በወጣትነት ቀንበር መሸከም
በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ ወጣቶች ከባድ ተጽዕኖዎች ይደርሱባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በየቀኑ የጾታ ብልግናን፣ ሲጋራ ማጨስንና ሌሎች መጥፎ ባሕርያትን ለሚያበረታታ የፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝ ይጋለጣሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚከተሉ ሰዎች ብዙሐኑን ለመከተል ስለማይፈልጉ ማፌዣ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በዚህ ምክንያት አንዳንድ ክርስቲያኖች ሌሎችን መስሎ መኖር እንደሚሻል ይሰማቸው ይሆናል።
በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጨረሻ ገደማ ኤርምያስ “ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው” ሲል ጽፏል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:27) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? አንድ ሰው በወጣትነቱ ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደሚችል መማሩ በጉልምስና ዕድሜው የሚያጋጥሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ ዝግጁ እንዲሆን ይረዳዋል። ምንም እንኳ አስደሳች ባይሆንም በክርስቲያን ወጣቶችም ሆነ በጎልማሶች ላይ መከራ መድረሱ የማይቀር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ይሁን እንጂ ታማኝነት የሚያስገኘው ጥቅም አቋምን ማላላት ሊያመጣ ከሚችለው ከማናቸውም ጊዜያዊ እፎይታ በጣም የላቀ ነው።
ወጣት ከሆንክ የሚያጋጥሙህን የእምነት ፈተናዎች አላንዳች ማወላወል ተጋፈጣቸው። መጥፎ ጠባይ እንድታሳይ ስትፈተን ከአቋምህ ፍንክች አትበል። በዚያን ጊዜ ይህን ማድረግ ሊያስቸግርህ ቢችልም በቀሪው ሕይወትህ የሚያጋጥሙህ ጭንቀቶች ይቀንሳሉ። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ . . . ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”— ማቴዎስ 11:29, 30
ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖር የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ ተቀበል። ይህን ማድረግህ በአሁኑ ጊዜ የተሻለ የሕይወት ጎዳና፣ ወደፊት ደግሞ እርግጠኛ ተስፋ እንድትጨብጥ ያስችልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”— 1 ዮሐንስ 2:17