ሌሎችን ቀድሞ የሚነሣው
በሜድትራንያን አካባቢ ከሚገኙት በጣም የሚማርኩ የፍራፍሬ ዛፎች መካከል የለውዝ ዛፍ አንዱ ነው። በጥር ወይም በየካቲት ማለቂያ ላይ ከአብዛኞቹ ሌሎች ዛፎች ቀደም ብሎ በበረዶ ወቅት ከነበረው የእንቅልፍ ሁኔታ ይነሳል። ያውም እንዴት ያለ አነሳስ ነው! ዛፉ ሙሉውን ሮዝ ወይም ነጭ የሚያምር የአበባ ካባ ይለብሳል። አበቦቹ ነጭ ሲሆኑ ልክ የአዛውንቶችን ሽበት ይመስላል። — ከመክብብ 12:5 ጋር አወዳድር።
የጥንቶቹ ዕብራውያን ከሌሎቹ ዛፎች ቀድሞ ማበቡን ለማመልከት የለውዝን ዛፍ “አንቂው ዛፍ” ብለው ይጠሩት ነበር። ይሖዋ በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድን መልዕክት በምሳሌ ለመጥቀስ ሲል ይህን የዛፉን ባሕርይ ተጠቅሞበታል። ኤርምያስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ በራእይ ለጋ የሆነ የለውዝ ተክል እንዲያይ ተደርጎ ነበር። ምን ማለቱ ነበር? ይሖዋ “እኔም እንዲሁ ቃሌ እንዴት እንደሚፈጸም በንቃት እመለከታለሁ” ሲል አብራርቶታል። — ኤርምያስ 1:12 የ1980 ትርጉም
ልክ የለውዝ ዛፍ አስቀድሞ ‘እንደሚያብብ’ ሁሉ አለመታዘዝ ስለሚያስከትለው ሁኔታ ነብያቶቹ ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቁ ለመላክ ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘በማለዳ ይነሳ’ ነበር። (ኤርምያስ 7:25) ትንቢታዊ ቃሉ እስኪፈጸም ድረስም ‘ነቅቶ ይቆያል’ እንጂ አያርፍም። ስለዚህ በተቀጠረው ጊዜ ማለትም በ607 ከዘአበ የይሖዋ ፍርድ በከሃዲዋ የይሁዳ ሕዝብ ላይ መጣ።
ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፍርድ በዚህ እኛ በምንኖርበት ክፉ ሥርዓት ላይ እንደሚመጣ የአምላክ ቃል አስቀድሞ ተናግሯል። (መዝሙር 37:9, 10፤ 2 ጴጥሮስ 3:10–13) ይህን ዓይነቱን የፍርድ እርምጃ በማመልከት ነቢዩ ዕንባቆም እንዲህ በማለት ያረጋግጥልናል:- “ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፣ . . . በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።” (ዕንባቆም 2:3) ውብ የሆነው የለውዝ አበባ ይሖዋ የቃሉን መፈጸም በሚመለከት ንቁ ሆኖ እንደሚጠብቅ ያስታውሰናል።
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.