-
ከሠራው ስህተት ተምሯልበእምነታቸው ምሰሏቸው
-
-
18, 19. ዮናስ ባሕሩ ውስጥ ከሰመጠ በኋላ ምን አጋጠመው? ምን ዓይነት ፍጡርስ ዋጠው? ይህ እንዲሆን ያደረገውስ ማን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
18 ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቅራቢያው አንድ ጠቆር ያለና በጣም ግዙፍ የሆነ ሕይወት ያለው ነገር ሲንቀሳቀስ ተመለከተ። ይህም ፍጡር እየተምዘገዘገ ወደ እሱ መጣ። ከዚያም አንድ ትልቅ አፍ ተከፍቶ ዋጠው!
ይሖዋ “ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ አዘጋጀ”
19 በዚህ ጊዜ ዮናስ ‘በቃ፣ አበቃልኝ’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ምንም አለመሆኑ ሳያስገርመው አልቀረም። አሁንም በሕይወት አለ! በሰውነቱ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም፤ ሌላው ቀርቶ አየር አጥቶ እንኳ አልታፈነም። መቃብር ውስጥ የገባ ቢሆንም በሕይወት አለ። ይህም በአድናቆት እንዲዋጥ አደረገው። “ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ” ያዘጋጀው አምላኩ ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።c—ዮናስ 1:17
20. ዮናስ በትልቅ ዓሣ ውስጥ ሆኖ ካቀረበው ጸሎት ምን ልንማር እንችላለን?
20 ደቂቃዎች አልፈው በሰዓታት ተተኩ። ዮናስ አይቶት በማያውቀው ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ የተለያዩ ነገሮችን ሲያውጠነጥን ከቆየ በኋላ ወደ ይሖዋ አምላክ ጸለየ። በዮናስ መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ጸሎቱ ብዙ የሚገልጸው ነገር አለ። ዮናስ በተደጋጋሚ ጊዜ ከመዝሙር መጽሐፍ መጥቀሱ ጥልቅ የሆነ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንደነበረው ያሳያል። በተጨማሪም ግሩም ባሕርይ እንዳለው ይኸውም አመስጋኝ እንደነበር ይጠቁማል። ዮናስ “እኔ ግን በምስጋና መዝሙር፣ መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እሰጣለሁ፤ ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” በማለት ጸሎቱን ደምድሟል።—ዮናስ 2:9
21. ዮናስ አምላክ ስለሚያድንበት መንገድ ምን ትምህርት አገኘ? እኛስ የትኛውን ሐቅ መዘንጋት የለብንም?
21 ዮናስ “በዓሣው ሆድ ውስጥ” ሆኖ ይሖዋ ማንኛውንም ሰው በየትኛውም ጊዜና ቦታ ማዳን እንደሚችል መማር ችሏል። ይሖዋ እዚያ ውስጥ የነበረውን አገልጋዩን እንኳ አድኖታል። (ዮናስ 1:17) የአንድን ሰው ሕይወት በዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት ጠብቆ ማቆየት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። እንግዲያው ‘ሕይወታችን በአምላክ እጅ’ እንደሆነ ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ዳን. 5:23) ሕይወትም ሆነ እስትንፋስ የሰጠን እሱ ነው። ታዲያ ለዚህ ነገር አመስጋኞች ነን? ይሖዋን ልንታዘዘውስ አይገባም?
22, 23. (ሀ) ዮናስ ምን ያህል አመስጋኝ እንደነበር የሚፈትን ምን ሁኔታ አጋጠመው? (ለ) ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ከዮናስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
22 ስለ ዮናስስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋን በመታዘዝ አመስጋኝነቱን በተግባር አሳይቷል? አዎ፣ አሳይቷል። ከሦስት ቀንና ከሦስት ሌሊት በኋላ ዓሣው ዮናስን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወስዶ “በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።” (ዮናስ 2:10) እስቲ አስበው፣ ይህ ሁሉ ከሆነም በኋላ ዮናስ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለመድረስ ትንሽ እንኳ መዋኘት አላስፈለገውም! እርግጥ ነው፣ ዓሣው የተፋው የትም ይሁን የት ከባሕሩ ዳርቻ ተነስቶ መጓዝ ነበረበት። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆነ የሚፈተንበት ሁኔታ ተፈጠረ። ዮናስ 3:1, 2 እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፤ ‘ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ የምነግርህን መልእክት ስበክላት።’” ታዲያ ዮናስ ምን ያደርግ ይሆን?
-
-
ከሠራው ስህተት ተምሯልበእምነታቸው ምሰሏቸው
-
-
c “ዓሣ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በግሪክኛ “አስፈሪ የባሕር እንስሳ” ወይም “ግዙፍ ዓሣ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህ ፍጡር ምን ዓይነት የባሕር እንስሳ እንደሆነ በትክክል ማወቅ ባይቻልም በሜድትራንያን ባሕር ውስጥ ሰውን ሙሉ በሙሉ መዋጥ የሚችሉ ሻርኮች እንዳሉ ማስተዋል ተችሏል። በሌሎች ቦታዎች ከእነዚህ በጣም የሚበልጡ ሻርኮች ይገኛሉ፤ ዌል ሻርክ የተባለው የዓሣ ዝርያ 15 ሜትር ወይም ከዚያ የሚበልጥ ርዝማኔ ሊኖረው ይችላል!
-