-
ምሥራቹ የሚያስገኛቸው በረከቶችመጠበቂያ ግንብ—2002 | ጥር 1
-
-
ምሥራቹ የሚያስገኛቸው በረከቶች
“ለድሆች [“ለየዋሆች፣” NW ] የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ . . . የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ።”—ኢሳይያስ 61:1, 2
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ማንነቱን በተመለከተ ምን ብሏል? እንደዚያ የሆነውስ በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢየሱስ ያወጀው ምሥራች ምን በረከቶች አስገኝቷል?
ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ በአንድ የሰንበት ቀን ናዝሬት በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ነበር። ዘገባው እንደሚገልጸው “የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፣ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ:- የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ . . . ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና . . . ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።” ኢየሱስ ተጨማሪ የትንቢቱን ክፍል ማንበቡን ቀጠለ። ከዚያም ተቀምጦ “ይህ በጆሮአችሁ የሰማችሁት የመጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” (አ.መ.ት ) አላቸው።—ሉቃስ 4:16-21
2 በዚህ መንገድ ኢየሱስ ትንቢት የተነገረለት ወንጌላዊ፣ ምሥራች አብሳሪና የመጽናኛ ምንጭ እሱ መሆኑን አሳወቀ። (ማቴዎስ 4:23) ኢየሱስ የተናገረው መልእክት በእርግጥም ምሥራች ነው! ለአድማጮቹ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ሲል ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 8:12) በተጨማሪም “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 8:31, 32) አዎን፣ ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ነበረው። (ዮሐንስ 6:68, 69) ብርሃን፣ ሕይወትና ነፃነት በእርግጥ እንደ ውድ ሀብት የሚታዩ በረከቶች ናቸው!
3. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን ምሥራች ሰብከዋል?
3 በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የጀመረውን የወንጌላዊነት ሥራ ቀጥለዋል። ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ ለእስራኤላውያንም ሆነ ለአሕዛብ ሰብከዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ ሥራ 15:7፤ ሮሜ 1:16) ወንጌሉን የተቀበሉ ሰዎች ይሖዋ አምላክን ማወቅ ችለዋል። ከሃይማኖታዊ ባርነት ተላቅቀው ጌታቸው ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ ለዘላለም የመግዛት ተስፋ ያላቸው የአዲሱ መንፈሳዊ ብሔር ክፍል ማለትም ‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ አባላት ሆነዋል። (ገላትያ 5:1፤ 6:16፤ ኤፌሶን 3:5-7፤ ቆላስይስ 1:4, 5፤ ራእይ 22:5) በእርግጥም እነዚህ ውድ በረከቶች ናቸው!
ወንጌላዊነት በዛሬው ጊዜ
4. ምሥራቹን የመስበኩ ተልእኮ በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
4 በዛሬው ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የ“ሌሎች በጎች” ክፍል በሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” እየታገዙ በመጀመሪያ ለኢየሱስ ተሰጥቶት የነበረውን ትንቢታዊ ተልእኮ በመፈጸም ላይ ናቸው። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) በመሆኑም ምሥራቹ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን በመሰበክ ላይ ይገኛል። በ235 አገሮችና ክልሎች የይሖዋ ምሥክሮች ‘ለድሆች የምሥራችን ለመስበክ፣ ልባቸው የተሰበረውን ለመጠገን፣ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን ለመናገር፣ የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካቸውም የሚበቀልበትን ቀን ለመናገር፣ የሚያለቅሱትንም ሁሉ ለማጽናናት’ ጥረት አድርገዋል። (ኢሳይያስ 61:1, 2) በመሆኑም ክርስቲያናዊው የወንጌላዊነት ሥራ ለብዙዎች በረከት እንዲሁም ‘በመከራ ሁሉ ላሉት’ እውነተኛ መጽናናት እያስገኘ ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
-
-
ምሥራቹ የሚያስገኛቸው በረከቶችመጠበቂያ ግንብ—2002 | ጥር 1
-
-
ዘላለማዊ በረከቶች የሚያስገኝ ምሥራች
6. በዛሬው ጊዜ እየተሰበከ ያለው ምሥራች ምንድን ነው?
6 የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት ምሥራች አቻ የለውም። ኢየሱስ የሰው ልጆች ወደ አምላክ መቅረብ የሚችሉበትን መንገድ ለመክፈት፣ የኃጢአት ይቅርታ ለማስገኘትና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ለመዘርጋት ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ መክፈሉን መልእክቱን ለሚቀበሉ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ እየገለጡ ያሳያሉ። (ዮሐንስ 3:16፤ 2 ቆሮንቶስ 5:18, 19) የአምላክ መንግሥት በተቀባው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር በሰማይ መቋቋሙንና በቅርቡ ከምድር ላይ ክፋትን አስወግዶ ምድር ተመልሳ ገነት እንድትሆን ሥራውን በበላይነት እንደሚቆጣጠር ያውጃሉ። (ራእይ 11:15፤ 21:3, 4) በኢሳይያስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የሰው ዘር ለምሥራቹ ምላሽ መስጠት የሚችልበት ‘የተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት’ አሁን መሆኑን ለጎረቤቶቻቸው ያሳውቃሉ። በተጨማሪም ይሖዋ ከአካሄዳቸው የማይመለሱ ክፉ አድራጊዎችን በማጥፋት ‘አምላካችን የሚበቀልበት ቀን’ በቅርቡ እንደሚመጣ ያስጠነቅቃሉ።—መዝሙር 37:9-11
-