የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ከሰሜን የሚመጣ ጥቃት!
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020 | ሚያዝያ
    • 14. ኢዩኤል 2:28, 29 ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው?

      14 በመቀጠል ኢዩኤል የተሃድሶ ዘመን እንደሚመጣ የሚገልጽ መልካም ዜና ተናገረ። ምድሩ ዳግመኛ ፍሬያማ ይሆናል። (ኢዩ. 2:23-26) ወደፊት ደግሞ መንፈሳዊ ምግብ የሚትረፈረፍበት ጊዜ ይመጣል። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ . . . በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር መንፈሴን አፈሳለሁ።” (ኢዩ. 2:28, 29) አምላክ መንፈሱን ያፈሰሰው እስራኤላውያን ከባቢሎን ወደ ትውልድ አገራቸው እንደተመለሱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህ የሆነው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ማለትም በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ ዕለት ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን?

      15. በሥራ 2:16, 17 ላይ እንደተገለጸው ጴጥሮስ ኢዩኤል 2:28⁠ን ጠቅሶ ሲናገር ምን ለውጥ አድርጓል? ይህስ ምን ይጠቁማል?

      15 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ በጴንጤቆስጤ ዕለት የተከናወነ አንድ አስደናቂ ነገር በኢዩኤል 2:28, 29 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር እንደሚገናኝ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ገልጾ ነበር። በዚያ ዕለት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ መንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በሰዎች ላይ ፈሰሰ፤ ሰዎቹም “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” መናገር ጀመሩ። (ሥራ 2:11) ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የኢዩኤልን ትንቢት ጠቅሶ ሲናገር የተጠቀመባቸው ቃላት ከመጀመሪያው ሐሳብ በተወሰነ መጠን ይለያሉ። ልዩነቱ ምን እንደሆነ አስተውለሃል? (የሐዋርያት ሥራ 2:16, 17⁠ን አንብብ።) ጴጥሮስ ሐሳቡን የጀመረው “ከዚያ በኋላ” ብሎ ሳይሆን “በመጨረሻው ቀን” በማለት ነው፤ ጴጥሮስ “በመጨረሻው ቀን” አምላክ መንፈሱን “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ” እንደሚያፈስስ ተናገረ፤ “በመጨረሻው ቀን” የሚለው ሐረግ በዚህ አገባቡ የአይሁድን ሥርዓት የመጨረሻ ቀን ያመለክታል። ይህም የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው ትንቢቱ ከተነገረ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ ይጠቁማል።

      16. የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በተከናወነው የስብከት ሥራ ላይ ምን ውጤት ነበረው? በዛሬው ጊዜስ?

      16 የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አስደናቂ በሆነ መንገድ ከፈሰሰ በኋላ የስብከቱ ሥራ እስከዚያ ድረስ ሆኖ በማያውቅ ስፋት መከናወን ጀመረ። ሐዋርያው ጳውሎስ በ61 ዓ.ም. ገደማ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ሲጽፍ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” እንደተሰበከ መናገር ችሏል። (ቆላ. 1:23) “ፍጥረት ሁሉ” የሚለው አገላለጽ በወቅቱ የሚታወቀውን ዓለም ያመለክታል። ኃያል በሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ በዛሬው ጊዜ የስብከቱ ሥራ ከዚያ በሚበልጥ ስፋት እየተከናወነ ሲሆን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተሰብኳል።—ሥራ 13:47፤ “መንፈሴን አፈሳለሁ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      “መንፈሴን አፈሳለሁ”

      በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች ተጠምቀው የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ። እነዚህ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን እውነት ወዲያውኑ ለሌሎች መናገር ጀመሩ። ታዲያ ይሖዋ በቅንዓት ያከናወኑትን አገልግሎት ባርኮላቸዋል? በሚገባ! “በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ” ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ነበር።—ሥራ 2:41፤ 21:20

      ታዲያ የአማኞቹ ቁጥር ስንት ሺህ ደርሶ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ አይናገርም፤ ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይም እንኳ የአማኞቹ ቁጥር ከ144,000 በጣም ያነሰ መሆን አለበት። በዚያ ዘመን ይሖዋ የሰማያዊው መንግሥት ወራሾች የሚሆኑ ወንዶችንና ሴቶችን ይመርጥ ነበር፤ ሆኖም ከእነዚህ ወራሾች መካከል አብዛኞቹ የተመረጡት በዘመናችን ነው። እንደዚያም ሆኖ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው አስደናቂ እድገት ይሖዋ በጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈሱን አፍስሶ እንደነበር ያረጋግጣል።—ሥራ 2:16-18

      ይሖዋ በዛሬው ጊዜም በአገልጋዮቹ ላይ መንፈሱን እንዳፈሰሰ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? እንዴታ! እስቲ ይህን መረጃ ተመልከት፦ በ1919 በዓለም ዙሪያ የነበሩት የምሥራቹ ሰባኪዎች 6,000 እንደማይሞሉ አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ። ይሁንና ይሖዋ የስብከቱን ሥራ ስለባረከው ከ1983 አንስቶ በእያንዳንዱ ዓመት ከ144,000 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል! በእርግጥም ይህ፣ ይሖዋ “መንፈሴን አፈሳለሁ” በማለት ለአገልጋዮቹ የገባውን ቃል እየፈጸመ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—ኢዩ. 2:28, 29

  • ከሰሜን የሚመጣ ጥቃት!
    መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020 | ሚያዝያ
አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ