የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 36—ሶፎንያስ
ጸሐፊው:- ሶፎንያስ
የተጻፈበት ቦታ:- ይሁዳ
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት ከ648 ቀደም ብሎ
የይሁዳ ንጉሥ በነበረው በኢዮስያስ የግዛት ዘመን (659-629 ከክርስቶስ ልደት በፊት) መጀመሪያ አካባቢ የበኣል አምልኮ ከመስፋፋቱም በላይ ‘የጣዖታቱ ካህናት’ በዚህ ርኩስ አምልኮ ውስጥ ዋና ተዋናይ ነበሩ፤ እንዲህ ባለው ወቅት ነቢዩ ሶፎንያስ ያወጃቸው መልእክቶች የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች በጣም አስደንግጠዋቸው መሆን አለበት። ሶፎንያስ፣ ከይሁዳ ንጉሣዊ ቤተሰብ የተወለደው የንጉሥ ሕዝቅያስ ዝርያ ቢሆንም በብሔሩ ውስጥ የሚታየውን ሁኔታ ክፉኛ ተቃውሟል። (ሶፎ. 1:1, 4 የ1954 ትርጉም) መልእክቱ ጥፋት እንደሚመጣ የሚገልጽ ነበር። የአምላክ ሕዝቦች እርሱን ለመታዘዝ አሻፈረን ብለዋል፤ ሕዝቡ “በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና” መሆን እንዲችሉ ወደ ንጹሕ አምልኮ ሊመልሳቸውና ሊባርካቸው የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነበር። (3:20 የ1954 ትርጉም) ሶፎንያስ፣ አንድ ሰው ‘በይሖዋ የቁጣ ቀን ሊሰወር’ የሚችለው እርሱ ጥበቃ ካደረገለት ብቻ እንደሆነ አመልክቷል። (2:3) ጼፋንያህ (በዕብራይስጥ) የተባለው የዚህ ነቢይ ስም “ይሖዋ ሸሸገ (ተንከባከበ)” የሚል ትርጉም ያለው መሆኑ ተስማሚ ነው!
2 የሶፎንያስ ጥረት ፍሬ አስገኝቷል። በስምንት ዓመቱ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ንጉሥ ኢዮስያስ በ12ኛው የንግሥና ዘመኑ ‘ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ማንፃት’ ጀመረ። ይህ ንጉሥ የሐሰት አምልኮን ከሥረ መሠረቱ ካስወገደ በኋላ “የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ” በመጠገን የማለፍ በዓል እንደገና መከበር እንዲጀምር አደረገ። (2 ዜና ምዕ. 34, 35) ይሁን እንጂ ከንጉሥ ኢዮስያስ በኋላ የነገሡት ሦስት ወንዶች ልጆቹና የልጅ ልጁ “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት” በመፈጸማቸው ኢዮስያስ ያካሄደው ተሃድሶ ዘላቂ ሊሆን አልቻለም። (2 ዜና 36:1-12) ይህ ሁኔታ ሶፎንያስ፣ “መሳፍንቱንና የንጉሡን ልጆች . . . የአማልክቶቻቸውን ቤት፣ በዐመፅና በማጭበርበር የሚሞሉትን እቀጣለሁ” በማለት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።—ሶፎ. 1:8, 9
3 ከላይ ከተመለከትነው ሁኔታ አንጻር፣ ‘የይሖዋ ቃል ወደ ሶፎንያስ የመጣው’ ከኢዮስያስ 12ኛ የንግሥና ዘመን ማለትም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ648 ቀደም ብሎ ይመስላል። የመጽሐፉ የመጀመሪያ ቁጥር ሶፎንያስ ትንቢቱን የተናገረው በይሁዳ እንደሆነ የሚጠቁም ሲሆን ይህ ነቢይ የኢየሩሳሌምን አካባቢና ባሕል ጠንቅቆ ማወቁ በይሁዳ ይኖር እንደነበረ ያሳያል። መጽሐፉ የሚያስፈራ እና የሚያጽናና መልእክት ይዟል። አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል መምጣቱ በማይቀረውና አስፈሪ በሆነው የይሖዋ ቀን ላይ ያተኮረ ቢሆንም “በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም የሚታመኑትን” ትሑት ሰዎች ይሖዋ መልሶ እንደሚያቋቁማቸውም ይተነብያል።—1:1, 7-18፤ 3:12
4 ይህ የትንቢት መጽሐፍ ትክክለኛ መሆኑ ፈጽሞ አጠያያቂ ሊሆን አይችልም። ሶፎንያስ ትንቢቱን ከተናገረ ከ40 ዓመታት በኋላ ማለትም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም ጠፍታለች። ለዚህ ማስረጃ የሚሆኑን ዓለማዊ ታሪኮች ብቻ አይደሉም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ሁኔታው ልክ ሶፎንያስ እንደተነበየው በትክክል መፈጸሙን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዟል። ኢየሩሳሌም ከወደመች ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኤርምያስ የተመለከተውን ሰቆቃ ሁኔታው ገና ከአእምሮው ሳይጠፋ በሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ ላይ አስፍሮታል። በርካታ ጥቅሶችን ስናነጻጽር የሶፎንያስ መልእክት በእርግጥም ‘የአምላክ መንፈስ ያለበት’ መሆኑን መመልከት እንችላለን። ሶፎንያስ ‘የይሖዋ ጽኑ ቁጣ በእነርሱ ላይ ሳይመጣ’ ንስሐ የመግባትን አስፈላጊነት ለሕዝቡ አስቀድሞ ሲያስገነዝብ ኤርምያስ ደግሞ “እግዚአብሔር . . . ጽኑ ቁጣውን አፈሰሰ” በማለት ስለተፈጸመው ነገር ይገልጻል። (ሶፎ. 2:2፤ ሰቆ. 4:11) ይሖዋ “እንደ ዕውር እንዲራመዱ፣ በሰዎች ላይ ጭንቀት አመጣባቸዋለሁ፤ . . . ደማቸው እንደ ትቢያ . . . ይጣላል” ብሎ መናገሩን ሶፎንያስ ተንብዮአል። (ሶፎ. 1:17) ኤርምያስ ደግሞ ይህ ሁኔታ እንደተፈጸመ ሲገልጽ “ታውረው በመንገድ ላይ ተቅበዘበዙ፤ . . . በደም ረክሰዋል” በማለት ተናግሯል።—ሰቆ. 4:14 የ1954 ትርጉም፤ በተጨማሪም ሶፎንያስ 1:13ን ከሰቆቃወ ኤርምያስ 5:2 ጋር፤ ሶፎንያስ 2:8, 10ን ከሰቆቃወ ኤርምያስ 1:9, 16 እና ከ3:61 ጋር አወዳድር።
5 ሶፎንያስ በአምላክ አነሳሽነት በተናገረው ትንቢት መሠረት አረማዊ የነበሩት ሞዓብና አሞን እንዲሁም አሦር (ዋና ከተማዋን ነነዌን ጨምሮ) መጥፋታቸውን ታሪክም ይዘግባል። ነቢዩ ናሆም ነነዌ እንደምትጠፋ እንደተነበየ ሁሉ (ናሆም 1:1፤ 2:10) ሶፎንያስም ይሖዋ “ነነዌንም ፍጹም ባድማ፣ እንደ ምድረ በዳም ደረቅ ያደርጋታል” በማለት አውጆአል። (ሶፎ. 2:13) ይህቺ ከተማ ሙሉ በሙሉ ስለወደመች ወደ 200 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ታሪክ ጸሐፊው ሄሮዶተስ ስለ ጤግሮስ ሲጽፍ “ከዚህ ቀደም የነነዌ ከተማ በነበረችበት ቦታ ላይ የሚያልፍ ወንዝ” ብሏል።a በ150 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ደግሞ ግሪካዊው ጸሐፊ ሉቺያን፣ “በአሁኑ ጊዜ የሚታይ ምንም ነገር የለም” በማለት ጽፏል።b ዘ ኒው ዌስትሚንስተር ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል (1970) ገጽ 669 ላይ እንደተገለጸው “የጤግሮስ ወንዝ በድንገት ሞልቶ የከተማዋን ቅጥር አብዛኛውን ክፍል ጠርጎ በመውሰድ ከተማዋን ያለ መከላከያ እንድትቀር በማድረጉ” ወራሪው ሠራዊት በጣም ተጠቅሟል። “ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በመደምሰሷ ምክንያት በግሪክና በሮም ዘመን ነነዌ በአፈ ታሪክ ብቻ የምትታወቅ ሆና ነበር። ቢሆንም የከተማዋ የተወሰነ ክፍል በቆሻሻ ክምር ሥር ተቀብሮ ነበር።” ይኸው ጥራዝ በገጽ 627 ላይ “ናቡከደነፆር ሞዓባውያንን ድል አድርጎ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር አዋላቸው” የሚል ሐሳብ መያዙ በትንቢት እንደተነገረው ሞዓብም መውደሟን ያሳያል። ጆሴፈስ አሞንም ድል መደረጓን ዘግቧል።c ውሎ አድሮ ሞዓባውያንም ሆኑ አሞናውያን ከምድር ገጽ ጠፍተዋል።
6 አይሁዳውያን የሶፎንያስን መጽሐፍ ሁልጊዜም ቢሆን በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል እንዲገኝ በማድረግ በትክክለኛ ቦታው አስቀምጠውታል። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት በይሖዋ ስም የተነገሩ አዋጆች ለይሖዋ ቅድስና በሚያመጣ መንገድ በትክክል ተፈጽመዋል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
10 ንጉሥ ኢዮስያስ የሶፎንያስን የማስጠንቀቂያ መልእክት ሰምቶ እርምጃ በመውሰዱ በእጅጉ ተጠቅሟል።። ይህ ንጉሥ ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ለማምጣት ትልቅ ዘመቻ አካሂዷል። እንዲህ ማድረጉ ደግሞ የይሖዋ ቤት ሳይታደስ በቆየባቸው ዓመታት ጠፍቶ የነበረው የሕጉ መጽሐፍ እንዲገኝ መንገድ ጠርጓል። ኢዮስያስ አለመታዘዝ ምን እንደሚያስከትል ከዚህ መጽሐፍ ሲነበብለት በጣም አዘነ፤ በሕጉ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረው ሙሴ የተናገረው ማስጠንቀቂያ፣ ሶፎንያስ ለረጅም ጊዜ ሲናገር የነበረው ትንቢት እንደሚፈጸም የሚያረጋግጥ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢዮስያስ በይሖዋ ፊት ራሱን አዋረደ፤ እንዲህ በማድረጉም በትንቢት የተነገረው ጥፋት በእርሱ የሕይወት ዘመን እንደማይመጣ ይሖዋ ቃል ገባለት። (ዘዳ. ምዕ. 28-30፤ 2 ነገ. 22:8-20) ምድሪቱም ሊመጣባት ከነበረው መዓት ተረፈች! ይሁን እንጂ የኢዮስያስ ልጆች እርሱ የተወውን ጥሩ ምሳሌ ባለመከተላቸው ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። ያም ቢሆን ግን ኢዮስያስና ሕዝቦቹ ‘ወደ ሶፎንያስ ለመጣው የይሖዋ ቃል’ ትኩረት በመስጠታቸው ከፍተኛ ጥቅም አግኝተዋል።—ሶፎ. 1:1
11 ከሁሉ የላቀው የአምላክ ነቢይ ክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ በሶፎንያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 3 ላይ ከሚገኘው “እናንት የምድር ትሑታን ሁሉ፣ . . . እግዚአብሔርን እሹ፤ ጽድቅንና ትሕትናን ፈልጉ” ከሚለው ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ትምህርት በመስጠት ሶፎንያስ እውነተኛ የአምላክ ነቢይ መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስ የሰጠው ምክር “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ” ይላል። (ማቴ. 6:33) ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥት የሚፈልጉ ሁሉ ሶፎንያስ ‘ይሖዋን ከመከተል ወደ ኋላ የሚመለሱ፣ ይሖዋን የማይፈልጉ፣ እንዲረዳቸውም የማይጠይቁ’ እንዲሁም ‘ክፉም ይሁን መልካም፣ ይሖዋ ምንም አያደርግም የሚሉ’ በማለት የገለጻቸውን ሰዎች ዓይነት የቸልተኝነት ዝንባሌ እንዳያዳብሩ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (ሶፎ. 1:6, 12) በተመሳሳይም ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ወደፊት ስለሚመጣው የፍርድ ቀን በመግለጽ ወደ ኋላ እንዳያፈገፍጉ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በማከልም “እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም” በማለት ተናግሯል። (ዕብ. 10:30, 37-39) ነቢዩ “ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል” ብሎ የተናገረው ወደ ኋላ ለሚሉ ወይም አድናቆት ለሚጎድላቸው ሰዎች ሳይሆን እምነት በማሳየት ይሖዋን በትሕትናና ከልባቸው ለሚፈልጉ ሰዎች ነው። ሶፎንያስ “ምናልባት” ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአንድ ግለሰብ የመጨረሻ መዳን በግለሰቡ አካሄድ ላይ የተመካ በመሆኑ ነው። (ማቴ. 24:13) በተጨማሪም የአምላክን ምሕረት እንደምናገኝ እርግጠኞች በመሆን እንደፈለግነው መኖር እንደማንችል ያስታውሰናል። የሶፎንያስ ትንቢት የአምላክ ቀን ሳይታሰብ በድንገት ከተፍ የሚል መሆኑን በማያሻማ መንገድ ገልጿል።—ሶፎ. 2:3 የ1954 ትርጉም፤ 1:14, 15፤ 3:8
12 በሶፎንያስ መጽሐፍ ውስጥ በይሖዋ ላይ ኃጢአት ለሚሠሩ ሰዎች ጥፋት እንደሚጠብቃቸው የሚገልጽ፣ ንስሐ ገብተው “እግዚአብሔርን ለሚፈልጉ” ግን ብሩሕ ተስፋ የያዘ መልእክት እናገኛለን። እነዚህ ንስሐ የገቡ ሰዎች “የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ከአንቺ ጋር ነው” በሚሉት የሶፎንያስ ቃላት ሊበረታቱ ይችላሉ። ይህ ጊዜ ጽዮን የምትፈራበት ወይም እጆቿ የሚዝሉበት ሳይሆን በይሖዋ የምትተማመንበት ነው። “እርሱ የሚታደግ ኀያል ነው፤ በአንቺ እጅግ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩ ያሳርፍሻል፤ በዝማሬም በአንቺ ሐሤት ያደርጋል።” ከዚህም በላይ የእርሱን ፍቅራዊ ጥበቃና ዘላለማዊ በረከቶች በተስፋ በመጠባበቅ ‘አስቀድመው መንግሥቱን የሚፈልጉ’ ደስተኞች ናቸው!—3:15-17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በ1981 በድጋሚ የታተመው የማክሊንቶክ እና ስትሮንግ ሳይክሎፒድያ ጥራዝ 7, ገጽ 112
b ሉቺያን፣ በ1968 በሃርሞን የተተረጎመ ጥራዝ 2 ገጽ 443
c ጅዊሽ አንቲክዊቲስ፣ X፣ 181, 182 (ix, 7)