-
‘ባቢሎን ወደቀች!’የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
-
-
5. ባቢሎን “ሸፍጠኛ” እና “አጥፊ” የሚል ስም ለማትረፍ የበቃችው እንዴት ነው?
5 በኢሳይያስ ዘመን ባቢሎን ገና ኃያል መንግሥት አልሆነችም ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ጊዜው ሲደርስ ሥልጣንዋን አላግባብ እንደምትጠቀምበት አስቀድሞ ተመልክቶ ነበር። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ከባድ ራእይ ተነገረኝ፤ ሸፍጠኛው ይሸፍጣል፣ በዝባዡም ይበዘብዛል።” (ኢሳይያስ 21:2ሀ NW) በእርግጥም ደግሞ ባቢሎን ይሁዳን ጨምሮ ድል አድርጋ የያዘቻቸውን ብሔራት ታጠፋለች እንዲሁም ሸፍጥ ትፈጽምባቸዋለች። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ይበዘብዛሉ፣ ቤተ መቅደስዋን ይዘርፋሉ፣ ሕዝብዋንም በምርኮ ወደ ባቢሎን ያግዛሉ። በዚያም እነዚህ ምስኪን ምርኮኞች ሸፍጥ ይፈጸምባቸዋል፤ በእምነታቸው ይፌዝባቸዋል እንዲሁም ወደ ትውልድ አገራቸው የመመለስ ተስፋቸው ሁሉ ይጨልምባቸዋል።—2 ዜና መዋዕል 36:17-21፤ መዝሙር 137:1-4
6. (ሀ) ይሖዋ መቋጫ የሚያበጅለት ትካዜ የትኛው ነው? (ለ) ባቢሎን ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ በትንቢት የተነገረላቸው ብሔራት የትኞቹ ናቸው? ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
6 በእርግጥም ባቢሎን ከፊቷ አስቸጋሪ ጊዜ እንደሚጠብቃት የሚጠቁመው ይህ “ከባድ ራእይ” ሲያንሳት ነው። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ኤላም ሆይ፣ ውጪ፤ ሜዶን ሆይ፣ ክበቢ፤ ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ።” (ኢሳይያስ 21:2ለ) በዚህች ሸፍጠኛ ግዛት ሲጨቆኑ የነበሩ ሁሉ እፎይ ይላሉ። በመጨረሻ ትካዜያቸው ሁሉ ያበቃል! (መዝሙር 79:11, 12) ይህን እፎይታ የሚያገኙት እንዴት ነው? ኢሳይያስ በባቢሎን ላይ ጥቃት የሚከፍቱትን ሁለት ብሔራት ስም ጠቅሷል። እነርሱም ኤላምና ሜዶን ናቸው። ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ ማለትም በ539 ከዘአበ የፋርሱ ቂሮስ የፋርስንና የሜዶንን ጥምር ኃይል በመምራት በባቢሎን ላይ ይዘምታል። ከ539 ከዘአበ ትንሽ ቀደም ብሎ የፋርስ ንጉሠ ነገሥታት የኤላምን ግዛት ቢያንስ በከፊል በቁጥጥራቸው ሥር ስለሚያስገቡት የፋርስ ሠራዊት ኤላማውያንንም የሚጨምር ይሆናል።a
-
-
‘ባቢሎን ወደቀች!’የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
-
-
a የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ “የአንሻን ንጉሥ” እየተባለ የሚጠራበት ጊዜ ነበር። አንሻን ደግሞ በኤላም ውስጥ የምትገኝ አውራጃ ወይም ከተማ ነበረች። በኢሳይያስ ዘመን ማለትም በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበሩት እስራኤላውያን ኤላምን ሊያውቋት ቢችሉም ፋርስን ላያውቋት ይችላሉ። ይህም ኢሳይያስ ፋርስ ከማለት ይልቅ ኤላም የሚለውን ስም ለመጠቀም የመረጠበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለን ይሆናል።
-