የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ መልእክት በአምላክ መንግሥት ላይ ያተኮረ ነው። ይሖዋ ምድርን ገነት ለማድረግ ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ ዳር የሚያደርሰው በዚህ መንግሥት አማካኝነት ነው። ለመሆኑ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ በመግዛት ላይ እንዳለ እንዴት እናውቃለን? እስካሁን ምን ነገሮችን አከናውኗል? ወደፊትስ ምን ነገሮችን ያከናውናል? ይህ ምዕራፍና ቀጣዮቹ ሁለት ምዕራፎች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።

      1. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ንጉሡስ ማን ነው?

      የአምላክ መንግሥት ይሖዋ አምላክ ያቋቋመው መስተዳድር ነው። የዚህ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የሚገዛውም ከሰማይ ነው። (ማቴዎስ 4:17፤ ዮሐንስ 18:36) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል” ይላል። (ሉቃስ 1:32, 33) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ወደፊት በምድር ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ይገዛል።

      2. ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት እነማን ናቸው?

      ኢየሱስ የሚገዛው ብቻውን አይደለም። “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ” የተውጣጡ ሰዎች ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ።’ (ራእይ 5:9, 10) ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት ሰዎች ምን ያህል ናቸው? ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣ ወዲህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች የእሱ ተከታዮች ሆነዋል። ሆኖም ወደ ሰማይ ሄደው ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት 144,000 የሚያህሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። (ራእይ 14:1-4⁠ን አንብብ።) በምድር ላይ የሚቀሩት ሌሎች ክርስቲያኖች በሙሉ የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ይሆናሉ።—መዝሙር 37:29

      3. የአምላክን መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሯቸው መንግሥታት የተሻለ የሚያደርገው ምንድን ነው?

      የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥሩ ነገሮችን ማድረግ ቢፈልጉም እንኳ የፈለጉትን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል የላቸውም። በተጨማሪም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ራስ ወዳድ በሆኑና ሰዎችን መርዳት በማይፈልጉ ሌሎች ባለሥልጣናት መተካታቸው አይቀርም። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ግን በማንም አይተካም። አምላክ ያቋቋመው መንግሥት “ፈጽሞ የማይጠፋ” ነው። (ዳንኤል 2:44) ኢየሱስ መላዋን ምድር የሚገዛ ሲሆን አንዱን ከሌላው አያበላልጥም። አፍቃሪ፣ ደግና ፍትሐዊ ከመሆኑም በላይ ሰዎችም ልክ እንደ እሱ እነዚህን ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ ያስተምራል።—ኢሳይያስ 11:9⁠ን አንብብ።

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      የአምላክን መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ከየትኛውም መንግሥት የተሻለ የሚያደርገው ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

      ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ካለው ዙፋኑ ሆኖ ምድርን ሲገዛ። አብረውት የሚገዙት ሰዎች ከጀርባው ተቀምጠዋል። ከበስተኋላቸው ከይሖዋ ዙፋን የሚፈነጥቀው ብርሃን ይታያል

      4. መላዋ ምድር በአንድ ታላቅ መስተዳድር ሥር ትሆናለች

      ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዛሬ ድረስ በምድር ላይ ከተነሱት ገዢዎች ሁሉ የበለጠ ሥልጣን አለው። ማቴዎስ 28:18⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ኢየሱስ በምድር ላይ ካለ ከየትኛውም ገዢ የበለጠ ሥልጣን አለው የምንለው ለምንድን ነው?

      በዓለም ላይ ያሉት መንግሥታት በየጊዜው ይቀያየራሉ፤ ደግሞም አንድ መንግሥት የሚያስተዳድረው የዓለማችንን የተወሰነ ክፍል ነው። የአምላክ መንግሥትስ? ዳንኤል 7:14⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • የአምላክ መንግሥት “የማይጠፋ” መሆኑ ምን ጥቅም አለው?

      • መላዋን ምድር የሚገዛ መሆኑ ምን ጥቅም አለው?

      5. የሰዎች አገዛዝ መተካት አለበት

      የሰዎች አገዛዝ በአምላክ መንግሥት ሊተካ የሚገባው ለምንድን ነው? ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      ቪዲዮ፦ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?—ተቀንጭቦ የተወሰደ (1:41)

      • የሰዎች አገዛዝ ምን ውጤት አስከትሏል?

      መክብብ 8:9⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • የሰዎች አገዛዝ በአምላክ መንግሥት ሊተካ እንደሚገባ ይሰማሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      6. የአምላክ መንግሥት ገዢዎች ያለንበትን ሁኔታ ይረዱልናል

      ንጉሣችን ኢየሱስ በአንድ ወቅት ሰው ሆኖ ስለኖረ ‘በድካማችን ይራራልናል።’ (ዕብራውያን 4:15) ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የመረጣቸው 144,000 ታማኝ ወንዶችና ሴቶች “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ” የተውጣጡ ናቸው።—ራእይ 5:9

      • ኢየሱስና ከእሱ ጋር የሚገዙት ሰዎች በሙሉ በአንድ ወቅት እንደ እኛው ሰው የነበሩ መሆናቸውን ማወቃችን የሚያጽናናን ለምንድን ነው?

      በተለያዩ ዘመናት የኖሩና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው በመንፈስ የተቀቡ ወንዶችና ሴቶች

      ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የመረጣቸው ወንዶችና ሴቶች የተለያየ ዘርና አስተዳደግ ያላቸው ናቸው

      7. የአምላክ መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ከየትኛውም መንግሥት የላቁ ሕጎች አሉት

      መንግሥታት ለዜጎቻቸው ጥቅምና ጥበቃ ያስገኛሉ ብለው የሚያስቧቸውን ሕጎች ያወጣሉ። የአምላክ መንግሥትም ተገዢዎቹ ሊያከብሯቸው የሚገቡ ሕጎች አሉት። አንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ሁሉም ሰው አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር ደንቦች ቢከተል ዓለማችን ምን መልክ የሚኖራት ይመስልሃል?a

      • ይሖዋ የመንግሥቱ ተገዢዎች እነዚህን ሕጎች እንዲያከብሩ መጠበቁ ምክንያታዊ ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

      • እነዚህን ሕጎች የማይታዘዙ ሰዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?—ቁጥር 11⁠ን ተመልከት።

      ብዙ ሰዎች በሚተላለፉበት መንገድ ላይ ትራፊኩን እያስተናበረ ያለ ፖሊስ። የተለያየ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች መንገዱን እያቋረጡ ነው

      መንግሥታት ለዜጎቻቸው ጥበቃና ጥቅም የሚያስገኙ የተለያዩ ሕጎችን ያወጣሉ። የአምላክ መንግሥት ለተገዢዎቹ ጥበቃና ጥቅም የሚያስገኙ የላቁ ሕጎች አሉት

      አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?”

      • ምን ብለህ ትመልሳለህ?

      ማጠቃለያ

      የአምላክ መንግሥት በሰማይ ያለ መስተዳድር ሲሆን ወደፊት መላዋን ምድር ይገዛል።

      ክለሳ

      • የአምላክ መንግሥት ገዢዎች እነማን ናቸው?

      • የአምላክ መንግሥት ሰዎች ከሚያስተዳድሩት ከየትኛውም መንግሥት የተሻለ የሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

      • ይሖዋ ከመንግሥቱ ተገዢዎች የሚጠብቃቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት የሚገኝበትን ቦታ በተመለከተ ምን አስተምሯል?

      “የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ነገር ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      የይሖዋ ምሥክሮች፣ ከሰዎች መንግሥት ይልቅ ለአምላክ መንግሥት ታማኝ ለመሆን የሚመርጡት ለምንድን ነው?

      ለአምላክ መንግሥት ታማኝ መሆን (1:43)

      መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የመረጣቸውን 144,000 ሰዎች አስመልክቶ ምን ይላል?

      “ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      እስር ቤት የነበረች አንዲት ሴት በዓለም ላይ ፍትሕ ሊያሰፍን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው ብላ እንድታምን ያደረጋት ምንድን ነው?

      “የፍትሕ ጥያቄዬ መልስ ያገኘበት መንገድ” (ንቁ! ኅዳር 2011)

      a ከእነዚህ የሥነ ምግባር ደንቦች መካከል አንዳንዶቹ ክፍል 3 ላይ ይብራራሉ።

  • የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
    • የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀምሯል። በቅርቡ በምድር ላይ ሥር ነቀል ለውጦችን ያደርጋል። እስቲ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የምታገኛቸውን አንዳንድ በረከቶች እንመልከት።

      1. የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን የሚያደርገው እንዴት ነው?

      የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ ክፉ ሰዎችንና መንግሥታትን ያጠፋል። (ራእይ 16:14, 16) በዚያ ወቅት “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል። (መዝሙር 37:10) ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት በመላዋ ምድር ላይ ሰላምና ፍትሕ እንዲሰፍን ያደርጋል።—ኢሳይያስ 11:4⁠ን አንብብ።

      2. የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ በሚፈጸምበት ጊዜ ምን ዓይነት ሕይወት ይኖረናል?

      በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) ክፉዎች በሌሉበት እንዲሁም ይሖዋን የሚወዱና እርስ በርስ የሚዋደዱ ሰዎች ብቻ ባሉበት ዓለም ውስጥ መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው! በሕመም የሚሠቃይ ሰው አይኖርም፤ ሁሉም ሰው ለዘላለም ይኖራል።

      3. ክፉዎች ከጠፉ በኋላ የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?

      ክፉዎች ከጠፉ በኋላ ኢየሱስ ለ1,000 ዓመት ያህል ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። በዚያ ወቅት ኢየሱስና አብረውት የሚገዙት 144,000 ገዢዎች፣ ሰዎች ፍጹምና ከኃጢአት ነፃ እንዲሆኑ ይረዳሉ። የሺህ ዓመቱ ግዛት መጨረሻ ላይ ምድር የይሖዋን ሕጎች በሚታዘዙ ደስተኛ ሰዎች የተሞላች ውብ ገነት ትሆናለች። ከዚያም ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ ለይሖዋ ያስረክባል። የይሖዋ ስም ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መንገድ ‘ይቀደሳል።’ (ማቴዎስ 6:9, 10) ይሖዋ ለተገዢዎቹ የሚያስብ ጥሩ ገዢ እንደሆነ ይረጋገጣል። ከዚያም ይሖዋ ሰይጣንንና አጋንንቱን ጨምሮ በእሱ አገዛዝ ላይ የሚያምፁትን ሁሉ ያጠፋል። (ራእይ 20:7-10) የአምላክ መንግሥት የሚያመጣቸው በረከቶች ለዘላለም ይቀጥላሉ።

      ጠለቅ ያለ ጥናት

      አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጣቸውን ተስፋዎች በሙሉ በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚፈጽም እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

      4. የአምላክ መንግሥት የሰዎችን አገዛዝ ያስወግዳል

      “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 8:9) ይሖዋ በፍትሕ መጓደል ምክንያት የተከሰቱ ችግሮችን በመንግሥቱ አማካኝነት ያስተካክላል።

      ዳንኤል 2:44⁠ን እና 2 ተሰሎንቄ 1:6-8⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ ሰዎች በሚያስተዳድሯቸው መንግሥታትና በደጋፊዎቻቸው ላይ ምን እርምጃ ይወስዳሉ?

      • ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ የተማርከው ነገር እነሱ የሚወስዱት እርምጃ ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደሆነ እንድትተማመን የሚያደርግህ እንዴት ነው?

      በሰማይ የነገሠው ንጉሣችን ኢየሱስ ገነት የሆነችውን ምድር ሲገዛ

      5. ኢየሱስ ከሁሉ የተሻለ ንጉሥ ነው

      ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ ላሉ ተገዢዎቹ ብዙ ጠቃሚ ነገሮችን ያከናውናል። ኢየሱስ ከዚህ በፊት ያደረጋቸው ነገሮች እንዲህ ለማድረግ ፍላጎቱ እንዳለውና አምላክም ኃይል እንደሰጠው ያሳያሉ። ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ቪዲዮው ላይ ተመልከቱ።

      ቪዲዮ፦ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን እንደሚያከናውን አሳይቷል (1:13)

      ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአምላክ መንግሥት ወደፊት የሚያከናውናቸውን ነገሮች በጥቂቱም ቢሆን አሳይቷል። አንተ በግልህ እዚህ ላይ ከተዘረዘሩት ነገሮች መካከል የትኛው ሲፈጸም ለማየት ትጓጓለህ? ከእያንዳንዱ ተስፋ ጋር አብረው የተጠቀሱትን ጥቅሶች አንብቡ።

      ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ . . .

      ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ . . .

      • የአየሩን ጠባይ ተቆጣጥሯል።—ማርቆስ 4:36-41

      • በፕላኔቷ ምድራችን ላይ የደረሰውን ጉዳት ያስተካክላል።—ኢሳይያስ 35:1, 2

      • በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መግቧል።—ማቴዎስ 14:17-21

      • ከዓለም ላይ ረሃብን ያስወግዳል።—መዝሙር 72:16

      • ብዙዎችን ከሕመማቸው ፈውሷል።—ሉቃስ 18:35-43

      • ሁሉም ሰው ፍጹም ጤንነት እንዲኖረው ያደርጋል።—ኢሳይያስ 33:24

      • የሞቱ ሰዎችን አስነስቷል።—ሉቃስ 8:49-55

      • ሞትን ያስወግዳል፤ የሞቱትን ያስነሳል።—ራእይ 21:3, 4

      6. የአምላክ መንግሥት ወደፊት አስደሳች ጊዜ ያመጣል

      የአምላክ መንግሥት ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው የመጀመሪያ ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ያደርጋል። ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት ዓላማውን ዳር ለማድረስ እየሠራ ያለው እንዴት እንደሆነ ለማየት ቪዲዮውን ተመልከቱ።

      ቪዲዮ፦ ወደፊት የምናገኘው አስደሳች ሕይወት (4:35)

      መዝሙር 145:16⁠ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

      • ይሖዋ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?

      አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “ሁላችንም ተባብረን ከሠራን የዓለማችንን ችግሮች ማስወገድ እንችላለን።”

      • ሰዎች ከሚያስተዳድሯቸው መንግሥታት አቅም በላይ የሆኑ ሆኖም የአምላክ መንግሥት የሚያስወግዳቸው ችግሮች የትኞቹ ናቸው?

      ማጠቃለያ

      የአምላክ መንግሥት ዓላማውን ዳር ያደርሳል። መላዋ ምድር ይሖዋን ለዘላለም በሚያመልኩ ጥሩ ሰዎች እንድትሞላና ገነት እንድትሆን ያደርጋል።

      ክለሳ

      • የአምላክ መንግሥት የይሖዋ ስም እንዲቀደስ የሚያደርገው እንዴት ነው?

      • የአምላክ መንግሥት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ተስፋዎች እንዲፈጸሙ እንደሚያደርግ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

      • የአምላክ መንግሥት ከሚያመጣቸው በረከቶች መካከል አንተ ለማየት የምትጓጓው የትኛውን ነው?

      ግብ

      ምርምር አድርግ

      ‘አርማጌዶን’ የሚለው ቃል ምን ያመለክታል?

      “የአርማጌዶን ጦርነት ምንድን ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      ኢየሱስ “ታላቅ መከራ” ብሎ በጠራው ወቅት ምን ነገሮች ይከናወናሉ?—ማቴዎስ 24:21

      “ታላቁ መከራ ምንድን ነው?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

      የአምላክ መንግሥት ወደፊት በሚያመጣቸው በረከቶች ላይ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ማሰላሰል የሚቻለው እንዴት ነው?

      በገነት ውስጥ ስትኖር ይታይህ (1:50)

      “አእምሮዬን የሚረብሹ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ” በሚለው ርዕስ ሥር ዓማፂ የነበረ አንድ ሰው ለጥያቄዎቹ መልስ ያገኘው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

      “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” (መጠበቂያ ግንብ ጥር 1, 2012)

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ