-
“ከተማዋ ‘ይሖዋ በዚያ አለ’ ተብላ ትጠራለች”የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ!
-
-
“ከተማዋ በመካከሉ ትሆናለች”
5, 6. (ሀ) የከተማዋ ባለቤት ማን ነው? (ለ) ይህች ከተማ ምን ልታመለክት አትችልም? ለምንስ?
5 ሕዝቅኤል 48:15ን አንብብ። ‘ከተማዋም’ ሆነች በከተማዋ ዙሪያ ያለው መሬት ምን ያመለክታሉ? (ሕዝ. 48:16-18) በራእዩ ላይ ይሖዋ ለሕዝቅኤል “የከተማዋ ርስት” ባለቤት ‘የእስራኤል ቤት ሁሉ’ እንደሚሆን ነግሮታል። (ሕዝ. 45:6, 7) በመሆኑም ከተማዋና በዙሪያዋ ያለው መሬት ‘ለይሖዋ የተለየው’ “መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ቅዱስ ስፍራ” ክፍል አይደለም። (ሕዝ. 48:9, 20) ይህን በአእምሯችን ይዘን፣ ስለዚህች ከተማ የተሰጠው መግለጫ ለእኛ ምን ትምህርት እንደያዘ እንመልከት።
6 ሆኖም ስለ ከተማዋ ከተሰጠው መግለጫ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ከመመልከታችን በፊት ይህች ከተማ ምን ልታመለክት እንደማትችል ማወቅ ያስፈልገናል። ቤተ መቅደሱ የሚገኝባትን ዳግመኛ የተገነባችውን የኢየሩሳሌም ከተማ ልታመለክት አትችልም። ለምን? ምክንያቱም ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከታት ከተማ በውስጧ ቤተ መቅደስ አይኖራትም። በተጨማሪም ከተማዋ ዳግመኛ በተቋቋመው የእስራኤል ምድር ውስጥ የሚገኝን የትኛውንም ከተማ አታመለክትም። ለምን? ምክንያቱም ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያንም ሆኑ ዘሮቻቸው በራእዩ ውስጥ የተገለጸችውን ዓይነት ከተማ ገንብተው አያውቁም። ከዚህም ሌላ ከተማዋ በሰማይ ላይ ያለችን ከተማ ልታመለክት አትችልም። ለምን? ምክንያቱም ለቅዱስ አምልኮ ብቻ ተለይቶ በተመደበ ቦታ ላይ ከተገነቡ ሕንፃዎች በተለየ መልኩ ይህች ከተማ የተገነባችው ‘ቅዱስ ላልሆነ’ ወይም ተራ ለሆነ አገልግሎት በተመደበ ቦታ ላይ ነው።—ሕዝ. 42:20
7. ሕዝቅኤል በራእይ ያያት ከተማ የምታመለክተው ምንን መሆን አለበት? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
7 ታዲያ ሕዝቅኤል በራእይ ያያት ከተማ ምን ታመለክታለች? ሕዝቅኤል ከተማዋን ያየው ስለ ምድሪቱ ባየው ራእይ ላይ እንደሆነ ልብ በል። (ሕዝ. 40:2፤ 45:1, 6) ምድሪቱ የምታመለክተው ምሳሌያዊ የሆነን “ምድር” እንደሆነ የአምላክ ቃል ይጠቁማል፤ በመሆኑም ከተማዋም የምታመለክተው ምሳሌያዊ የሆነን ከተማ መሆን አለበት። “ከተማ” የሚለው ቃል በአብዛኛው ምን ሐሳብ ያስተላልፋል? ይህ ቃል፣ በርካታ ሰዎች ተደራጅተውና አንድ ዓይነት መዋቅር ፈጥረው አብረው የሚኖሩበትን ቦታ ያመለክታል። በመሆኑም ሕዝቅኤል የተመለከታት አራቱም ጎኗ እኩል የሆነው ከተማ፣ በሚገባ የተደራጀን መስተዳድር የምታመለክት ይመስላል።
8. የዚህ መስተዳድር የግዛት ክልል ምንድን ነው? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
8 የዚህ መስተዳድር የግዛት ክልል ምንድን ነው? የሕዝቅኤል ራእይ ከተማዋ የምትገኘው በምሳሌያዊው ምድር ውስጥ እንደሆነ ይገልጻል። በመሆኑም ይህ መስተዳድር በዛሬው ጊዜ ሥራውን የሚያከናውነው የአምላክ ሕዝቦች የእንቅስቃሴ ቀጠና በሆነው በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ነው። ከተማዋ የተገነባችው ቅዱስ ባልሆነ ወይም ለተራ አገልግሎት በሚውል መሬት ላይ መሆኑስ ምን ይጠቁማል? ከተማዋ የምታመለክተው ሰማያዊ የሆነን መስተዳድር ሳይሆን በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ጥቅም ሲባል የተቋቋመውን ምድራዊ መስተዳድር መሆኑን ያስታውሰናል።
-