የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሚያዝያ 2017
ከሚያዝያ 3-9
it-2-E 776 አን. 4
ንስሐ
አንድ ሸክላ ሠሪ አንድ ዓይነት ዕቃ በመሥራት ላይ ሳለ ዕቃው ‘እጁ ላይ ቢበላሽበት’ ሐሳቡን ቀይሮ ሌላ ዕቃ ሊሠራ ይችላል። (ኤር 18:3, 4) ይሖዋ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው ልክ እንደ ሰብዓዊ ሸክላ ሠሪ ጭቃው ‘በእጁ ውስጥ እንደሚበላሽበት’ ለማመልከት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በሰው ልጆች ላይ መለኮታዊ ሥልጣን እንዳለው ይኸውም እነሱ ለጽድቁና ለምሕረቱ ምላሽ የሚሰጡበትን ሁኔታ መሠረት በማድረግ እነሱን የሚይዝበትን መንገድ የመቀያየር ሥልጣን እንዳለው ለማመልከት ነው። (ኢሳ 45:9፤ ሮም 9:19-21) በመሆኑም ይሖዋ፣ ብሔሩ በሚሰጠው ምላሽ ላይ ተመሥርቶ ‘ሊያመጣው ያሰበውን ጥፋት ሊተው’ አሊያም ለብሔሩ ‘አደርገዋለሁ ብሎ ያሰበውን መልካም ነገር ሊተው’ ይችላል። (ኤር 18:5-10) ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ አይሳሳትም። ‘በጭቃ’ የተመሰለው ግለሰብ የልብ ሁኔታ ግን ከአባጨጓሬነት ወደ ቢራቢሮነት የመለወጥን ያህል ከፍተኛ የቅርጽ ወይም የባሕርይ ለውጥ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህም ይሖዋ እንዲጸጸት ወይም ሐሳቡን እንዲለውጥ ሊያደርገው ይችላል።
ከሚያዝያ 17-23
jr-E 21 አን. 13
“በመጨረሻዎቹ ቀናት” ይሖዋን ማገልገል
13 በይሁዳ ከነበረው ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ አንጻር የሃይማኖት መሪዎቹ ለኤርምያስ መልእክት ምን ምላሽ ይሰጡ ይሆን? ነቢዩ ራሱ ስለተከናወነው ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ካህናቱ፣ ነቢያቱና ሕዝቡ ሁሉ ይዘው እንዲህ [አሉኝ]፦ ‘አንተ በእርግጥ ትሞታለህ።’” በተጨማሪም በጣም ተበሳጭተው “ይህ ሰው በሞት ሊቀጣ ይገባዋል” በማለት ተናገሩ። (ኤርምያስ 26:8-11ን አንብብ።) ይሁንና የኤርምያስ ጠላቶች አልተሳካላቸውም። ይሖዋ ከኤርምያስ ጎን በመሆን ከጠላቶቹ እጅ ታድጎታል። ኤርምያስም ቢሆን በጠላቶቹ ዛቻም ሆነ ብዛት አልተርበደበደም። አንተም ፍርሃት እንዲያሸንፍህ መፍቀድ አይኖርብህም።
jr-E 27 አን. 21
“በመጨረሻዎቹ ቀናት” ይሖዋን ማገልገል
21 ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው በሴዴቅያስ የግዛት ዘመን መጀመሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም ከኤዶም፣ ከሞዓብ፣ ከአሞን፣ ከጢሮስና ከሲዶና የተላኩ መልእክተኞች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ነበር። ዓላማቸው ሴዴቅያስ ከእነሱ ጋር ግንባር ፈጥሮ ናቡከደነጾርን እንዲወጋ ማድረግ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ኤርምያስ፣ ሴዴቅያስ ለባቢሎን እጁን እንዲሰጥ ነግሮት ነበር። በተጨማሪም ኤርምያስ ለመልእክተኞቹ ቀንበር ሠርቶ በመስጠት የእነሱ ሕዝቦችም ቢሆኑ ባቢሎናውያንን ማገልገል እንዳለባቸው በምሳሌያዊ መንገድ አሳይቷቸዋል። (ኤር. 27:1-3, 14) ኤርምያስ የተናገረው መልእክት በብዙዎች ዘንድ እንዲጠላ አድርጎታል፤ በኤርምያስ አቋም በእጅጉ ከተበሳጩ ሰዎች መካከል አንዱ ሃናንያህ ነበር። ይህ የሐሰት ነቢይ የባቢሎን ቀንበር እንደሚሰበር በሕዝቡ ሁሉ ፊት በአምላክ ስም ተናግሮ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ይህ አስመሳይ ነቢይ በዚያው ዓመት እንደሚሞት በኤርምያስ በኩል ተናግሯል። ሃናንያህ ልክ ኤርምያስ እንደተናገረው በዚያው ዓመት ሞተ።—ኤር. 28:1-3, 16, 17
jr-E 187-188 አን. 11-12
“ዝም ማለት አልችልም”
11 ኤርምያስ መልእክቱን በሚያውጅበት ጊዜ ከሰዎች ጋር አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ አይገባም ነበር። ሁኔታዎች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሲሄዱ ከአካባቢው ዞር በማለት ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ወስዷል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሃናንያህ ጋር ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ይህ ሐሰተኛ ነቢይ ይሖዋ በትንቢት ያስነገረውን ቃል በሕዝቡ ፊት በተቃወመ ጊዜ ኤርምያስ ያረመው ከመሆኑም ሌላ አንድ እውነተኛ ነቢይ ተለይቶ የሚታወቀው እንዴት እንደሆነ ተናግሯል። ኤርምያስ ሕዝቡ በባቢሎን ቀንበር ሥር እንደሚወድቅ ለማሳየት የእንጨት ቀንበር አንገቱ ላይ አድርጎ ነበር፤ ሃናንያህ ኤርምያስ በተናገረው ነገር በጣም ተበሳጭቶ ቀንበሩን ሰበረው። ሃናንያህ ከዚህ በኋላስ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማን ያውቃል? ኤርምያስ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን? ዘገባው “ነቢዩ ኤርምያስም ትቶት ሄደ” በማለት ይናገራል። ኤርምያስ አካባቢውን ለቆ ሄዷል። ከጊዜ በኋላም ኤርምያስ፣ ይሖዋ ባዘዘው መሠረት ተመልሶ በመምጣት አይሁዳውያኑ በባቢሎን ንጉሥ ቀንበር ሥር እንደሚወድቁና ሃናንያም እንደሚሞት በመናገር አምላክ ምን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።—ኤር. 28:1-17
12 በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው ከዚህ ዘገባ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ምሥራቹን ስንሰብክ ደፋር መሆን ቢኖርብንም አስተዋይ መሆን ያስፈልገናል። የምናነጋግረው ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናሳየውን ማስረጃ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆን ከተበሳጨ አልፎ ተርፎም የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ከተነሳሳ በትሕትና ቤቱን ለቀን በመሄድ ሌላ ቤት ማንኳኳት እንችላለን። ስለ መንግሥቱ ምሥራች ከማንም ሰው ጋር አላስፈላጊ ንትርክ ውስጥ መግባት አያስፈልግም። ‘በደል ሲደርስብን ራሳችንን የምንገዛ’ ከሆነ የቤቱ ባለቤት በሌላ አጋጣሚ መልእክቱን ለመስማት ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል።—2 ጢሞቴዎስ 2:23-25ን አንብብ፤ ምሳሌ 17:14
ከሚያዝያ 24-30
it-1-E 524 አን. 3-4
ቃል ኪዳን
አዲሱ ቃል ኪዳን። ይሖዋ በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚያቋቁም የተነበየ ሲሆን ይህ ቃል ኪዳን እስራኤላውያን ካፈረሱት የሕጉ ቃል ኪዳን የተለየ እንደሚሆን ገልጿል። (ኤር 31:31-34) ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ማለትም ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ላይ የጌታ ራት በዓልን ሲያቋቁም እሱ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካኝነት የሚጸድቅ አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚቋቋም አስታውቋል። (ሉቃስ 22:20) ከሞት በተነሳ በ50ኛው ቀን ማለትም ወደ አባቱ ካረገ ከ10 ቀን በኋላ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ሰገነት ላይ ተሰብስበው በነበሩት ደቀ መዛሙርቱ ላይ ከይሖዋ የተቀበለውን መንፈስ ቅዱስ አፈሰሰ።—ሥራ 2:1-4, 17, 33፤ 2ቆሮ 3:6, 8, 9፤ ዕብ 2:3, 4
ቃል ኪዳኑን የተጋቡት ይሖዋና ‘የአምላክ እስራኤል’ ማለትም የክርስቶስ ጉባኤ ወይም አካል የሆኑትና ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ናቸው። (ዕብ 8:10፤ 12:22-24፤ ገላ 6:15, 16፤ 3:26-28፤ ሮም 2:28, 29) አዲሱ ቃል ኪዳን የጸናው በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም (መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው ሰብዓዊ ሕይወቱ) አማካኝነት ነው፤ የመሥዋዕቱ ዋጋ ለይሖዋ የቀረበው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ነው። (ማቴ 26:28) አምላክ አንድን ሰው ለሰማያዊ ጥሪ በሚመርጥበት ጊዜ (ዕብ 3:1) በክርስቶስ መሥዋዕት አማካኝነት በቃል ኪዳኑ እንዲታቀፍ ያደርገዋል። (መዝ 50:5፤ ዕብ 9:14, 15, 26) ኢየሱስ ክርስቶስ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ (ዕብ 8:6፤ 9:15) ከመሆኑም ሌላ የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል ነው። (ገላ 3:16) ኢየሱስ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኖ በሚያከናውነው አገልግሎት አማካኝነት በቃል ኪዳኑ ውስጥ የታቀፉት ሰዎች የኃጢአት ይቅርታ በማግኘት በእርግጥም የአብርሃም ዘር ክፍል መሆን እንዲችሉ ይረዳቸዋል። (ዕብ 2:16፤ ገላ 3:29) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ጻድቃን ይላቸዋል።—ሮም 5:1, 2፤ 8:33፤ ዕብ 10:16, 17
jr-E 173-174 አን. 11-12
ከአዲሱ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ መሆን ትችላለህ
11 አዲሱ ቃል ኪዳን ያሉትን ተጨማሪ ጉልህ ገጽታዎች ማወቅ ትፈልጋለህ? በአዲሱ ቃል ኪዳንና በሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት የተጻፉበት ነገር ነው። (ኤርምያስ 31:33ን አንብብ።) በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ያሉት አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉት በድንጋይ ጽላቶች ላይ ሲሆን እነዚህ ጽላቶች ደግሞ ከጊዜ በኋላ ጠፍተዋል። ከዚህ በተቃራኒ የአዲሱ ቃል ኪዳን ሕግ በሰዎች ልብ ላይ እንደሚጻፍና ይህ ሕግ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ኤርምያስ ትንቢት ተናግሯል። በአዲሱ ቃል ኪዳን የታቀፉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለዚህ ሕግ ከፍተኛ አድናቆት አላቸው። ይሁንና በቀጥታ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ስላልታቀፉትና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ስላላቸው “ሌሎች በጎች” ምን ማለት ይቻላል? (ዮሐ. 10:16) እነሱም ቢሆኑ በአምላክ ሕግ ደስ ይላቸዋል። የሌሎች በጎች ሁኔታ የሙሴን ሕግ ከተቀበሉትና ከዚህ ሕግ ጥቅም ካገኙት በእስራኤል ይኖሩ የነበሩ የባዕድ አገር ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል።—ዘሌ. 24:22፤ ዘኁ. 15:15
12 ‘በቅቡዓን ክርስቲያኖች ልብ ላይ የተጻፈው ሕግ ምንድን ነው?’ ተብለህ ብትጠየቅ ምን መልስ ትሰጣለህ? ይህ ሕግ ‘የክርስቶስ ሕግ’ ተብሎም ተጠርቷል። መጀመሪያ ላይ ይህ ሕግ የተሰጠው በአዲሱ ቃል ኪዳን ለታቀፉት መንፈሳዊ እስራኤላውያን ነበር። (ገላ. 6:2፤ ሮም 2:28, 29) “የክርስቶስን ሕግ” በአንድ ቃል እንግለጸው ከተባለ ፍቅር በሚለው ቃል ሊገለጽ ይችላል። (ማቴ. 22:36-39) ይህ ሕግ በቅቡዓኑ ልብ ላይ የሚጻፈው እንዴት ነው? ቅቡዓኑ በዋነኝነት ይህ ሕግ በልባቸው ላይ እንዲጻፍ የሚያደርጉት የአምላክን ቃል በማጥናትና ወደ ይሖዋ በመጸለይ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በአዲሱ ቃል ኪዳን ያልታቀፉ ክርስቲያኖችም ጭምር ከዚህ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ መሆን እስከፈለጉ ድረስ እነዚህን የእውነተኛ አምልኮ ገጽታዎች ቋሚ የሕይወታቸው ክፍል ሊያደርጓቸው ይገባል።
jr-E 177 አን. 18
ከአዲሱ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ መሆን ትችላለህ
18 አዲሱ ቃል ኪዳን ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆችን ይኸውም በቃል ኪዳኑ የታቀፉትን ቅቡዓንንም ሆነ በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች የሚይዝበትን አስገራሚ መንገድ ጎላ አድርጎ ያሳያል። ይሖዋ ኃጢአታችንን አንዴ ይቅር ካለ በኋላ ዳግመኛ እንደማያነሳው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ አዲሱን ቃል ኪዳን እንደሚያቋቁም ከገባው ቃል እያንዳንዳችን ግሩም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የበደሉኝን ሰዎች ይቅር እንዳልኳቸው ከተናገርኩ በኋላ በደላቸውን ዳግመኛ ባለማንሳት ይሖዋን ለመምሰል ጥረት አደርጋለሁ?’ (ማቴ. 6:14, 15) ይህ ትምህርት ቀላል ከሆኑ በደሎችም ሆነ እንደ ምንዝር ካሉ ከባድ በደሎች ጋር በተያያዘ ይሠራል። ተበዳዩ ወገን ምንዝር የፈጸመውን ግለሰብ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ‘ኃጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስታውስም’ ያለውን የይሖዋን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረጉ ተገቢ አይሆንም? እርግጥ ነው፣ የተፈጸመብንን በደል መርሳት ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ይህ ይሖዋን መምሰል የምንችልበት አንዱ መንገድ ነው።