ሰው ሁሉ ይሖዋን ያክብር!
“በብርሃንም ምድር ያሉ ይሖዋን ያከብሩታል።”— ኢሳይያስ 24:15 አዓት
1. ነቢያቱ ለይሖዋ ስም ምን ዓይነት አቋም ነበራቸው? በአንጻሩ ዛሬ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለው አመለካከት ምን ዓይነት ነው?
ይሖዋ፤ ገናና የሆነው የአምላክ ስም! የጥንቶቹ የታመኑ ነቢያት በዚህ ስም መናገር በመቻላቸው ምንኛ ተደስተው ይሆን! ስሙ ራሱ ታላቅ የዓላማ አምላክ መሆኑን የሚመሠክረውን ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን በታላቅ ደስታ አክብረውታል። (ኢሳይያስ 40:5፤ ኤርምያስ 10:6, 10፤ ሕዝቅኤል 36:23) አናሳ የተባሉት ነቢያት እንኳን ሳይቀሩ ይሖዋን በማክበር በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ሐጌ ነበር። 38 ቁጥሮች ብቻ ባሉበት በሐጌ መጽሐፍ ውስጥ የአምላክ ስም 35 ጊዜ ተጠቅሷል። ራሳቸውን እንደ አዋቂ የሚቆጥሩት የሕዝበ ክርስትና ሐዋርያት ነን ባዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ላይ እንዳደረጉት ይሖዋ የሚለውን ክቡር ስም “ጌታ” በሚለው የማዕረግ ስም መተካት እንደዚህ ያሉት ትንቢቶች ለዛቸውን እንዲያጡ ማድረግ ነው።— ከ2 ቆሮንቶስ 11:5 አዓት ጋር አወዳድር።
2, 3. (ሀ) የእስራኤል እንደገና መልሶ መቋቋም በተመለከተ የተነገረ አንድ አስገራሚ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) አይሁዳውያን ቀሪዎቹና ተባባሪዎቻቸው ምን ደስታ አግኝተዋል?
2 በኢሳይያስ 12:2 ላይ [እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ] ስሙ በድርብ መልክ ተቀምጧል።a ነቢዩ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ያህ ይሖዋ ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፣ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ።” (በተጨማሪም ኢሳይያስ 26:4 አዓት ተመልከት።) በመሆኑም እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ከመውጣታቸው ከ200 ዓመታት ቀደም ብሎ ያህ ይሖዋ ኃያል አዳኝ እንደሚሆንላቸው በነቢዩ በኢሳይያስ አማካኝነት አረጋግጦላቸው ነበር። የምርኮው ዘመን ከ607 አንስቶ እስከ 537 ከዘአበ ድረስ የሚዘልቅ ነበር። በተጨማሪም ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሁሉን የፈጠርሁ . . . እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” አዓት ] እኔ ነኝ፤ ቂሮስንም:- እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን:- ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ።” ይህ ቂሮስ ማን ነበር? በ539 ከዘአበ ባቢሎንን ድል ነስቶ የተቆጣጠረው የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ነው።— ኢሳይያስ 44:24, 28
3 ቂሮስ በምርኮ ለነበሩት እስራኤላውያን የሚከተለውን ድንጋጌ ባወጣ ጊዜ ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ያስመዘገባቸው ቃላት በትክክል ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል:- “ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፣ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፣ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ።” በደስታ የተዋጡት አይሁዳውያን ቀሪዎች እስራኤላውያን ካልሆኑት ናታኒሞችና የሰሎሞን ባሪያዎች ልጆች ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። በ537 ከዘአበ በዚያ የዳስ በዓልን ለማክበርና ለይሖዋም በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት ለማቅረብ በቅተዋል። በሚቀጥለው ዓመት በሁለተኛው ወር በታላቅ ሆታና እልልታ ይሖዋን በማወደስ የሁለተኛውን ቤተ መቅደስ መሠረት ጣሉ።— ዕዝራ 1:1-4፤ 2:1, 2, 43, 55፤ 3:1-6, 8, 10-13
4. ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 እና ምዕራፍ 55 እውን የሆኑት እንዴት ነው?
4 ይሖዋ ተመልሶ ስለ መቋቋም ያስነገረው ትንቢት በእስራኤል ላይ ታላቅ ፍጻሜውን ማግኘት ነበረበት:- “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሴት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። . . . የእግዚአብሔርን ክብር የአምላካችንን ግርማ የሚያዩ ይኖራሉ።” “እናንተም በደስታ ትወጣላችሁ በሰላምም ትሸኛላችሁ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፣ . . . ለእግዚአብሔርም መታሰቢያና ለዘላለም የማይጠፋ ምልክት ይሆናል።”— ኢሳይያስ 35:1, 2፤ 55:12, 13
5. የእስራኤላውያኑ ደስታ ያልዘለቀው ለምንድን ነበር?
5 ይሁን እንጂ ይህ ደስታ ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። አጎራባቾቹ ብሔራት እምነታቸውን በማቀላቀል ቤተ መቅደሱን በኅብረት ለመገንባት ጥያቄ አቀረቡ። አይሁዳውያኑ በመጀመሪያ “የአምላካችንን ቤት መሥራት ለእኛና ለእናንተ አይደለም፤ እኛ ብቻችንን ግን የፋርስ ንጉሥ እንዳዘዘን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት እንሠራለን” በማለት የጸና አቋማቸውን ገለጹ። ይሄን ጊዜ እነዚያ ጎረቤቶቻቸው መራራ ጠላቶች ሆኑባቸው። “የይሁዳን ሕዝብ እጅ ያደክሙ ነበር፣ እንዳይሠሩም አስፈራሯቸው።” ይባስ ብለው በዳሪዮስ እግር ለተተካው ለአርጤክስስ ጉዳዩን አጣምመው አቀረቡለት፤ እርሱም የቤተ መቅደሱ ግንባታ እንዲታገድ አደረገ። (ዕዝራ 4:1-24) 17 ለሚያክሉ ዓመታት ሥራው ቆመ። በዚህ መሀል አይሁዳውያኑ በፍቅረ ነዋይ መጠመዳቸው የሚያሳዝን ነበር።
“የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” ተናገረ
6. (ሀ) ይሖዋ በእስራኤል ውስጥ ለነበረው ሁኔታ ምን ምላሽ ሰጠ? (ለ) የሐጌ የስሙ ትርጉም ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚገመተው ፍቺ ተስማሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
6 ቢሆንም ይሖዋ ነቢያቱን በተለይ ደግሞ ሐጌንና ዘካርያስን በመላክ ሕዝቡ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዳይዘነጋ በማሳሰብ ለእስራኤል ሕዝብ ‘ኃይሉና ዝማሬው’ መሆኑን አሳይቷል። የሐጌ ስም ትርጉሙ “በበዓል ቀን የተወለደ” ማለት ሳይሆን ስለማይቀር ከደስታ በዓል ጋር የተያያዘ ነው። ትንቢት መናገር የጀመረውም አይሁዳውያን ‘ፈጽሞ ደስ ይበላችሁ’ ተብለው የታዘዙበት የዳስ በዓል በሚከበርበት ወር የመጀመሪያ ዕለት መሆኑ ከዚህ ጋር የሚስማማ ነው። (ዘዳግም 16:15) ይሖዋ በሐጌ አማካኝነት በ112 ቀናት ውስጥ አራት መልእክቶችን አስተላልፏል።— ሐጌ 1:1፤ 2:1, 10, 20
7. የሐጌ የመክፈቻ ቃላት ሊያበረታቱን የሚገባው እንዴት ነው?
7 ሐጌ በትንቢቱ መክፈቻ ላይ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል’ በማለት ተናግሯል። (ሐጌ 1:2) እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ሠራዊት” ምን ሊሆን ይችላል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልፎ አልፎ እንደ ጦር ሠራዊት ተደርገው የተገለጹት የይሖዋ መላእክታዊ ኃይሎች ናቸው። (ኢዮብ 1:6፤ 2:1፤ መዝሙር 103:20, 21፤ ማቴዎስ 26:53) ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ የምንሠራውን ሥራ ለመምራትና እውነተኛውን አምልኮ በምድር ላይ መልሶ ለማቋቋም በእነዚህ የማይበገሩ ሰማያዊ ኃይሎች መጠቀሙ ዛሬ ያለነውን የሚያበረታታ አይደለምን?— ከ2 ነገሥት 6:15-17 ጋር አወዳድር።
8. የእስራኤልን ሕዝብ የጎዳው ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
8 የሐጌ የመጀመሪያው መልእክት ይዘቱ ምን ነበር? ሕዝቡ “ዘመኑ አልደረሰም፣ የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራበት ዘመን አልደረሰም” ይሉ ነበር። የመለኮታዊውን አምልኮ እንደገና መቋቋም የሚያሳየውን የቤተ መቅደስ ግንባታ ሥራ ወደኋላ ገሸሽ አድርገውት ነበር። ለራሳቸው ከቤተ መንግሥት የማይተናነሱ መኖሪያዎችን ወደ መገንባት ዘወር ብለው ነበር። ፍቅረ ነዋይ ለይሖዋ አምልኮ የነበራቸውን አድናቆት ቀንሶባቸዋል። በመሆኑም የእርሱን በረከት ተነፍገው ነበር። እርሻቸው ፍሬያማ መሆኑ ቀርቶና ከባዱን የክረምት ወቅት የሚያወጣ ልብስ እንኳን ማግኘት ቸግሯቸው ነበር። ገቢያቸው ከእጅ ወደ አፍ ብቻ ከመሆኑ የተነሣ ገንዘባቸውን በቀዳዳ ከረጢት እንደሚያስቀምጥ ሰው ሆነው ነበር።— ሐጌ 1:2-6
9. ይሖዋ ምን ጠንከር ያለና የሚያበረታታ ማሳሰቢያ ሰጥቷል?
9 ይሖዋ ከአንድም ሁለት ጊዜ “ልባችሁን በመንገዳችሁ ላይ አድርጉ” የሚል ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰጣቸው። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የኢየሩሳሌም ገዥ የነበረው ዘሩባቤልና ሊቀ ካህናቱ ኢያሱb ለዚህ ጥሪ ምላሽ በመስጠት የቀሩት ሕዝብ ሁሉ ‘የአምላካቸውን የይሖዋን ድምፅ እንዲሰሙ የሐጌንም ቃል፣ አምላካቸው ይሖዋ እንደላከው እንዲሰሙ’ በድፍረት አበረታተዋቸዋል። “ሕዝቡም በእግዚአብሔር ፊት ፈሩ።” በተጨማሪም “የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ሐጌ በእግዚአብሔር መልእክት ሕዝቡን:- እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፣ ይላል እግዚአብሔር ብሎ ተናገረ።”— ሐጌ 1:5, 7-14
10. ይሖዋ ለእስራኤል ሲል ኃይሉን የተጠቀመው እንዴት ነው?
10 በኢየሩሳሌም የነበሩት አንዳንድ አረጋውያን እንደገና የሚገነባው ቤተ መቅደስ ከቀድሞው ቤተ መቅደስ ጋር ሲወዳደር “እንደ ምናምን” እንደሚሆን ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከ51 ቀናት በኋላ ሐጌ ሁለተኛውን መልእክት እንዲናገር ይሖዋ አነሳስቶታል። እንዲህ ሲል ተናገረ:- “ዘሩባቤል ሆይ፣ በርታ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ታላቁም ካህን የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፣ በርታ፣ እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፣ በርቱና ሥሩ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። . . . አትፍሩ።” በተገቢው ጊዜ ሁሉን ማድረግ የሚችለውን ኃይሉን በመጠቀም ‘ሰማይንና ምድርን የሚያናውጠው’ ይሖዋ ንጉሠ ነገሥቱ የጣለውን እገዳ ጨምሮ ማንኛውንም ተቃውሞ ማክሸፉ የማይቀር ነበር። በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የቤተ መቅደሱ ግንባታ በድል ተጠናቀቀ።— ሐጌ 2:3-6
11. አምላክ ሁለተኛውን ቤተ መቅደስ ‘በክብር የሞላው’ እንዴት ነው?
11 በዚህ ጊዜ አንድ አስገራሚ ተስፋ ፍጻሜውን አግኝቷል:- “በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” (ሐጌ 2:7) እነዚህ ‘የተመረጡ ዕቃዎች’ የአምላክ የመገኘቱ ግርማ ሲያንጸባርቅ አይተው ለአምልኮ ወደ ቤተ መቅደሱ የመጡ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ነበሩ። ይህ እንደገና የተገነባው ቤተ መቅደስ በሰሎሞን ዘመን ከተሠራው ቤተ መቅደስ ጋር ሲወዳደር ምን ይመስል ነበር? የአምላክ ነቢይ እንዲህ ብሏል:- “ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፣ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።” (ሐጌ 2:9) ይህ ትንቢት በመጀመሪያ ፍጻሜው ላይ እንደገና የተገነባው ቤተ መቅደስ ከፊተኛው ይበልጥ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። መሲሑ በ29 እዘአ በተገኘበት ጊዜ ሁሉ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ መሲሑ ራሱ ከሐዲ የሆኑት ጠላቶቹ በ33 እዘአ እስከገደሉት ድረስ በዚህ ቤተ መቅደስ እውነትን መስበኩ ተጨማሪ ክብር አጎናጽፎታል።
12. የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቤተ መቅደሶች ምን ዓላማ አከናውነዋል?
12 በኢየሩሳሌም የነበረው የመጀመሪያውም ሆነ የኋለኛው ቤተ መቅደስ መሲሑ ለሚያከናውነው ከፍተኛ የክህነት አገልግሎት ጥላ በመሆን ትልቅ ድርሻ ከማበርከታቸውም በላይ መሲሑ እስኪገለጥ ድረስ የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ በምድር ላይ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ አገልግለዋል።— ዕብራውያን 10:1
ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ
13. (ሀ) ከ29 እስከ 33 እዘአ ድረስ ባለው ጊዜ ከመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ጋር በተያያዘ የተከናወኑት ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) በዚህ ውስጥስ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የተጫወተው ወሳኝ ሚና ምንድን ነው?
13 ሐጌ እንደገና ስለ መቋቋም የተናገረው ትንቢት ለኋለኞቹ ዘመናት ልዩ ትርጉም አለውን? አዎን አለው! እንደገና የተገነባው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በምድር ላይ ለእውነተኛ አምልኮ ሁሉ ማዕከል ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ ይበልጥ ታላቅ ለሆነ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ጥላ ሆኖ አገልግሏል። ይህ ቤተ መቅደስ ሥራውን የጀመረው በ29 እዘአ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል በወረደበትና ሊቀ ካህናት እንዲሆን በይሖዋ በተቀባበት ጊዜ ነበር። (ማቴዎስ 3:16) ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት ምድራዊ አገልግሎቱን ካጠናቀቀ በኋላ ትንሣኤ አግኝቶ የቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ምሳሌ ወደሆነለት ወደ ሰማይ በመሄድ የመሥዋዕቱን ዋጋ ለይሖዋ አቅርቧል። ይህም የደቀ መዛሙርቱን ኃጢአት የሚሸፍን ቤዛ ሆኖ ከማገልገሉም በላይ በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ የበታች ካህናት ሆነው ለማገልገል በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት እንዲቀቡ በር ከፍቶላቸዋል። በምድር ላይ በቤተ መቅደሱ አደባባይ እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ሆነው ማገልገላቸው ወደፊት ሰማያዊ ትንሣኤ በማግኘት ቀጣይ የካህንነት አገልግሎት ለማከናወን ያበቃቸዋል።
14. (ሀ) የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ካከናወነው ቅንዓት የተሞላበት እንቅስቃሴ ምን ደስታ አግኝቷል? (ለ) ይህ ደስታ ያልዘለቀውስ ለምንድን ነው?
14 በሺህ የሚቆጠሩ ንስሐ የገቡ አይሁዳውያንና ቆየት ብሎም አሕዛብ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ በመቀላቀል ምድርን ስለምታስተዳድረው ስለ መጪዋ የአምላክ መንግሥት ምሥራች በማወጁ ሥራ ተካፍለዋል። 30 የሚያክሉ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” ተሰብኳል ብሎ ለመናገር ችሎ ነበር። (ቆላስይስ 1:23) ይሁን እንጂ ከሐዋርያት ሞት በኋላ ታላቅ ክህደት ተነሣና የእውነት ብርሃን ብልጭ ድርግም ማለት ጀመረ። እውነተኛው የክርስትና እምነት በአረመኔያዊ ትምህርቶችና በፍልስፍና ላይ በተመሠረቱት የሕዝበ ክርስትና ኑፋቄዎች ተዋጠ።— ሥራ 20:29, 30
15, 16. (ሀ) በ1914 አንድ ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻና በ20ኛው መቶ ዘመን ላይ የተከናወነው የመሰብሰብ ሥራ ምንድን ነው?
15 በዚህ መልክ ብዙ መቶ ዓመታት አለፉ። ከዚያም በ1870ዎቹ ዓመታት ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች የተሰባሰቡበት አንድ ቡድን መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናት ጀመረ። “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” የሚያበቁበት ዓመት 1914 እንደሚሆን ከቅዱሳን ጽሑፎች መረዳት ችለው ነበር። የምድር መሲሐዊ ንጉሥ ለመሆን “መብት ያለው” ክርስቶስ ኢየሱስ ሰማያዊ ሥልጣኑን የሚጨብጠውና ሰባቱ ምሳሌያዊ “ዘመናት” (የአውሬ መሰል ሰብዓዊ አገዛዝ የሰፈነባቸው 2, 520 ዓመታት) የሚፈጸሙት በዚህ ጊዜ ነበር። (ሉቃስ 21:24 አዓት፤ ዳንኤል 4:25፤ ሕዝቅኤል 21:26, 27) ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቁት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በተለይ ከ1919 ወዲህ ባሉት ዓመታት ስለ መጪው መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች በዓለም ዙሪያ በማሠራጨቱ ሥራ በትጋት ሲሳተፉ ቆይተዋል። ከእነዚህ መካከል በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች በ1919 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ዩ ኤስ ኤ ለቀረበላቸው የሥራ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ወደ 1935 እየተጠጉ ሲሄዱ ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ሲሆን በዚህ ዓመት የመስክ አገልግሎት ሪፖርታቸውን የመለሱት ቁጥር 56, 153 ነበሩ። በዚህ ዓመት 52, 465 የሚያክሉ በዓመታዊው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን በመካፈል በታላቁ ሰማያዊ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ካህናት የመሆን ተስፋ እንዳላቸው አሳይተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በመሲሐዊው መንግሥቱ ተባባሪ ነገሥታት ሆነው ያገለግላሉ።— ሉቃስ 22:29, 30፤ ሮሜ 8:15-17
16 ይሁን እንጂ በራእይ 7:4-8 እንዲሁም በ14:1-4 ላይ የእነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጠቅላላ ቁጥር 144, 000 ብቻ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ብዙዎች ታላቁ ክህደት ከመጀመሩ በፊት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተሰብስበዋል። ይሖዋ ከ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አንስቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን ድረስ የ144, 000ዎቹን ቁጥር ሙሉ የሚያደርጉት በቃሉ ውኃ ታጥበው የነጹ፣ ኃጢአት በሚያስተሠርየው የኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ባላቸው እምነት መሠረት እንደ ጻድቅ የተቆጠሩና በመጨረሻም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሆነው የታተሙ ሰዎች የሚገኙበትን የዚህን ቡድን መሰብሰብ ሲያጠናቅቅ ቆይቷል።
17. (ሀ) ከ1930ዎቹ ወዲህ ምን የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ ነው? (ለ) በዚህ ረገድ ዮሐንስ 3:30 ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? (በተጨማሪም ሉቃስ 7:28ን ተመልከት።)
17 ጠቅላላው የቅቡዓኖች ቁጥር ከተመረጠ በኋላ የሚቀጥለው ምንድን ነው? በ1935 በዋሽንግተን ዲሲ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በተካሄደውና ጉልህ ሥፍራ በሚሰጠው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በራእይ 7:9-17 ላይ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ተብሎ የተገለጸው 144, 000ዎቹ ከተሰበሰቡ “በኋላ” የሚስተዋሉና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ያቀፈ ቡድን መሆኑ ተብራርቶ ነበር። ከ“ሌሎች በጎች” ጋር ምድራዊ ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ ያለው አጥማቂው ዮሐንስ የተቀባውን የኢየሱስን ማንነት ካሳወቀ በኋላ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል” በማለት ስለ መሲሑ ተናግሯል። (ዮሐንስ 1:29፤ 3:30፤ 10:16፤ ማቴዎስ 11:11) ኢየሱስ በወቅቱ ቁጥራቸው እያደገ የመጣውን ከ144, 000ዎቹ መካከል የሚሆኑ ሰዎች መምረጥ በጀመረበት ጊዜ የአጥማቂው ዮሐንስ ለመሲሑ ደቀ መዛሙርት የማዘጋጀት ሥራ ወደ ማብቃቱ ተቃርቦ ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ነበር። ከ144, 000ዎቹ መካከል እንዲሆኑ ‘የተጠሩትና የተመረጡት’ ሰዎች ቁጥር ሲቀንስ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት የ“እጅግ ብዙ ሰዎች” ቁጥር በአስገራሚ ሁኔታ እያደገ ሄዷል። የዓለም ክፉ ሥርዓት በአርማጌዶን ፍጻሜውን ወደሚያገኝበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ የእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ መጨመሩን ቀጥሏል።— ራእይ 17:14
18. (ሀ) “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” ብለን በልበ ሙሉነት ልንጠብቅ የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ሐጌ 2:4 ላይ ያለውን ምክር በቅንዓት መፈጸም የሚኖርብን ለምንድን ነው?
18 በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ያቀረቡት ልዩ መልእክት ያለው የሕዝብ ንግግር “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚል ነበር። ይህ ምናልባት በወቅቱ ትንሽ ቸኮሉ የሚያሰኝ ሊሆን ይችላል። ዛሬ ግን ይህን በልበ ሙሉነት መናገር ይቻላል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተገኘው እየጨመረ የመጣ ብርሃንና እያጣጣረ ያለው የዚህ ዓለም ሥርዓት አልበኝነት የሰይጣን ሥርዓት ፍጻሜ በጣም፣ በጣም እንደ ቀረበ የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው! በ1996 የተከበረው የመታሰቢያው በዓል ሪፖርት እንደሚያሳየው በበዓሉ የተገኙት ተሰብሳቢዎች ቁጥር 12,921,993 ሲሆን ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን በመካፈል ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸው ያሳዩት 8,757 (.068 በመቶ) ብቻ ናቸው። እውነተኛውን አምልኮ መልሶ የማቋቋሙ ሂደት ወደ ፍጻሜው ተቃርቧል። ይሁን እንጂ ይህን ሥራ ከመሥራት እጃችን እንዲዝል ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም። አዎን፣ ሐጌ 2:4 እንዲህ ይላል:- “እናንተም የአገሩ ሕዝብ ሆይ፣ በርቱና ሥሩ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” ፍቅረ ነዋይም ሆነ ሌላ ዓለማዊ አስተሳሰብ ለይሖዋ ሥራ ያለንን ቅንዓት እንዲያቀዘቅዝብን ላለመፍቀድ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!— 1 ዮሐንስ 2:15-17
19. በሐጌ 2:6, 7 ፍጻሜ መካፈል የምንችለው እንዴት ነው?
19 በሐጌ 2:6, 7 ላይ ያለው ትንቢት ዘመናዊ ፍጻሜውን ሲያገኝ እኛም የዚሁ ተካፋይ መሆናችን አስደሳች መብት ነው:- “ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፤ አሕዛብንም አናውጣለሁ፣ በአሕዛብም የተመረጠው ሁሉ ዕቃ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ዓለም ውስጥ ስግብግብነት፣ ሙስና እና ጥላቻ እንደ አሸን እየፈሉ ነው። በእውነትም ይህ ዓለም በመጨረሻ ቀኖቹ ላይ ነው፤ ይሖዋም ምሥክሮቹ ‘የበቀል ቀኑን እንዲያውጁ’ በመላክ ‘እያናወጠው’ ነው። (ኢሳይያስ 61:2) ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ነውጥ ዛሬ ያለው ዓለም በአርማጌዶን ሲመደሰስ ታላቁ መደምደሚያው ላይ ይደርሳል፤ ይህ ጊዜ ከመድረሱ በፊት ግን ይሖዋ ‘በአሕዛብ ሁሉ የተመረጠውን ዕቃ’ ማለትም ገርና በግ መሰል የሆኑትን የምድር ሰዎች እንዲያገለግሉት ወደ እርሱ በመሳብ ላይ ነው። (ዮሐንስ 6:44) በአሁኑ ጊዜ እነዚህ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በይሖዋ የአምልኮ ቤት ምድራዊ አደባባይ ውስጥ ‘ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ።’— ራእይ 7:9, 15
20. ከሁሉ የበለጠው ውድ ሃብት የሚገኘው ከምንድን ነው?
20 በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ማገልገል ከማንኛውም ቁሳዊ ሃብት የበለጠ ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው። (ምሳሌ 2:1-6፤ 3:13, 14፤ ማቴዎስ 6:19-21) ከዚህም በላይ ሐጌ 2:9 እንዲህ ይላል:- “ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። በዚህም ሥፍራ ሰላምን እሰጣለሁ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” እነዚህ ቃላት ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አላቸው? የሚቀጥለው ርዕስ መልሱን ይሰጠናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ያህ ይሖዋ” የሚለው መግለጫ የሚሠራበት በተለየ መንገድ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 1248 ተመልከት።
b በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ በዕዝራና በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ውስጥ ጄሽዋ ተብሎ ተጠርቷል።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የይሖዋን ስም በተመለከተ ነቢያት የተዉልንን የትኛውን ምሳሌ መከተል ይገባናል?
◻ ይሖዋ ተመልሶ ለሚቋቋመው የእስራኤል ብሔር ካስነገረው ጠንካራ መልእክት ምን ማበረታቻ እናገኛለን?
◻ ዛሬ በሥራ ላይ ያለው ታላቅ ቤተ መቅደስ የትኛው ነው?
◻ በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ዘመን በቅደም ተከተል የተከናወኑት የመሰብሰብ ሥራዎች ምንድን ናቸው? ከፊታቸው የተዘረጋውስ ታላቅ ተስፋ ምንድን ነው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ሰማያዊ ሠራዊት በምድር ላይ ያሉትን ምሥክሮቹን ይመራሉ ይደግፏቸውማል