-
‘በግንባራቸው ላይ ምልክት አድርግ’የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
-
-
16. ከጥፋት በሚተርፉት ሰዎች ላይ ምልክት የሚያደርጉት የይሖዋ ሕዝቦች ናቸው? አብራራ።
16 ከጥፋት በሚተርፉት ሰዎች ላይ ምልክት የሚያደርጉት የይሖዋ ሕዝቦች አይደሉም። በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ በሚድኑት ላይ ምልክት እንዲያደርግ የታዘዘው ሕዝቅኤል እንዳልሆነ አስታውስ። በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችም ከጥፋት መትረፍ በሚገባቸው ሰዎች ላይ ምልክት የማድረግ ተልእኮ አልተሰጣቸውም። ከዚህ ይልቅ የክርስቶስ ቤተሰቦች እንደመሆናችን መጠን የመስበክ ተልእኮ ተሰጥቶናል። የአምላክን መንግሥት ምሥራች በቅንዓት ለሰዎች በማካፈልና ይህ ክፉ ዓለም ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ መሆኑን በማስጠንቀቅ ይህን ተልእኮ አክብደን እንደምንመለከት እናሳያለን። (ማቴ. 24:14፤ 28:18-20) በዚህ መንገድ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በንጹሕ አምልኮ እንዲካፈሉ በመርዳቱ ሥራ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።—1 ጢሞ. 4:16
17. ሰዎች ወደፊት ከጥፋት ለመትረፍ የሚያስችለው ምልክት እንዲደረግባቸው ከወዲሁ ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?
17 ሰዎች ከመጪው ጥፋት ለመዳን ከወዲሁ እምነት እንዳላቸው ማስመሥከር አለባቸው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በ607 ዓ.ዓ. ከደረሰው የኢየሩሳሌም ጥፋት የተረፉት፣ ለክፋት ያላቸውን ጥላቻና ለንጹሕ አምልኮ ያላቸውን ታማኝነት አስቀድመው ያስመሠከሩ ሰዎች ናቸው። በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሰዎች በሕይወት ለመትረፍ፣ ጥፋቱ ከመምጣቱ በፊት በዓለም ላይ ባለው ክፋት ከልባቸው ‘ማዘንና መቃተት’ አለባቸው። በተጨማሪም ስሜታቸውን በውስጣቸው ብቻ ከመያዝ ይልቅ ለንጹሕ አምልኮ ያላቸውን ታማኝነት በቃልም ሆነ በድርጊት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ እየተከናወነ ለሚገኘው የስብከት ሥራ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት፣ ክርስቶስን በመምሰል፣ ራሳቸውን ለይሖዋ በመወሰንና በመጠመቅ እንዲሁም የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት በመደገፍ ነው። (ሕዝ. 9:4፤ ማቴ. 25:34-40፤ ኤፌ. 4:22-24፤ 1 ጴጥ. 3:21) ከጥፋቱ እንዲተርፉ ምልክት የሚደረግባቸው ከወዲሁ እነዚህን እርምጃዎች የሚወስዱና ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ከንጹሕ አምልኮ ጎን የሚሰለፉ ሰዎች ብቻ ናቸው።
18. (ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ መዳን በሚገባቸው ሰዎች ላይ ምልክት የሚያደርገው መቼና እንዴት ነው? (ለ) ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምልክት ይደረግባቸዋል? አብራራ።
18 ከጥፋት በሚተርፉት ሰዎች ላይ ምልክት የማድረጉ ሥራ የሚከናወነው በመንፈሳዊው ዓለም ነው። በሕዝቅኤል ዘመን መላእክት ከጥፋት በሚድኑት ሰዎች ላይ ምልክት በማድረጉ ሥራ ተካፍለው ነበር። በዘመናችን የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው በሕዝቦች ሁሉ ላይ ለመፍረድ “በክብሩ” የሚመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል። (ማቴ. 25:31-33) ኢየሱስ ፈራጅ ሆኖ የሚመጣው በታላቁ መከራ ወቅት የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ነው።c በዚያ ወሳኝ ወቅት፣ ማለትም ልክ አርማጌዶን ከመጀመሩ በፊት ኢየሱስ ሰዎችን በጎች ወይም ፍየሎች ብሎ በመለየት ፍርድ ይሰጣል። ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ‘በጎች ናችሁ’ ተብለው ይፈረድላቸዋል ወይም ምልክት ይደረግባቸዋል፤ ይህም ‘ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚሄዱ’ ያመለክታል። (ራእይ 7:9-14፤ ማቴ. 25:34-40, 46) ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እነሱ ከአርማጌዶን ለመትረፍ ምልክቱ አያስፈልጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ከመሞታቸው በፊት ወይም ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻው ማኅተም ይደረግባቸዋል። ከዚያም በታላቁ መከራ ወቅት በምድር ላይ የሚኖሩ ቅቡዓን፣ አርማጌዶን ከመጀመሩ በፊት ወደ ሰማይ ይሄዳሉ።—ራእይ 7:1-3
-
-
ማዘንና መቃተት፣ ምልክት ማድረግ፣ ማጥፋት—መቼና እንዴት?የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
-
-
“ምልክት ማድረግ”
መቼ፦ በታላቁ መከራ ወቅት
እንዴት፦ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው በሕዝቦች ሁሉ ላይ ለመፍረድ የሚመጣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይወክላል። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ‘በጎች ናችሁ’ ተብለው ይፈረድላቸዋል ወይም ምልክት ይደረግባቸዋል፤ ይህም ከአርማጌዶን እንደሚተርፉ ያመለክታል
-