-
ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2002 | ግንቦት 1
-
-
ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?
“እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል።”—ሚልክያስ 4:1
1. ሚልክያስ የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ የገለጸው እንዴት ነው?
ነቢዩ ሚልክያስ በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ በጣም በቅርቡ ስለሚፈጸሙ አስደናቂ ክንውኖች የሚናገሩ ትንቢቶችን መዝግቧል። እነዚህ ክንውኖች በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱን ግለሰብ የሚነኩ ናቸው። ሚልክያስ 4:1 እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፣ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ የሚደርሰው ጥፋት ምንኛ ታላቅ ነው? ዳግመኛ እንደማያቆጠቁጥ ከሥሩ እንደተነቀለ ዛፍ ይሆናል።
2. አንዳንድ ጥቅሶች የይሖዋን ቀን የሚገልጹት እንዴት ነው?
2 ‘ነቢዩ ሚልክያስ ትንቢት የተናገረው ስለየትኛው “ቀን” ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይህ “ቀን” በኢሳይያስ 13:9 ላይ ከተተነበየው ቀን ጋር አንድ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ፣ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ ጨካኝ ሆኖ በመዓትና በጽኑ ቁጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል።” ሶፎንያስ 1:15 ደግሞ ስለዚያ ቀን “ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን” የሚል መግለጫ ይሰጣል።
“ታላቁ መከራ”
3. “የይሖዋ ቀን” የተባለው ምንድን ነው?
3 በሚልክያስ ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜ መሠረት “የይሖዋ ቀን” በሚከሰተው ‘ታላቅ መከራ’ ተለይቶ የሚታወቅ ወቅት ነው። ኢየሱስ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና” በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:21) ዓለም በተለይ ከ1914 ጀምሮ የተፈራረቀበትን ችግር አስብ። (ማቴዎስ 24:7-12) ሌላው ቢቀር ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብቻ እንኳን ከ50 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል! ሆኖም ‘በታላቁ መከራ’ ከሚደርሰው መቅሰፍት ጋር ሲወዳደር ይህ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። ይህ ክስተት ማለትም የይሖዋ ቀን በአርማጌዶን ሲደመደም ለዚህ ክፉ ሥርዓት መቋጫ ይበጅለታል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13፤ ራእይ 7:14፤ 16:14, 16
4. የይሖዋ ቀን ወደ መደምደሚያው ሲቃረብ ምን ይከሰታል?
4 በይሖዋ ቀን መጨረሻ ላይ የሰይጣን ዓለምና አጫፋሪዎቹ በሙሉ ድምጥማጣቸው ይጠፋል። በመጀመሪያ የሚሰናበተው መላው የሃሰት ሃይማኖት ይሆናል። ከዚያም የይሖዋ ፍርድ በሰይጣን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ላይ ይገለጣል። (ራእይ 17:12-14፤ 19:17, 18) ሕዝቅኤል “ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጉድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 7:19) ያንን ቀን በሚመለከት ሶፎንያስ 1:14 “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል” ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ቀን አስመልክቶ ከሚናገረው አንጻር ሲታይ ከአምላክ የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተን ለመኖር ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል።
-
-
ከይሖዋ ቀን በሕይወት የሚተርፈው ማን ነው?መጠበቂያ ግንብ—2002 | ግንቦት 1
-
-
9. የሚልክያስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
9 እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ዳግም ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። አይሁዳውያን ቀሪዎች ይሖዋን ማገልገልና ከጊዜ በኋላ አሕዛብን ያቀፈው በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች አዲስ “ብሔር” አባል መሆን ችለው ነበር። ሆኖም በጣም የሚበዙት ሥጋዊ እስራኤላውያን ኢየሱስን አልተቀበሉትም። በመሆኑም ኢየሱስ በወቅቱ ለነበረው የእስራኤል ሕዝብ “እነሆ፣ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:38፤ 1 ቆሮንቶስ 16:22) በሚልክያስ 4:1 ላይ በትንቢት እንደተነገረው በ70 እዘአ በሥጋዊ እስራኤላውያን ላይ “እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን” መጥቶባቸው ነበር። ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ የወደሙ ሲሆን በረሃብ፣ በሥልጣን ሽኩቻና የሮማውያን ሠራዊት በሰነዘረው ጥቃት ምክንያት ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች እንደሞቱ ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ያመልኩ የነበሩ ሰዎች በዚያ ወቅት ከደረሰው መከራ አምልጠዋል።—ማርቆስ 13:14-20
-