የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • አባትና ዓመፀኛ ልጆቹ
    የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
    • 11, 12. (ሀ) ይሁዳ የነበረችበትን አስከፊ ሁኔታ ግለጽ። (ለ) ለይሁዳ ልናዝንላት የማይገባው ለምንድን ነው?

      11 ቀጥሎ ኢሳይያስ የይሁዳ ሰዎች የነበሩበትን ሕመም በመጠቆም ለማስረዳት ሞክሯል። እንዲህ አለ:- “ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሠፋላችሁ?” በሌላ አባባል ኢሳይያስ ‘እስካሁን የተሰቃያችሁት አይበቃምን? በዓመፃችሁ በመቀጠል በራሳችሁ ላይ ለምን ተጨማሪ ጉዳት ታስከትላላችሁ?’ በማለት እየጠየቃቸው ነበር። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኖአል። ከእግር ጫማ አንሥቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም።” (ኢሳይያስ 1:​5, 6ሀ) ይሁዳ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ ታምማ ነበር። በመንፈሳዊ ሁኔታ ከራስ ፀጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ በደዌ ተመትታለች። እንዴት አስከፊ ውጤት ነው!

      12 ለይሁዳ ልናዝንላት ይገባልን? በፍጹም! ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት መላው የእስራኤል ብሔር አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ቅጣት በተመለከተ ተገቢውን ማስጠንቀቂያ አግኝቶ ነበር። ማስጠንቀቂያው በከፊል እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በክፉ ቁስል ጉልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል።” (ዘዳግም 28:​35) በምሳሌያዊ ሁኔታ ይሁዳ እየደረሰባት ያለው ስቃይ የተከተለችው የማናለብኝነት ጎዳና ውጤት ነው። የይሁዳ ሰዎች ይሖዋን ታዝዘው ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ባልደረሰባቸው ነበር።

      13, 14. (ሀ) ይሁዳ ምን ዓይነት ጉዳት ደርሶባታል? (ለ) ይሁዳ የደረሰባት ጉዳት የዓመፀኝነት ጎዳናዋን መለስ ብላ እንድትመለከት አድርጓታልን?

      13 ኢሳይያስ፣ ይሁዳ ስላለችበት አሳዛኝ ሁኔታ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ቁስልና እበጥ የሚመግልም [“የተተለተለ፣” NW ] ነው፤ አልፈረጠም፣ አልተጠገነም፣ በዘይትም አልለዘበም።” (ኢሳይያስ 1:​6ለ) እዚህ ላይ ነቢዩ ስለ ሦስት ዓይነት ጉዳት ተናግሯል:- ቁስል (እንደ ሰይፍ ወይም ቢላዋ ባለ ስለት የተቆረጠ)፣ እበጥ (በድብደባ ምክንያት የተቆጣ ሰውነት)፣ የተተለተለ (የሚድንም የማይመስል አፉን የከፈተ ትኩስ ቁስል) ናቸው። እዚህ ላይ የተሰጠው መግለጫ የቅጣት ዓይነት የተፈራረቀበትንና ምንም ሰውነት ያልተረፈውን ሰው የሚያመለክት ነው። በእርግጥም ይሁዳ የነበረችበት ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነው።

      14 ይሁዳ የነበረችበት አሳዛኝ ሁኔታ ወደ ይሖዋ እንድትመለስ አነሳስቷታልን? በፍጹም! ይሁዳ በ⁠ምሳሌ 29:​1 ላይ እንደተገለጸው ዓመፀኛ ሆና ነበር:- “ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፣ ፈውስም የለውም።” ብሔሩ ፈውስ የማይገኝለት ሆኖ ነበር። ኢሳይያስ እንደገለጸው ቁስሏ “አልፈረጠም፣ አልተጠገነም፣ በዘይትም አልለዘበም።”b ይሁዳ ገና አፉን ከከፈተና ካልታሸገ መላ አካልን ከሚያዳርስ ቁስል ጋር የተመሳሰለች ያህል ነው።

      15. ራሳችንን ከመንፈሳዊ ሕመም መጠበቅ የምንችለው በምን መንገዶች ነው?

      15 በይሁዳ ላይ ከደረሰው ነገር በመማር ራሳችንን ከመንፈሳዊ በሽታ መጠበቅ ይኖርብናል። እንደ አካላዊው ሕመም ሁሉ ይህም ቢሆን ማንኛችንንም ሊያጠቃ ይችላል። ደግሞስ በሥጋ ምኞት የማይፈተን ማን አለ? ስግብግብነትና ከልክ ያለፈ የተድላ ምኞት በልባችን ውስጥ ሥር ሊሰዱ ይችላሉ። በመሆኑም ራሳችንን ‘ክፋትን መጸየፍን’ እና ‘ከመልካም ነገር ጋር መተባበርን’ ማስለመድ ይኖርብናል። (ሮሜ 12:​9) በተጨማሪም በዕለታዊ ሕይወታችን የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ማፍራት ይኖርብናል። (ገላትያ 5:​22, 23) ይህንን በማድረግ ከራስ ጠጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ በመንፈሳዊ በሽታ የተመታችው ይሁዳ ከገጠማት ዓይነት ሁኔታ እንጠበቃለን።

  • አባትና ዓመፀኛ ልጆቹ
    የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን ጥራዝ 1
    • b ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት በዘመኑ የነበረውን የሕክምና ልማድ የሚያንጸባርቁ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪ የሆኑት ኢ ኤች ፕላመትረ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “መግል የያዘውን ቁስል ‘ማሰር’ ወይም ‘ማፍረጥ’ ፈሳሹን ለማውጣት የሚደረግ የመጀመሪያ እርምጃ ነው፤ ከዚያም በሕዝቅያስ ሁኔታ እንደታየው (ምዕ. xxxviii. 21) መድኃኒት የሚሆን ነገር ተደርጎበት ‘ይጠገናል።’ ከዚያም ምናልባት በሉቃስ x. 34 ላይ እንዳለው ቁስሉን ለማጽዳት ሲባል እንደ ዘይት ያሉ ወይም ቁስሉን የሚመዘምዙ ሌሎች ፈሳሾች ይደረጉበታል።”

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ