-
ለአሕዛብ የፈነጠቀ ብርሃንየኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
-
-
“ለእግዚአብሔር ስጦታ” ማቅረብ
12, 13. ከ537 ከዘአበ አንስቶ ‘ወንድሞች’ ወደ ኢየሩሳሌም የሚመጡት በምን መንገድ ነው?
12 ኢየሩሳሌም ዳግመኛ ከተገነባች በኋላ ከትውልድ አገራቸው ርቀው በተለያዩ የምድር ክፍሎች ተበትነው የሚገኙ አይሁዳውያን ቀደም ሲል የነበረው የክህነት አገልግሎት እንደገና የሚቋቋምባትን የኢየሩሳሌም ከተማ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል አድርገው ይመለከቷታል። ብዙዎቹ በከተማዋ ውስጥ በሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት ላይ ለመገኘት ረጅም ጉዞ ያደርጋሉ። ኢሳይያስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጻፈ:- “የእስራኤል ልጆች ቁርባናቸውን በጥሩ [“በንጹሕ፣” የ1980 ትርጉም ] ዕቃ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፣ እንዲሁ ለእግዚአብሔር ቁርባን [“ስጦታ፣” የ1980 ትርጉም ] ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፣ በፈረሶችና በሰረገሎች፣ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፣ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፣ ይላል እግዚአብሔር። ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ።”—ኢሳይያስ 66:20, 21
13 ‘ከአሕዛብ ሁሉ ከመጡት ከእነዚህ ወንድሞች’ መካከል አንዳንዶቹ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ በፈሰሰ ጊዜ በቦታው ተገኝተው ነበር። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር።” (ሥራ 2:5) ወደ ኢየሩሳሌም የመጡት በአይሁድ ልማድ መሠረት የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም ቢሆንም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ሲሰሙ ብዙዎቹ በእርሱ በማመን ተጠምቀዋል።
14, 15. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ተጨማሪ መንፈሳዊ ‘ወንድሞቻቸውን’ የሰበሰቡት እንዴት ነው? የተሰበሰቡት ሰዎች ‘በንጹሕ ዕቃ ላይ እንዳለ ስጦታ’ ሆነው ለይሖዋ የቀረቡትስ እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ አንዳንዶችን ‘ካህናት እንዲሆኑ የወሰደው’ በምን መንገድ ነው? (ሐ) መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውን በመሰብሰቡ ሥራ ከተካፈሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ እነማን ናቸው? (በዚህ ገጽ ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
14 ይህ ትንቢት ዘመናዊ ፍጻሜ አለውን? አዎን፣ አለው። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ መቋቋሙን ከቅዱሳን ጽሑፎች ተረዱ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር በማካሄድ ተጨማሪ የመንግሥቱ ወራሾች ወይም ‘ወንድሞች’ እንደሚሰበሰቡ ተገነዘቡ። ልበ ሙሉ የሆኑ አገልጋዮች ሁሉንም ዓይነት የመጓጓዣ መንገድ በመጠቀም የቅቡዓን ቀሪዎች አባላት የሚሆኑ ግለሰቦችን ለማግኘት ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ የተጓዙ ሲሆን ከተገኙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትናን አብያተ ክርስቲያናት እየጣሉ የወጡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከተገኙ በኋላ ለይሖዋ እንደ ስጦታ ሆነው ቀርበዋል።—ሥራ 1:8
15 ቀደም ባሉት ዓመታት የተሰበሰቡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ካወቁ በኋላ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት ለውጥ ማድረግ እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። ‘በንጹሕ ዕቃ ያለ ስጦታ’ ወይም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ‘ለክርስቶስ ንጽሕት ድንግል’ ሆነው መቅረብ እንዲችሉ ራሳቸውን ከመንፈሳዊና ከሥነ ምግባራዊ ርኩሰቶች ለማንጻት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:2) ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተሳሳቱ መሠረተ ትምህርቶችን ከማስወገድ በተጨማሪ ከዚህ ዓለም የፖለቲካ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ መሆን የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መማር አስፈልጓቸው ነበር። በ1931 አገልጋዮቹ በሚፈለገው ደረጃ ከነጹ በኋላ ይሖዋ በምሕረቱ ተገፋፍቶ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ስሙን እንዲሸከሙ መብት ሰጥቷቸዋል። (ኢሳይያስ 43:10-12) ይሁንና ይሖዋ አንዳንዶችን ‘ካህናት እንዲሆኑ የወሰደው’ በምን መንገድ ነው? እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ ለአምላክ የምሥጋና መሥዋዕት የሚያቀርቡ ‘የንጉሥ ካህናትና ቅዱስ ሕዝብ’ አባላት ሆነዋል።—1 ጴጥሮስ 2:9፤ ኢሳይያስ 54:1፤ ዕብራውያን 13:15
-
-
ለአሕዛብ የፈነጠቀ ብርሃንየኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 2
-
-
[በገጽ 409 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከአሕዛብ ሁሉ የመጡ ለይሖዋ የቀረቡ ቅቡዕ ስጦታዎች
በ1920 ሁዋን ሙንዪስ ከዩናይትድ ስቴትስ ተነስቶ ወደ ስፔን ከዚያም ወደ አርጀንቲና በመጓዝ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤዎችን አቋቋመ። ሚስዮናዊው ዊልያም አር ብራውን (በአብዛኛው ባይብል ብራውን በሚለው መጠሪያው ይታወቃል) ከ1923 አንስቶ እንደ ሴራሊዮን፣ ጋና፣ ላይቤሪያ፣ ጋምቢያና ናይጄሪያ በመሳሰሉ አገሮች የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩ የእውነት ብርሃን በምዕራብ አፍሪካ በሚገኙ ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች ላይ ፈንጥቋል። በዚያው ዓመት ካናዳዊው ጆርጅ ያንግ ወደ ብራዚል ከዚያም ወደ አርጀንቲና፣ ኮስታሪካ፣ ፓናማ፣ ቬንዝዌላና አልፎ ተርፎም ወደ ሶቭየት ኅብረት በማቅናት ምሥራቹን ሰብኳል። ኤድዊን ስኪነርም በዚሁ ጊዜ ከእንግሊዝ ወደ ሕንድ በመርከብ በመጓዝ ለበርካታ ዓመታት የመከሩን ሥራ በትጋት ሠርቷል።
-