እርግጠኞች ነበሩ። (ኢሳይያስ 59:1⁠ን አንብብ።) የስብከቱ ሥራ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ በመገኘቱ ወንድሞቻችን አገልግሎታቸውን ይበልጥ እንዲያቀጣጥሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ታዲያ ምን ምላሽ ሰጡ?

8. በ1921 ወንድሞቻችን የስብከቱን ሥራ በተመለከተ የትኞቹን ሁለት ነጥቦች አስተዋሉ?

8 የታኅሣሥ 1921 መጠበቂያ ግንብ የሚከተለውን ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ይህ ዓመት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዓመት ነው፤ ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት ይበልጥ በ1921 በጣም ብዙ ሰዎች የእውነትን መልእክት ሰምተዋል።” መጽሔቱ አክሎም “መሠራት ያለበት ገና ብዙ ነገር አለ። . . . ይህንን ሥራ በደስታ እናከናውን” ብሏል። ኢየሱስ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ለሐዋርያቱ የነገራቸውን ሁለት አስፈላጊ ነጥቦች ይኸውም ሥራው አጣዳፊ መሆኑን እንዲሁም ሠራተኞቹ በደስታ እንደሚያከናውኑት ወንድሞች ማስተዋላቸውን ልብ በል።

9. (ሀ) በ1954 መጠበቂያ ግንብ ስለ መከሩ ሥራ ምን ብሎ ነበር? ለምንስ? (ለ) ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በዓለም ዙሪያ የአስፋፊዎች ቁጥር ምን ያህል ጨምሯል? (“በዓለም ዙሪያ ያለው ጭማሪ” የሚለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።)

9 በ1930ዎቹ ዓመታት ወንድሞቻችን፣ የሌሎች በጎች አባላት የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ የመንግሥቱን መልእክት እንደሚቀበሉ ከተገነዘቡ በኋላ የስብከቱ ሥራ ይበልጥ ተፋፋመ። (ኢሳ. 55:5፤ ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 7:9) ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? በ1934 የመንግሥቱን መልእክት የሚሰብኩት ክርስቲያኖች ቁጥር 41,000 የነበረ ሲሆን በ1953 ቁጥራቸው 500,000 ደረሰ! በእርግጥም የታኅሣሥ 1, 1954 መጠበቂያ ግንብ “ይህ ዓለም አቀፋዊ ታላቅ የመከር ሥራ ሊከናወን የቻለው በይሖዋ መንፈስ እና ቃሉ ባለው ኃይል የተነሳ ነው” ማለቱ ተገቢ ነበር።b—ዘካ. 4:6

በዓለም ዙሪያ ያለው ጭማሪ

አገር

1962

1987

2013

አውስትራሊያ

15,927

46,170

66,023

ብራዚል

26,390

216,216

756,455

ፈረንሳይ

18,452

96,954

124,029

ጣሊያን

6,929

149,870

247,251

ጃፓን

2,491

120,722

217,154

ሜክሲኮ

27,054

222,168

772,628

ናይጄሪያ

33,956

133,899

344,342

ፊሊፒንስ

36,829

101,735

181,236

ዩናይትድ ስቴትስ

289,135

780,676

1,203,642

ዛምቢያ

30,129

67,144

162,370

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች

1950

234,952

1960

646,108

1970

1,146,378

1980

1,371,584

1990

3,624,091

2000

4,766,631

2010

8,058,359

የመከሩ ሥራ የሚያስገኘው ውጤት ግሩም በሆነ ምሳሌ አስቀድሞ ተነግሯል

10, 11. ስለ ሰናፍጭ ዘር በሚገልጸው ምሳሌ ላይ ከዘሯ እድገት ጋር በተያያዘ የጎሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

10 ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ በተናገራቸው ምሳሌዎች ላይ የመከር ሥራው የሚያስገኘውን ውጤት ግሩም በሆነ መንገድ አስቀድሞ ገልጾታል። ስለ ሰናፍጩ ዘር እና ስለ እርሾው የሚናገሩትን ምሳሌዎች እስቲ እንመልከት። እነዚህ ምሳሌዎች በመጨረሻው ዘመን ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት እንደሆነ በትኩረት እንመረምራለን።

11 የሰናፍጭ ዘር ምሳሌ። አንድ ሰው የሰናፍጭ ዘር ዘራ። ከዚያም ዘሯ አድጋ ትልቅ ዛፍ ሆነች፤ በመሆኑም እዚህች ዛፍ ላይ ወፎች ይሰፍሩ ጀመር። (ማቴዎስ 13:31, 32⁠ን አንብብ።) ከዘሯ እድገት ጋር በተያያዘ በዚህ ምሳሌ ላይ የጎሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? (1) የሰናፍጯ ዘር ምን ያህል እንዳደገች ማየቱ አስገራሚ ነው። በምድር ላይ ካሉት “ዘሮች ሁሉ እጅግ የምታንስ” የተባለችው ዘር አድጋ “ትላልቅ ቅርንጫፎች” ያሉት ዛፍ ሆነች። (ማር. 4:31, 32) (2) ዘሯ እንደምታድግ የተረጋገጠ ነው። የሰናፍጯ ዘር ‘ከተዘራች በኋላ ታድጋለች።’ ኢየሱስ፣ ይህችን ዘር በተመለከተ “ታድግ ይሆናል” አላለም። ከዚህ ይልቅ ዘሯ ‘እንደምታድግ’ ተናግሯል። እድገቷን ሊገታ የሚችል ነገር አይኖርም። (3) ዛፏ ማደጓ የተለያዩ ፍጥረታትን የሚስብ ሲሆን መስፈሪያም ትሆንላቸዋለች። “የሰማይ ወፎች በጥላዋ ሥር መስፈሪያ ያገኛሉ።” እነዚህ ሦስት ነጥቦች በዘመናችን ከሚከናወነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ ጋር የሚያያዙት እንዴት ነው?

12. የሰናፍጯ ዘር ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ከሚከናወነው የመከር ሥራ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (“ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች” የሚለውን ሠንጠረዥም ተመልከት።)

12 (1) ምን ያህል እንዳደገች፦ ምሳሌው፣ የመንግሥቱ መልእክት እና የክርስቲያን ጉባኤ እድገት ማድረጋቸውን ያጎላል። ቀናተኛ የሆኑ የመከሩ ሠራተኞች ከ1919 ጀምሮ፣ ክርስቶስ ወዳነጻው የክርስቲያን ጉባኤ ተሰብስበዋል። በዚያ ወቅት የሠራተኞቹ ቁጥር ጥቂት የነበረ ቢሆንም ቁጥራቸው በፍጥነት እያደገ ሄደ። በእርግጥም በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ቁጥር አድጎ በዛሬው ጊዜ ምን ያህል እንደደረሰ መመልከት አስገራሚ ነው። (ኢሳ. 60:22) (2) የተረጋገጠ መሆኑ፦ የክርስቲያን ጉባኤ እድገት ሊገታ እንደማይችል ታይቷል። የአምላክ ጠላቶች ትንሿን ዘር ለማጥፋት እንደ ዓለት ከባድ የሆነ የስደት ናዳ ቢጭኑባትም ዘሯ ማንኛውንም መሰናከል ተቋቁማ ማደጓን ቀጥላለች። (ኢሳ. 54:17) (3) መስፈሪያ መሆኗ፦ በዛፏ ላይ የሰፈሩት “የሰማይ ወፎች” ወደ 240 ገደማ ከሚሆኑ አገሮች የተውጣጡና የክርስቲያን ጉባኤ አባል በመሆን ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ የሰጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦችን ያመለክታሉ። (ሕዝ. 17:23) እነዚህ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በመንፈሳዊ ሁኔታ ምግብ፣ እረፍትና እና ጥበቃ አግኝተዋል።—ኢሳ. 32:1, 2፤ 54:13

የተለያየ ዓይነት ያላቸው ወፎች በሰናፍጭ ዛፍ ላይ አርፈው

የሰናፍጩ ዘር ምሳሌ፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የታቀፉ ሰዎች ማረፊያና ጥበቃ እንደሚያገኙ ያሳያል (አንቀጽ 11, 12⁠ን ተመልከት)

13. በእርሾው ምሳሌ ላይ ከእድገት ጋር በተያያዘ የጎሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

13 የእርሾው ምሳሌ። አንዲት ሴት ዱቄት ውስጥ እርሾ በመጨመር ደባለቀችው፤ እርሾውም ሊጡ በሙሉ እንዲቦካ አደረገ። (ማቴዎስ 13:33⁠ን አንብብ።) በዚህ ምሳሌ ላይ ከእድገት ጋር በተያያዘ የጎሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? እስቲ ሁለቱን ነጥቦች እንመርምር። (1) እድገት ለውጥ ያስከትላል። እርሾው በሊጡ ውስጥ በመሰራጨቱ “ሊጡ በሙሉ [ቦክቷል]።” (2) እድገቱ ብዙ ቦታዎችን የሚያዳርስ ነው። እርሾው ‘በሦስት ትላልቅ መስፈሪያ’ የተሰፈረው ዱቄት በሙሉ እንዲቦካ አድርጓል። እነዚህ ሁለት ነጥቦች በዘመናችን ከሚከናወነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ ጋር የሚያያዙት እንዴት ነው?

14. የእርሾው ምሳሌ በዘመናችን ከሚከናወነው የመከር ሥራ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

14 (1) ለውጥ፦ እርሾው የመንግሥቱን መልእክት ሲወክል ዱቄቱ የሰውን ዘር ያመለክታል። ዱቄት ከእርሾ ጋር ሲቦካ ሊጡ ላይ ለውጥ እንደሚታይ ሁሉ ሰዎችም የመንግሥቱን መልእክት ሲቀበሉ ልባቸው ይለወጣል። (ሮም 12:2) (2) ብዙ ቦታዎችን የሚያዳርስ፦ እርሾው መላውን ሊጥ ማዳረሱ የመንግሥቱ መልእክት መላውን ምድር እንደሚያዳርስ ይጠቁማል። እርሾው ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ ይሰራጫል። በተመሳሳይም የመንግሥቱ መልእክት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተሰራጭቷል። (ሥራ 1:8) ከዚህም በተጨማሪ ከእርሾው ምሳሌ ጋር በተያያዘ የሚጎላው ሁለተኛው ነጥብ፣ ሥራችን በታገደባቸው አገሮች የስብከቱ ሥራ እንደሚከናወን ብዙዎች ባያስተውሉም በእነዚህ ቦታዎችም እንኳ የመንግሥቱ መልእክት እንደሚስፋፋ ይጠቁማል።

15. በኢሳይያስ 60:5, 22 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (በገጽ 93 ላይ የሚገኘውን “ይሖዋ እንዲቻል አድርጓል” የሚለውን ሣጥን እና ከገጽ 96-97 ላይ የሚገኘውን “‘ትንሽ የሆነው፣ ኃያል ብሔር’ የሆነው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

15 ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ከመናገሩ ከ800 ዓመታት በፊት ይሖዋ፣ በዘመናችን የሚከናወነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረው እንዲሁም ይህ የመከር ሥራ ደስታ እንደሚያስገኝ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት በማይረሳ መልኩ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር።c ይሖዋ፣ ሰዎች “ከሩቅ” አካባቢዎች ወደ ድርጅቱ እንደሚጎርፉ ገልጿል። በዛሬው ጊዜ ምድር ላይ ያሉትን ቅቡዓን ቀሪዎች በአንዲት ሴት በመመሰል ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ታያለሽ፤ ፊትሽም ይፈካል፤ ልብሽ በኃይል ይመታል፤ በደስታም ይሞላል፤ ምክንያቱም የባሕር ብልጽግና ወደ አንቺ ይጎርፋል፤ የብሔራትም ሀብት ወደ አንቺ ይመጣል።” (ኢሳ. 60:1, 4, 5, 9) በእርግጥም ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል! በዛሬው ጊዜም ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩ አገልጋዮቹ፣ ባሉበት አገር ውስጥ የነበሩት ጥቂት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥራቸው ጨምሮ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን ሲመለከቱ ልባቸው በደስታ ይሞላል።

ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች የሚደሰቱበት ምክንያት

16, 17. ‘ዘሪውም ሆነ አጫጁ በአንድነት እንዲደሰቱ’ የሚያደርጋቸው አንዱ ምክንያት ምንድን ነው? (“በአማዞን የሁለት ሰዎችን ልብ የነኩ ሁለት ትራክቶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

16 ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “አጫጁ . . . ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው፤ ስለዚህ ዘሪውም ሆነ አጫጁ በአንድነት ደስ ይላቸዋል” እንዳላቸው ታስታውስ ይሆናል። (ዮሐ. 4:36) ይሁንና በዓለም አቀፉ የመከር ሥራ “በአንድነት ደስ [የሚለን]” ለምንድን ነው? የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። እስቲ ሦስቱን እንመልከት።

17 አንደኛ፣ ከዚህ ሥራ ጋር በተያያዘ ይሖዋ የሚያከናውነውን ነገር መመልከታችን ያስደስተናል። የመንግሥቱን መልእክት ስንሰብክ ዘሩን እየዘራን ነው። (ማቴ. 13:18, 19) አንድ ሰው፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን ስንረዳ ደግሞ ፍሬ እየሰበሰብን ነው። ይሖዋ የመንግሥቱ ዘር ‘እንዲበቅልና እንዲያድግ’ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ስንመለከት ሁላችንም በጣም እንደሰታለን። (ማር. 4:27, 28) ከዘራነው ዘር መካከል የተወሰነው የሚያድገው ቆየት ብሎ በመሆኑ የሚሰበስቡት ሌሎች ናቸው። ምናልባት አንተም እንደ እህት ጆን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል፤ በብሪታንያ የሚኖሩት እህት ጆን የተጠመቁት ከ60 ዓመታት በፊት ነው። እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳንዶች፣ ምሥራቹን በመስበክ ከዓመታት በፊት በልባቸው ውስጥ የእውነትን ዘር የዘራሁት እኔ እንደሆንኩ ነግረውኛል። እነዚህ ሰዎች እኔ ሳላውቅ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው የይሖዋ አገልጋዮች ሆነዋል። የዘራሁት ዘር በማደጉና ለፍሬ በመብቃቱ ደስተኛ ነኝ።”—1 ቆሮንቶስ 3:6, 7⁠ን አንብብ።

ይሖዋ እንዲቻል አድርጓል

ኢየሱስ “በሰዎች ዘንድ የማይቻል፣ በአምላክ ዘንድ ይቻላል” ብሏል። (ሉቃስ 18:27) ብዙዎቻችን የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት በሕይወታችን ተመልክተናል። የስብከቱን ሥራ ለማስቆም የሚፈልጉ ሰዎች የተለያየ ጥረት ቢያደርጉም ይሖዋ ሥራውን እንድናከናውን ረድቶናል።

ዛካሪ

ዛካሪ ኤሌግቤ (ዕድሜ 66፣ የተጠመቁት በ1963) በቤኒን በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ የተጣለው እገዳ ወንድሞችን እንዴት እንደረዳቸው ያስታውሳሉ፤ እንዲህ ብለዋል፦ “በ1976 በአገሪቱ 2,300 አስፋፊዎች በነበርንበት ወቅት መንግሥት፣ ሥራችን መታገዱን የሚገልጽ ማስታወቂያ በአገሪቱ ባሉ ቋንቋዎች ሁሉ እንዲነገር ትእዛዝ ሰጠ። እንዲህ ያለ ነገር ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም። በቤኒን ከ60 የሚበልጡ ቋንቋዎች የሚነገሩ ቢሆንም በወቅቱ የሬዲዮ ፕሮግራሞች የሚተላለፉት በአምስት ቋንቋዎች ብቻ ነበር። በመሆኑም ሥራችን መታገዱን የሚገልጸው ማስታወቂያ በአገሪቱ ባሉት ቋንቋዎች በሙሉ ሲነገር፣ ራቅ ባሉ ቦታዎች የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰሙ። እነዚህ ሰዎች ‘የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው? ሥራቸው የታገደውስ ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረባቸው። ከጊዜ በኋላ ወደ እነዚያ አካባቢዎች ስንሄድ ብዙዎች እውነትን ለመቀበል ጊዜ አልወሰደባቸውም።” በዛሬው ጊዜ በቤኒን ከ11,500 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።

ማሪያ

ማሪያ ዚኒች (ዕድሜ 74፣ የተጠመቁት በ1957)፦ “የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ መላው ቤተሰባችን ከዩክሬን በሩሲያ ወደሚገኘው ሳይቤሪያ ተጋዘ። መንግሥት በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የምንገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ዝም ለማሰኘት ብዙ ጥረት ቢያደርግም ቁጥራችን ማደጉን ቀጥሎ ነበር። ከፍተኛ ተቃውሞ እያለም አስደናቂ የሆነ እድገት መኖሩን ማየቴ ሥራው የይሖዋ እንደሆነ እንዳምን አድርጎኛል። ማንም ቢሆን ሥራውን ሊያስቆመው አልቻለም!” ማሪያ (ዕድሜ 73፣ የተጠመቁት በ1960) የተባሉ ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ብለዋል፦ “መንግሥት ወንድሞችን ወደ ሳይቤሪያ ማጋዙ፣ ርቀው ባሉ ቦታዎች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች እውነትን የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ መንገድ ከፍቷል።”

ሄሱስ

ሄሱስ ማርቲን (ዕድሜ 77፣ የተጠመቁት በ1955) እንዲህ ብለዋል፦ “እውነትን በሰማሁበት ወቅት በስፔን 300 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። የሚደርስብን ስደት በ1960 ይበልጥ እየተባባሰ መጣ። መንግሥት፣ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በኃይል ተጠቅመው እንዲያስቆሙ ለፖሊሶች ትእዛዝ አስተላለፈ። በዚያን ጊዜ፣ ምሥራቹን በመላ አገሪቱ መስበክ እንችላለን ብሎ ማሰብ ይከብድ ነበር። ሁሉ ነገር የጠመመብን ይመስል ነበር። ዛሬ ግን በስፔን ወደ 111,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። ተቃውሞ እያለም እንኳ እንዲህ ያለ እድገት መገኘቱ ይሖዋ ከእኛ ጋር እስከሆነ ድረስ ምንም የማይቻል ነገር እንደሌለ እንድተማመን አድርጎኛል!”

18. በ1 ቆሮንቶስ 3:8 ላይ ለደስታችን ምክንያት የሚሆን ምን ነገር ተጠቅሷል?

18 ሁለተኛ፣ ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ማስታወሳችን በሥራችን ደስተኛ ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል። (1 ቆሮ. 3:8) ሽልማት የምናገኘው ሥራችን ባስገኘው ውጤት መሠረት ሳይሆን በሥራችን መጠን ነው። ብዙም ውጤት በማይገኝበት አካባቢ ለሚሰብኩ ክርስቲያኖች ይህ ማረጋገጫ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! አምላክ፣ ዘር በመዝራቱ ሥራ በሙሉ ልቡ የሚካፈልን እያንዳንዱን የይሖዋ ምሥክር “ብዙ ፍሬ [እንደሚያፈራ]” አድርጎ ይመለከተዋል፤ ይህ ደግሞ ሁላችንም ደስተኛ እንድንሆን ያደርገናል።—ዮሐ. 15:8፤ ማቴ. 13:23

19. (ሀ) በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ከደስታችን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (ለ) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ባይሳካልንም እንኳ የትኛውን ነጥብ ማስታወስ ይኖርብናል?

19 ሦስተኛ፣ ሥራችን ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርግ መሆኑ ያስደስተናል። የኢየሱስ ሐዋርያት “የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” ብለው ሲጠይቁት ኢየሱስ የሰጣቸውን መልስ እንመልከት። ኢየሱስ የምልክቱ አንዱ ገጽታ በዓለም ዙሪያ የሚካሄድ የስብከት ሥራ እንደሆነ ነግሯቸዋል። ይህን ሲል ደቀ መዛሙርት ስለማድረጉ ሥራ መናገሩ ነበር? አይደለም። “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” ብሏል። (ማቴ. 24:3, 14) ከዚህ አንጻር የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ማለትም ዘር የመዝራቱ ሥራ የምልክቱ አንድ ገጽታ ነው። በመሆኑም የመንግሥቱን ምሥራች ስንሰብክ ደቀ መዛሙርት ማድረግ ባንችል እንኳ ‘ምሥክርነት’ በመስጠቱ ሥራ እየተሳካልን እንደሆነ ሁልጊዜ ማስታወስ ይኖርብናል።d በእርግጥም ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን የኢየሱስን ትንቢት በመፈጸም ረገድ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን፤ በተጨማሪም “ከአምላክ ጋር አብረን [የመሥራት]” መብት አለን። (1 ቆሮ. 3:9) ይህም እንድንደሰት የሚያደርግ ትልቅ ምክንያት ነው!

“ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ”

20, 21. (ሀ) በሚልክያስ 1:11 ላይ የሚገኘው ትንቢት እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ከመከሩ ሥራ ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው? ለምንስ?

20 በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ኢየሱስ የመከሩ ሥራ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ሐዋርያቱን ረድቷቸዋል። ከ1919 ወዲህም ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ ደቀ መዛሙርቱን ይህንኑ እውነታ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። የአምላክ ሕዝቦችም ሥራቸውን ይበልጥ አጠናክረው ቀጥለዋል። ደግሞም የመከሩን ሥራ ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ታይቷል። ነቢዩ ሚልክያስ አስቀድሞ እንደተናገረው በዛሬው ጊዜ የስብከቱ ሥራ “ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ” እየተካሄደ ነው። (ሚል. 1:11) በእርግጥም ከፀሐይ መውጫ አንስቶ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ይኸውም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ዘሪዎችና አጫጆች የሚኖሩት የትም ይሁን የት፣ በአንድ ላይ እየሠሩና እየተደሰቱ ነው። በተጨማሪም ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ማለትም ከጠዋት እስከ ማታ ወይም ቀኑን ሙሉ በጥድፊያ ስሜት እንሠራለን።

21 ወደ 100 የሚጠጉ ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፣ ጥቂት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች በዝተው “ኃያል ብሔር” እንደሆኑ ማወቃችን ‘ልባችን በኃይል እንዲመታና በደስታ እንዲሞላ’ ያደርጋል። (ኢሳ. 60:5, 22) ይህ ደስታ እንዲሁም “የመከሩ ሥራ ኃላፊ” ለሆነው ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሁላችንም እስከ ዛሬ ከተካሄዱት ሁሉ በሚበልጠው ታላቅ የመከር ሥራ የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት ጥረት ማድረጋችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን ይሁን!—ሉቃስ 10:2

a ኢየሱስ “አዝመራው እንደነጣ” የተናገረው በርካታ ሳምራውያን ነጭ ልብስ ለብሰው ወደ እሱ እየመጡ መሆናቸውን ስለተመለከተ ሊሆን ይችላል።

b ስለ እነዚህ ዓመታትና ከዚያ በኋላ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ስለተከናወነው ነገር ለማወቅ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 425-520 እንድታነብብ እናበረታታሃለን፤ እዚያ ላይ ከ1919 እስከ 1992 ባሉት ዓመታት ውስጥ የመከሩ ሥራ ምን ውጤት እንዳስገኘ የሚገልጽ ዘገባ ይገኛል።

c ይህን አስገራሚ ትንቢት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 303-320 ተመልከት።

d በቀደሙት ዘመናት የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ወሳኝ እውነት ተረድተው ነበር። የኅዳር 15, 1895 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ጥቂት ስንዴ መሰብሰብ ከተቻለ ስለ እውነት ብዙ ምሥክርነት ተሰጥቷል ማለት ይቻላል። . . . ሁሉም ወንጌሉን መስበክ ይችላሉ።”

የአምላክ መንግሥት ለአንተ ምን ያህል እውን ነው?

  • የአምላክ መንግሥት ከመንፈሳዊው መከር ጋር በተያያዘ ምን ነገሮችን አከናውኗል?

  • ስለ ሰናፍጩ ዘር እና ስለ እርሾው የሚናገሩት ምሳሌዎች አገልግሎትህን እንድታከናውን የሚያበረታቱህ እንዴት ነው?

  • በአገልግሎትህ ደስተኛ እንድትሆን የሚያደርጉህ ምን ምክንያቶች አሉ?

በአማዞን የሁለት ሰዎችን ልብ የነኩ ሁለት ትራክቶች

አንቶኒዮ ሲሞይንስ

አንቶኒዮ ሲሞይንስ

አንቶኒዮ ሲሞይንስ የተባሉ የ91 ዓመት አረጋዊ፣ አባታቸውና የአክስታቸው ባል የይሖዋ ምሥክሮች ባዘጋጇቸው ሁለት ትራክቶች አማካኝነት እውነትን እንዴት እንዳወቁ ያስታውሳሉ። እኚህ ታማኝ የጉባኤ ሽማግሌ፣ ሊጎበኟቸው የመጡትን ባልና ሚስት “ታሪኩን መስማት ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቋቸው። ባልና ሚስቱም “ደስ ይለናል” በማለት መለሱ። ደግነት የሚንጸባረቅባቸው የአንቶኒዮ ዓይኖች በደስታ አበሩ፤ ከዚያም ፊታቸው በፈገግታ ተሞልቶ ታሪኩን መናገር ጀመሩ።

“አባቴ ዜኖ በባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰባኪ ነበር። በ1931 በአማዞን ደን ውስጥ ርቆ በሚገኝ ቦታ የምትኖር አንዲት የቤተ ክርስቲያኑ አባልን ለመጎብኘት ሄደ። ሴትየዋ ቤት ውስጥ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትራክቶችን ተመለከተ። ይህች ሴት ትራክቶቹን ያገኘችው ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ቢሆንም ማን እንዳስቀመጣቸው አላወቀችም። አንደኛው ትራክት የሚናገረው ስለ ገሃነመ እሳት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ስለ ትንሣኤ ያወሳል። አባቴ ባነበበው ነገር ልቡ ተነካ። ወዲያውኑ ያስታወሰው የእህቱን ባል ጊልዬርምን ነበር፤ ጊልዬርም ‘በገሃነመ እሳት አላምንም። አፍቃሪ የሆነ አምላክ እንዲህ ያለ ቦታ ሊያዘጋጅ አይችልም’ እያለ ብዙ ጊዜ ይናገር ነበር። አባቴ ትራክቶቹን ለጊልዬርም ለማሳየት ስለጓጓ በታንኳው እየቀዘፈ ለስምንት ሰዓት ያህል በመጓዝ ጊልዬርም ወደሚኖርበት ማናኪሪ የተባለ በመናዉስ አቅራቢያ የሚገኝ አካባቢ ሄደ።

አንቶኒዮ ሲሞይንስ በማናኪሪ፣ አማዞናስ ግዛት፣ ብራዚል የተቋቋመውን የመጀመሪያ ጉባኤ የሚያሳዩ ሁለት ፎቶግራፎች ይዘው

በብራዚል አማዞናስ ግዛት የመጀመሪያው ጉባኤ

“አባቴና ጊልዬርም ትራክቶቹን ካነበቡ በኋላ ሁለቱም ‘ይህ እውነት ነው!’ ተባባሉ። ወዲያውኑ በብራዚል ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በመጻፍ ጽሑፎች እንዲላኩላቸው ጠየቁ። አባቴ፣ የቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ሆኖ ማገልገሉን ተወና ከአክስቴ ባል ጋር ሆነው በዚያ ገለልተኛ አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መስበክ ጀመሩ። በዚያ ያሉ ሰዎች ምሥራቹን ስለተቀበሉ በአንድ ዓመት ውስጥ በማናኪሪ ጉባኤ ተቋቋመ። ብዙም ሳይቆይ 70 የሚያህሉ የመንደሩ ነዋሪዎች በስብሰባዎች ላይ መገኘት በመጀመራቸው ጉባኤው በወቅቱ በብራዚል ከነበሩት ጉባኤዎች ሁሉ ትልቁ ሆነ።” ወንድም አንቶኒዮ ለጥቂት ጊዜ ዝም አሉ። ከዚያም “የመንግሥቱ መልእክት ወደ አማዞን አካባቢ የደረሰበት መንገድ አስገራሚ አይደለም?” በማለት ጠየቁ። በእርግጥም አስገራሚ ነው። በአማዞን ደን ውስጥ የተዘሩ ሁለት ትናንሽ ዘሮች ማለትም ሁለት ትናንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ትራክቶች ሰፊ በሆነው በዚህ አካባቢ ሥር በመስደዳቸውና ፍሬ በማፍራታቸው ትልቅ ጉባኤ ሊቋቋም ችሏል። ከተቋቋመ 83 ዓመታትን ያስቆጠረው የማናኪሪ ጉባኤ በአሁኑ ጊዜ በብራዚል አማዞናስ ግዛት የሚገኘው ብቸኛው ጉባኤ መሆኑ ቀርቷል፤ በዚህ አካባቢ 143 ጉባኤዎች ይገኛሉ።

‘ትንሽ የሆነው፣ ኃያል ብሔር’ የሆነው እንዴት ነው?

“ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል። እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ።” (ኢሳ. 60:22) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ የይሖዋ ምሥክሮች የዚህን ትንቢት ፍጻሜ ሲመለከቱ ምን ተሰምቷቸዋል?

በርየ ኒልሰን

በርየ ኒልሰን (ዕድሜ 84፣ የተጠመቁት በ1943)፦ “በ1920ዎቹ ዓመታት ኮልፖርተር ሆኖ ያገለግል የነበረ አንድ ቅቡዕ ወንድም ትዝ ይለኛል። የስዊድን ግማሽ የሚሆነው ቦታ የአገልግሎት ክልሉ እንደሆነ ሲነገረው ታዛዥ በመሆን በዚያ መስበክ ጀመረ፤ ደግሞም ይህ ወንድምና ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች ያከናወኑት ሥራ ተባርኳል! በዛሬው ጊዜ ከ22,000 በላይ አስፋፊዎች አሉን። በአሁኑ ወቅት ዕድሜዬ ቢገፋም ታዛዥ በመሆን በይሖዋ አገልግሎት መካፈሌን መቀጠል እፈልጋለሁ። ይሖዋ ምን ሌላ አስገራሚ ነገር እንዳስቀመጠልን ማን ያውቃል?”

ኤትየን ኤስተርሄሴ

ኤትየን ኤስተርሄሴ (ዕድሜ 83፣ የተጠመቁት በ1942)፦ “በ1942 በደቡብ አፍሪካ 1,500 የይሖዋ ሕዝቦች ነበሩ፤ ይህ ቁጥር አድጎ ዛሬ ከ94,000 በላይ ሆነናል። ይህን ሳስብ በጣም እደነቃለሁ። እንዲህ ባለው ትልቅ ድርጅት ውስጥ መታቀፍ በእርግጥም እምነትን የሚያጠናክር ነው!”

ኪት ጌደን

ኪት ጌደን (ዕድሜ 82፣ የተጠመቁት በ1948)፦ “በ1948 በብሪታንያ 13,700 የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር አድጎ በዛሬው ጊዜ ወደ 137,000 ገደማ መድረሱን መመልከቴ ሥራው የይሖዋ እንደሆነ አረጋግጦልኛል። ይህ በሰው ኃይል የማይቻል ነገር ነበር፤ ይሖዋ ግን “ድንቅ ነገሮችን [የሚያደርግ]” አምላክ ነው።—ዘፀ. 15:11

ኡልሪክ ክሮሎፕ

ኡልሪከ ክሮሎፕ (ዕድሜ 77፣ የተጠመቁት በ1952)፦ “ናዚዎች ያደረሱባቸውን ስደት በጽናት የተቋቋሙት የይሖዋ ምሥክሮች ቅንዓት፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጀርመን የነበሩትን ጉባኤዎች ይበልጥ ለሥራ እንዲነሳሱ አደረጋቸው። ሰዎች ማጽናኛ ማግኘት ይፈልጉ ነበር፤ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ በዚህ አስከፊ ጦርነት ስላልተካፈልን አፋችንን ሞልተን ልናጽናናቸው እንችል ነበር። ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ የአምላክ መንፈስ ሕዝቦቹን እንዴት እንደመራቸው መመልከት ችያለሁ። ዛሬ ቁጥራችን ከ164,000 በላይ ደርሷል፤ ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ውጤት ነው!”

ማሪያ ብሪንዬትስካያ

ማሪያ ብሪንዬትስካያ (ዕድሜ 77፣ የተጠመቁት በ1955)፦ “የተጠመቅኩት ምሽት ላይ ጨለማን ተገን በማድረግ ነበር፤ ይህን ያደረግነው እንዳንያዝ በመፍራት ነው። ከጊዜ በኋላ፣ ባለቤቴ የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ምክንያት ርቆ ወደሚገኝ የጉልበት ሥራ ካምፕ ተላከ። እኔም ሩሲያ ውስጥ በሚገኘው መንደራችን ሆኜ በጥንቃቄ መስበኬን ቀጠልኩ፤ በዚህም ምክንያት ብዙዎች እውነትን ተቀበሉ። በዚያ ወቅት የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ጥቂት ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ በሩሲያ ከ168,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች መኖራቸውን ስመለከት በጣም እደሰታለሁ!”

ኪማኮ ያማዋ

ኪሚኮ ያማኖ (ዕድሜ 79፣ የተጠመቁት በ1954)፦ “በ1970 በጃፓን 10,000 የሚያህሉ አስፋፊዎች እንዳሉ ሳውቅ የደስታ እንባ አንብቼ ነበር፤ ለይሖዋም ‘በሕይወት እስካለሁ ድረስ ለአንተ ታማኝ እሆናለሁ’ ብዬ እንደገና ቃል ገባሁ። ዛሬ ከ216,000 በላይ አስፋፊዎች እንዳሉን ስመለከት ምን ያህል እንደምደሰት መገመት ትችላላችሁ!”

ዳንዬል ኦዶገን

ዳንዬል ኦዶገን (ዕድሜ 83)፦ “በ1950 ስጠመቅ በናይጄሪያ 8,000 አስፋፊዎች ነበሩ። ዛሬ 351,000 ያህል ሆነናል! በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ብዙዎች ሲገኙ ስመለከት ልቤ በደስታ ይሞላል፤ እንዲሁም ሐጌ 2:7⁠ን አስታውሳለሁ። ይሖዋ ብሔራትን እያናወጠ ነው፤ በብሔራት መካከል ያሉ የከበሩ ነገሮችም እየመጡ ነው። አሁንም ቢሆን በስብከቱ ሥራ አቅሜ የሚፈቅደውን ያህል ለማድረግ እጥራለሁ፤ ምክንያቱም መስበክ ይሖዋን ‘አመሰግንሃለሁ!’ የምልበት መንገድ ነው።”

ካርሎስ ሲልቫ

ካርሎስ ሲልቫ (ዕድሜ 79)፦ “በ1952 ስጠመቅ በብራዚል 5,000 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በዚያ ዓመት በሳኦ ፓውሎ በሚገኝ የስፖርት ማዕከል ውስጥ ትልቅ ስብሰባ ነበረን። በመኪና ማቆሚያው ቦታ የቆሙት ሁለት መኪኖች ብቻ ነበሩ። አንድ ወንድም በአቅራቢያችን ወደሚገኘው ፓካኤምቡ ስታዲየም እያመለከተ ‘ይህን ስታዲየም ሞልተን የምንሰበሰብበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልሃል?’ አለኝ። ይህ ፈጽሞ የማይቻል ይመስል ነበር፤ ሆኖም በ1973 ባደረግነው ስብሰባ ላይ 94,586 ሰዎች በመገኘታቸው ስታዲየሙ ጢም ብሎ ሞላ! ዛሬ በብራዚል ከ767,000 በላይ ውድ ወንድሞች አሉ፤ ይህን እድገት መመልከት በጣም አስደናቂ ነው!”

ካርሎስ ካሳሬስ

ካርሎስ ካሳሬስ (ዕድሜ 73)፦ “በ1954 ስጠመቅ በሜክሲኮ 10,500 አስፋፊዎች ነበሩ። በወቅቱ ሠራተኞች በጣም ያስፈልጉ ስለነበር በ21 ዓመቴ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ኢሳይያስ 60:22 ሲፈጸም የዓይን ምሥክር መሆን መቻሌ ትልቅ በረከት እንደሆነ ይሰማኛል። በአሁኑ ጊዜ ከ806,000 በላይ አስፋፊዎች ያሉን ሲሆን እነሱም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራሉ! ይህ በጣም አስደናቂ ነው!”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ